የሴት ካንሰር ታማሚዎችን ሸክም ያቀለለው ማረፊያ

ከተለያዩ ክልሎች ለሕክምና ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ ሰዎች ውጣውረዱ ቀላል አይደለም፡፡ ለነዚህ ሰዎች ችግራቸው ከሕመማቸው ጋር መጋፈጥ ብቻ አይደለም፡፡ በተለይም ለካንሰር ታማሚዎች በመንግሥት ሆስፒታል በአልጋ እጥረትም ይሁን ተመላልሰው ለመታከም የማረፊያ ቦታ ሁሌም ጭንቀት ነው፡፡ ስለዚህም አንዳንዶች የቅርብ ዘመድ ጋር አርፈው ለመታከም ይጥራሉ፡፡ ይህም ቢሆን ይሰለቻል፣ ለሌላ ሰው ሸክም እሆናለሁ በሚል ለሌላ ጭንቀት ይዳርጋል።ሌሎች ታማሚዎች ደግሞ ዛሬን ምድነው፤ ነገ በጤና ለመኖር ‹‹ማንንም አላስቸግርም›› ብለው ያላቸውን ሸጠው እና ጥሪታቸውን አሟጠው በከተማዋ ቤት ተከራይተው፣ በመድኃኒት፣ በምግብ፣ በትራንስፖርት እና መሰል ወጪዎች ገንዘባቸውን ይጨርሳሉ፡፡ ከዚህ የሚከፋው ደግሞ የሌሎችን እጅ ጠብቀው ሕይወታቸውን የሚገፉ ሴቶች ይህን ፈተና ሲጋፈጡ ችግራቸው ዓይነተ ብዙ መሆኑ ነው፡፡

ወይዘሮ አዳኑ ኩሪ ከአርሲ ወደ አዲስ አበባ ለሕክምና ከመጡ ዘጠኝ ወራትን አስቆጥረዋል፡፡ የማህጸን ካንሰር ታማሚ ናቸው፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ካንሰር አሶሴሽን የሴት ካንሰር ታካሚዎች መንከባከቢያና ማቆያ ማዕከል›› ውስጥ የጠዋቷን ፀሐይ ሲሞቁ ነበር ያገኘናቸው፡፡ በአሁን ወቅት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሕክምናቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ፡፡ በማዕከሉ በሚሰጠው አገልግሎት ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡ ስለማዕከሉ ሲናገሩም ‹‹ከቤት የበለጠ እንክብካቤ እዚህ አገኛለሁ›› ይላሉ፡፡

በጤንነታቸው ላይ መሻሻል እየታየ እንደሆነ የሚገልጹት የአምስት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ አዳኑ በበኩላቸው፤ ከዚህ ቀደም በኪራይ ቤት ተቀምጠው ክትትል ያደርጉ የነበረ ሲሆን፤ በሰዎች ጥቆማ ወደ ማዕከሉ በመግባት ከአስታማሚ ልጃቸው ጋር የምግብ፣ የማረፊያ ቦታ እና የንጽህና ቁሳቁሶችን ድጋፍ እያገኙ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ማዕከሉ ለጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ቅርብ እንደመሆኑ ለወይዘሮ አዳኑ እና መሰል ታካሚዎች ያለምንም እንግልት ሕክምናቸውን እንዲከታተሉ አድርጓቸዋል፡፡ በዚህም ወይዘሮ አዳኑ፤ ‹‹የዓለም ብድር ይግባቸው፡፡ ድርጅቱን ሰፊ ያድርግልኝ፡፡ ድኜ ልጆቼን በማስተባበር ማዕከሉን ለመርዳት ያብቃኝ፡፡›› በማለት መልካም ምኞታቸውን በምስጋና እና በምርቃት ይገልፃሉ።

‹‹የኢትዮጵያ ካንሰር አሶሴሽን የሴት ካንሰር ታካሚዎች መንከባከቢያና ማቆያ ማዕከል›› በኢትዮጵያ በካንሰር ምክንያት የሚከሰተውን የበርካታ ሰዎች ስቃይ እና ሞት ለመቀነስ ብሎም ለመከላከል ታኅሳስ 1995 ዓ.ም በበጎ ፈቃደኞች፣ የካንሰር ሕክምና ባለሙያዎች፣ የካንሰር ህመምተኞች እንዲሁም በቤተሰቦቻቸው የተቋቋመ ሀገር በቀል መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው፡፡ የማዕከሉ ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ህሊና ዮሐንስ እንደሚናገሩት፣ ማዕከሉ ራዕይ አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ያለው በቂ የካንሰር ሕክምና ያለባትና ካንሰር ለብዙ ሰዎች ስቃይና ሞት ምክንያት ያልሆነባት ኢትዮጵያን ማየት ነው። ማዕከሉ የተመሰረተው የሕዝቡን የካንሰር ግንዛቤ ከፍ በማድረግ ካንሰርን በመቆጣጠር ሕክምናው እንዲስፋፋና የሚፈጥረውን ማሕበራዊ ቀውስ ከመቀነስ አኳያ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚደረጉ ጥረቶችን በማገዝ ለሀገሪቱ ዘላቂ ልማት የበኩሉን አስተዋፅኦ ማድረግ ላይ በማተኮር ነው፡፡

