ኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሚኖሩባት ሀገር እንደመሆኗ የብዝኃ ባሕል ባለቤት ናት። ለዚህም ማሳያ የሚሆኑትን በመስከረም ወር ብቻ የተከበሩትን የመስቀል፣ የኢሬቻ፣ ያሆዴ፣ መሣላ፣ ጊፋታ በዓላትን መጥቀስ ይቻላል፡፡በዓላቱ የአደባባይ መሆናቸው ደግሞ ወቅቱ የበለጠ ደማቅ እንዲሆን አድርገውታል፡፡
በዓላቱ ከኃይማኖታዊ ትውፊታቸው ባሻገር በርካታ ማኅበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፋይዳ ያላቸው ናቸው፡፡ በእነዚህ የአደባባይ በዓላት ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አኗኗራቸውን፣ ማንነታቸውን፣ አብሮነታቸውን፣ ቋንቋቸውን፣አልባሳቶቻቸውን፣ ባሕላዊ ምግብና መጠጣቸውን፣ በአጠቃላይ እሴቶቻቸውን አንጸባርቀዋል፡፡ በዚህ መሐልም ኢትዮጵያዊነት ደምቆ ታይቷል፡፡
በዓላቱ በቅብብሎሽ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር የመጡና ሕዝቡም በእኔነት ስሜት ጠብቋቸው ያቆያቸው መንግሥትም በዓላቱ ወደ አደባባይ እንዲወጡና የቱሪዝም ሃብትም እንዲሆኑ ጭምር ያደረገው ጥረት በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡
ይህንን ስራ በዋነኝነት ካስተባበሩና ከመሩ ተቋማት አንዱ የኢፌድሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ነው። የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም በዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከባህልና ስፖርት ሚኒስትር ከአቶ ቀጄላ መርዳሳ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡መልካም ንባብ፡፡
አዲስ ዘመን፡- መስከረም ወር በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በርካታ የአደባባይ በዓላት ይከበራሉ፡፡ ዘንድሮ በዓላቱ በምን ሁኔታ አለፉ?
አቶ ቀጄላ፡- ከመስከረም ወር በፊት ጀምሮ ነው ኃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው ግን ደግሞ በውስጣቸው የባሕል እሴት የያዙ የአደባባይ በዓላት መከበር የጀመሩት፡፡ ከነሐሴ ወር አጋማሽ ጀምሮ በተለይ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ሻደይ፤ አሸንድዬ፤ ሶለልና አሸንዳን የመሳሰሉት የአደባባይ በዓላት ሲከበሩ ቆይተዋል፡፡
በመስከረም የዘመን መለወጫ በዓልም ቢሆን ልጃገረዶች ተሰብስበው የሚጫወቱት እንቁጣጣሽ የመስከረም ወር መጀመሪያ በዓል ነው ማለትም ይቻላል፡፡
መስከረም በራሱ የዘመን መለወጫ መሆኑ እንደ አንድ እሴት ይወሰዳል፡፡ አንድ ሀገር የራሱ መለያ የሆነ የዘመን መለወጫ ሊኖረው ይገባል። በዚህ ውስጥ ወቅት፣ ቀናት፣ ዓመታት አሉ፡፡ በነዚህ ጊዜያቶች ደግሞ ክንውኖች አሉ፡፡ እነዚህን ለመፈጸም መርሐ ግብሮች ይወጣሉ፡፡
ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰብና ሕዝቦች ሀገር እንደመሆኗ የተለያዩ እሴቶች አሏቸው፡፡ ከእሴቶቹ አንዱ ኃይማኖታዊና ባሕላዊ ይዘት ያላቸው በዓላት ይጠቀሳሉ፡፡ አብዛኞቹ በዓላት ደግሞ በመስከረም ወር የሚከናወኑ ናቸው፡፡ እንደ ያሆዴ፣ጊፋታ፣ ፊቼ ጨምበላላ፣ ኢሬቻ ያሉ በዓላት የመስቀል ወቅትን ተከትለው የሚከናወኑ ቢሆኑም ከጨለማው ወቅት ወደ ብርሃን ወይንም ከአንዱ ዘመን ወደ ሌላኛው ዘመን መሸጋገራቸውን የሚያበስሩ ናቸው፡፡
በዓላቱ እንደ የአካባቢው ወግና ባሕል የሚከበሩ ቢሆንም ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ናቸው፡፡ አንዳንድ ቦታ ደግሞ ተደራራቢ ናቸው፡፡
እንዲህ ያሉ እሴቶች ለገጽታ ግንባታ ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው፡፡ ኢትዮጵያ እምቅ ሀገር በቀል እውቀቶች፣ ትልቅ የሆነ ማኅበረሰብ ያላት ሀገር መሆኗ በሌላው ማኅበረሰብ እንድትታወቅ ጉልህ ፋይዳ አለው፡፡ በበዓላቱ ውስጥ የሚንጸባረቀው ከመንፈሳዊ ይዘቱ በተጨማሪ ጭፈራው፣ ደስታው፣ በባሕል አልባሳት መድመቁ፣ የባሕል ምግብና መጠጡ ጭምር ናቸው እሴቶቹን የሚገልጹት፡፡
በዓላቱ አንዱ ከሌላው አካባቢ ማኅበረሰብ ጋር ትስስር እንዲፈጥር ከማድረጋቸው በተጨማሪ በሰዎች መካከል ሰላም፣ፍቅር፣ መተሳሰብ እንዲፈጠር በማድረግ አበርክቷቸው ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ በተለያየ ምክንያት በመካከላቸው ግጭት የፈጠሩ ሰዎች ቀድመው ሰላም ፈጥረው ነው በዓሉን ለመታደም የሚዘጋጁት፡፡
እንዲህ ዘርፈ ብዙ እሴቶች ያሏቸው የአደባባይ በዓላት ፍጹም ሰላም ያስፈልጋቸዋል፡፡ ደስታቸውን በአደባባይ ለማሳለፍ ከቤታቸው የወጡ ሰዎች በሰላም ወደ ቤታቸው መመለስ አለባቸው፡፡ ከዚህ አንፃር በዓላቱ በጣም ባማረና በተሳካ ሁኔታ ተከብረው አልፈዋል፡፡ በጣም ደማቅና አስደሳችም ነበሩ፡፡
በዓላቱ ከሰላሙና ከማኅበራዊ ትስስራቸው በተጨማሪም ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውም የጎላ ነበር፡፡ በበዓላቱ በርካታ ግብይቶች ነበሩ። የባሕል አልባሳት በስፋት ይሸጡ ነበር፡፡ ለአብነት ወላይታ ላይ የጊፋታ በዓል ከመድረሱ በፊት በዓሉን አስመልክቶ የሚዘጋጅ ገበያ አለ፡፡ ማኅበረሰቡም ለበዓሉ የሚሆነውን ለመሸመት ይወጣል፡፡ ከእንዲህ ያሉ ኩነቶች የሚመነጨው ኢኮኖሚ ከግለሰቦች አልፎ ለአካባቢዎች እድገት አስተዋጿቸው የጎላ ነው፡፡ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት በበዓሉ ለመታደም የሚመጡ ቱሪስቶችም በሚኖራቸው ቆይታ ማደሪያዎችን ጨምሮ የተለያዩ ነገሮችን ስለሚጠቀሙ ሀገራዊ ተጠቃሚነቱን ከፍ ያደርገዋል፡፡ በዓላቱ በዚህ ቅኝት ውስጥ ነው ያለፉት፡፡
አዲስ ዘመን፡- በቀጣይ ሀገራዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ባሕሎች ወደ አደባባይ እንዲወጡና የቱሪስት መስሕብ እንዲሆኑ ምን የታቀደ ነገር አለ?
