ትምህርት ለማህበረሰብ ለውጥና ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ቁልፍ መሣሪያ ነው። ነገር ግን በሀገራችን ባለፉት ዓመታት የፖለቲካ ትግል መሣሪያ አድርጎ ለመጠቀም በተደረገው ያልተገባ ርብርብ የፈተና አስተዳደር ሥራ ላይ በርካታ ችግሮች ሲከሰቱ ቆይቷል። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው በትምህርት ሥርዓቱ ከሚስተዋለው ስብራት ላይ የፈተና አስተዳደር ችግር ሲደመርበት ዘርፉን በእጅጉ ጎድቶታል። የኢትዮጵያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ ሰርተፊኬት ፈተና ውጤት ተፈታኞች አጠቃላይ ትምህርትን የሚያጠናቅቁበት፣ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያነት የሚገለገሉበትና ወደተለያየ ዘርፍ ሲሰማሩ የሚጠቀሙበት ከመሆኑ ውጭ ተሻግሮ ጥቂት በማይባሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ለፖለቲካ ሴራ ፣ የማህበራዊ ቀውስ መፍጠሪያ እና በማህበራዊ ሚዲያዎች ባልተገባ መንገድ ጥቅም ማግኛ ሆኖ ቆይቷል።
በመሆኑም ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ከመፈለግ አንጻር የፈተና አስተዳደር ሥራ ኮምፒዩተርን መሠረት ያደረገ እንዲሆን የተለያዩ ጥረቶች የተደረጉ ቢሆንም ለሥራው የሚያስፈልጉ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ግብዓቶች ባለመሟላታቸው ሳይተገበር ቆይቷል። ስለሆነም ከ2014 የትምህርት ዘመን አንስቶ የትምህርት ሚኒስቴር የፈተና ዝግጅት፣ ሕትመት፣ ሥርጭት፣ አሰጣጥና እርማት ሥራዎች ሚስጢራዊነታቸውና ደህንነታቸው የተረጋገጠ እንዲሆን የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትን በማስተባበርና በማቀናጀት ውጤታማ ሥራ እየተሠራ ይገኛል። በተለይም ፈተናው በፌዴራል የትምህርት ተቋማትና በዩኒቨርሲቲ መምህራን እንዲሰጥ መደረጉና በሂደቱ የነበሩ ውስጣዊና ውጫዊ ተጋላጭነትን በሚዘጋ አግባብ እንዲመራ ተደርጓል።
በመሆኑም የፈተና አስተዳደር ችግር በተለይም የፈተና ሌብነትና ኩረጃ በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ሲያሳድር የነበረውን አሉታዊ ተጽዕኖ በመከላከል እንዲሁም በምትኩ ተፈታኞች የልፋታቸውን ውጤት ብቻ የሚያገኙበት፣ የትምህርት ማህበረሰብም ተማሪዎችንና ትምህርት ቤቶችን በቅርበት የሚደግፍበትና አዎንታዊ ሚና የሚጫወትበት ሥርዓት የመገንባት ሥራ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል። ለዚህም ለፈተና አስተዳደሩ እና ለትምህርት ሥርዓት ማሻሻያ ሪፎርሞች መንግሥት ከፍተኛ ሀብት በመመደብ እና ከፍተኛ የሰው ኃይል በማሰማራት ለሁለተኛ ጊዜ ፈተናው ከፈተና ሌብነትና ኩረጃ በጸዳ መልኩ የተሳካ እንዲሆን ማድረግ ተችሏል።
1. መሠረታዊ መረጃዎች
