«ልዩነቶቻችንን በማጥበብ ሀገራችንን በማይናወጥ መሠረት ላይ ለማቆም በትጋት መሥራት ይጠበቅብናል»  – የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ

(ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ለ6ኛው የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የጋራ ስብሰባ ያደረጉት ንግግር ሙሉ ቃል )

– የተከበሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ

– የተከበሩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ

– የተከበራችሁ የሁለቱ ምክር ቤቶች አባላት

– ክቡራትና ክቡራን

– ውድ ኢትዮጵያውያን፤

የሀገራችንን የዘመናት ታሪክ ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንመለከት፤ የተለያዩ ገጽታዎችን እናስተውላለን። በአንድነት ብዙ ችግሮችን ተሻግረን ህልውናችንን አስጠብቀናል። ተከባብረንና ተሳስበን በአብሮነት ዘመናትን ተሻግረናል። በኅብረት ቆመን ተባብረን ሀገራችንን ለመውረር እና ሕዝባችንን ለማንበርከክ የተንቀሳቀሱ ጠላቶችን አሳፍረናል። የታላላቅ ሥልጣኔዎች መገለጫ የሆኑ ትእምርትን አንፀናል። ለዓለም ሕዝብ ጥበብ፣ ፍልስፍናን፣ ሕግን፣ የእህል ዘሮችን፣ ተቋማትን፣ አበርክተናል። የአልገዛም ባይነት ምሳሌዎች በመሆን ጥቁር ሕዝቦች ከጫፍ እስከ ጫፍ ለነፃነታቸው እንዲንቀሳቀሱ የአርበኝነት መንፈስ ፈጥረናል።

በሌላ በኩል ደግሞ ሁላችንንም ሊያግባባ የሚችል ሀገራዊ ትእምርት መፍጠር አቅቶናል፤ ሁላችንም ሊያሰባስብ የሚችል ትርክት መገንባት ተስኖናል፤ በአብዛኞቻችን ዘንድ ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥት ማጽናት አቅቶናል፤ እርስ በእርስ ተከፋፍለን፤ ልዩነቶችንም ማቻቻል አቅቶን፤ ወደ እርስ በእርስ ግጭትና ጦርነት በመግባት እንደ ሀገር የማይተካ ዋጋ ከፍለናል አሁንም እየከፈልን እንገኛለን። ሀገራዊ ጸጋዎቻችንን ባለመጠቀም በድህነት ማቅቀናል።

በዚህ የተነሣ ባለ ሁለት መልኮች ሆነናል። አንዱ ያለንን ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ፣ ባህላዊ እና መልክአ ምድራዊ ዕድል የሚያሳየው መልካችን ነው። ሌላው ይሄን ከመጠቀም ይልቅ ራሳችንን በሚያቀጭጭ መንገድ የተጋጨንበት፣ የተከፋፈልንበትና ራሳችንን በራሳችን ያወደምንበት መልክ ነው። በመሆኑም ጥንካሬያችንና መልካም ገጽታችንን የሚያበላሹ፤ የታደልነውን ጸጋ በአግባቡ እንዳንጠቀም የሚያባክኑ፤ ትውልድ የሚያመክኑ፤ የተቃረኑ ገጽታዎቻችንን ማረም አለብን። ስብራቶቻችንን በመጠገን፤ ልዩነቶቻችንን በማጥበብ ሀገራችንን በማይናወጥ መሠረት ላይ ለማቆም በትጋት መሥራት ይጠበቅብናል።

ይህንን ለማድረግም አሁን ቆም ብለን የመጣንበትን መንገድ መገምገም ይገባናል። ያተረፍነውንና ያጎደልነውን ማስላት አለብን። ያተረፍንበትን አብልጠን በመያዝ፣ ያላዋጣንን ደግሞ በሌላ መንገድ በመተካት፣ በተለወጠ ሃሳብና በተለወጠ ልቦና ልንነሣ ይገባል።

– የተከበራችሁ የምክር ቤት አባላት

– ክቡራትና ክቡራን

ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ በዚህ ትውልድ አዲስ የለውጥ ፋና ተለኩሷል። አዲስ የሁለንተናዊ ብልጽግና ምዕራፍ ተከፍቷል። ይህ የለውጥ ምዕራፍ የተወሰኑ ግለሰቦች፣ የጥቂት ቡድኖች ወይም የሆነ አካባቢ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያውያን ምዕራፍ ነው። በሃሳቦች ልንስማማም ላንስማማም እንችላለን። ነገር ግን ዕድሉ የሀገር፣ ዕድሉ የትውልድ ነው። ስለዚህም የጎደለውን እየሞላን፤ ያነሰውን እየጨመርን፣ ያልተስማማንበትን እያቆየን፣ በተስማማንበት እየሠራን፤ በልዩነቶች ላይ ቆመን ሳንጋጭ፤ በተግባባንበት አብረን እየተጓዝን፤ ባልተግባባንበት ወሳኝ ሀገራዊ ጉዳይ ሲኖር ምልዐተ ሕዝቡ በነፃነት ተወያይቶ እንዲወስንበትና የሕዝብን ድምጽ እያከበርን በመሄድ ለመጪው ትውልድ የተሻለች ሀገር ልናስረክብ ይገባል።