አቶ ቀጄላ፡- ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የባሕል ፖሊሲ ቀርጿል፡፡ ክብረ በዓላትን ጨምሮ ሀገር በቀል እውቀቶች ፣እሴቶች ጎልተው እንዲወጡ የጥናት ሥራዎች ይሠራሉ፡፡ በበዓላት ወቅትም በሚዘጋጁ የውይይት መድረኮች ላይ የተለያዩ የጥናት ሥራዎች ይቀርባሉ፡፡
በተጨማሪም በዓላቱ በክልሎች የሚከበሩ በመሆናቸው ከክልሎች ጋርም እስከ ዞን፣ ወረዳና ልዩ ወረዳ ጋር ወርደንም የምንሠራበት ሁኔታ አለ። ለአብነት የም ልዩ ወረዳን ማንሳት ይቻላል፡፡ ሄቦ የሚባል የዘመን መለወጫ አላቸው፡፡ አካባቢው ላይ ድንቅ የሆነ በዓል ነው፡፡
በዘመን መለወጫ በዓላቸው ጊዜ ከሚያደርጉት አንዱ ቀደም ሲል ወንጀል ተፈጽሞ ከሆነ ወንጀሎች ተደብቀው እንዳይቀሩ፣ጥፋቶችና ስርቆቶች ተፈጽመው ከሆነ ተለይተው እንዲወጡ ወይንም እንዲጋለጡ ይደረጋል፡፡ እነዚህን ድርጊቶች ማኅበረሰቡ ስለሚፀየፋቸው ነው ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራባቸው፡፡ እንዲህ ማኅበረሰቡ ለረጅም ጊዜ ይዞ ያስቀጠላቸው ግን ደግሞ ያልተነገረላቸው መልካም የሆኑ እሴቶች አሉን፡፡ ስለዚህም እነዚህን መሰል ባሕሎች ወደ አደባባይ እንዲወጡ እየተደረጉ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በነዚህ የተለያየ እሴት ባላቸው በዓላት ላይ ያለው ሚና እንዴት ይገለፃል?
አቶ ቀጄላ፡- የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሚና ማስተባበር ነው፡፡ የባሕልና የቋንቋ ፖሊሲ በአጠቃላይ የሕግ ማዕቀፎች አሉ፡፡ እነዚህን ወደ ክልሎች በማውረድ ሥራዎች በእቅድ እንዲከናወኑ ማስቻል ነው፡፡ በዓመት ሁለት ጊዜ ከክልሎችና ከተጠሪ ተቋማት ጋር የምንገናኝበት መድረክ ስላለ በእቅዶች ላይ እንወያያለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሥራ ላይ ያለው የባሕል ፖሊሲ የሀገሪቱን ብዝኃ ባሕል በማውጣት በኩል እገዛው ምን ያህል ነው ?
አቶ ቀጄላ፡- ሥራ ላይ ማዋል ከተቻለ ጥሩ ፖሊሲ ነው ያለው፡፡ ምንም እንኳን በዓሉ የሕዝብ ቢሆንም ማቀናጀትና ማስተባበር ይፈልጋል፡፡ እንደ መንግሥት በዓሉ እንዲከበር ትኩረት መሥጠት፣ ለበዓሉ የሚሆን ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ በተለያየ ነገር ማገዝ ይጠበቃል፡፡
ለሀገር ገጽታ ግንባታም ሆነ የኢኮኖሚ ጥቅም እንዲያስገኙ እገዛ አስፈላጊ ነው፡፡ በበዓሉ ላይ በአባቶች የሚተላለፉ መልእክቶች፣ በዓሉ ለሰላም ያለውን ጠቀሜታ ለሀገራዊ ሰላም ትልቅ ፋይዳ ያላቸው በመሆኑ በጋራ መሥራቱ ጥቅም አለው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በዓላቱ አብሮነትን፣ መዋደድን፣ ሰላምን የሚያስተላልፉ ወይንም የሚሰብኩ ናቸው፡፡ ሆኖም ግን ከዚህ መልካም እሴት በተቃራኒ የፀጥታ ስጋት የሚሆኑበት አጋጣሚ አለ፡፡ ለዚህ እንደመንስኤ የሚነሳ ነገር ካለ ቢገልጹልን?
