የዛሬው ፍረዱኝ ዝግጅታችን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 ኬቨርኮቭ አርመን ትምህርት ይወስደናል። የጉዞ ምክንያታችንም «በወረዳችን ለትምህርት አገልግሎት እንዲውል ቦታ የተሰጠው እና ለዓመታት ትምህርት ሲሰጥ የነበረው የኬቨርኮቭ አርመን ትምህርት ቤት ባለቤቶቹ ሆነ ብለው ከደረጃ በታች እንዲሆን በማድረግ ዘግተውታል፤» የሚል አቤቱታ ደርሶን ነው።
«በትምህርት ቤቱ ባለቤቶች የተፈጸመብንን በደል የኢትዮጵያ ሕዝብ አይቶ እንዲፈርድ አድርሱልን» ሲሉ የአካባቢው ነዋሪዎችና የተማሪ ወላጆች ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አዲስ ዘመን ጋዜጣ የመልካም አስተዳደር እና ምርመራ ክፍል ጉዳያቸውን ይዘው የቀረቡት እነዚህ አቤቱታ አድራሾች እንደሚሉት፤ ለትምህርት ቤቱ መዘጋት ዋና ምክንያቱ የትምህርት ቤቱ ባለቤቶች ቦታውን ከተመሠረተበት ዓላማ ውጪ ለመጠቀም በማሰባቸው ነው።
ለዚህ ማሳያው ደግሞ ቀድሞ ትምህርት ቤት የነበረው ቦታ አሁን ላይ ለመጠጥ ቤት እና ላልተገባ ዓላማ እየዋለ ይገኛል። በዚህም ለልጆቻችን በቅርብ ትምህርት ቤት ለማግኘት ተቸግረናል። የአርመን ትምህርት ቤት ባለቤቶች በፈጠሩት እኩይ ተግባርም ልጆቻችን ለእንግልት ተዳርገዋል። በጊቢው ውስጥ የተፈጸመው ተግባርም ትውልድን ያንጽ የነበረው ትምህርት ቤት ወደ ትውልድ አጥፊነት እንዲሸጋገር አድርጎታል።
እኛም ይሄንን ቅሬታቸውን በማድመጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግራ ቀኙን አይቶ መፍረድ ይችል ዘንድ፣ በዛሬው የፍረዱኝ ዓምድ እትማችን በትምህርት ቤቱ ልጆቻቸውን ያስተምሩ የነበሩ ወላጆች ያነሱትን ሃሳብ ለማገናዘብ ያስችል ዘንድ ከሰነድ ያገኘናቸውን ማስረጃዎች በጥልቀት በመመርምር፤ እንዲሁም ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተገኙ ምላሾች እና የሰነድ መረጃዎች በማካተት የሚከተለውን ዘገባ አሰናድተናል። መልካም ንባብ!
በአራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ 06 ትምህርት ጽሕፈት ቤት
በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበራ ዲና፣ ስለትምህርት ቤቱ መዘጋት ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የመልካም አስተዳደርና ምርመራ ክፍል እንደተናገሩት፤ አሁን ላይ የተዘጋው የአርመን ትምህርት ቤት ከቅድመ መደበኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ባሉት የክፍል ደረጃዎች የትምህርት ሥራ ሲሠራ ቆይቷል። ትምህርት ቤቱ ከመዘጋቱ በፊት በትምህርት ተደራሽነት ላይ የነበረውን ጫና እንዲቀንስ ተብሎ የተጀመረ ትምህርት ቤት ነበር።
አሁን ላይ በወረዳው የአጸደ ሕፃናት እና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ዕጥረት አለ የሚሉት አቶ አበራ፤ ይህም በወረዳው የአጸደ ሕፃናት እና የመጀመሪያ ደረጃ የትምህርት ተደራሽነት ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን ያስረዳሉ።