ያደጉ የምንላቸው ሀገራት ዛሬ ላይ የደረሱት ልዩነቶች ስለሌሏቸው አይደለም። ልዩነቶቻቸውን በማቻቻል፤ ልዩነቶቻቸውን ከግጭት በመለስ በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት ስለቻሉ ነው። ልዩነትም አንድነትም ተፈጥሯዊ ነው። የሰው ልጅ የመልክ፣ የእምነት፣ የባህል፣ የቋንቋ፣ የመኖሪያ አካባቢ፣ የአስተሳሰብ ልዩነት አለው። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ የሚያደርጉት የሰውነት ጉዳዮችም አሉ። ወሳኙ ነገር ልዩነትን እንደ ጌጥ አንድነትን እንደ ማስተሳሰሪያ ኃይልና አቅም መጠቀሙ ነው። ትናንት ለነገ ዕንቅፋት መሆን የለበትም። ትምህርት እንጂ። የትናንት ታሪክ የአብሮነት መገንቢያ እንጂ የልዩነት መነሻ እንዳይሆን መሥራት አለብን። እየተደማመጥን፤ እየተመካከርን፤ ለሃሳብና ለውይይት በራችንን ክፍት እያደረግን እንጓዝ። ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን እናጠንከር፤ ለሀገራችን መፃኢ ዘመን በጋራ እንትጋ። ከትናንት ይልቅ ጉልበታችንንና ጊዜያችንን በነገ ላይ እናውል። ይህ ነው የዚህ ትውልድ ትልቁ ኃላፊነት።

– የተከበራችሁ የምክር ቤት አባላት

– ክቡራትና ክቡራን

መንግሥት የሀገራችንን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ ከሦስት ዓመት በፊት የአሥር ዓመት የልማት ዕቅድ አዘጋጅቶ ወደ ተግባር ገብቷል። በዕቅዱ የመጀመሪያ ሦስት ዓመታት ከ2013 እስከ 2015 በሁሉም የዕድገት አመላካች ዘርፎች ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ተገኝተዋል።

ያለፈውን አንድ ዓመት አፈጻጸም ብቻ ብንመለከት በጥቅሉ ጥሩ ውጤቶች ተመዝግበዋል። በፈታኝና በተለያዩ ተግዳሮቶች ውስጥ እያለፍን ቢሆንም ጠንክረን መውጣታችንን ያሳያል። ተግተን ከሠራን ደግሞ ከዚህ የተሻለ ውጤት ማምጣት እንደምንችል ተምረንበታል። በአንድ በኩል እንደ ሀገር የገጠሙንን ፈተናዎች መቋቋም፣ በሌላ በኩል ደግሞ በእነዚህ ፈተናዎች ውስጥ ፈታኝ ሁኔታዎችን ወደ ዕድል መቀየርና ዕድገት እና ለውጥ ለማስመዝገብ መቻል ታላቅ ስኬት ነው።

በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ሲካሄድ የነበረውን ደም አፋሳሽ ጦርነት በሠላም ስምምነት እንዲቋጭ አድርገናል። «ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ» የሚለው የአህጉራችን መርሕ በተግባር ተፈትሾ ውጤታማ እንደሆነ አሳይተናል። አሁን ላይ ስምምነቶቹ ወደ ተግባር ተቀይረው የመልሶ ግንባታ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን። ይህ ሂደት ለሀገራችን ትልቅ ትምህርት የሚወሰድበት ሆኖ አልፏል።

የሰሜኑን ጦርነት በንግግር ለመፍታት መቻሉ ብዙ ዜጎችን ከእልቂት እና ሰቆቃ የገላገለና እፎይታን የፈጠረ ነው። ከዚህም ባሻገር ከዚህ በኋላ በሀገራችን በጠመንጃና በኃይል ልዩነቶችን የመፍታት አማራጭ ማክተም እንደሚኖርበትና እንደሚችልም በተግባር ያሳየ ነው። በዚህም መንግሥት ምንጊዜም ከማንኛውም ኃይል ጋር ችግሮችን በመወያየትና በንግግር የመፍታት ቁርጠኝነት እንዳለው በተግባር ያስመሰከረበት ነው። ምንጊዜም ቢሆን ለንግግርና ለሠላም የሚረፍድ ጊዜ የለም። ተነጋግረን ባንግባባ እንኳን ጦርነት አማራጭ ሆኖ መቅረብ የለበትም። በጦርነት ሜዳ አንድ አሸናፊን ይፈጥራል። ውይይት ግን ሁሉን አሸናፊ ያደርጋል። አለመግባባቶችና ጥያቄዎች ሁሉ በንግግር ሲፈቱ ድሉ የሁላችንም መሆኑን በመረዳት በየትኛውም አካባቢ የሚፈጠሩ አለመረጋጋቶችን እና ግጭቶችን በማቆም የሠላም አማራጮችን ከመጠቀም ውጪ የተሻለ አማራጭ እንደሌለን መገንዘብ ይኖርብናል።

ያደሩና ለዘመናት የነበሩ የሃሳብ ልዩነቶችን ለማስታረቅና ለማቀራረብ ብሎም ወደተሻለ መግባባት እንዲወስደን ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አቋቁመናል። የቀደሙ ክፍተቶችንና ዝንፈቶችን በማረም፤ የወደፊት ዕድላችንን ተመካክረን በማቅናት፤ የተሻለች ኢትዮጵያን የመፍጠሩ ዕድል እጃችን ላይ ነው። በተደጋጋሚ በታሪካችን ውስጥ እንዳመለጡን ዕድሎች ይህ ዕድል ሊያመልጠን አይገባም። አንድ ነባር ክፉ ልማድ አለን። ዕድሎች በእጃችን እያሉ እንደዋዛ እናሳልፋቸዋለን። ከዘመናት በኋላ እንቆጭባቸዋለን።

ምክክሩ ያጠፋናቸውን ለማረም፣ ያልተግባባነውን ለማግባባት፣ የተሰበረውን ለመጠገን፣ የተጣመመውን ለማቃናት፣ የተራራቀውን ለማቀራረብ፣ ዳር እና ዳር ያለውን ወደ መሐል ለማምጣት እና ለሁላችንም የምትሆን ሀገር ለመገንባት፣ ሁላችንም ተግባብተን እና ተማምነን መሠረት የምንጥልበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነው።