አቶ ቀጄላ፡- እንዲህ ያሉትን መልካም ነገሮች በመጠቀም የራሳቸውን ፍላጎት ለማሳካት ጥረት በሚያደርጉ አካላት ምክንያት ነው ስጋቱ የሚፈጠረው እንጂ ሕዝቡ በተለመደው መልኩ በዓሉን አክብሮ ወደ ቤቱ ለመመለስ የሚፈልግ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በአደባባይ በዓላት ላይ ትንሽ ግጭት ሰፊ ጉዳት ያስከትላል፡፡ ከዛሬ አምስት አመት በፊት ቢሾፍቱ ላይ የኢሬቻ በዓል ሲከበር የተፈጠረውን ማስታወስ ይቻላል፡፡ በዓል ለማክበር የወጣ በማያውቀው ነገር ብዙ ሰው ነበር የተጎዳው። በመንግሥትም ቢሆን ጥንቃቄ የጎደለው እርምጃ ሲወሰድ ትርምስ ይፈጠራል፡፡
በዓላት የፖለቲካ ዓውድ መሆን የለባቸውም።
ለምሳሌ በገዳ ሥርዓት በክብረ በዓሉ ቀን ፖለቲካዊም ሆነ ጦርነትን የተመለከተ በንግግር እንኳን አይነሳም፡፡ የጦር መሣሪያም አይያዝም። ብረት ይዞ ኃይለ ቃል መናገር በሕግ የተከለከለ ነው። ባሕሉም፣ ሕጉም አይፈቅድም፡፡ እርጥብ ሣር ነው ተይዞ የሚወጣው፡፡
ይህን ጥሰው ጣልቃ ለመግባት የሚሞክሩ ናቸው ችግር የሚፈጥሩት ለዚህም ነው መንግሥት በልዩ ጥበቃ ሰላምን ለማስከበር ጥረት የሚያደርገው፡፡ በዚሁ መሠረት የአደባባይ በዓላቱ በሰላም ሊጠናቀቁ ችለዋል፡፡ ወደፊት የፖለቲካ ሥርዓቱ እየዘመነ ሲሄድ ስጋት የሚሆኑ ነገሮች እየተቀረፉ ይሄዳሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የሕዝብ በሆኑ በዓላት ላይ ጣልቃ በመግባት በኩል መንግሥትንም የሚተቹ ወገኖች አሉ፡፡ ለዚህ ምላሽዎ ምንድነው?
አቶ ቀጄላ፡- ብዙ መንግሥታት አልፈዋል። ጥያቄው የትኛውን መንግሥት እንደሚመለከት ባላውቅም፤ እኔ እስከማውቀው ድረስ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ መንግሥት የሕዝቡን ሰላም እየጠበቀ ነው፡፡ ከዚያ በፊት በነበሩት ግን ግጭቶች ነበሩ፡፡ በተለይም በኢሕአዴግ ጊዜ ግርግር ነበር፡፡ ሰዎችም ይታሰሩ ነበር፡፡ ጉዳትም ደርሶባቸዋል፡፡
አሁን ባለንበት ወቅት ይሄን አላስተዋልንም። መንግሥት በኃይማኖት ጣልቃ አይገባም፡፡ ሁሉንም በእኩል ያያል፡፡ ሕገመንግሥቱም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ እንደ መንግሥትም በሁሉም ላይ ለመገኘት ጥረት ይደርጋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የአደባባይ በዓላት በተባበሩት መንግሥታት የባሕል፣ የትምህርትና ሳይንስ ድርጅት(ዩኔስኮ) ይመዘገባሉ። ጠቀሜ ታው ምንድነው? እስካሁን የተመዘገቡትስ ያስገኙት ጥቅም እንዴት ይገለጻል?