ትምህርት ቤቱ ከመዘጋቱ በፊት የወረዳው ትምህርት ጽሕፈት ቤት ድጋፍና ክትትል ያደርግለት እንደነበር የሚናገሩት ኃላፊው፤ ይሁን እንጂ ትምህርት ቤቱ የሚሰጠውን ድጋፍና ክትትል በአግባቡ ባለመተግበሩ እንዲሁም የሚሰጡትን ግብረ መልሶች ተቀብሎ ማስተካከል ባለመቻሉ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርት ሥልጠናና ቁጥጥር ባለሥልጣን ሊዘጋ መቻሉን አስረድተዋል።
ከወረዳው ትምህርት ጽሕፈት ቤት በተጨማሪ የትምህርት ቤቱን ችግር ለመቅረፍ በከተማ አስተዳደሩ የቂርቆስና የአራዳ ክፍለ ከተማ የትምህርት ሥልጠናና ቁጥጥር ባለሥልጣን በአካል በመገኘት በተደጋጋሚ ካለበት ችግር እንዲወጣ የድጋፍና ክትትል ሥራ ሲያከናውን መቆየቱን ያስረዳሉ። ነገር ግን የትምህርት ሥራ በትውልድ ላይ የሚደረግ ሥራ እንጂ የንግድ ሥራ ባለመሆኑ፣ ከበርካታ ድጋፍና ቁጥጥር በኋላም ትምህርት ቤቱ የከተማ አስተዳደሩን የትምህርት የጥራት ደረጃ ማሟላት ባለመቻሉ ሊዘጋ መቻሉን ያብራራሉ።
የትምህርት ቤቱ ባለቤቶች ተቋሙን ለመዝጋት ይፈልጉ ስለነበር ርዕሳነ መምህራንን እና አጠቃላይ ሠራተኞችን በማሸማቀቅ ትምህርት ቤቱን ጥለው እንዲሄዱ የማድረግ ሥራ ይሠሩ እንደነበር የገለጹት ኃላፊው፤ ተቋሙ የሕዝብ ትምህርት ቤት እንደመሆኑ መጠን የሚሰጠውን የክትትልና ድጋፍ ግብረ መልስ በመቀበል ክፍተቶችን የመቅረፍ ኃላፊነት ነበረበት። ነገር ግን ይህን ማድረግ አልቻለም። ከተማሪ ወላጆች (ወተመህ) ተወካዮች ጋር በጋራ በመሆን ክፍተቶችን በማሳየት ካላስተካከሉ ትምህርት ቤቱ እንደሚዘጋ፤ ከተዘጋ ደግሞ በአካባቢው ማኅበረሰብ ላይ ጫና እንደሚፈጥር ማሳሰቢያ ጭምር ተሰጥቷቸው እንደነበር አስረድተዋል።
ይሁን እንጂ የትምህርት ቤቱ ባለቤቶች ተቋሙን ማስቀጠል ስላልፈለጉ ትምህርት ቤቱ ከመዘጋቱ በፊት ርዕሰ መምህራንና መምህራን ቀድሞ አሰናብተው ነበር። ይህም ግልጽም ባይሆንም በስውር ትምህርት ቤቱን ማስቀጠል እንዳልፈለጉ ማሳያ ነው የሚሉት ኃላፊው፤ ትምህርት ቤቱ እንዳይዘጋ የሚፈልጉ ቢሆን ኖሮ የሚሰጠውን ግብረ መልስ በመቀበል በቀላሉ ማስተካከል ይቻል እንደነበር ይገልጻሉ።
ባለቤቶቹን እንደማያውቋቸው የሚናገሩት የትምህርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊው፤ የትምህርት ጽሕፈት ቤቱ በቀጥታ ባለቤቶችን አግኝቶ አያውቅም፣ ግንኙነቱም ከርዕሰ መምህሩ ጋር ብቻ ነበር። ባለቤቶቹን ለማግኘት ጥረት ቢደረገም ማግኘት አልተቻለም። በርዕሰ መምህሩ በኩል የባለቤቶቹን ስልክ አግኝቶ ባለቤቶችን ለማወያየት ቢጥሩም ጥረታቸው አለመሳካቱን ይናገራሉ።
ትምህርት ቤቱ ተማሪዎችን ሲበትን በቀጣይ የት ይማራሉ? ቀጣይ ዕጣ ፈንታቸው ምን ይሆናል? የሚለው ጉዳያቸው አልነበረም። ከወላጆች ጋር አልተወያዩም የሚሉት አቶ አበራ፤ ተማሪዎች ወደሌላ ትምህርት ቤት የሚገቡበትን መንገድ የወረዳው ትምህርት ጽሕፈት ቤት ማመቻቸቱን ያስረዳሉ።
ትምህርት ቤቱ ያለበት ቦታ ፈቃድ የተሰጠው ለትምህርት አገልግሎት ብቻ ለማዋል ነበር። ነገር ግን አሁን ላይ ትምህርት ቤቱ ደረጃውን ማሟላት ባለመቻሉ ምክንያት ፈቃዱ ተሰርዞ ሥራ አቁሟል። ባለቤቶችም ቦታውን ለትምህርት ቤት ለመጠቀም ፈቃደኛ አይደሉም። ስለሆነም ትምህርት ቤቱ ለመንግሥት ተመልሶ የትምህርት አገልግሎት ቢሰጥበት በወረዳው ያለውን የትምህርት ተደራሽነት ችግር መቅረፍ እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር ምላሽ