በ2015 ትምህርት ዘመን 12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከተመዘገቡ የማህበራዊ ሳይንስ 502,767 እና የተፈጥሮ ሳይንስ 365,789 በድምር 868,570 ተፈታኞች መካከል በማህበራዊ ሳይንስ 488,511 (97.2%) እና በተፈጥሮ ሳይንስ 356,677 (97.5%) በድምር 845,188 (97.3%) ተፈታኞች ፈተናውን ወስደዋል። በምዝገባ ሂደት አጥጋቢውን የመመዝገቢያ መስፈርት ሳያሟሉ የተመዘገቡ የተፈጥሮ ሳይንስ 1,041 የማህበራዊ ሳይንስ 205 በድምር 1,246 ግለሰቦች ምዝገባቸው ተሰርዟል።
2. የፈተና አስፈጻሚዎች መረጃ
የፈተና አሰጣጡን ተዓማኒና ከፈተና ስርቆትና ኩረጃ ለመከላከል ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር አንጻር የ12ኛ ክጠፍል ብሔራዊ ፈተና አስፈጻሚዎች ከሚሰሩበትና ከትውልድ ቦታቸው ውጭ ወደሆኑ የፈተና ማዕከላት እንዲሠማሩ ተደርጓል። በዚህም የፈተና ሥራውን ለማስፈጸም የመጀመሪያ ዙር 31,500 ሁለተኛ ዙር 869 በድምሩ 32,369 የፈተና አስፈጻሚዎች በተለያየ ኃላፊነት ተሳትፈዋል።
3. የፈተና አስተዳደር መመሪያ ድንጋጌ ጥሰቶችና የሥነ-ምግባር ግድፈቶች
በፈተና አስተዳደር ወቅት በ450 የተፈጥሮ ሳይንስ እና በ409 የማህበራዊ ሳይንስ በድምሩ በ859 ተፈታኞች የተለያዩ የፈተና አስተዳደር መመሪያ ድንጋጌ ጥሰቶች ተፈጽመዋል። ከነዚህም ውስጥ 376 ተፈታኞች
በቡድን 483 በግል ጥፋት ፈጽመዋል። ከተፈጸሙት ጥፋቶች መካከል ዋና ዋናዎቹ
• ለሌላ ሰው ለመፈተን መሞከር፣
• የፈተና ሥራ ከሚሰራ የቀን የጉልበት ሠራተኛ ጋር በመመሳጠር ከፈተና በኋላ የመልስ ወረቀት ቀይሮ ለማስገባት ሙከራ ማድረግ፣
• እርስ በእርስ ለመኮራረጅ መሞከር፣
• የፈተና ሂደቱን በመፈተኛ ግቢ እና በመፈተኛ ክፍል ውስጥ በግልና በቡድን መረበሽ፣
• ያልተፈቀዱ ቁሳቁሶችን ይዞ መገኘት ዋና ዋና የፈተና ደንብ ጥሰት ችግሮች ሆነው ተመዝግበዋል።
ሆኖም የፈተና አስተዳደር መመሪያ ድንጋጌዎች ጥሰት የፈጸሙ ተፈታኞች ከ2014 የትምህርት ዘመን ጋር ሲነጻጸር በ2014 ትምህርት ዘመን 20,170 ተፈታኞች ሲሆኑ፤ በ2015 ትምህርት ዘመን 859 ተፈታኞች ናቸው። በሁሉም ላይ እንደተመዘገበው የጥፋት ዓይነት ከአንድ የትምህርት ዓይነት እስከ ሙሉ በሙሉ መሰረዝ ድረስ የሚደርስ ቅጣት ተጥሎባቸዋል። ይህ ጉዳይ ምንም እንኳን አሁንም ሰፊ ሥራ የሚጠይቅ መሆኑን የምንገነዘብ ቢሆንም ከ2014 ትምህርት ዘመን አንጻር የተገኘው መሻሻል ቀላል ግምት የማይሰጠውና የትምህርት ማህበረሰቡ በሠራው የተቀናጀ ሥራ በመሆኑ የሚበረታታ ነው።
4. የ2015 ትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ትንተና እንድምታው
4.1. በሀገር አቀፍ ደረጃ የተመዘገበ አማካይ ሀገራዊ ውጤት 28.65% ሲሆን ከፍተኛው ውጤት 30.99% በኬሚስትሪ ትምህርት ዝቅተኛው 25.62% በማህበራዊ ሳይንስ ሂሳብ ተመዝግቧል።
