እንደ ኢማክሌ – ለኢትዮጵያ ሰላም

 ሞኝን እባብ ሁለት ጊዜ ነደፈው፡፡ አንድም ሳያውቀው፤ ሁለትም እንዴት እንደነደፈው ለሰዎች ሲያሳይ፡፡ የእኛ ሀገር ምሑራን፣ ፖለቲከኞች፣ ገበሬዎች፣ ተማሪዎች ወዘተ የፖለቲካል ኢኮኖሚ አካሄድ ልክ እባብ እንደነደፈው ሞኝ ሰው አይነት ነው፡፡

እንደ ሀገር ከደረሱብን አያሌ ችግሮች ተምረው ኢትዮጵያ እና ሕዝቦቿን ከጦርነት እና መሰል ችግሮች መጠበቅ ሲገባቸው በነጋ በጠባ ዋኝተን በማንጨርሰው የችግር ውቅያኖስ ውስጥ ሲዘፍቁን ይስተዋላሉ ፡፡

ምን አልባትም በዓለም ታሪክ አንድን ጦርነት በቅጡ ሳይጨርሱ ወደ ሌላ ጦርነት የሚገቡ፤ የአንድ ችግር መፍቻ ውል ሳያበጁ ወደሌላ ችግር የሚነከሩ፤ የጦርነት ልክፍት ያለባቸው ፤ዜጎቻቸው የቱንም ያህል በጦርነት ቢያልቁ ከመቆጨት ይልቅ በጦርነቱ በነበረው ኩነት የሚኮፈሱ ከንቱዎች ብለው የሚሳለቁብን ይመስለኛል፡፡ ቢሉም እውነት አለው፡፡ ምክንያቱም በእኛ ሀገር ልማት አልምተን ፅድቅ ታገኛላችሁ ቢባል እንኳን ጦርነት አድርገን ኩነኔ ይሻለናል የምንል አይነት ሆነናል፡፡

እኔ እምለው ! ሁሌም ጦርነት፣ ሁሌም ግጭት፤ በጦርነት ተፈጥረን በጦርነት እንድንኖር ምን አይነት እርግማን ተረግመን ይሆን? ከጥንት ዘመን ጀምሮ እስካሁን የኢትዮጵያን የማያባራ ጦርነት ስመለከት ሁሌም ትዝ የሚለኝ የምሥራቁ ጥያቄ (The Eastern Question) እየተባለ የሚጠራው ፖለቲካል ኢኮኖሚ ትርምስምስ እና ጦርነት ነው፡፡ የምሥራቁ ጥያቄ (The Eastern Question) ምንድን ነው? የሚለውን በወፍ በረር እንመልከትና ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በምን ይመሳሰላል የሚለውን እናያለን ፡፡

የደቡብ ምሥራቅ አውሮፓ ወይም (Balkan Countries) የሚባሉት ወደ ስምንት የሚሆኑ ሀገራት ለብዙ መቶ ዓመታት በኦቶማን ቱርክ ኢምፓየር ቅኝ ግዛት ስር ኖረዋል፡፡ ይሁን እና ከኢንዱስትሪ አብዮት መፈንዳት ጋር ተያይዞ በኦቶማን ኢምፓየር ስር ይገኙ የነበሩ የባልካን ሀገራት ውስጥ እና በመላ አውሮፓ የብሔርተኝነት አስተሳሰብ እያደገ መጣ፡፡

ይህ የብሔርተኝነት አስተሳሰብ ተበታትነው እና ተበጣጥሰው የነበሩትን ጣሊያን እና ጀርመንን የመሰሉ ሀገራትን አንድ ሲያደርግ የባልካን ሀገራት ደግሞ ራሳቸውን ችለው ነፃ ሃገር እንዲሆኑ ተነሳሽነትን ፈጠረ፡፡ በአንጻሩ በዚህ ወቅት የኦቶማን ኢምፓየር ኃይል እጅጉን የተዳከመበት ነበር ፡፡

የኦቶማን ኢምፓየር መዳከም እንደመልካም አጋጣሚ የተጠቀሙት የባልካን ሀገራት ነፃ ሃገር ለመሆን የኦቶማን ኢምፓየርን ተፋለሙ፡፡ እነዚህ ሀገራት ነፃነታቸውን ለማግኘት ከኦቶማን ቱርክ ጋር አንገት ለአንገት ተናንቀው በሚፋለሙበት ወቅት በቀጠናው ጥቅማቸው እንዳይነካባቸው ስጋት ያደረባቸው ሁለት የውጭ ኃይሎች ተፈጠሩ፡፡ አንደኛው ወገን እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እና ኦስትሪያን የያዘ ሲሆን ሌላኛ ደግሞ ሩሲያ ያለችበት ነው ፡፡

