ሁለገቡ የጥበብ ሰው፤-ጽጌ ገብረአምላክ(1951-2016)

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አንጋፋ ጋዜጠኞችንና ፀሐፍትን ያፈራ ተቋም ነው፡፡ ባለፈው 2015 ዓ.ም 83 ዓመቱን የደፈነው ይኸው ተቋም በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነትና ሥነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ዐሻራቸውን ያሳረፉ ጉምቱ ሰዎችን ያፈራ ቤት ነው፡፡

ከእነዚህ ጉምቱ ጋዜጠኞችና የሥነ ጽሑፍ ሰዎች ውስጥ ከ1970ዎቹ ጀምሮ በጋዜጠኝነት እና በዜማና ግጥም ደራሲነት የሚታወቀው ጽጌ ገብረአምላክ አንዱ ነው።

አቶ ጽጌ ከአባቱ ከአቶ ገብረአምላከ ገ/ሚካኤል እና ከእናቱ ከወይዘሮ ፀሐይነሽ ገዛኸኝ ሰኔ 27 ቀን 1951 ዓ.ም በመቀሌ ከተማ ተወለደ ሲሆን፤ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአፄ ዮሐንስ ት/ቤት አጠናቅቋል።

በመቀጠልም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በውጭ ቋንቋዎችና እና ሥነ ጽሑፍ የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል።

አቶ ጽጌ ገ/አምላክ በዘመነ ኢህአፓ በነበረው የፖለቲካ ተሳትፎ ምክንያት በአዲስ አበባ ፒያሳ አካባቢ በሚገኘው ከፍተኛ 2 ቀበሌ 13 ለአንድ ዓመት ያህል በእስር ቤት ቆይቷል፡፡ ከእስር ከተፈታ በኋላ የከፍተኛውን የኪነት ቡድን ካቋቋሙት የጥበብ ባለሙያዎች አንዱ ሲሆን፤ የከፍተኛውን የኪነት ቡድን ታዋቂ ካደረጉት ሥራዎቹም ውስጥ “የአፍ ታጋይ” የተሰኘው መዝሙር አንዱ ነበር።

በዚያን ወቅትም ከታዋቂው የግጥምና የዜማ ደራሲ ይልማ ገብረአብ ጋር የቅርብ ወዳጅ ለመሆን ችሏል።

በወቅቱ የከፍተኛ 2 ቀበሌ 10 የኪነት ቡድን ጊታሪስት የነበረው ይልማ ገብረአብ ስለዚያን ዘመኑ ጽጌ ገብረአምላክ ሲያስታውስ “ምድራዊ ዓለምን የሚንቅ፣ ለካድሬ የማይገዛ፣ የራሱ አቋም ያለው ጠንካራ ስብዕና የተቸረው ሰው ነበር’’ ብሏል።

‘’ጽጌ እስር ቤት ውስጥ ሆኖ ለእኛ የኪነት ቡድን ቅኔ የተላበሱ ግጥሞችን በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ጽፎ ይልክልን ነበር ‘’ ሲልም በአድናቆት ያነሳዋል።

አቶ ጽጌ ከእስር ከተፈታ በኋላ ለበርካታ ታዋቂ የሀገራችን ድምፃውያን የበለጠ ተደማጭነትና ተወዳጅነት ምክንያት የሆኑ የግጥምና የዜማ ሥራዎችን እየደረሰ ለመስጠት የቻለ ምጡቅ አዕምሮ ያለው ባለሙያ ነበር።

የአቶ ጽጌን ሥራዎች ከተጫወቱት ድምፃውያን መካከል የክብር ዶክተር ጥላሁን ገሠሠ፣ ሂሩት በቀለ፣ ነፃነት መለሰ፣ ፀሐዬ ዮሐንስ፣ መልካሙ ተበጀ፣ ተሾመ ወልዴ እና ዘመነ መለሰ ተጠቃሽ ናቸው።

በተለይም ክቡር ዶክተር ጥላሁን በወቅቱ ከነበረበት ህመም አገግሞ የተጫወተውና ’ ይቺ ናት ጨዋታ”’ በሚል ርዕስ ያወጣው አልበም ውስጥ ሰባቱ ዘፈኖች የአቶ ጽጌ ገ/ አምላክ ሥራዎች ናቸው።

የድምፃዊ መልካሙ ተበጀ “ጉድ አንድ ሰሞን ነው’’ እና “ያን ጎራ፤ ያን ሰፈር በየት አግኝቼ በየት ልክሰሰው” የተሰኙ ተወዳጅ ዜማዎች ጨምሮ የሁለት አልበሞቹን 16 ሥራዎች ግጥምና ዜማ የደረሰው ያልተዘመረለት አቶ ጽጌ ገብረ አምላክ ነው።