‹‹ እአአ ከ2014 ጀምሮ ‹‹Compassionate Home Care›› በተባለ ፕሮጀክት ስር ከሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች ለጨረርና ኬሞቴራፒ ወደ ጥቁር አንበሳ የሚመጡ ሴት የካንሰር ታካሚዎችን ማቆያና መንከባከቢያ ቦታን በማዘጋጀት በቀን ሦስት ጊዜ የምግብ አገልግሎት፣ የንፅህና መጠበቂያ፣ መኝታ እንዲሁም ሥነ ልቦናዊና ማሕበራዊ ድጋፎችን እንዲያገኙ እያደረገ ይገኛል፡፡›› ያሉት ሥራ አስኪያጇ፤ በዚህም እስካሁን ድረስ ከ4500 በላይ ሴት ካንሰር ታካሚዎችን ከእነ አስታማሚዎቻቸው በፕሮጀክቱ ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ አብራርተዋል፡፡

እንደ ሥራ አስኪያጇ ገለፃ፤ በኢትዮጵያ የካንሰር ፖሊሲ እንዲኖር ማድረግ፣ የኅብረተሰቡ የካንሰር ግንዛቤ ከፍ እንዲልና የካንሰር ሕክምና አማራጮች እንዲስፋፉ ማስቻል እንዲሁም የካንሰር ታማሚዎች ሥነ ልቦናዊ እና ማህበራዊ ድጋፎችን እንዲያገኙ ማድረግ የማዕከሉ ቀዳሚ አላማዎች ናቸው፡፡ ይህንን መሠረት በማድረግ ማዕከሉ አላማዎቹን ለማሳካት የተለያዩ ስልቶችን እንደሚጠቀም የሚገልጹት ዶክተር ህሊና፤ የተለያዩ መገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመስጠት የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ፣ መንግሥትን የመቀስቀስ ሥራዎችን በመሥራት በካንሰር ላይ ያለውን ትኩረትና ቁርጠኝነት መጨመር እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ ‹‹የተደራጀ የካንሰር ማዕከል›› በሀገሪቱ ውስጥ በማቋቋምና ባሉት የመንግሥት ጤና ተቋማት ላይ የአቅም ግንባታ ሥራ በመሥራት የካንሰር ሕክምና አገልግሎቶችን እና የህሙማን እንክብካቤን ማስፋፋት ከስልቶቹ መካከል በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡

ከነዚህ በተጨማሪም ድጋፍ (የፈንድ) ማፈላለግ ሥራዎችን በመሥራት የማዕከሉን አቅም ማጎልበት፣ የተሻሉ የካንሰር መረጃ አያያዝ ዘዴዎችን በማዘጋጀትና በማስተዋወቅ የካንሰር የምዝገባ ሥርዓትን ማስፋፋት እንዲሁም በካንሰር ላይ ምርምሮችን ማድረግ እና የሚደረጉትን በመደገፍ ካንሰር ነክ የሆኑ መረጃዎች የሚገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይገኙበታል፡፡

እንደ ዶክተር ህሊና ማብራሪያ፤ ማዕከሉ ከተለያዩ ክልሎች ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሚመጡ ሴት ታማሚዎችን ተቀብሎ የምግብ የንጽህና መጠበቂያ ድጋፍ የሚያደርገው ሴቶች በአብዛኛው ጊዜ የኢኮኖሚ ጥገኛ በመሆናቸው ነው፡፡ በመሆኑም ወደ ማዕከሉ ለመግባት የሚጠየቁ መስፈርቶችም፤ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ታካሚ መሆን፣ ሴት የካንሰር ታካሚ መሆን፣ በአዲስ አበባ ከተማ ማረፊያ ቦታ የሌላቸው እና የገንዘብ እጥረት ያለባቸው ሴቶች መሆንን ብቻ ነው፡፡

ማዕከሉ ከላይ የተጠቀሱትን አገልገሎት ይስጥ እንጂ ተደራሽነቱን ለማስፋፋት እና የታካሚዎችን ቁጥር ከፍ ለማድረግ የማቆያ ቦታ እና የገቢ ምንጭ አለማግኘት ያሰበውን እንዳያሳካ እንቅፋት ሆኖበታል፡፡ በተጨማሪም ማዕከሉ ብዙ የሰው ቁጥር እንዳይጨምር ያለው አልጋ 15 ብቻ ነው፡፡ ስለዚህም ከአንድ አስታማሚ ጋር በተገቢ ቦታ ለማስተናገድ በቂ አይደለም፡፡ በመሆኑም ሌሎች ቅርንጫፎችን በመክፈት ገቢ የሚገኝበትን መንገድ ለመፍጠር መታቀዱን ዶክተር ህሊና ተናግረዋል፡፡

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You