የምሥራቁ ችግር (The Eastern Question) ዋና መነሻውም እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እና ኦስትሪያ የተዳከመችውን ኦቶማን ቱርክ ደግፈው በኦቶማን ቱርክ ስም የራሳቸውን ፍላጎት በቀጠናው ለማስፈጸም የነበራቸው ፍላጎት ነበር፡፡ በአንጻሩ ሩሲያ ደግሞ ነፃነት ከተጠሙት የባልካን ሀገራት ጋር ተባብራ ደካማዋን ኦቶማን ቱርክ በመጣል የስላቭን ግዛቶች ወደራሷ መጠቅለ ል ትፈልግ ነበር ፡፡

በዚህም ሁለቱ ጎራዎች ጉዳዩን ከባልካን ሀገራት እና ከኦቶማን ቱርክ ነጥቀው የራሳቸው አደረጉት፤ የራሳቸውን ከማድረግም አልፈው ጦርነት ከፍተው ተዋጉ፡፡ ይህም የባልካን ሀገራት የነፃነት ጥያቄን ከማጓተት ባለፈ ቀጣናውን ለዘመናት የጦር አውድማ አደረገው፡፡ ነፃነት የናፈቀው የደቡብ ምሥራቅ አውሮፓ ቀጣና እንኳንስ ነፃ ሊወጣ በችግር ላይ ችግር ተደራረበበት፡፡ የበርካታ ሰዎች ሕይወትም አይሆኑ ሆኖ ተመሰቃቀለ፡፡ ለአንደኛው የዓለም ጦርነት መፈንዳት ቅጽበታዊ ምክንያት (Immediate Couse) ለመሆን በቃ ፡፡

እዚህ ላይ አንድ ነገር ልብ ሊባል ይገባል። መጀመሪያ ላይ በምሥራቁ ጥያቄ (The Eastern Question) የችግሩ ገፈት ቀማሾች የደቡብ ምሥራቅ አውሮፓ ሀገራት (Balkan Countries) ቢሆኑም ዋና ተዋናዮች ግን በቀጣናው ልዩ ፍላጎት የነበራቸው በአንደኛው የዓለም ጦርነት ጉልህ ሚና የነበራቸው ሀገራት ናቸው፡፡

እዚህ ላይ ዋና ዓላማዬ ስለምሥራቁ ጥያቄ (The Eastern Question) ለማንሳት ፈልጌ ሳይሆን በቀጣናው የነበረው አለመረጋጋት ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በተወሰነ መልኩ የተገጣጠመ ስለሆነ ነው፡፡ የባልካን ሀገራት ለበርካታ ዓመታት በቀጣናው ጦርነት እንዲያስተናግዱ ያደረጋቸው ዋና ምክንያት አንደኛው የሚገኙበት ቦታ ከአውሮፓ ወደ ኤዥያ መሸጋገሪያ በመሆኑ ሲሆን ሁለተኛ ደግሞ አካባቢው ያለው የተፈጥሮ ሀብት ነው ፡፡

”ለዝሆን ሞት ምክንያቱ የራሱ ጥርስ ” እንዲሉ የእኛም ሀገር ሕዝብ ለበርካታ ዓመታት በጦርነት እንዲሞት እና እንዲጎሳቀል ሁነኛ ምክንያቱ ኢትዮጵያ ያላት የተፈጥሮ ሃብት እና የምትገኝበት ቦታ ነው።” በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ” እንዲሉ ውጭዎች ከሚያደርሱብን ጫና በተጨማሪ እኛ በራሳችን ይቅርባይነትን መለማመድ አቅቶን ለበቀል መነሳሳታችን የጥፋት ድንጋይ ለሚያቀብሉን ኃይሎች ሥራቸውን ያቀለልንላቸው ይመስለኛል፡፡

ስለእውነት የኢትዮጵያን ሰላም የምንፈልግ ከሆነ የጥፋት ድንጋይ ከሚያቀብሉን ኃይሎች በመራቅ ይቅርባይ መሆን ይገባናል፡፡ አለበለዚያ ”ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል” ነው የምንሆነው፡፡ አሁን ላይ በእኛ ሀገር የሚታዩ ፖለቲከኞች ግን ይቅርባይነትን እንደ መጥፎ ባሕል ከመቁጠራቸው ካለፈ ቀደም ብሎ ቅሬታ በፈጠሩ ጥፋቶች ላይ ከፊት እና ከኋላ ቀንድ እና ጅራት ጨምረውበት ዜጎችን ለበቀል ሲያነሳሱ ይስተዋላል፡፡