4.2. ሀገራዊ አማካይ ውጤቱ ከጾታ አንጻር ሲታይ የወንዶች አማካይ ውጤት 29.55% ሲሆን የሴቶች ደግሞ 27.64% ሆኗል። በአጠቃላይ ሲታይ በሁሉም የትምህርት አይነቶች ወንዶች ከሴቶች የተሻለ ውጤት አስመዝግበዋል።
4.3. ሀገራዊ የተማሪዎች አማካይ ውጤት በትምህርት መስክ (Stream) ሲታይ የተፈጥሮ ሳይንስ በአማካይ 29.98% ከማህበራዊ ሳይንስ 27.68% የተሻለ ውጤት ሆኗል። በሁሉም የትምህርት ዓይነት ተፈጥሮ ሳይንስ ከማህበራዊ ሳይንስ የተሻለ ነው።
4.4. ሀገራዊ የተመዘገበ አማካይ ውጤት በተፈታኝ ዓይነት ሲታይ መደበኛ 29.22%፣ የማታ 26.11% የግል 26.72% ሲሆን መደበኛ ተፈታኞች በአንጻራዊነት የተሻለ ውጤት አስመዝግበዋል።
4.5. የተማሪዎች አማካይ ውጤት በየትምህርት ዓይነት ሲታይ እንግሊዝኛ 27.92%፣ ሂሳብ ለተፈጥሮ ሳይንስ 28.48%፣ አፕቲትዩድ 30.74%፣ ሂሳብ ለማህበራዊ ሳይንስ 25.62%፣ ፊዚክስ 26.49%፣ ኬሚስትሪ 30.99% ባዮሎጂ 29.93%፣ ጂኦግራፊ 28.03%፣ ታሪክ 27.07%፣ ሲቪክስ 30.40% አማካይ ውጤት ሆኖ ተመዝግቧል።
4.6. በሀገር ደረጃ የተመዘገበ ከፍተኛ ውጤት
4.6.1. በሀገር ደረጃ የተመዘገበ ከፍተኛ ውጤት ከሰባት መቶ 649 (በተፈጥሮ ሳይንስ ) ሲሆን በማህበራዊ ሳይንስ ከስድስት መቶ 533 ተመዝግቧል።
4.6.2. በጾታ ስንመለከት በተፈጥሮ ሳይንስ ከሰባት መቶ ወንድ 646 ሴት 649 ተማሪዎች አስመዝግበዋል።
4.6.3. በማህበራዊ ሳይንስ ከስድስት መቶ ወንድ 533 ሴት 514 ተፈታኞች አስመዝግበዋል።
4.6.4. በአጠቃላይ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ 220 ተማሪዎች ናቸው። ከነዚህ መካከል፡-
– በማህበራዊ ሳይንስ ከ500 እና በላይ (ዓይነ ስውር ከ400ና በላይ) ያስመዘገቡ 15 ተማሪዎች፣
– በተፈጥሮ ሳይንስ ደግሞ ከ600ና በላይ ያስመዘገቡ 205 ተማሪዎች ናቸው።
4.10. ካስፈተኑት 3106 የመደበኛ ት/ቤቶች መካከል
o ከ50% እና በላይ ያስመዘገበ ተማሪ ያላቸው ት/ ቤቶች ብዛት (ቢያንስ 1 ተማሪ) ብዛት 1778 (57.2%) ናቸው፡፡
o ከ50% እና በላይ ያስመዘገበ አንድም ተማሪ የሌላቸው ት/ቤቶች ብዛት 1328 (42.8%) ናቸው፡፡
4.11 ማጠቃለያ
በ2015 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከማንኛውም የፈተና ስርቆትና ኩረጃ በጸዳ መልኩ ተሰጥቷል፡፡ ሆኖም የተመዘገበው ውጤት በተለይም 50% እና በላይ ያስመዘገቡ ተፈታኞች ብዛት ዝቅተኛ መሆኑ በትምህርት ሥርዓታችን ውስጥ ያለው ስብራት አሁንም ብዙ ሥራ የሚጠይቅ በመሆኑ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ትብብርና ቅንጅት በከፍተኛ ደረጃ ይፈልጋል፡፡ ችግሩ በሁለቱ ዙር በተደረገው ፈተና ይበልጥ ተጋለጠ እንጂ ለረጅም ዓመታት ሲንከባለል የሰነበተ ነው። መፍትሔውም ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ በመፍጠርና በመፍጠን እሳቤ ለውጥ ለማምጣት በተለይም የትምህርት አመራሩ ቁርጠኛ አመራር ከመስጠትና በቅርበት ድጋፍና ክትትል ከማድረግ አንጻር የጋራ ርብርብ ይፈልጋል፡፡