ዝግጅት ክፍላችን በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ፕሮግራሞችና ጥራት ማሻሻል መሪ ሥራ አስፈጻሚ ለሆኑት አቶ ዮሐንስ ወጋሶ ስለአርመን ኮሚኒቲ ስኩል ምን ያውቃሉ? ትምህርት ቤቱን እንደ አንድ ኮሙኒቲ ስኩል ታስተዳድሩታላችሁ ወይ? የሚል ጥያቄ አንስተንላቸው ነበር። ለተጠየቁት ጥያቄ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ዮሐንስ «በትምህርት ሚኒስቴር የተመዘገበ አርመን ኮሙኒቲ ስኩል የሚባል ትምህርት ቤት የለም፤ ካለም የዘጋነው ትምህርት ቤት የለም» ሲሉ አጭር መልስ ሰጥተዋል።
የትምህርትና ሥልጠና ጥራት፣ ቁጥጥር ሙያ ብቃት እና ምዘና ማረጋገጫ ባለሥልጣን የአራዳ እና ቂርቆስ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ምላሽ
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርትና ሥልጠና ጥራት፣ ሙያ ብቃት እና ምዘና ማረጋገጫ ባለሥልጣን የአራዳ እና ቂርቆስ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ተወካይ ሥራ አስኪያጅ የሆኑትን አቶ ተስፋዬ አሰፋን፣ ውዝግብ ስለተነሳበት ትምህርት ቤት ምን ያውቃሉ? የሚል ጥያቄ በዝግጅት ክፍላችን ተነስቶላቸው ነበር።
ስለጉዳዩ ማብራሪያ የሰጡት ኃላፊው፤ ትምህርት ቤቱ ሲዘጋ እርሳቸው በቦታው እንዳልነበሩ ይገልጻሉ። ይሁንና አሁን ላይ በእርሳቸው ስር ባሉ ባለሙያዎች እና ከሰነዶች የተገኙ ማስረጃዎችን ዋቢ በማድረግ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥዋል።
በትምህርት ዘርፍ የሚሰማራ ግለሰብም ይሁን ማኅበር እውቅና ፈቃድ ሲፈልግ ተቋማቸው አስፈላጊውን ግብዓት ማሟላቱን በማረጋገጥ ፈቃድ ይሰጣል። ፈቃዱን ከሰጠ በኋላ የመከታተልና ቁጥጥር የማድረግ ሥራ ያከናውናል፤ የእውቅና ፈቃዱን በየሁለት አመቱ የማደስ ሥራ ይሠራል።
ተቋሙ ለትምህርት ቤቶች የእውቅና ፈቃድ ከመስጠት ባሻገር ትምህርት ቤቱ እየሰጠ ያለውን ትምህርት በከተማ አስተዳደሩ የትምህርት ‹‹ስታንዳርድ›› መሠረት ደረጃውን ያሟላ መሆኑን በተቋሙ የ‹‹ኢንስፔክሽን›› ዘርፍ አማካኝነት የማረጋገጥ ሥራ ይሠራል። በዚህም ትምህርት ቤቱ ከደረጃ በታች ከሆነ በአሠራሩ መሠረት ተቋሙ ደረጃውን እንዲያሟላ ግብረ መልስ ይሰጣል። በዚህ መሠረት አርመን ትምህርት ቤት በተደረገው የቁጥጥርና የክትትል ሥራ ከደረጃ በታች ሆኖ ተገኝቷል። ደረጃውን እንዲያሻሻል በተደጋጋሚ ድጋፍ ቢደረግለትም የተደረገለትን ድጋፍ ተጠቅሞ ራሱን ማሻሻል ባለመቻሉ ፈቃዱ መሰረዙን ይናገራሉ።
አንድ ትምህርት ቤት የደረጃ መለኪያውን መስፈርት ለማሟላት በራሱ ማሟላት የሚገባቸውን ነገሮች እና ከተቋሙ ውጪ በሆኑ እንደ ትምህርት ቢሮና መሰል አካላት መሟላት የሚገባቸው እንደ መጽሐፍት ያሉ ቁሳቁሶች እንዲያሟላ ይጠበቃል ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ ይህን በማድረግ ችግሮችን የማይፈታ ከሆነ በቀጣይ የበጀት አመት ትምህርት ከመጀመሩ ሦስት ወር በፊት ለወላጅ አሳውቆ ተማሪዎች ሳይንገላቱ በማሰናበት ትምህርት ቤቱ የትምህርት ሥራውን እንዲያቆም እና ተማሪዎች እውቅና ወደአለው ተቋም ሄደው እንዲማሩ የማድረግ ሥራ እንደሚሠራ ያስረዳሉ።
ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ትምህርት ቤቶችን ከመከታተል፣ መደገፍና ቁጥጥር ባሻገር ከደረጃ በታች በሆኑ ጊዜም ወደ ማስተካከል ቁመና እንዲመለሱ ለማድረግ ይሠራል። መስተካከል ካልቻሉ ደግሞ እውቅና ፈቃዱን ይሰርዛል።
አንድ ድርጅት ወይም ማኅበር ለትምህርት ቤት ብሎ ከመንግሥት ቦታ ከወሰደ በኋላ ለሌላ ተግባር ሲያውል ቢገኝ መሥሪያ ቤታችሁ ምን ዓይነት የእርምት እርምጃ ይወስዳል? ተበለው የተጠየቁት አቶ ተስፋዬ፤ አንድ ተቋም የትምህርት አገልግሎት ለመስጠት በሚል
የተሰጠውን ቦታ ለሌላ ዓላማ ቢያውል ተቋማቸው ያንን ተቋም ለትምህርት የተሰጠህን ቦታ ከትምህርት አገልግሎት ውጪ ማዋል አትችልም ብሎ ሊቆጣጠር እንደማይችል ጠቁመው፤ ይህን የመቆጣጠር ሥልጣን ያለው ለትምህርት አገልግሎት እንዲውል የኢንቨስትመንት ፈቃድ ቦታ የሰጠው አካል መሆኑን ያብራራሉ።
ትምህርት ቤቱ እውቅና እንደሌለው በ2014 ዓ.ም በአራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ 06 ትምህርት ጽሕፈት ቤት ለክትትል እና ድጋፍ በተዘጋጀው ሰነድ ተመላክቷል። እውቅና የሌለው ትምህርት ቤት ማስተማር ይችላል ወይ? ተብለው በዝግጅት ክፍላችን የተጠየቁት አቶ ተስፋዬ፤ የቁጥጥር ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ መዋቅር ከአስር ዓመት በፊት ወረዳ ላይ ነበር። አሁን ላይ ግን ራሱን ችሎ በከተማ አስተዳደር ደረጃ መዋቅር ዘርግቶ እየሠራ ነው። ተጠሪነቱም ለከንቲባ ጽሕፈት ቤት ነው። ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በወረዳ ደረጃ በነበረበት ወቅት የእውቅና ፈቃድ ይሰጡ እና ይሰርዙ ነበር። ከዚህ አኳያ አርመኒያን ትምህርት ቤት እውቅና ነበረው ወይ? የሚለውን መረጃ ከወረዳ ማጣራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ለአቶ ተስፋዬ፣ ሌላው ከዝግጅት ክፍላችን ተነስቶላቸው ከነበሩ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የአርመን ትምህርት ቤት ኮሚኒቲ ስኩል ነው። ኮሙኒቲ ስኩል ደግሞ የእውቅና ፈቃድ የሚሰጠው እና የእውቅና ፈቃዱ የሚሰረዘው በትምህርት ሚኒስቴር እንጂ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ሥልጠና ጥራት፣ ሙያ ብቃት ምዘና ማረጋገጫ ባለሥልጣን አለመሆኑ በመመሪያ የተቀመጠ ነው። ከዚህ አኳያ የእናንተ መሥሪያ ቤት በምን አግባብ የአርመን ትምህርት ቤትን እውቅና ሊሰርዝ ቻለ? የሚል ነበር።
አቶ ተስፋዬ በምላሻቸው፤ በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የእውቅና ፈቃድ የሚሰጠው እና የሚሰረዘው የትምህርት ሚኒስቴር የወረደውን የትምህርት ‹‹ካሪኩለም›› መሠረት አድርገው ለሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች ብቻ ነው።