ለእነዚህ አይነት ፖለቲከኞች “የኢማክሌን” ልብ እንዲሰጣቸው እመኛለሁ፡፡ ኢማክሌ በሩዋንዳው የእርስ በርስ ጦርነት የዓለምን ሕዝብ እንባ ያራጨች እና በሠራቻቸው ጥሩ ሥራዎች ተምሳሌት መሆን የቻለች እንስት ነች ፡፡

ሩዋንዳውያን ጎሳን መሠረት አድርገው መጨፋጨፋቸው የሚታወቅ ነው፡፡ በግጭቱ ወቅት ከቱትሲ ወገን የነበረች ኢማክሌ የተባለች አንዲት ወጣት ከሁቱ ወገን ከሆነ አንድ የካቶሊክ ቄስ ቤት ተደበቀች፡፡ በካቶሊኩ ቄስ ቤት ተደብቃ እያለች እናት፣ አባቷ እና ወንድሞቿ ዘግናኝ በሆነ መንገድ እንደተገደሉ፤ ማን እንደገደላቸው ትሰማ ነበር ፡፡

ከዚህ ባሻገር በሰፈራቸው ብቸኛው የማስተርስ ምሩቅ የነበረውን ወንድሟን ከገደሉ በኋላ አንገቱን ቆርጠው ትልቅ ጭንቅላት ያለው የሰፈራችን ሰው እያሉ እያፌዙ አንጎሉን እንደፈጠፈጡት ታዳምጥ ነበር፡፡ በቄሱ ቤት መቆየቷ ለሕይወቷ አደገኛ መሆኑን የተረዳቸው ኢማክሌ ከትውልድ ሰፈሯ ሸሸች፡፡

በመጨረሻም ቱቲሲዎች ሁቱዎችን አሸንፈው ወደ ሰፈራቸው በመጡ ጊዜ ከሞት መንጋጋ የተረፈችው ኢማክሌ በተባበሩት መንግሥታት ሥር ትልቅ ሥራ አግኝታ በሄሊኮፕተር ወደ ሰፈሯ ተመለሰች፡፡ በተመለሰች ጊዜም የወንድሟን ጭንቅላት ፈጥፍጦ የገደለውን ሰው በእስር ቤት አገኘችው፡፡

ቱትሲዎችም “የወንድምሽ ገዳይ ይሄ ነው። የራስሽን ፍርድ ሰጥተሽ ግደይው ፤እንደፈለግሽ አድርጊው” አሏት፡፡ የኢማክሌ መልስ ግን የተለየ ነበር ፡፡ “የእኔን ወንድም በአሰቃቂ ሁኔታ ቢገድልም እኔ ግን እሱን መግደል አልፈልግም፡፡ ለጥፋቱ ፈጣሪ ቅጣቱን ራሱ ይስጥ! እኔ ይቅር ብየዋለሁ” ስትል መለሰች፡፡ ሰዎች በኢማክሌ ምላሽ፤ ይቅርባይነት ተገረሙ፡፡ አሁን ላይ ሩዋንዳ ኢማክሌ እና መሰል ይቅር ባይ ሰዎች ባደረጉት ትልቅ ሥራ በመካከላቸው የነበረውን ግጭት ቀርፈው በሰላም መኖር ችለዋል፡፡

በይቅርታ ውስጥ ብዙ ትርፍ አለ፤ በይቅርታ ውስጥ ከግለሰብ አልፎ ሀገር ማትረፍ ፣ማቆምና ማጽናት አለ። በይቅርታ ውስጥ አሮጌ የታሪክ ትርክቶችን ማደስ፤ በዚህም ለአዲስ የታሪክ ትርክት ራስን ማዘጋጀት አለ። እኛ ኢትዮጵያውያን ከሁሉም በላይ ለይቅርታ ልባችን ሊከፈት ይገባል፤ ብሩህ ነገዎቻችን ያሉት በይቅርታ ወስጥ ነው። እንደ ኢማክሌ ያሉ ዜጎች እንዲበዙልንም እራሳችንን፤ አተያያችንን እናዘመን ! መልዕክቴ ነው፡፡ ሰላም !

 ሙሉቀን ታደገ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You