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የቅድመ ዝግጅት ምዕራፉን አጠናቆ በዚህ ዓመት ወደ ምክክር ምዕራፍ ይሸጋገራል። ይህ ምክክር ልዩነታችንን ማጥበቢያ ነው። አብሮነታችንን አጉልተን በሀገረ መንግሥት ግንባታችን ሂደት የታዩ መሠረታዊ ስብራቶችን አክመን፣ የተረጋጋ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ጥሩ መደላድል የምንፈጥርበት ዕድል ነው። ኢትዮጵያ ሁላችንንም መስላ፣ በሁላችንም እኩል ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ላይ በአስተማማኝ መሠረት ላይ እንድትታነጽ የሚያስችለን ልዩ አጋጣሚ ነው። ስለዚህም የታለመለትን ዓላማ፣ እንዲሁም የተጣለበትን ተስፋ እውን እንዲያደርግ የሁላችንም ድጋፍና ጥረት ያስፈልጋል።

ከሀገራዊ የምክክር መድረኩ ማንም መጉደል የለበትም። ሁሉም በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ድርሻ ያለው ሁሉ ሊሳተፍ ይገባል። ለምን ቢባል የምንነጋገረው ስለ ሀገራችን ነው፤ የምንነጋገረው ስለ ጋራ ቤታችን ነው። የምንነጋገረው የትናንት ጉድለቶቻችንን ሞልተን፤ ዛሬን በአብሮነት እና በይቅርታ ተሻግረን፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ ብልጽግናዋን እንድታረጋግጥ ለማድረግ ነው። ኅብረ ብሔራዊነት ጌጣችን፤ አንድነት መተሣሠሪያ ገመዳችን እንዲሆን ነው።

 ከትውልድ ዕዳ ነፃ የሆነች በዛሬው ሀብታችን ላይ የተመሠረተች ሀገር እንድንገነባ ነው። መነጋገር፤ መከራከር፤ መግባባት የዚህ ትውልድ ኢትዮጵያውያን መለያ ሊሆን ይገባል። በኃይል ፍላጎትን ማስፈጸም ለዘመናት አይተነዋል። ውጤቱም ጊዜያዊ ድል ሲያመጣ እንጂ በዘላቂነት ሀገር ሲያስቀጥል አላየንም። የተዋጊነት ሥነ ልቦና ከውጭ የመጣ ጠላትን መክተን ሉዓላዊነታችንን ለማስከበር እጅግ ጠቅሞናል። የሠለጠነ ሥርዓተ መንግሥት ለመመሥረት ግን አልጠቀመንም። ለሠለጠነ ሥርዓተ መንግሥት መነጋገር፣ መመካከር፣ መወያየት፣ መከራከር፣ ሰጥቶ መቀበል፤ ወሳኞቹ መሣሪያዎች ናቸው።

የሠለጠነ ሥርዓተ መንግሥት መፍጠሪያ ከሆኑ መንገዶች አንዱ ይህ ሀገራዊ ምክክር በመሆኑ ማናችንም ከዚህ መድረክ ሳንጎድል ስለ ሀገራችን እንነጋገር፤ እንሟገት፤ እንተማመን በመጨረሻም ሁላችንም እናሸንፍ። ኢትዮጵያም ታሸንፍ። ያኔ በኩራት ለልጆቻችን የምንናገረው ታሪክ ይኖረናል። ፍላጎቱን በጠመንጃ ሳይሆን በሃሳብ የበላይነት የሚያስፈጽም ትውልድ በኢትዮጵያ መፈጠሩን ዓለም ይመሰክርልናል። ታሪክም ስማችንን በልዩነት በደማቁ ያነሣዋል።

– የተከበራችሁ የምክር ቤት አባላት

– ክቡራትና ክቡራን

ድህነትና ኋላቀርነት ካለፉ ዘመናት የወረስናቸው ነባር ችግሮች ናቸው። በዋነኝነትም መዋቅራዊና ሥር የሰደዱ የኢኮኖሚ ስብራቶች ሀገራችን ወደፊት እንዳትጓዝ አድርጓታል። መንግሥት እነዚህን ችግሮች ከመሠረታቸው ለመቀየር ዘርፈ ብዙ የዕድገት አማራጮችን ነድፎ እየሠራ ነው። በዚህም ኢኮኖሚያችን ከገባበት ቅርቃር እየወጣ በለውጥ አዙሪት ውስጥ እንዲገባ በማድረግ ተከታታይ ዕድገቶች እንዲመዘገቡ አስችሏል።

በፈታኝና አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ጭምር እያለፍን፣ ባለፈው አንድ ዓመት የ7.5 በመቶ ጥቅል ሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ተመዝግቧል። ይሄም ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ሥጋቶችንና ፈተናዎችንም ወደ ዕድል በመቀየር ተጨባጭ ውጤት እያመጣን ለመሆኑ ጉልህ ማሳያ ነው።

ኢኮኖሚያችን አዲስ የታሪክ እጥፋት ላይ ነው። ደረጃ በደረጃ ተወዳዳሪና ገበያ መር እየሆነ፤ ከነጠላ ዘርፍ ዕድገት ተኮርነት ወደ ዘርፈ ብዙ ተኮርነት እየተሸጋገረ ነው። መሠረቱን ብዝኃ ኢኮኖሚ በማድረግ የሕዝቦች ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ እያደረገ ይገኛል። በዚህም ምክንያት በአስር ዓመት ውስጥ እናሳካቸዋለን ብለን ዐቅደን እየሠራንባቸው ያሉት ጥቅል ሀገራዊ የምርታማነት እና የኢኮኖሚ ዕድገት ግቦች በታቀደው ጊዜ እየተሳኩ ይገኛሉ።