የ‹‹ኮሚዩኒቲ›› ትምህርት ቤት ማለት ከሆነ ቦታ ለመጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች ለማኅበረሰባቸው ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ ትምህርት ቤት ማለት ነው። ከዚህ አኳያ ለኮሚዩኒቲና ለኢንተርናሽል ትምህርት ቤቶች ፈቃድ የሚሰጠው ደግሞ ትምህርት ሚኒስቴር ነው፤ ነገር ግን አርመን ትምህርት ቤት በስያሜ ደረጃ የ‹‹ኮሚዩኒቲ ስኩል›› ይባል እንጂ ትምህርት ቤቱ የሚሰጠው ትምህርት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር የሚዘጋጀውን ‹‹ካሬኩለም›› መሠረት አድርጎ በመሆኑ የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የእውቅና ፈቃዱን እንዳነሳ ያብራራሉ።
ከሰነዶች የተገኙ ማስረጃዎች
ከተፈጠረው ውዝግብ ጋር ተያይዞ ዝግጅት ክፍላችን ባደረገው ምርመራ በርካታ የሰነድ ማስረጃዎችን ማግኘት ችሏል። በመሆኑም ሁሉንም ሰነዶች በጽሑፉ ማካተት አስቸጋሪ ስለሚሆን ስለጉዳዩ ለአንባቢያን እና ለባለድርሻ አካላት የተሻለ ግንዛቤ ይሰጣሉ ያላቸውን ሰነዶች ለማካተት ጥረት አድርገናል።
ማስረጃ አንድ፡- በዚህ ማስረጃ የአርመን ትምህርት ቤት የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት ባለመቻሉ የእውቅና ፈቃዱ ሊነጠቅ ስለመሆኑ ከአዲስ አበባ ከተማ የትምህርትና ሥልጠና ጥራት፣ ሙያ ብቃት እና ምዘና ማረጋገጫ ባለሥልጣን የአራዳ እና ቂርቆስ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የተሰጡ ማስጠንቀቂያዎች እና የአርመን ትምህርት ቤት ለማስጠንቀቂያዎች ይሰጣቸው የነበሩ ምላሾች ተካተዋል። የመጀመሪያው የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ በቁጥር አ/ቂ/718/ተዕ-43/12 በቀን 11/03/2012 ዓ.ም የተጻፈው ነው ።
በዚህ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እንደተመላከተው፤ ለአርመን ትምህርት ቤት ለቅድመ መደበኛ ትምህርት የተሰጠው እውቅና በ2011ዓ.ም በመጠናቀቁ የእውቅና ፈቃድ እድሳት ምዘና በማድረግ ፍቃዱን ማሳደስ እንደሚገባቸው ተገልጿል።
ከዚህ ባሻገር የቅድመ መደበኛ ተቋሙ ከመጀመሪያ ደረጃ ወጥቶ ራሱን በቻለ ግቢ አገልግሎት እንዲሰጥ በተሰጠው ማሳሰቢያ መሠረት ወደ ሌላ ግቢ የተዘዋወረ ቢሆንም፤ በእውቅና ፈቃድ እድሳት መመዘኛ መስፈርት መሠረት ምዘና ለማድረግ በሚያስችል ሁኔታ የተደራጀ ባለመሆኑ ምዘና ሳይደረግ ቆይቷል።
በአጠቃላይ የትምህርት የተቋማት እውቅና ፈቃድና እድሳት ቡድን እና ባለሙያዎች በቀን 26/01/2012 ዓ.ም በተቋሙ በተገኙበት ወቅት ከመማሪያና ማሽለቢያ ክፍል ውጪ የሌሎች አገልግሎት መስጫ ክፍሎች የሌሉ እና ለሕፃናቱም ምቹ ባልሆነ ሁኔታ ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን ለማረጋገጥ መቻሉን እና በዚህም ተቋሙ የማስተማር ፍቃድ ሳይኖረው ተማሪ ማስተማር ሕገ ወጥ በመሆኑ የተገኘውን ግኝት አስመልክቶ እንደ ጽሕፈት ቤት ለመነጋገር በቀን 04/03/2012 ዓ.ም የትምህርት ቤቱ ባለቤቶች በቁጥጥር ባለሥልጣን ጽሕፈት ቤት እንድትገኙ የሚል ጥሪ ቢተላለፍላቸውም የተቋሙ ባለቤቶች ሳይገኙ ቀርተዋል።
