የትምህርትጥራትንየማረጋገጥተግባርተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል!

ትምህርት ለአንዲት ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ወሳኝ ሚና አለው። ትምህርት ለአንድ ሀገር የዕድገትና ሥልጣኔ መሠረት ነው። በአንፃሩ ደግሞ የትምህርት አለመስፋፋት ለኋላቀርነት ቀዳሚ ምክንያት እንደሆነ ይታወቃል። ትምህርት ለሰው ልጆች ኑሮ ቅልጥፍና፣ ለሀገራት ዕድገትና ልማት፣ ባህልንና እውቀትን ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማሸጋገር እንደ ድልድይ ሆኖ የሚያገለግልም መሳሪያ ነው፡።

ይህንኑ በመረዳትም ኢትዮጵያ ለትምህርቱ ሴክተር ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ ምድባ ትምህርትን ስታስፋፋ ቆይታለች፡፡ በዚሁ መሠረትም ባለፉት 30 ዓመታት በሁሉም አካባቢዎች የተለያዩ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተከፍተው ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የመማር ዕድሎችን አግኝተዋል። ትምህርትን በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ ከማድረግ አንፃር 40ሺ የሚጠጉ የአንደኛ ደረጃና ከ3ሺ በላይ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተከፍተው የተማረ ዜጋን ለመፍጠር ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡

በእነዚህ ትምህርት ቤቶችም በአሁኑ ወቅት ከ28 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን በመማር ላይ ይገኛሉ። ከአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ባሻገርም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች 50 የሚጠጉ ዩኒቨርሲቲዎች ተከፍተው የተማረ የሰው ኃይል በማፍራት ላይ ይገኛሉ። በተጨማሪም 130 የሚሆኑ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተከፍተው ከፍለው መማር ለሚፈልጉ ተማሪዎች ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥሯል።

ሆኖም የትምህርት ተደራሽነትን የማስፋቱን ያህል በትምህርት ጥራት ላይ በቂ ትኩረት ባለመሰጠቱ ተመራማሪና ችግር ፈቺ ዜጎችን ማፍራት አልተቻለም፡፡ ቀደም ሲል የነበረው የትምህርት ፖሊሲ ከጥራት ይልቅ ለብዛት ትኩረት ይሰጥ ስለነበረ ተማሪዎች በቂ ዕውቀት ሳይጨብጡ ጭምር ወደ ቀጣይ ክፍል እንዲያልፉ ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ይህ ተማሪዎችን በገፍ የመሳለፍ አካሄድ ሀገሪቱን ዋጋ አስከፍሏታል፡፡

የተማሪው የብቃት ደረጃ በየደረጃው እየተፈተሸ ስለማይሄድም ለተቀመጡበት የትምህርት ደረጃ የማይመጥኑ ተማሪዎችና ሰልጣኞችም ከመብዛታቸውም ባሻገር ትምህርታቸውን አጠናቀው ሲወጡ በገበያ የማይፈለጉና በሰለጠኑበት የሙያ መስክ የራሳቸውን ሥራ እንኳን መፍጠር የማይችሉ ዜጎች እንዲበራከቱ አድርጓል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ አልፈው የሚቀጠሩ ምሩቃንም ብዙውን ጊዜ ባላቸው ብቃት የማይተማመኑ እንዲሁም የዕውቀት እና ክህሎት ችግር የሚታይባቸው ይሆናሉ፡፡ ለመልካም አስተዳደርና ለብልሹ አሠራርም ምክንያት ሆነው ይገኛሉ፡፡

በአጠቃላይ ጥራት የሌለው ትምህርት ጉዳቱ ብዙ ነው። ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት በሌለበት ጥራቱን የጠበቀ ሕክምና ማግኘት አይቻልም። ደረጃውን የጠበቀ የሕንፃ ግንባታ አይኖርም፤ ለሀገሩ ፍቅር የሌለው፤ ኪሳራን የሚያስከትል እና ሙሰኛ ዜጋ እንዲበራከት በር ይከፍታል። ይህም ዜጎች ፍትሕን እንዳያገኙ የሚያደርግ ስለሆነ የተረጋጋ ሰላም እንዳይኖርም ያደርጋል።

ይህንኑ ችግር ከስር ከመሠረቱ ለመቀየር ከለውጡ ወዲህ አዲስ ፍኖተ ካርታ ተቀርጾና በሂደትም አዲስ ሥርዓት ትምህርት ተነድፎ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡ በዚሁ መሠረትም ተማሪዎች በየደረጃው ብቃታቸው እየተረጋገጠ የሚሄድበትና በመጨረሻም ተወዳዳሪ ሆነው ራሳቸውንም ፤ሀገርንም የሚጠቅሙበት አካሄድ ተነድፎ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል፡፡ ከእነዚህ የም ዘና ሂደቶች አንዱ ደግሞ የከፍተኛ ተቋማት መግቢያ ፈተና ዋነኛው ነው፡፡

ካለፈው ዓመት ጀምሮ እየተሰጠ ባለው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ተማሪዎች በግል ጥረታቸው ወደ ዩኒቨርሲቲ እንዲገቡ ዕድል ከመፈጠሩም ባሻገር ባለፉት ዓመታት ሀገሪቱ ስትከተለው የነበረው አካሄድ አቅም የሌላቸው ተማሪዎች ጭምር ወደ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲገቡ ሲያደርግ እንደቆየ ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ቀደም ሲል የነበረው የትምህርት ሥርዓት በራሱ የማይተማመን፣ ለራሱ ክብር የሌለው፣ የአስተሳሰብ አድማሱ የጠበበ እና ኃላፊነት የማይሰማው ዜጋ እና ማህበረሰብ እንዲፈጠር ሲያደርግ ከመቆየቱም በተጨማሪ ሀገሪቱን ለኪሳራ ሲዳርግ መቆየቱን የሚያመላክት ነው።

የአምናና የዘንድሮ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት እንደሚያሳየው 50 በመቶ እና ከዚያ በላይ ያመጡ ተማሪዎች ቁጥር ከ3 በመቶ ብዙም የዘለለ ባይሆንም በቀጣይ የትምህርት ሥርዓቱ በሚያመጣው መነቃቃት ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎች ቁጥር እያደገ እንደሚሄድ ይታመናል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡት ተማሪዎች አቅምና ችሎታ ያላቸው ብቻ መሆናቸው እየተረጋገጠ ስለሚሄድ በትምህርት ጥራቱ ላይ አዎንታዊ ሚና የሚጫወት ይሆናል፡፡ ጥራትን የማረጋገጡ ተግባርም በአንድ ጀምበር የማይታይና ረጅም ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ በቀጣይ ጥራት ያላቸው በርካታ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲዎችን የሚቀላቀሉበት ሂደት እየተፈጠረ እንደሚመጣ ማመን ያስፈልጋል፡፡

በመሆኑም የሀገራችን ብልጽግና ይቀጥል ዘንድ የተጀመረው የትምህርት ጥራትን የማረጋገጥ ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

አዲስ ዘመን መስከረም 30/2016

Recommended For You