5. ምስጋና
በ2015 ትምህርት ዘመን የፈተና አስተዳደር ወቅት የተለያዩ አካላት የተሳተፉና የላቀ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሲሆን የትምህርት ሚኒስቴር ለሚከተሉት አካላት በልዩነት ከፍተኛ ምስጋና ያቀርባል፡፡
o መንግሥት እንደሀገር የበጀት እጥረት እያለ ለትምህርት ሥራ በተለይም ለፈተና አስተዳደር ሥራ ከፍተኛ በጀት በመመደብ ሌብነትንና ሳይሰሩ ውጤት ማግኘትን ለመዋጋት የያዘውን እቅድ ተፈጻሚነት በተጨባጭ ርምጃ በመውሰድ ማሳየቱ ፣
o ከፌዴራል ጀምሮ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አካላት የፈተና ሥራ ስኬታማ እንዲሆን ለሰጡት ቁርጠኛ አመራርና የቅርብ ድጋፍና ክትትል፣
o መላው ሕዝባችን በትምህርት ላይ የነበረው ክፍተት በተለይም የፈተና ስርቆትና ኩረጃ መታረም መጀመር አለበት በሚል ላሳየው ቁርጠኝነት፣
o በየደረጃው ላለው የፀጥታ መዋቅራችን በተለይም የፌዴራል ፖሊስ ተቋም አመራርና አባላት የትኛውንም ትንኮሳ ተቋቁሞ እና እስከ ሕይወት ድረስ መስዋዕትነት ከፍሎ ፈተናው በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ ላሳየው ውጤታማ ትጋትና ትዕግስት፣
o የሀገር መከላከያ ሠራዊት ካለበት ሀገራዊ ግዳጅ ጎን ለጎን ለሰጠን ተኪ የማይገኝለት ድጋፍ፣
o የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ማህበራት ተፈታኞችን፣ ፈተና አስፈፃሚዎችንና የፈተና ወረቀቶችን በማጓጓዝ ላበረከቱት አስተዋጽኦ፣
o ዩኒቨርሲቲዎች ተፈታኞችን ተቀብለው በማስተናገድ እና የመፈተኛ ክፍሎችን በማዘጋጀት እንደዚሁም ፈተና አስፈፃሚዎችን መልምለው በመላክና በፈተና ወቅት ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦ፤
o የሚዲያ አካላት ፈተናውን በሚመለከት ተከታታይ መረጃዎችን በማድረስ ላደረጉት ከፍተኛ ሙያዊ እገዛ ከፍ ያለ ምስጋናችንን እናቀርባለን።
በተጨማሪም የዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ ዝርዝር ሪፖርት በድረ-ገጻችን ለመላው ሕዝብ እንዲደርስ እናደርጋለን።
ትምህርት ሚኒስቴር
መስከረም 28 ቀን/ 2016 ዓ.ም
ለተጨማሪ መረጃ፦
አመለወርቅ ህዝቅኤል የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ
ስልክ 0911235322
ኢሜል– ameleworkhizkeal@ethernet. edu.et
እሴተ የሺጥላ ከፍተኛ የኮሙኒኬሽን አማካሪ
ስልክ- 0911235322
ኢሜል–esete.yeshitla@ethernet.edu.et
ትምህርት ሚኒስቴር
MINISTRY OF EDUCATION
አዲስ ዘመን መስከረም 30/2016