በግብርናው መስክ እንደ ሀገር የስንዴ ምርት ላይ የታየው እመርታ የሚበረታታ ሆኗል። በዓመቱ 103 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ተመርቷል። በታሪክም ለመጀመሪያ ጊዜ ስንዴን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ያገኘንበት ዓመት ሆኗል። በሩዝና በበቆሎ ምርትም እየተከናወነ ያለው ምርታማነትን የማሳደግ ተግባር ጠቅላላ ሀገራዊ የሰብል ምርቱን ወደ 639 ሚሊዮን ኩንታል በማሳደግ፣ ለውጭ ገበያም እንድናቀርብ በር ከፍቷል።

በክረምቱ ከ2 ሚሊዮን በላይ ሄክታር ተጨማሪ መሬት በመስኖ ለማልማት የተደረገው ጥረት በግብርናው ዘርፍ ዓይነተኛ ለውጥ እያመጣን እንዳለን ማሳያ ነው። በሌማት ትሩፋት ንቅናቄ በሁሉም ክልሎች ከፍተኛ ምርታማነት ታይቷል። በማር፤ በእንስሳትና በእንስሳት ተዋጽዖ፣ በጓሮ አትክልትና በፍራፍሬ ምርት ላይ የጎላ ለውጥ መጥቷል። በዚህም ዜጎች እየተፈጠረ ያለውን የዋጋ ግሽበት እንዲቋቋሙ፣ ተጨማሪ የሥራ ዕድል እንዲያገኙና ብሎም ከራሳቸው ተርፎ ለገበያ እንዲያቀርቡ አስችሏል።

በአምራች ኢንዱስትሪው መነቃቃት እየታየ ነው። በተለይም ‹ኢትዮጵያ ታምርት› በሚል ንቅናቄ አምራችነትን በየአካባቢው ለማስፋፋት የታየው ጥረትና 160 ፋብሪካዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጋቸው፣ በዘርፉ መሠረታዊ ለውጥ እየመጣ ለመሆኑ ማሳያ ነው።

በሥራ ዕድል ፈጠራም በዓመቱ 3.5 ሚሊዮን የሥራ ዕድል ለመፍጠር ተችሏል። የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪትን ሕጋዊ ማዕቀፍ በማበጀት፣102 ሺህ ዜጎች ተጠቃሚ ሆነዋል።

በአገልግሎት ዘርፍ በዓመቱ የ7.8 በመቶ ዕድገት ለማስመዝገብ ተችሏል። ቱሪዝም በብዝኃ ዘርፍ የዕድገት አማራጭ አንዱ ቁልፍ ዘርፍ ነው። በዚህ በኩል በዓመቱ የቱሪስት ፍሰቱን በማሳደግ በኩል ፈታኝ እና አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነንም አበረታች ዓመታዊ ዕድገት ለማስመዝገብ ተችሏል። በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እና በአገልግሎት የውጭ ንግድ የታየው ዕድገትም በርግጥም ሀገራችን የወረስናቸውን የኢኮኖሚ ስብራቶች ለመጠገን የምታደርገው ጥረት በመልካም ጎዳና ላይ እንደሚገኝ አመላካች ነው።

የፋይናንስ ዘርፉ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከፍተኛ ዕድገት እያስመዘገበ ነው። የሁሉም ባንኮች የተቀማጭ ገንዘብ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ መሻሻል አሳይቷል። አጠቃላይ የብድር አሰጣጥ ዕድገት ያሳየ ሲሆን ባለፈው በጀት ዓመት ከ547 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ተሠራጭቷል።

ዲጂታላይዜሽንን ከማስፋፋት አንጻር በፋይናንስ ዘርፉ የተሻለ አፈጻጸም እየታየ ነው። በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት የሞባይል ዋሌት ተጠቃሚዎች መጠን፣ በ2014 ከነበረበት 43.32 ሚሊዮን፣ በ2015 ወደ 68.66 ሚሊዮን ተጠቃሚ ለማሳደግ ተችሏል። የሞባይል ባንኪንግ ተጠቃሚዎች መጠን በ2014 ከነበረበት 16.34 ሚሊዮን፣ በ2015 ወደ 27.35 ሚሊዮን ከፍ ብሏል። በአጠቃላይ በዲጂታል ሥርዓቱ የተላለፈ የገንዘብ መጠን በ2014 ከነበረው 1.6 ቢሊዮን ብር አፈጻጸም ወደ 4.777 ቢሊዮን ብር በማደግ ከፍተኛ ዕድገት አስመዝግቧል።

ኢትዮጵያ 50 ቢሊዮን ችግኞችን እተክላለሁ በማለት በጀመረችው የአረንጓዴ ዐሻራ ጉዞ በአንደኛ ዙር 25 ቢሊዮን ችግኞችን ተክላለች። በ2015 ደግሞ ከ7.2 ቢሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል ተችሏል። በተለይም በዚህ ሀገራችንን አረንጓዴና ለምለም ለማድረግ በተያዘው ግብ ዘንድሮ በአንድ ጀምበር ብቻ ከ566 ሚሊዮን በላይ ችግኞች በመትከል አዲስ ታሪክ ለመጻፍ በቅተናል።

– የተከበራችሁ የምክር ቤት አባላት

– ክቡራትና ክቡራን

2015 ዓ.ም የሕዳሴ ግድብ አራተኛ ዙር የውኃ ሙሌት እና ከ90 በመቶ በላይ ግንባታው መጠናቀቁን የሰማንበት ዓመት ነበር። የሕዳሴው ግድብ የኢትዮጵያን የከፍታ ዘመን ለማብሰር ቁልፍ እንደሆነ አምናችሁ ገንዘባችሁን፣ ላባችሁን እና ድጋፋችሁን የሰጣችሁ ኢትዮጵያውያን፣ ይህ የእናንተ ውጤት በመሆኑ እንኳን ደስ አላችሁ። በያዝነው ዓመት የግድቡ የሲቪል ግንባታ ሥራ ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅ ይገመታል።

የሕዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ሀብት ብቻ አይደለም። የቱሪዝም ሀብት፣ የውኃ ውስጥ ሀብት፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ የሞራል ልዕልና፣ የኅብረ ብሔራዊ አንድነት ትዕምርትም ጭምር ነው። በጋራ ሀብቶቻችን ላይ የምናደርገው ልማት የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ፣ የመልማት ፍላጎታችንን የሚያሳካ፤ ጎረቤቶቻችንን እና የወንዙ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራትንም የማይጎዳ መሆኑን በተግባር አሳይተናል።

በጥቅሉ የተመዘገበው ዕድገት እና የመጣው ሀገራዊ ስኬት በአንድ በኩል ስንመለከተው አመርቂ ቢሆንም በሌላ በኩል ቁጭትን የሚቀሰቅስ ነው። ሀገራችን በብዙ ፈተናዎች እና ተግዳሮቶች ውስጥ ሆና የተመዘገበ በመሆኑ፣ ውጤቱን የተለየ ያደርገዋል። በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህ ሁሉ ፈተናዎችና ተግዳሮቶች ባይኖሩ ኖሮ ከዚህ በላይ ዕድገት ሊመዘገብ እንደሚችል ታሳቢ ሲደረግ በርግጥም ቁጭት የሚፈጥር ነው። እነዚህ ውጤቶች ቢኖሩም ሕዝባችንን የሚፈትኑ ተግዳሮቶችም አሉብን። ዋነኞቹ የጸጥታ ሥጋት፣ የኑሮ ውድነት፣ ሌብነትና ብልሹ አሠራር፣ እንዲሁም ኮንትሮባንድና ሕገ ወጥነት ናቸው።

የዋጋ ግሽበትን ለመቋቋም የመጀመሪያው መፍትሔ ምርትና ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ ማስፋፋት ነው። ከዚህም ጋር ተያይዞ የፊስካልና ገንዘብ ፖሊሲ አፈጻጸማችንን ለመቃኘት የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። ይሄም በዚህ ዓመት መልካም ውጤት ከታየባቸው መስኮች አንዱ ነው። 543 የእሑድ ገበያዎችን በዚህ ዓመት በመጨመር በጥቅሉ 703 የገበያ ማዕከላትን ለማስፋፋት ተችሏል። እንዲሁም በየአካባቢው የዳቦ ፋብሪካዎችን በማሳደግ ቢያንስ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎቻችን በኑሮ ጫናው ለከፋ ችግር እንዳይጋለጡ የማድረግ ሥራው ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።

ማዕድ ማጋራት እና የአቅመ ደካሞችን ቤት የማደስ ሥራዎች፣ በዜጎች የኑሮ ደረጃ መሻሻል እና የድህነት ቅነሳ ዙሪያ ተጨባጭ ውጤት እንዲመጣ አስችለዋል። በተማሪዎች ምገባ ከ6.9 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ቁርስና ምሳ እንዲመገቡ በማድረግ ድህነት ከመቀነስ ባሻገር አምራች ዜጋ ለመፍጠር እና ትውልድ ለመገንባት የሚያስችል የሰብአዊ ልማት ለውጥ ማምጣት ተችሏል።

ከዚህም በተጨማሪ በየምገባ ማዕከላቱ ብዙ ወገኖች እንዲመገቡ መደረጋቸው የሰው ተኮር ልማታችን አንዱ መገለጫ ነው። ማዕከላቱ የሚመገበው ሕዝብ እንደ ሀገር ቢቆጠር በሕዝብ ብዛት ከአፍሪካ በ35ተኛ ደረጃ የሚቀመጥ ነው። በመሆኑም የሀገራችንን ኢኮኖሚ ጥንካሬ የሚያሳይ ትልቅ ስኬት ነው። የአቅመ ደካሞች ቤት እድሳትም በተመሳሳይ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ በማሻሻል እና ሕፃናት በተሻለ የመኖሪያ ሁኔታ እንዲያድጉ በማድረግ በትውልድ ግንባታ ላይ እየፈጠረው ያለው ለውጥ ትልቅ ነው።

– የተከበራችሁ የምክር ቤት አባላት

– ክብራትና ክቡራን

ባለፈው ዓመት የውኃ አቅርቦትን በማሻሻል፣ ድርቅ በተደጋጋሚ የሚያጠቃቸው አካባቢዎች ላይ የውኃ አቅርቦት እንዲያገኙ ተደርጓል። የጎርፍ ሥጋት ያለባቸውን አካባቢዎች የአደጋ ተጋላጭነት ለመቀነስ አበረታች እንቅስቃሴዎች ተከናውነዋል።

በዓመቱ በዲፕሎማሲው መስክም በዓለም አቀፍ እና በቀጣናው ላይ ወሳኝ የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎች ተሠርተዋል። ለአብነትም ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ የዓመቱ ብሔራዊ የዲፕሎማሲ ድል ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ይህም የኢትዮጵያን ተደማጭነት ከፍ ያደርገዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶች መሥራች ናት። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በዲፕሎማሲው መስክ እየተገኙ ያሉ ስኬቶች ለኢትዮጵያ የዳበረ የዲፕሎማሲ ታሪክ ዕውቅና የሰጡ ጭምር ናቸው ማለት ይቻላል። ከዚህም ባሻገር ሀገራችን እያስመዘገበች ላለው ፈጣን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴም ተገቢ ዕውቅና የሰጠም ጭምር ነው።