አቶ ቀጄላ፡- የሚዳሰስ ወይንም የማይዳሰስ ቅርስ በዩኔስኮ ሲመዘገብ የተለያየ ጠቀሜታ አለው። አንዱ ጥቅም እውቅና እንዲያገኙ ይረዳል።
ሁለተኛው የዓለም ሀብት ይሆናሉ፡፡ ሌላው ጥበቃው እንዲጠናከርና የበለጠ ለምቶ ጥቅም እንዲያስገኝ ድጋፍ ያገኛል፡፡ ቅርሱም እንዳይረሳ ወይንም እንዳይዘነጋ ያግዛል፡፡
እስካሁን በተመዘገቡትም በእንከን የሚነሳ ነገር አላጋጠመም፡፡ ያልተመዘገቡት እንዲመዘገቡ መንገድ የከፈቱ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ብዙ ያልተመዘገቡ ቅርሶች አሉ፡፡ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚታወቀው ባሕላዊ የሙዚቃ መሣሪያ ዙንባራና ሌሎችም አሉ። ለመመዝገብ የሚያስችሉ መሥፈርቶች እንዲያሟሉ የጥናት ሥራዎች መሠራት አለባቸው፡፡ አንዳንዶቹም የጥናት ሥራቸው ተጠናቅቋል፡፡ በሂደት ላይ ያሉም አሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ስፖርትንም ስለሚመራ፤ የሀገሪቱን ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ለማሳደግ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን ቢያብራሩልን፤
አቶ ቀጄላ፡- ስፖርቱም እንደ ባሕሉ ሁሉ የሕዝብ ነው፡፡ ስፖርት ያገናኛል፣ ያቀራርባል፣ ለሰላምም እንዲሁ ጉልህ ድርሻ አለው፡፡ ስፖርት ለዲፕሎማሲም እንጠቀማለን፡፡ ስፖርት በርካታ ክንውኖች ያሉት ዘርፍ ነው፡፡
ማኅበረሰቡ በሚኖርበት፣ በሚሠራበት አካባቢ፣ በትምህርት ቤት፣ በሚመቸው ቦታ ሁሉ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ ነው የሚፈለገው፡፡ ሕዝባዊነቱም ከዚህ አንጻር ነው የሚገለጸው፡፡ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እንዲጠናከሩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በተለያየ መልኩ እየሠራ ይገኛል፡፡
የስፖርት ሥራ ሰፊ ነው፡፡ አደረጃጀቶች አሉ፡፡ በዚህ ዘርፍም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ፖሊሲዎችን መተግበር ነው ዋነኛ ሥራው፡፡ የስፖርት ፖሊሲው የስፖርት አደረጃጀቶችን ማመቻቸት ነው፡፡ ዜጎች ተደራጅተው በስፖርት እንዲሳተፉ ማድረግ ነው። በዚህ ላይ የተለያዩ አደረጃጀቶች አሉ፡፡ የስፖርት ፌዴሬሽን፣ በክልልና በፌዴራል የተደራጁ የስፖርት ማኅበራት አሉ፡፡ አብዛኞቹ ማኅበራትም ከተደራጁ የቆዩ ናቸው፡፡ በእንቅስቃሴም ላይ ይገኛሉ፡፡
ከነዚህ ውስጥም እንደ አትሌቲክስ ያሉ ጠንክረው የወጡ አሉ፡፡ የሚቀራቸውም አሉ። በተለይም ወደኋላ የቀሩትን ለማጠናከር ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ተተኪዎችን በማፍራት ዘርፉን ለማጠናከር ታዳጊዎችን አሰልጥኖ ለማብቃት በትኩረት እየተሠራ ነው፡፡ ለስፖርቱ የሚያግዙ የሥልጠናና ተያያዥ ለሆኑ አገልግሎቶች የሚውሉ ማዕከላት ግንባታዎችና የማስፋፊያ ሥራዎች ጎን ለጎን ማከናወንና የማደራጀት ተግባራት ተጠናክረዋል፡፡
አዲስ አበባ ከተማ ላይ አንድ ትልቅ የስፖርት ማዕከል አለ፡፡ በክልሎችም ወደ 15 የሚሆኑ የስፖርት ማሠልጠኛዎች በየአካባቢው ይገኛሉ። ተተኪ ታዳጊዎችን የማፍራት ሥራ የሚሠራው በነዚህ ማዕከላት ውስጥ ነው፡፡ ታዳጊዎቹ በሥልጠና ከበቁ በኋላ ነው ወደ ክለቦች የሚቀላቀሉት፡፡
