ለመንገዳገዳችን ጥንት የበረታንበትን የአንድነት ምርኩዝ እንጨብጥ

አንድነት ኢትዮጵያዊነትን የቀለመ የታሪክ እና የማንነት መልክ ነው። ደማማቆቹ የታሪክ ገድሎቻችን አብረን ተራምደን ተያይዘንና ተደጋግፈን የጻፍናቸው ናቸው። ብቻነትን የማያውቀው ይህ ጥንት ታሪካችን ከዓለም ፊተኛ፣ ከአፍሪካ ደግሞ ገናና አድርጎን ዛሬም ድረስ የምንጠራበትን የበኩር ስም ሰጥቶናል።

ይሄ እንዴት ሆነ፣ ከየት መጣ ብለን ስንጠይቅ የምናገኘው አብሮነትን ነው። አብሮነት በፍቅር የሚመጣ፣ በመቻቻል የሚወለድ ውበታም መልክ ነው። በዚህ መልክ ቆንጅተን ነው አፍሪካን ያቆነጀነው። በዚህ መልክ አምረን ነው የዓለ ምን ውበት አካል የሆነው።

የእኔነት ሃሳቦች በድህነት በጎበጠ ጫንቃችን ላይ የኋላቀርነትን ቀንበር ከመጫን ባለፈ ዋጋ የላቸውም። ከዚህ ከዛም በምንሰማቸው ተንሸራታች አሉባልታዎች ከነበርንበት መውጣት አቅቶን እልፍ ዋጋ ስንከፍል እንደቆየን ምስክሮች ነን።

ባልነቃና ባልበቃ ከራስ ርቆ ወደ ሀገርና ማህበረሰብ በማይዘልቅ ጥላቻ ወለድ ስሜት ድሮነትን አጥተን በዝቅታ ውስጥ እንደነበርን የማይካድ ሀቃችን ነው። ድህነትና ኋላቀርነት ላጎበጧት ሀገር፣ በፍቅርና በወዳጅነት ወደነገ ለመሄድ ለሚያሻቅብ ትውልድ ዘረኝነት ምኑ ነው? ምንም ሳንጨምርባቸው ያሉን ጣጣዎቻችን በቂዎች ናቸው።

እስኪ ድልድይ እንስራ… የፍቅር ድልድይ። ትውልዱ ተያይዞ የሚሻገርበትን፣ ሀገር ነውሮቿን ጥላ በተስፋ የምትራመድበትን የአብሮነት ድልድይ እንገንባ። ያዕቆብ በፍኖቶሎዛ አሸልቦ ሳለ በህልሙ ከምድር ወደ ሰማይ የተዘረጋ የወርቅ መሰላል አይቶ ነበር።

የአብረሃም ልጅ ይስሀቅ በመልካም ሃሳቡ ዘመን ተሻጋሪ ታሪክ ጽፏል። አብረሃም ብዙ የገፋውን ሎጥን ወንድሜ በማለቱ ታሪክ ይዘክረዋል። እኔና እናተ ለሀገርና ለሕዝብ ምን ዓይነት ታሪክ እየሰራን ነው?

ሃሳባችን ትውልድ የሚፈጠርበት፣ ሀገር የምትጸናበት መነሻችን ነው። ሃሳብ ፍቅር የሚንጸባረቅበት፣ ጥላቻም የሚጸነስበት ማህጸን ነው። ለፍቅር የበረታና ለአብሮነት የጠነከረ ሃሳብና ምግባር ከሌለን ራሳችንን ዞር ብለን እንመልከት። ፍቅር ሌላውን የማይበድል እሱም የማይበደልበት ተፈጥሮ ነው። ብዙዎች ታሪክ የሰሩት እኛም ታሪክ የሰራነው በዚህ ተፈጥሮ በኩል ነው።

በትርክትና በወሬ ፍቅሩን ላጣ ሕዝብ መመለሻው ይቅርታና ምክክር ነው። ባስከፉን ላይ ጥርስ መንከስና ለበቀል መሰናዳት ሳይሆን በአብረሃምና በሎጥ የወንድማማችነት መንፈስ በመነጋገር ወደ መግባባት መምጣት ይቻላል። ጥላቻ እንደፍቅር የሚያፍርበት የለም።

አሁን ላይ በድርጊታችን ፍቅርን አሸማቀን ጥላቻን እያኩራራን ነው። ፍቅር በተሸማቀቀበት ሀገርና ማህበረሰብ ውስጥ ደግሞ መግባባትም ሆነ አብሮ መቆም የማይታሰብ ነው። ጥላቻን አኮስሰን ፍቅርን ስናጀግን ብቻ ነው ወዳጣናቸው በረከቶቻችን የምንመለሰው።