ይህ ዕድል በኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዘርፎችን እንዲነቃቁ ያደርጋል፤ በንግድና በኢንቨስትመንት ተጨማሪ ዕድል ይፈጥራል፤ የገበያ አማራጮችን ያሰፋል። የትብብር ማዕቀፎቻችንም እንዲጎለብቱ ትልቅ ሚና ይኖረዋል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ ያላትን ተቀባይነት በመጠቀም በባለብዙ ወገን መድረኮች ከራሷ ባለፈ ለአፍሪካ ጥቅሞች እንድትቆም ዕድል የሚሰጣትም ይሆናል።

 – የተከበራችሁ የምክር ቤት አባላት

– ክቡራትና ክቡራን

ይህ ዓመት ከአሥር ዓመቱ የልማት ዕቅድ ሁለተኛውን ምዕራፍ የምንጀምርበት ዓመት ነው። በመሆኑም ያለፉት ሦስት ዓመታት የዕቅድ አፈጻጸማችንን ጥንካሬዎች በማስፋት ድክመቶቻችንን ማረም አለብን።

በቀጣይ ሦስት ዓመታት ሁለንተናዊ የሀገራችንን ዕድገት ማስቀጠል ዋነኛ ዓላማችን ነው። በመሆኑም ልማት እና ጥፋት መሳ ለመሳ ይዞ መጓዝ ለዘላቂ ሀገራዊ ዕድገት ዕንቅፋት ነው። ዕቅፋቶችን ማንሣት እና የሀገራችንን ዘላቂ ዕድገት ማፍጠን ለአፍታም የምናቆመው ጉዳይ አይሆንም።

የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ እና የሠላም መንገዶችን አሟጦ መጠቀም፤ እንዲሁም ዘላቂ ሀገራዊ ሠላምን ለማረጋገጥ መሥራት የዚህ ዓመት የመንግሥት ዋና ተግባር ይሆናል። የሕግ የበላይነት ሲባል ሕገ መንግሥቱን እና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በማስጠበቅ፤ የዜጎችን ሠላም እና ደኅንነት በማረጋገጥ፤ (ዓለም አቀፋዊ በሆነው ሥርዓት መሠረት) ኃይልን የመጠቀም ብቸኛ ባለቤት የመንግሥት የሕግ አስከባሪ ተቋማት ብቻ መሆናቸውን ማረጋገጥ ነው።

የሠላም በር ሁልጊዜም ክፍት ነው። በተናጠልም ይሁን በጋራ በሠላማዊ መንገድ ከማንኛውም ወገን ጋር ለመነጋገር መንግሥት ሁሌም ዝግጁ ነው። ለዚህ ደግሞ በሀገራዊ ምክክሩ ሁሉም ወገኖች ፍላጎቶቻቸውን አቅርበው እንዲነጋገሩ የሚሠራ ይሆናል። ከዚህ ውጪ ግን የኃይል አማራጭን በመጠቀም ፖለቲካዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት የሚደረጉ ሕገ ወጥ ተግባራትን መንግሥት አይታገስም።

በሌላ በኩል ለዘመናት በክፉም በደጉም አብሮ የኖረውን ሕዝባችንን አብሮነት እና ወንድማማችነት/ እኅትማማችነት ለማላላት፤ ብሎም ለመበጠስ በማለም፣ የሚካሄዱ ዘመቻዎች እየተበራከቱ መጥተዋል። ይህ ከኢትዮጵያዊ ባህል እና ሥነ ምግባር የወጣ፤ ሕዝብን ሕዝብ ለማቃቃር የሚሠራ፤ የጥላቻና የሐሰት መረጃ የማሠራጨት ሥራ የሕዝባችንን አብሮነት እንዳይሸረሽር ያሠጋል። ስለሆነም ሐሰተኛ መረጃ፣ የጥላቻ ንግግርና ሕዝብን የሚያጋጩ ተግባራትን በመፈጸም፣ የሕዝቦችን አብሮነት እና ማኅበራዊ መስተጋብር አደጋ ላይ በሚጥሉ አካላት ላይ፣ መንግሥት በሕግ ተጠያቂ የማድረግ ሥራዎችን የሚሠራ ይሆናል። የሀገራችን የፖለቲካ ምኅዳር የሃሳብ ፍልሚያ ሜዳ እንዲሆን ባለፉት ዓመታት የተጀመረው የዴሞክራሲ ተቋማትን የማብቃት ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል። ፖለቲካችን ወደ ምክንያታዊነት እንዲያድግ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ ሥራዎች ይሠራሉ።

ኢትዮጵያ ሀገራችን ትልቅ ሀገር ናት። በመሆኑም ይህን ትልቅነቷን በሚመጥን መልኩ ለዓለም መገለጥ አለባት። ሀገራት ወደ ሁለንተናዊ ብልጽግና ጫፍ የወጡት ቀርጸው በተነሡት ትርክት ነው። በዋነኝነትም ከነጠላ ቡድናዊ ትርክት ይልቅ ሁሉን አሰባሳቢ ገዢ ትርክት ይዘው የተነሡ ሀገራት ሀገራቸውን አበልጽገው ዓለምን እየዘወሩ ይገኛሉ። እኛም ታሪካችንን፤ጥንታዊ የሥልጣኔ ባለቤትነታችንን፣ ብዝኃነታችንን የሚመጥን፤ የበለጸገ፣ የጠነከረ፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገር እና ሕዝብ ለመሆን ከነጠላ ቡድናዊ ትርክት ተላቀን አሰባሳቢ ሀገራዊ ትርክት ግንባታ ላይ መሥራት አለብን። በመሆኑም ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን የሚያጎለብቱ ሥራዎችን በመሥራት ሀገራዊ ገዢ ትርክታችን ‹ብሔራዊነት› እንዲሆን እንሠራለን። ብሔራዊነት – ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን፤ እኩልነትን እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማዕከል ያደረገ አሰባሳቢ ትርክት ነው።

