የአንድ ሀገር ሰላም ከሁሉም በላይ ከዜጎቿ የሰላም መሻት የሚመነጭ ነው። ከዚህ የተነሳም ሀገራት ሰላማቸውን ለማጽናት የዜጎቻቸው መንፈሳዊና ሥነ ልቦናዊ ማንነት ሰላማዊ እና በሁለንተናዊ መልኩ ለሰላም የተገዛ እንዲሆን ሰፊ ሥራዎችን ይሠራሉ። የሥራቸው ስኬታማነትም በተጨባጭ በሚታይ ሀገራዊ ሰላም ሲገለፅም ይታያል ።
ሰላም በየትኛውም የዓለም ክፍል ያሉ ሕዝቦች በጋራ የሚጋሩት ትልቅ ሰብዓዊ እሴት ነው። የየትኛውም ማኅበረሰብ መንፈሳዊ፣ ባሕላዊ እና ማኅበራዊ እሴቶች ለሰላም ከፍ ያለ ትኩረት ይሰጣሉ። ትውልዶችን በነዚህ እሴቶች ኮትኩቶ ማሳደግ እንደ ማኅበረሰብ በዛሬዎች ሆነ ነገዎች ላይ ላላቸው ተስፋ ስኬት ትልቅ አቅም ተደርጎ ይወሰዳል ።
እኛ ኢትዮጵያውያንም እንደ ሀገር ለምናልማቸው ብሩህ ነገዎች ሆነ፤ ለዛሬ ኑሯችን የሰላም ጉዳይ አልፋና ኦሜጋ እንደሆነ በአግባቡ መገንዘብ የቻልንና ለዚህ የሚሆን የዘመናት መነቃቃት ያለን ሕዝቦች ነን። ሰፊው መንፈሳዊ፣ ባሕላዊና ማኅበራዊ እሴቶችችንም ይህንኑ እውነታ በስፋት የሚሰብኩ፣ በተጨባጭ መኖርንም የሚያበረታቱ ናቸው ።
ከዚህም የተነሳም ስለሰላም ያለን እሳቤ፤ እሳቤው በእለት ተእለት ሕይወታችን የፈጠረው ማንነት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላም ወዳድ ሕዝቦች ስለመሆናችን ምስክር መሆን ችሏል። እንደ ሀገርም ስለ ሰላም ከራሳችን አልፈንም የሰላም ሐዋሪያ በመሆን እስከ ሕይወት መስዋዕትነት የጠየቁና በዓለም አቀፍ ደረጃ አንቱታ ያጎናጸፉንን ተግባራትን መከናወን ችለናል ።
እንደሕዝብ ለሰላም ካለን ከፍያለ መሻት የሚቀዳው ለሰላም ያለን ቁርጠኝነት፤ በርግጥም የማኅበረሰባዊ ማንነታችን አንድ አካል ቢሆንም፤ በየዘመኑ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ለማለፍ መገደዱ የአደባባይ ሚስጥር ነው። በዚህም ለመክፈል የተገደድነው ያልተገባ ዋጋ አሁን ላለንበት ድህነትና ኋላ ቀርነት ምክንያት ስለመሆኑም ለመናገር የሚከብድ አይደለም ።
በተለይም በኃይልና በሴራ ላይ የተመሠረተው ኋላቀር የፖለቲካ ባሕላችን ከሁሉም በላይ የሕዝባችንን የሰላም መሻት በመፈታተን በየዘመኑ ሕዝባችን ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍል አስገድዶታል፤ ከአንድ ግጭት ወደ ሌላ ግጭት እየተገላበጠ በግጭት አዙሪት ውስጥ እንዲኖር፤ በዚህም በነገዎቹ ላይ ያለውን ተስፋ ከማጨለም ባለፈ ዛሬን በአግባቡ እንዳይኖርም ያደርጋል።
ለዘመናት ሰፍኖ የኖረው የፖለቲካ ባሕላችን አሁን አሁን ሕዝባችን ለዘመናት ይዟቸው የዘለቃቸውን የሰላም እሴቶች ከመፈታታን አልፎ፤ አዳዲስ የግጭት ትርክቶችን በመፍጠር፤ እንደሀገር ለጀመርነው ድህነትን ታሪክ የማድረግ መነቃቃት ትልቅ ፈተና ከሆነ ውሎ አድሯል። ትናንት ላይ ብሩህ ሆነው ባየናቸው ነገዎቻችን ላይ ያጠላውም ጥላ እንዲሁ በቀላሉ የሚታይ አይደለም ።
ይህ ከሕዝባችን የሰላም መሻት በተቃርኖ እየሄደ ያለው እና እንደሀገር ያልተገባ ብዙ ዋጋ እያስከፈለን ያለው የፖለቲካ ባሕላችን፤ አሁን ላይ በሕዝባችን መልከ ብዙ የሰላም እሴቶች ሊገራ፤ ሊስተካከልና ዘመኑን በሚዋጅ የአስተሳሰብ መሠረት ላይ ሊዋቀር ይገባል። ችግሩ ቀደም ሲል ካስከፈለን ይልቅ ወደፊት ሊያስከፍለን የሚችለው ዋጋ የከፋ ስለሚሆን ፈጥነን ልንቀሳቀስ ይገባል ።
ለዚህ ደግሞ በሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በኩል የትናንትም ሆኑ የዛሬ ችግሮቻችንን በንግግር ለዘለቄታው ለመፍታት የጀመርነው ጥረት ስኬታማ እንዲሆን እያንዳንዱ ዜጋ በኃላፊነት መንፈስ ሊንቀሳቀስ ይገባል። እንደ ሕዝብ በተገዛንበት የሰላም መሻት ራሳችንን እና አስተሳሰባችንን፤ ከዚያም አልፈን ፖለቲከኞቻችንን ልንገራ ያስፈልጋል።
ፖለቲካችን ሆነ ፖለቲከኞቻችን በየትኛውም ሁኔታ እንደሕዝብ ላለን የሰላም እሴቶች ተገዥ በመሆን ፤ ሀገራዊ ሰላማችን ተጨባጭና ዘላቂ እንዲሆን አቅም መሆን የሚችሉበትን አስገዳጅ ሁኔታ እንደ ሕዝብ መፍጠር ይጠበቅብናል። ይህን ማድረግ ደግሞ ለመጭው ትውልድ የተሻለች ሀገርን ከመፍጠር ያለፈ ባለውለታነት ነው።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1 ቀን 2016 ዓ.ም