ኢትዮጵያዊነት በአንድነት ኮስሶ አያውቅም። ፊተኛ ያደረጉን የታሪክ ገድሎቻችን የእኔ የአንተ በሌለበት አእምሮና ልብ የተፈጠሩ ናቸው። አሁንም ታሪክ ለመሥራት እንዲሁም ድሮነትን ለመመለስ ከዚህ ውጭ ሌላ ምርጫ የለንም።

ጥሩ መስለውን ጥሩ ያልሆነ ብዙ ነገሮችን ሞክረናል። ልክ ሳይሆኑ ልክ በመምሰል ብዙ ነገሮች ወርቃማ እድሎቻችንን ነጥቀውናል። ለተሰናዳ አእምሮ ሁሌም ለውጥ አለ። ጊዜው ያጣነውን ለማግኘት በአንድነት የምንቆምበት እንጂ እንዳለፈው አንድ ዓይነት ነገር እየደጋገምን የምንባክንበት እንዳይሆን ፍቅርን ፊተኛ እናድርግ።

ታላላቅ የመንፈስ ልዕልናዎች ከአብሮነት በቀር በየትኛውም ምድራዊ ኃይል ውስጥ የሉም። ብዙሀነትን ላቀፉ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ድብልቅ ሀገራት እንደ ሀገር ለመቀጠልም ሆነ ለመበርታት አብሮ ከመቆም የተሻለ አማራጭ የላቸውም።

እንደ ሀገር ስንነሳ፣ እንደ ሕዝብ ስንበረታ፣ እንደ ታሪክና ትውልድ ስንገን ይሄን የልዕልና ፍኖት ፊተኛ አድርገን ነው። የተራመድንባቸው የታሪክ ዳናዎች፣

 ያነጠፍናቸው የክብርና የብኩርና ምንጣፎች፣ በነጻነትና በፍትሀዊነት ከዓለም ፊት ያቆሙን ገናና እሴቶቻችን ከአንድነት ጀምረው በአንድነት ያበቁ ናቸው።

መስቀል፣ መውሊድ እንዲሁም ኢሬቻ ከመንፈሳዊና ከሕዝባዊ በዓልነታቸው ጎን ለጎን የማንነታችንና የአብሮነት ማሳያዎች ናቸው። ጥንታዊነትን ከአሁናዊነት ጋር የቋጠሩ የፍቅርና የመተሳሰብ በዓላት ናቸው። መነሻቸው ከየትም ሳይሆን ከእኔና ከእናንተ አብራክ ውስጥ ነው። በአንድ ላይ ስናከብራቸው ውበት ይጨምሩልናል፣ አንድነት ያበዙልናል፣ ከሁሉም ትልቁን ፍቅርን ይገልጡልናል።

ኢሬቻ ፍቅር ከፍ የሚልበት የምስጋና በዓል ነው። ሌሎቹም የአደባባይ በዓሎቻችን ኢትዮጵያዊነትን የሚገልጡበት የሆነ ውበት አላቸው። ትልቁና ሊታወቅ የሚገባው ይሄ ውበት የሚታየውም ሆነ የሚደምቀው ከጥላቻ ርቀን በፍቅር ዓይን ስናስተውለው ነው።

ጥላቻ ውበት የለውም። ብርሃን የሚደብቅ፣ ማማር የሚሸሽግ የፍቅር ባላንጣ ነው። ለፍቅር የተከፈቱ አፎች እንዲበረቱ፣ ለምርቃት የተጀመሩ እንዲቀጥሉ መንገድ ጠራጊዎች በመሆን አስተዋጽኦ ማድረግ አለብን።

የታሰርንበት የብዙሀነት ገመድ አንዱን አጥብቆ ሌላውን ያላላ አይደለም። ኢትዮጵያዊነት መልኩ ብዙሀነት ተቀይጦበት ዥንጉርጉር ነው። ማንንም አድምቆ ማንንም የሚያደበዝዝ አይደለም። የምንጠብቀውም ሆነ የምንላላው፣ የምንደምቀውም ሆነ የምንደበዝዘው ለአንድነታችን በሰጠነው ዋጋ ልክ ነው። አንድነት መጥበቅ እና መድመቅ የተዋሃዱበት የክብር ማማ ነው። መለያየት በተቃራኒው ዝቅታ።

በአንድነት ወደ አንድነት ለመሄድ ጥንት የበረታንበትን አሁንም ለመንገዳገዳችን ምርኩዝ የሚሆንን የአንድነት ምርኩዝ እንጨብጥ። በአንድነት ካልተጓዝን ሩቅ አንደርስም። የስኬትም ሆኑ የሰላም መንገዶች ተያይዘውና ተቃቅፈው ለሚሄዱ እግሮች የተመቹ ናቸው። በፍቅር እስካልቆምን፣ የቡዳኔና የጎጥ አስተሳሰባችንን እስካልተውን ድረስ ክብር የሚጨምር ምንም መፍጠር አንችልም።

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን መስከረም 30/2016

Recommended For You