የድምፃዊት ነፃነት መለሰም “እንደ ሀምሌ ፀሐይ’’፣ “ኧረ ምን ሆነሃል ሰሞኑን አንተ ሰው’’ እና “ምነው ጃል” የመሳሰሉት ግጥሞች የእሱ ሥራዎች ናቸው።

በ1977 በውጭ ቋንቋዎችና እና ሥነ ጽሑፍ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተመረቀው አቶ ጽጌ፣ ለዩኒቨርሲቲው የባህል ማዕከል በርካታ ግጥሞችንና ዜማዎችን ያበረከተ ሲሆን በተማሪዎች የምረቃ ወቅት “’እማ መርቂኝ’’ በሚል ርዕስ የፃፈው ግጥም ተጠቃሽ ነው።

በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ በሚዘጋጁ ፕሮግራሞች ላይ ጥልቅ፣ ለየት ያሉና ሥርዓቱን የሚጎሽሙ ግጥሞችን በማቅረብም ይታወቅ ነበር።

በተለይም የአቶ ጽጌ ገ/አምላክ ሥራ የሆነውና ታላቁ የኪነጥበብ ሰው ጥላሁን ገሠሠ የተጫወተው “ይቺ ናት ጨዋታ’’ በወቅቱ አነጋጋሪና የኢሠፓ ልሳን የነበረውን “ሠርቶ አደር” ጋዜጣ ጨምሮ በአዲስ ዘመንና በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ጋዜጦች ላይ ከፍተኛ የፖለቲካ ትችትና የሥነ ጽሑፍ መወያያ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ እንደነበርና በወቅቱ ባለስልጣናት ጥርስ ውስጥ አስገብቶት ነበር።

በተለይም በ1970ዎቹ በኢትዮጵያ ሬዲዮ የሕፃናት ፕሮግራም ላይ እጅግ ተወዳጅ የነበረውና የሕፃናት አምባ ልጆች ያዜሙት “’ፀሐዬ ደመቀች” የተሰኘው ዜማ የጽጌ ገ/አምላክ ግጥም እንደሆነ ይታወቃል። ሌሎች የእኛ ነው ሲሉም፥ ጉዳዩን በዝምታ ሲያልፍ የቆየው ዝምተኛውና ታጋሹ አቶ ጽጌ፣ አንድ ጊዜ ብቻ በፌስቡክ ገጹ ላይ ትዝብት ነው ትርፉ የሚል አጭር መልዕክት ጣል አድርጎ ነበር።

ጽጌ በሥራው እጅግ ታታሪ፣ ሰፊ ንባብ ያካበተ፣ ጥልቅና ነፃ አስተሳሰብ ያለው ባለሙያ እንደነበር የሥ ራ ባልደረቦቹና ጓደኞቹ ይመሰክሩለታል።

ገና በወጣትነት ዕድሜው በግጥምና በዜማ ድርሰት መሳተፍ የጀመረው ጽጌ፤ ይህን ዝንባሌውን የበለጠ በልምድና በንባብ በማዳበር በርካታ ያልታተሙና ይፋ ያልወጡ የተውኔት፣ የግጥምና የዜማ ሥራዎች እንዳሉት ይናገር እንደነበርም ለመረዳት ተችሏል።

በጽሑፍ ደረጃም እጅግ ጥልቀት ያላቸው ትንታኔዎችን፣ ሂሶችንና ጥበበኛ ሥራዎችን በጋዜጦች ላይ በማቅረብ ተደናቂና ተወዳጅ እንደነበርም ይታወቃል። ጽጌ በተለይም በእንግሊዝኛ ጽሑፉ ተደናቂ የነበረ ሲሆን ሲሰራበት ከነበረው የእንግሊዝኛው የሄራልድ ጋዜጣ ወደ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እንዲዛወር ተደርጎ ለ3 ዓመታት ያህል በእንግሊዝኛ ክፍል ኃላፊ ሆኖ ሰርቶ በማሰራት አገልግሏል።

በዘኢትዮጵያን ሄራልድ በመግባት ለብዙ ዓመታት በዋና አዘጋጅነት ያገለገሉት አቶ ጽጌ፤ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በእንግሊዝኛው ክፍል በኃላፊነት አገልግለዋል። ደራሲና ጋዜጠኛ ጽጌ ጥልቀት ያላቸው ትንታኔዎችን፣ ሂሶችንና ጥበበኛ ሥራዎችን በጋዜጦች ላይ በማቅረብ ተደናቂና ተወዳጅነት እንዳተረፉም የሕይወት ታሪካቸው ያትታል።