በመሆኑም የቁጥጥር መሥሪያ ቤቱ ባለቤቶች ባልተገኙበት ከመጀመሪያ ደረጃ ርዕሰ መምህርና ከወላጅ ኮሚቴ ተወካዮች ጋር በቃለ ጉባኤ የተደገፈ ውይይት በማድረግ ውሳኔ እንዲደርሱ መገደዳቸውን ይገልጻል። ውይይቱ ከተደረገበት ቀን ጀምሮ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ መስተካከል ያለባቸውን የግብዓትና የአደረጃጀት ክፍተቶች በአስቸኳይ በማሟላት ለምዘና ዝግጁ እንዲሆን በጥብቅ ተነግሯቸዋል። በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ በመጠቀም ስታንዳርዱ ላይ የሚጠየቁትን መስፈርቶች የማያሟሉ ከሆነ ለሚሰጠው ውሳኔ ተቋሙ ተጠያቂ አለመሆኑን የሚያትት ነበር።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የባለሥልጣኑ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በቀን 13/05/2012 ዓ.ም በቁጥር አ/ቂ/2038/ፅፈ-43/12 ለሁለተኛ ጊዜ ለአርመን ትምህርት ቤት ደብዳቤ ጻፈ። በደብዳቤው እንዳመለከተው የአራዳና ቂርቆስ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በ2012 ዓ.ም ትምህርት ዘመን የእውቅና ፈቃድ ሳይኖራቸው በማስተማር ላይ የሚገኙ ተቋማትን በቀጣይ በ2013 የትምህርት ዘመን መቀጠል የማይችሉ ስለመሆናቸው የማሳወቅ ተግባር እያከናወነ መሆኑን፤ ከዚህ አንጻር የኬቨርኮቭ አርመን ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤትም እውቅና ፈቃድ እድሳት ሳይኖረው በሕገ ወጥ መንገድ ትምህርት እየሰጠ መሆኑን በመረዳት እና ችግሩን ለመቅረፍ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ባደረገው ምዘና 37 ነጥብ 5 በመቶ ያመጣና ከስታንዳርድ የራቀ በመሆኑ ተቋሙ ዝቅተኛውን የማለፊያ ነጥብ ባለማምጣቱ የእውቅና ፈቃድ ሊሰጠው ባለመቻሉ የ2012 የትምህርት ዘመን ሲጠናቀቅ የመማር ማስተማር አገልግሎት የማይሰጥ መሆኑን ተመላክቷል።
ይህን ተከትሎ የአርመን ትምህርት ቤት በቀን 19/08/2012 ዓ.ም በቁጥር አ/ት/ቤት/34/ 2012 ለባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በተጻፈው ደብዳቤ እንደገለጸው፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሸኝ ምክንያት ትምህርት እንደተዘጋ፤ በዚህም ከቁጥጥር ባለሥልጣኑ የተሰጠውን ትዕዛዝ ለወላጆች ለማሳወቅ እንደማይችል ገልጾ፤ ችግሩ እስኪቀረፍ ድረስ ለአንድ ዓመት የመማር ማስተማር ሥራ እንዲያከናውን የሚችልበት ሁኔታ እንዲመቻችለት ጠይቆ ነበር።