በሩጫ፣ በእግር ኳስና በተለያዩ የስፖርት አይነቶች በክልሎች፣ በሀገር አቀፍ፣ በአህጉራዊና በዓለም አቀፍ ደረጃ ውድድሮች ይደረጋሉ፡፡ በዚህ መልኩ በተለያየ ጊዜ በተደረጉ ውድድሮች ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ በተለይም በሩጫው ከፍ ያለ ስኬት ማስመዝገብ ተችሏል።
የስፖርት ማዘወተሪዎች እንደመጫወቻ፣ መዝናኛ ቦታዎች በመሥራትና ምቹ በማድረግ ረገድ መንግሥት አቅሙ በፈቀደ መጠን እየሠራ ይገኛል። የስፖርት ልማት ሥራ ሰፊ በመሆኑ በመንግሥት አቅም ብቻ ውጤታማ ለመሆን ጊዜና አቅምን ስለሚጠይቅ ፣የግሉ ዘርፍም ሊሳተፍበት ይገባል፡፡ በዚህ ረገድም አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
እስካሁን ሲሠራበት የቆየው ስፖርትን ማልማት በሚል አካሄድ ነበር፡፡ አሁን ግን ስፖርትን ለልማት ማዋል የሚቻልበት አቅጣጫ ነው ያለው። ስፖርት የኢኮኖሚ ምንጭ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል። የብዙ ሀገራት ተሞክሮ የሚያሳየው ስፖርት የገቢ ምንጭ ሆኖ ሀገራዊ ጥቅም ሲያስገኝ ነው። መንግሥት ስፖርትን ከመደገፍ አልፎ ዘርፉ በራሱ መንግሥትን እንዲደግፍ መሥራት ይገባል። በኢትዮጵያም ዘርፉን ለኢንቨስመንት ክፍት በማድረግ ተጠቃሚ በምንሆንበት ላይ ነው እየሠራን የምንገኘው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በዘርፉ የሚሰማሩት ምን ላይ እንዲሳተፉ ነው የሚበረታቱት? ወደ ሥራውስ ተገብቷል?
አቶ ቀጄላ፡- በሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ባለሀብቶች እንዲሰማሩ እንደሚደረገው ሁሉ በስፖርት ዘርፉም ባለሀብቶች ሜዳ በማሠራት፣ ለስፖርታዊ ተግባራት የሚውሉ ሱቆችንም ሊሆኑ ይችላሉ የተለያዩ የአገልግሎት መስጫዎች በመገንባት ሊሳተፉ ይችላሉ፡፡
ይህ ፍላጎት ገና ወደተግባር የተቀየረ ባይሆንም በሀሳብ ደረጃ ግን አስፈላጊነቱ ታምኖበታል፡፡ ይህን ሀሳብ ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚያስችል ለስፖርት ፈንድ የሚል አዋጅ ለማውጣት በእንቅስቃሴ ላይ እንገኛለን፡፡ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቷል፡፡ አዋጁ ፀድቆ ሥራ ላይ ሲውል የስፖርት ኢንቨስትመንትን ለማጠናከር እገዛው ከፍተኛ እንደሚሆን ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን፡- በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ እግር ኳሱ በምን ደረጃ ይገኛል? ለስፖርቱ የሚያግዙ እንደ እግር ኳስ ሜዳዎችን ማመቻቸት ላይ የተሠሩ ሥራዎችን ቢገልጹልን።
አቶ ቀጄላ፡- በቅድሚያ ከስታዲየም ግንባታ ጋር የተያያዘውን ማንሳት እወዳለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ የእግር ኳስ መጫወቻ ሜዳዎች ወይንም ስታዲየሞች አሉ፡፡
እኔ ወደ እዚህ የሥራ ኃላፊነት ስመጣ በርካቶቹ ስታዲየሞች የተሟላ ነገር የሌላቸውና ያለአገልግሎት የተቀመጡ ሆነው ነው ያገኘኋቸው፡፡ መጠገን የሚቻለውን በመጠገንና በማሳደስ፣ አዲስ ግንባታ ላይ የሚገኘውም ግንባታው እንዲፋጠን ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡
በተለይም በግንባታ ላይ የሚገኘው የአደይ አበባ ስታዲየምን እንዲገነባ የተሰጠው ተቋራጭ ሥራውን በማጓተቱ ለሌላ እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡ አሁን ግንባታው ጥሩ በሚባል ደረጃ እየሄደ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ስታዲየምም አንዳንድ የማጠናቀቂያ ሥራዎች ካልሆኑ በስተቀር ሥራው አልቋል፡፡ በኅዳር ወር ላይ ሙሉ ለሙሉ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡
እዚህ ላይ አንድ መዘንጋት የሌለበት ጥሩ ስታዲየም ስላለን በእግር ኳስ ስፖርቱ አሸናፊ ወይንም ውጤታማ እንሆናለን ማለት አይደለም። አሁን በሀገራችን ያለው የሕዝቡ ስፖርት ፍቅርና የስፖርት ቡድኖቻችን ውጤት አይጣጣምም። ታዳጊዎች ላይ መሥራት ይጠበቃል፡፡ በሚሰጡ ሥልጠናዎችና ልምምዶች እንዲሁም የሚመለመሉት ላይ ብዙ ሥራ ይቀራል፡፡ በመሆኑም በጥሩ ሁኔታ መያዝና አደረጃጀቱ ላይ መሥራት ያስፈልጋል፡፡
ብዙዎች ስለመጫወቻ ሜዳ ጉዳይ ያነሳሉ። የእግር ኳስ ስፖርት ውጤታማ ያልሆነው በመጫወቻ ሜዳ ማጣት፣ ወይንስ በሌላ ምክንያት የሚለው መፈተሽ ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱን ለይቶ መፍትሔ መሥጠት ስለሚያስፈልግ እኛም እየገመገምን እንገኛለን፡፡
ከእግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራሮች ጋርም በጋራ በመምከርና በባለሙያዎችም እንዲጠና ሥራ ለመሥራት ተነጋግረናል፡፡ የእግር ኳስ ዘርፉ የግል ነው ማለት ይቻላል። ክበቦቹ የሚፈልጉትን ይይዛሉ። የማይፈልጉትን ደግሞ ያስወጣሉ፡፡ ከመንግሥት ውጭ ናቸው፡፡ ሆኖም ግን እንዴት አድርጎ ማሻሻል ይቻላል በሚለው ላይ መሥራትና እንዲጠናከሩ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
የግንባታ ሥራዎችን በተመለከተ ትኩረት የተሰጠው ትላልቅ ስታዲየሞችን ከመገንባት፣ በመንደር አካባቢ አነስተኛ መጫወቻዎች እንዲጠናከሩ ነው፡፡ እነዚህ ከስር ጠንካራ የሆኑ ተተኪዎችን ለማፍራት ያግዛሉ፡፡ በዚህ ረገድም በዘርፉ ልምድና እውቅና ካላቸው ሀገራት የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም በጋራ እየሠራን ነው።
አዲስ ዘመን፡- የስታዲየም ግንባታዎች ከፍተኛ በጀት የሚጠይቁ በመሆናቸው በምን ምልኩ ነው ግንባታዎች እየተከናወኑ የሚገኙት?
አቶ ቀጄላ፡- እርግጥ ነው ከባድ ነው፡፡ የአደይ አበባ ስታዲየም በከፍተኛ የገንዘብ ወጭ ነው የሚገነባው፡፡ የግንባታ እቃዎቹ ከውጭ የሚገቡ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ነው የግንባታ ዋጋው የናረው፡፡ ከላይ ለክዳን ወይንም ጣሪያ የሚውለው ብቻ ወደ 70 ሚሊዮን ዶላር ይፈጃል፡፡ በብዙ እጅ ውስጥ የሚያልፍ በመሆኑ ውስብስብ ነው፡፡
ከመንግሥት በጀት በተጨማሪ በአንዳንድ ነገሮች ላይ የተለያዩ አጋሮችን ድጋፍ በመጠየቅ ግንባታውን በቁርጠኝነት ለመጨረስ ጥረት እየተደረገ ይገኛል። በዓለም አቀፍ ተከስቶ የነበረው ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝና ሀገራዊ ሁኔታም ለግንባታው አለመፋጠን የራሱ አስተዋጽዖ ነበረው።
በተለይ በኮቪድ ምክንያት ከቻይና የግንባታ እቃዎችን ለማስመጣት ትልቅ ፈተና ሆኖ ነበር። በዚህ ምክንያት ሥራው ለአንድ ዓመት ተስተጓጉሏል፡፡ የግንባታ እቃዎች ንረት መከሰቱ ችግሩን ተደራራቢ አድርጎታል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከአዲስ አበባ ከተማ ስታዲየም እድሳት ጋር በተያያዘ ተደጋግመው ከተነሱት ውስጥ አንዱ የሳር ተከላ ጉዳይ ነው። ከዚህ ጋር የተፈጠረው ችግር ምንድን ነው?