ሀገራችን የእኩልነት ሀገር፤ ሁሉንም ኢትዮጵያውያንን የምትመሰል ሀገር፤ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የተድላ እና የፍስሐ ምድር፤ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሀገሬ ብለው ደም እና አጥንታቸውን ለነፃነቷና ለሉዓላዊነቷ የሚከፍሉላት ሀገር መሆን ይገባታል። በመሆኑም ሀገራዊ ገዢ ትርክታችን ለሁሉም ኢትዮጵያውያን፤ ከሁሉም ኢትዮጵያውያን፤ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ንቁ ተሳትፎ እውን እንዲሆን ይደረጋል።

ባለፈው ዓመት ጅምር ውጤት ያየንበት የፀረ ሌብነት ትግል በዚህ ዓመትም በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል። ሕዝባችን ተጨባጭ የሆኑ ጥቆማዎችን በመስጠት የተለመደ ትብብሩን አጠክሮ እንዲቀጥል መንግሥት በዚህ አጋጣሚ ጥሪውን ያቀርባል። በሌላ በኩል ሕዝባችን በመንግሥት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚገጥመውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ሥራችን ተጠናክሮ ይቀጥላል። በዚህ ዓመት በተከታታይ በምንወስደው የአገልግሎት ማሻሻያ ሥራ የሕዝባችንን ፍላጎት ለማርካት ይሠራል።

– የተከበራችሁ የምክር ቤት አባላት

– ክቡራትና ክቡራን

ባለፉት ሦስት ዓመታት ያስመዘገብነው ጥቅል ሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት በዚህ ዓመትም 7.9 በመቶ እንዲሆን በሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች በልዩ ትኩረት እንሠራለን። የግብርና ዘርፉን ምርታማነት በዚህ ዓመትም በማስቀጠል ከ22.1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ ይታረሳል። ከዚህም 810 ሚሊዮን ኩንታል አጠቃላይ የሰብል ምርት ለመሰብሰብ የምንሠራ ይሆናል።

ዝቅተኛ የኅብረሰብ ክፍሎችን እየፈተነ ያለውን የዋጋ ግሽበት ለመቀነስ ጥብቅ የፊስካል እና የገንዘብ ፖሊሲ ይተገበራል። ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ከምርት አቅርቦት የሚመነጭ የዋጋ ግሽበት ጫናን ለመቀነስ ይሠራል። ገቢ ንግድን በመተካት ተጋላጭነት እንዲቀንስ ይደረጋል። የሀገር ውስጥ ንግድን ሥርዓትና ጥራት በማረጋገጥ ተግባር ላይ ትኩረት ይደረጋል።

የመንግሥት ገቢ አሰባሰብን ለማሳደግ በዚህ ዓመት ከታክስ ገቢ 441 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዷል። በተጨማሪም ከውጭ ሀብት ግኝትና ፍሰት በበጀት ዓመቱ 4.3 ቢሊዮን ለማግኘት ታስቧል። በተመሳሳይ የውጭ ሀብት ፍሰቱን 4.3 ቢሊዮን ለማድረስ ይሠራል።

በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት ውስጥ 9.15 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚሠራ ይሆናል። በ2016 በጀት ዓመት ለ3.05 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንሠራለን። በተጨማሪም በ2016 በውጭ ሀገራት በሕጋዊ መንገድ በአምስት የመዳረሻ ሀገራት ለ500ሺ ሰዎች የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት ለመፍጠር የሚሠራ ይሆናል።

የትውልዶችን ጤናማነት ለማረጋገጥ የመንግሥታት የጤና እና የትምህርት ፖሊሲዎች ወሳኝ ናቸው። በትምህርት ዘርፉ ላይ ባለፉት ሦስት ዓመታት የተመዘገበው አበረታች ለውጥ በዚህ ዓመትም መሠረት እንዲይዝ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል። በጤናው ዘርፍም የእናቶች የወሊድ ጤናማነት እና የመቀንጨር መጠንን የመቀነስ ተግባር ዋነኛ የትኩረት ማዕከል ሆኖ በዚህ ዓመትም የምንሠራበት ይሆናል።

የሀገራችን የውጭ ግንኙነት ከጫናዎች ተላቅቆ ወደ መደበኛ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እየተመለሰ ነው። በመሆኑም ባለፈው ዓመት በዲፕሎማሲው ዘርፍ የተገኘው ሀገራዊ ስኬት በዚህ ዓመትም የሀገራችንን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መርሕን ጠብቆ አፈጻጸሙ ወደ ላቀ ደረጃ እንዲያድግ ይሠራል። ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለን ግንኙነት ከፖለቲካ ወደ ኢኮኖሚያዊ ትሥሥር እንዲያድግ በትኩረት እንሠራለን።

የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ የሚደረጉ ድርድሮች የሀገራችንን በተፈጥሮ ሀብቷ የመልማት መብት እንዲሁም የተፋፈሱ ሀገራትን የመልማት ዕድል በማይነፍግ መልኩ ይከናወናሉ። እኩል ተጠቃሚነትን መሠረት አድርጎ በሠላማዊ መንገድ ድርድሮችን ለመጨረስ ይሠራል። ሀገራችን ድንበር ከምትጋራቸው ሀገራት ጋር ያልተጠናቀቁ የድንበር ጉዳዮችን በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ምላሽ እንዲያገኙ የበሰለ ዲፕሎማሲያዊ ሥራን እንሠራለን። የድንበር ጉዳዮች ብሔራዊ ጥቅማችንን እና ዘላቂ ጎረቤታዊ ወዳጅነትን ታሳቢ በማድረግ ምላሽ እንዲያገኙ ይደረጋል።