ይሁን እንጂ የአራዳና ቂርቆስ ትምህርትና ሥልጠና ጥራትና ሙያ ብቃት ማረጋገጫ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ለአርመን ትምህርት ቤት በቀን 13/09/2012 ዓ.ም በቁጥር አ/ቂ/5277/እ-43 በተጻፈ ሦስተኛ ደብዳቤ የውሳኔ ሃሳብ አሳውቋል። በውሳኔ ሃሳቡም የአርመን ትምህርት ቤት ያለ እውቅና ፈቃድ እድሳት በሕገወጥ መንገድ ተማሪዎችን ማስተማሩንና ትምህርት ቤቱ የተጀመረው የትምህርት ዘመን ሲጠናቀቅ የማይቀጥል መሆኑንም ቀደም ብሎ በተደጋጋሚ ያሳወቀ በመሆኑ ትምህርት ቤቱ ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት የለውም። ስለሆነም ይህን በመገንዘብ ለወላጆች በ2013 የትምህርት ዘመን ተቋሙ የማይቀጥል መሆኑን የማሳወቅ ተግባር እንድታከናውኑ እየገለፅን እንደማንኛውም መንግሥታዊ ያልሆነ የትምህርት ተቋም በሀገራችን የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ተከትሎ በትምህርት ሚኒስቴር በወጣው መመሪያ መሠረት ለተማሪዎች ባሉበት ከንክኪ ነፃ የሆነ የትምህርት አገልግሎት እየሰጣችሁ እንድትቆዩና በትምህርት ዘመኑ እየተማሩ ያሉ ተማሪዎችን ሳያጠናቅቁ መበተን የማትችሉ መሆኑን በጥብቅ እናሳስባለን የሚል ነበር።
በዚህ ሳቢያ የአርመን ትምህርት ቤት በቀን 27/09/12 ዓ.ም ለአራዳና ቂርቆስ ትምህርትና ሥልጠና ጥራትና ሙያ ብቃት ማረጋገጫ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ለትምህርትና ሥልጠና ተቋማት እውቅና ፈቃድና እድሳት ዳይሬክቶሬት በደብዳቤ መልስ ሰጠ። በደብዳቤውም የትምህርት ሥራው ላይ ያለባቸውን ተግዳሮቶች በድጋሚ በማሳወቅ የትምህርት ሥራውን የሚያከናውኑበት ቤትና ግቢ ለሥራው አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መሆኑን ገልጸው፤ ይሁንና ትምህርት ቤቱ ከነባራዊው ሁኔታ በመነሳት የግድ መቀጠል አለበት ከተባለም በራሱ በትምህርት ቤቱ ክፍሎችና ከክለቡ እንግዶች ጋር ተማሪዎች የማይገናኙበት ራሱን በቻለ የተለየ መግቢያ ብቻ መቀጠል የሚቻል መሆኑን። ይህም ለተማሪዎቹ የትምህርት ቅበላም ሆነ ጥራት ምቹ ያለመሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት የቀደመ የትምህርት ቤታችን ሕንፃና ግቢ እንዲመለስልንና የትምህርት ሥራውን በደንቡ መሠረት ማከናወን እንድንችል ይፈቀድልን የሚል ነበር።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአርመን ትምህርት ቤት ለአራዳና ቂርቆስ ትምህርትና ሥልጠና ጥራትና ሙያ ብቃት ማረጋገጫ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የትምህርትና ሥልጠና ተቋማት እውቅና ፈቃድና እድሳት ዳይሬክቶሬት በቀን 5/11/2013ዓ.ም በቁጥር ኬ/አር/ት/ቤት 00043/2021 ሌላ ደብዳቤ ጻፈ። በደብዳቤውም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርትና ሥልጠና ጥራትና ሙያ ብቃት ማረጋገጫ ባለሥልጣን በቁጥር የት/ስ/ጥ/ሙ/ብ/ም/ማ/ባ/አም/02/8523 በቀን ግንቦት 10/2013ዓ.ም የተጻፈን ደብዳቤ መሠረት አድርጎ መሆኑን ይገልጻል። በዚህ መሠረት የአርመን ትምህርት ቤት ከተማሪ ወላጆች ኮሚቴ፣ ወላጆች እና በተለያዩ ደረጃዎች ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት ለ2014 ዓ.