ደራሲና ጋዜጠኛ ጽጌ፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባልደረባ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፤ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ውስጥ በጡረታ እስከተሰናበቱበት ጊዜ ድረስም ሀገራቸውን በቅንነትና በትጋት አገልግለዋል። ጽጌ ገብረአምላክ በዘመነ ኢህአፓ በነበረው የፖለቲካ ተሳትፎ ምክንያት ለአንድ ዓመት ያህል በእስር ቤት ቆይተው፤ ከእስር ከተፈቱ በኋላም የከፍተኛውን የኪነት ቡድን ከሌሎች ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን አቋቁመዋል።

ከዚያም ከፍሪላንስ ጋዜጠኝነት ጀምሮ የሀገራችን ታላቁ የእንግሊዝኛ ጋዜጣ የኢትዮጵያን ሄራልድ ዋና አዘጋጅ እስከመሆን ደርሶ ለ4 ዓመታት በዋና አዘጋጅነት ሰርቷል። ብቃቱን በተግባር ያረጋገጠ መሆኑን የተገነዘቡት በወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር የነበሩት ነጋሶ ጊዳዳ(ዶ/ር) የአንደኛው የሚዲያ ተቋም ዋና ሥራ አስኪያጅ እናድርግህ ብለው በተደጋጋሚ ቢሮአቸው ድረስ እያስጠሩ ቢጠይቁትም “’ባለሙያ መሆን እንጂ ኃላፊነት አልፈልግም”’ ማለቱን የቅርብ ወዳጆቹ ይመሰክራሉ።

ጽጌ በ1990ዎቹ አጋማሽ በሀገሪቱ ይካሄድ የነበረው “መሠረታዊ የሥራ ሂደት ለውጥ (BPR) “በዚህ ዓይነት አመራርና የአሰራር ዘይቤ ተግባራዊ ሊሆን አይችልም’’ የሚል በደብዳቤ መልክ የተላከ ጽሑፍ በጋዜጣው ላይ እንዲወጣ አድርገሃል’’ በሚል ሰበብ በወቅቱ የነበሩት ከፍተኛ የፖለቲካ ኃላፊዎች እጅ ተጨምሮበት ከሄራልድ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅነትና ከሥራ እንዲባረርም ተደርጓል። ከዚያ በኋላም በተለያዩ ተቋማት ውስጥ በትጋት ሲያገለግል የነበረ ምርጥ ባለሙያ ነበር።

በተለይም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባልደረባ ሆኖ ባገለገለበት ወቅት የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ላይ የሚወጡ መግለጫዎችንና ሌሎች የጽሑፍ ዝግጅቶችን በላቀ የሃሳብ ጥልቀት በማዘጋጀት በጡረታ እስከተሰናበተበት ጊዜ ደረስ ሀገሩን በቅንነትና በትጋት ያገለገለ ድንቅ ባለሙያ ነበር ይህን ድንቅና አርቆ አሳቢ ባለሙያ ነው ዛሬ የተለየነውና ያጣነው።

በሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቡድን መሪነት በሚሰራበት ወቅት ወደ ጋና እና ግሪክ ከባለሙያዎች ጋር በመጓዝ የተሞክሮ ልውውጥ አድርጓል። ቀደም ሲልም በሥራ አጋጣሚዎች አሜሪካ ፣ ቻይና፣ እስራኤል፣ በጂቡቲና ሌሎች ሀገሮችን የመጎብኘት ዕድል አጋጥሞታል።

አቶ ጽጌ በ1967 ዓ.ም የዕድገት በህብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ ተሳታፊ በመሆንም ወደ ቀብሪ ደሀር የዘመተ ሲሆን፣ ዩኒቨርሲቲ እያለም በደርግ የመንደር ምስረታ ወደ መተከል ጉምላክ ዘምቶ ባልደረቦቹን በግጥሞቹ ያዝናና ነበር።

የባለብዙ የኪነጥበብና የጋዜጠኝነት ሥራዎች ባለቤት የሆነውና ብዙ ያልተነገረለት ሁለገብ ባለሙያው አቶ ጽጌ ገብረአምላክ ባደረበት ሕመም ምክንያት በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ መስከረም 27 ቀን 2016 ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

የጋዜጠኛ እና የዜማና ግጥም ደራሲ ጽጌ ገ/አምላክ የቀብር ሥነ-ሥርዓት ሰኞ መስከረም 28 ቀን 2016 ሲኤምሲ በሚገኘው ሳሊተ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል።

 በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን መስከረም 30/201

Recommended For You