በጥቅሉ የውጭ ግንኙነታችን ወዳጅ ሀገራትን የሚያበዛ፣ ጠላትን የሚቀንስ፣ የልማት አጋሮችን የሚያቅፍ እንዲሆን ይሠራል።

– ክቡራን የሁለቱ ምክር ቤት አፈ ጉባኤዎች

– የተከበራችሁ የሁለቱ ምክር ቤት አባላት

– ክቡራትና ክቡራን

በአጠቃላይ ባለፉት ዓመታት ካጋጠሙን ፈተናዎችና ተግዳሮቶች ትምህርትን በመቅሰም፤ ለቀጣይ ጉዟችን አቅም የጥንካሬ ምንጭ ልናደርጋቸው ይገባል። ውስጣዊ ችግሮቻችንን በሰላማዊ መንገድ በውይይት ብቻ እንፍታ።

ሁሉንም አቅሞቻችንን ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገብን ላለንበት ሁለንተናዊ የሀገራችንን ብልጽግና የማረጋገጥ ተልዕኮ እንጠቀምባቸው። አርበኛ ትውልድ እንሁን፤ ትብብራችን ለወንድማማችነት/ እኅትማማችነት፤ ለአብሮነት እና ገዢ ሀገራዊ ትርክታችን ለሆነው ለብሔራዊነት ይሁን።

የዘመናችን አርበኛ ትውልድ ታሪክ ሠሪ ነው። የኢትዮጵያን ብልጽግና በላቡ ለማረጋገጥ የሚሠራ ነው፤ ለኢትዮጵያ ከፍታ የሚታትር ነው። ነፃነታችንንና ሉዓላዊነታችንን በደማችን አስከብረናል። ብልጽግናችንን ደግሞ በላባችን ማስከበር አለብን። ከሁለቱ አንዱ ከጎደለ ሀገር ሙሉ አትሆንም። አርበኛ ትውልድ ጥላቻን ይጸየፋል፤ ፍቅርን ያንጻል። መከፋፈልን ያስወግዳል፤ ትብብርን ያነግሣል። ፈተናዎችን ወደ ዕድል ቀይሮ ሀገራዊ ዕድገትን ያፋጥናል። ይህ ነው የዘመናችን አርበኛ ትውልድ።

አሁን ያሉብንን ፈተናዎች እንድንሻገርና እንደ ሀገር የምናልመውን ብልጽግና እውን እንድናደርግ ሀገራዊ የማምረት ዐቅማችንን በእጥፍ ለማሳደግ ልንረባረብ ይገባል። ለዚህ ደግሞ የሥራ ባህላችንን በመለወጥ፣ በጊዜ የለኝም ስሜት መሥራት ከሁላችንም ይጠበቃል። እያንዳንዱ እንቅስቃሴያችን በውጤት የታጀበ እንዲሆንና ካለ ውጤት የሚባክን ዕቅድም፣ ጊዜም፣ ሀብትም እንዳይኖረን በትኩረት መሥራት ይኖርብናል።

ከ10 ዓመት የልማት ትልሞቻችን፣ የመካከለኛውን ዘመን ዕቅድ ለመፈጸም የቀረን ጊዜ አጭር ነው። በመሆኑም በመፍጠርና በመፍጠን ለዕቅዶቻችን ስኬት መረባረብ ይኖርብናል። ባለፉት ዓመታት ጉዟችን ተግዳሮቶች ቢገጥሙንም፣ ሰፊ ዕድልም ከፊታችን አምጥተዋል። ከዚህ በላይ ከተጋንና ከተባበርን የላቀ ውጤት እንደምናስመዘግብ አረጋግጠናል።

ስለዚህ ካለፍንባቸው ጎዳናዎች በአስተውሎት መማር፤ ያመጣናቸውን ውጤቶች ማባዛትና ማሳደግ፤ ከዚያም ለቀጣይ ሩጫ ራስን ማዘጋጀት ይጠበቅብናል። እኛ ኢትዮጵያውያን ከተባበርንና ከተጋገዝን የማናሳካው ዕቅድ፣ የማንጽፈው ታሪክ እንደማይኖር የመጣንበት መንገድ ህያው ምስክር ነው። ይበልጥ በተባበርን፤ ይበልጥ በተደማመጥን እና በተከባበርን ጊዜ ሁሉ ታላላቅ ድሎችን እናሳካለን።

ከሠራነው ያልሠራነው ይበልጣል። ከተጠቀምንበት አቅማችን ገና ያልተጠቀምንበት ይልቃል። ትንንሽ ነገሮች የሚሸነፉት በትልልቅ ነገሮች ነው። ለሀገራችን ትልቅ እናስብ፤ በትልቁ እንሥራ፤ ትንንሽ ችግሮችን ለትልቁ ስንል እንለፋቸው፤ እንሸከማቸው። ትልቁን ግብ ስናሳካው ትንንሾቹ ችግሮች በራሳቸው ጊዜ ይሸነፋሉ። ስለ ሀገር ማሰብ፣ መንደርተኝነትን ያሸንፈዋል። ስለሁላችን እኩል ተጠቃሚነት ማሰብ፣ ግልኝነትን ድል ያደርገዋል። ለኢትዮጵያ ጥያቄዎች መታገል፣ የአካባቢ ጥያቄዎችን ይፈታቸዋል። ከዓለም ጋር መፎካከር፣ የወገንን ትብብር ያሳድገዋል።

ታላቅ፣ ለሁላችን የምትበቃ፤ ሁላችንንም በፍትሐዊነትና በእኩልነት የምትይዝ፣ ከሁላችን ድምር በላይ የሆነች ኅብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት ቆርጠን፣ ታጥቀንና ተባብረን እንነሣ።

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን አብዝቶ ይባርክ!

አመሰግናለሁ!

አዲስ ዘመን መስከረም 29/2016

አዲስ ዘመን መስከረም 29/2016

Recommended For You