ም የመማር ማስተማር ሂደት እንደሚቀጥል እና ትምህርት ቤቱ የገጠሙትን ችግሮች ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት በመወያየት የተጓደሉ ቁሳቁሶችን በሂደት እያሟሉ መሄድ እንደሚችሉ በደብዳቤው ተገልጾላቸዋል። የወቅቱን ሁኔታዎች በመገንዘብ የአርመንያ ኮሚኒቲ ክለብ ይዞታ ላይ ያሉት የተማሪዎች መመገቢያ ድንኳን፣ ለስፖርት መጫወቻ የሚያገለግለው ሜዳ ለትምህርት ቤቱ አገልግሎት የማይሰጥ መሆኑ ታውቆ በተጨማሪም የተማሪዎች መግቢያና መውጫ በትምህርት ቤቱ በር ተደርጎ ለ2014 ዓ.ም የመማር ማስተማሩ ሂደት እንደሚቀጥል ደብዳቤው ያትታል።
ነገር ግን ይህን ሁሉ ድጋፍ የተደረገለት ትምህርት ቤት ያሉበትን ችግሮች ማስተካከል ባለመቻሉ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርትና ሥልጠና ጥራትና ሙያ ብቃት ማረጋገጫ ባለሥልጣን የአራዳ እና ቂርቆስ ቅርንጫፍ በቀን 20/10/2014 ዓ.ም በቁጥር አ/ቂ6891/መ-26/14 በተጻፈ ደብዳቤ የአርመን ትምህርት ቤት የእውቅና ፈቃዱ መነሳቱ ተገልጿል።
ማስረጃ ሁለት፡- የወረዳ 6 ትምህርት ጽሕፈት ቤቶች በስሩ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ያሉበት ደረጃ ምን እንደሚመስል የክትትልና የቁጥጥር ሥራ በየጊዜው ያከናውናሉ። በዚህም በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 አስተዳደር ትምህርት ጽሕፈት ቤት የ2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን አጀማመርን አስመልክቶ በትምህርት ቤቱ ባከናወናቸው ድጋፍና ክትትል መሠረት የአርመን ትምህርት ቤት በ2013 ዓ.ም እቅድ አፈጻጸም የነበሩ ድክመቶችና ጥንካሬዎችን ገምግሟል። ለ2014ዓ.ም የመማር ማስተማር ዕቅድ ቼክ ሊስት አዘጋጅቶ ተወያይቷል። ነገር ግን ትምህርት ቤቱ የመማር ማስተማር ሥራውን መከወን የማይችልበት ደረጃ መድረሱን የተረጋገጠበት ሰነድ ለዝግጅት ክፍላችን ደርሷል።
የትምህርት ቤቱ ባለቤቶች እና የምርመራ ቡድኑ ግኝት
የትምህርት ቤቱን ባለቤቶች በተመለከተ የምርመራ ቡድኑ በምርመራው ሂደት በርካታ ጉዳዮችን ማግኘት ተችሏል። በዚህም ለአንድ ዓመት ተኩል በተካሄደ የምርመራ ዘገባ ትምህርት ቤቱን በበላይነት የሚመሩት ባለቤቶች ማግኘት አልተቻለም። ይህ በምርመራ ቡድኑ ብቻ ሳይሆን ጉዳዩ በሚመለከታቸው የትምህርት ዘርፍ ተቋማትም ባደረጉት ክትትል ባለቤቶችን ማግኘት አልቻሉም። ሁለተኛው ግኝት ደግሞ ትምህርት ቤቱ አሁን ላይ ለመጠጥ መሸጫ እና ለሌላ አላስፈላጊ ድርጊት ማከናወኛ እየዋለ መሆኑን በምርመራ ሂደቱ አረጋግጧል።
በመሆኑም በቀጣይ በሚኖረን ዝግጅት ጉዳዩ የሚመለከታቸውና በዚህ ዘገባ ያልተካተቱ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ምላሽ የምናቀርብ ሲሆን፤ ትምህርት ቤቱ የእኔ ነው የሚል አካል ከመጣም ሃሳቡን አለኝ ከሚለው ማስረጃ ጋር አገናዝበን የምናስተናግድ መሆኑን እንገልጻለን።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር፣ሙሉቀን ታደገ እና ሞገስ ተስፋ
አዲስ ዘመን መስከረም 30/2016