አቶ ቀጄላ፡- እኔ ባለሙያ አይደለሁም። ሆኖም ግን ያለውን ነገር ግልጽ ለማድረግ ከባለሙያዎች እንደተነገረው የመሬት ድልድሉ ወይም ሌየሩ አሠራር መሠረቱ ጥሩ ከሆነ የሀገር ውስጥም የሆነ ከውጭ የሚመጣው ሳር ሊሆን ይችላል፡፡ የተዳቀለም ቢሆን ችግር የለውም፡፡ አርቲፊሻሉም እንዲሁ፡፡
እኔ ወደ ኃላፊነት ከመምጣቴ በፊት ነበር ስታዲየሙ እንዲታደስ ለተቋራጭ የተሰጠው፡፡ ወደ ሥራ ከመጣሁ በኋላ ነው ሳር ከውጭ መጥቶ እንዲተከል የሚል ሀሳብ የመጣው፡፡ ከፈረንሳይ የመጣ ባለሙያ ሳሩን ለመትከል ወደ 60 ሚሊዮን ብር ጠየቀ፡፡ የስፖርት ዘርፉን የሚመሩ አመራሮች ዋጋው ውድ እንደሆነና ከሀገር ውስጥ በሚገኝ ሳር እንዲተከል ሀሳብ ሰጡ፡፡ በዚሁ መሠረት ሳሩ ተተክሎ በጥሩ ሁኔታ ፀደቀ፡፡ እስካሁንም ሳሩ አያስፈልግም የሚል ተቋውሞ አልገጠመም፡፡ ጥያቄ አልቀረበም፡፡
ሳሩ በባለሙያዎችም ታይቶ ጥሩ እንደሆነ ነው የተረጋገጠው፡፡ በዝናብ ወቅት ውሃ የማስረግ ወይንም መምጠጥ ላይ ችግር ይኖራል የሚል ስጋት ሲነሳ እሰማለሁ፡፡
የእድሳቱ ሥራ ሙሉ በሙሉ አልተጠናቀቀም። ባለሙያዎችም ገና መጥተው የሚያዩት በመሆኑ በዚህ ላይ ግንዛቤ እንዲኖር እንጂ የተሟላ መረጃ መስጠት የሚቻለው ሥራው ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ ነው፡፡ ችግሮችም ካሉ እየታረሙ ይሄዳሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንደሀገር ምንያህል የመጫወቻ ሜዳዎች አሉ?ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየምስ አለ?
አቶ ቀጄላ፡- ምንም እንኳን ደረጃውን የጠበቀ የስታዲየም ግንባታ አስፈላጊ ቢሆንም አሁን ባለው ሁኔታ ቀደም ሲል እንደገለጽኩት ጠንካራ የሆኑ ተተኪዎችን ለማፍራት ታዳጊዎች ላይ መሥራት ስለሚያስፈልግ ትኩረታችን አነስተኛ ስታዲየም ግንባታ ላይ ነው፡፡
በየመንደሩ ያሉትን የመጫወቻ ሜዳዎች ምቹ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ 15 የሚሆኑ አነስተኛ እና አንድ ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም ግንባታዎች ለማከናወን ከሞሮኮ መንግሥት ጋር ተነጋግረናል። ስለዚህም በቀጣይ የአደይ አበባ ስታዲየምን የማጠናቀቅና አነስተኛ የመጫወቻ ሜዳዎችን የማስፋፋት ሥራዎች ላይ ትኩረት እናደርጋለን ማለት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።
አቶ ቀጄላ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1 ቀን 2016 ዓ.ም