ለሰላም ሁላችንም ልንሠራና የሚፈልገውንም ዋጋ ልንከፍል ይገባል!

ማልደው ከቤት ሲወጡ ‘ሰላም አውለኝ’፣ ውለውም አመሻሽ ወደ ቤት ሲገቡ ‘ሰላም አሳድረኝ’፣ ማለቱ በታላላቆች የተለመደ ተግባር ነው፡፡ ይሄ የፀሎት ገጽ ያለው የልመናና መልካም ነገርን የመሻት እሳቤ፣ የፍጡርና የፈጣሪ ግንኙነትን ብቻ አሳይቶ የሚያልፍ አይደለም፡፡ ይልቁንም የሰው ልጆች ስለ ሰላማቸው ምን ያህል የሚጨነቁ ስለመሆናቸው የሚናገር እውነት እንጂ፡፡

አንድ ሰው ማለዳ ከቤቱ ሊወጣ ሲሰናዳ ‘በሰላም ያሳደርከኝ አምላክ በሰላም አውለኝ’ ማለቱ የተለመደ ነው፡፡ ስለ ሰላማዊ አዳሩ ምስጋናን፤ ስለ መልካም ውሎው ልመናን ወደ አምላኩ ያቀርባል፡፡ በምስጋናና ልመና የተጀመረው ቀኑን አገባድዶ ምሽት ወደ ቤቱ ሲገባም፣ ‘በሰላም ያዋልከኝ አምላክ በሰላም አሳድረኝ’ ሲል፣ ተለምዷዊ የሆነውን ምስጋናም፣ ልመናም ወደ ፈጣሪው አንጋጥጦ ያቀርባል፡፡

ይሄ መልካም ልምድ፤ መልካም ተግባርም ነው፡፡ ምክንያቱም መልካሙን መመኘት፤ ሰላምን መሻት የሰው ልጆች ላቅ ያለ ተግባር ነው፡፡ ይሄን የሚያደርጉት ደግሞ፣ ‘እኔ የሰላም አምላክ ነኝ’ ያላቸውን ፈጣሪ እያሰቡ፤ ‘ሰላምን ፈልጉ’ የተባለውን ትዕዛዝም እያሰላሰሉ ሊሆን ይችላል፡፡ እዚህ ጋር ልብ ሊባል የሚችለው ጉዳይ ግን፣ እኛ የምንፈልጋት ሰላም እሷ እኛጋ እንድትገኝ ምን ያህል ራሳችንን አዘጋጅተናል? የሚለው ነው፡፡

በዚህ ጉዳይ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ብዙ ልንልም፤ ብዙ ሊባልልንም ይችላል፡፡ ምክንያቱም ሰላም ውለን ሰላም ለማደራችን ከፈጣሪ በብዙ የምንሻ ‘ሃይማኖተኛ ሕዝቦች’ የመሆናችንን ያህል፤ ሃይማኖታችን አብዝተን ገንዘባችን እንድናደርገው የሚያዝዘውን ሰላም ምን ያህል ከእኛ ዘንድ አኑረነዋል? የሚለው ጉዳይ በእጅጉ አጠያያቂ ስለሆነ ነው፡፡

እኛ አማኝ ሕዝቦች፤ እኛ ሰላምን አብዝተን የምንሻ ሕዝቦች፤ እኛ የሰላም አምላክ አለን የምንል ሕዝቦች፤ እኛ ስለ ፍቅርና ይቅርታ በብዙ ተምረናል የምንል ሕዝቦች፤… ለምን ሰላም ራቀን? ለምንስ እርስ በእርስ ተስማምቶ በፍቅር አብሮ ለመቆም እየተቸገርን መጣን? ለምንስ ነፍጥ ከመማዘዝ አዙሪታችን መውጣት ተሳነን?… የሚሉ አያሌ ጉዳዮችን አንስቶ ለመልሳቸው ማሰላሰል በራሱ በሰላምና በእኛ መካከል ስላለው እውነት ለመረዳት እድል ይፈጥራል፡፡

ለምሳሌ፣ በብዙ ዋጋ በ2010 ላይ የተገኘው ሀገራዊ ለውጥ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ብዙ የመልማት ብቻ ሳይሆን፤ የሰላምና ዴሞክራሲን ተስፋ ያጎናጸፈ ነበር፡፡ አብሮነትና አንድነታችንም በብዙ የተገለጸበትን ሁነትና ሁኔታም የፈጠረ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ይሄ ተስፋ፣ ይሄ ፈንጠዝያ፤ ይሄ ሕልምና ሕብረት በመካከላችን መብረር የጀመረችው የሰላም ርግብ ላይ ጥይት ከመተኮስ ሊገታን አልቻለም፡፡

ለውጡ ሁለት ዓመት ሳይሞላው እርስ በእርስ መናቆር ብቻ ሳይሆን መታኮስ ጀመርን፡፡ በሰሜኑ ከፍ ብሎ የተገለጠው የውስጣችን ጦርነት፤ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች በሚለኮሱ ትናንሽ እሳቶች ታጅቦ ሁለት ዓመታትን ዘለቀ፡፡ ይሄኛው በውይይት ታግዞ በሰላም ተቋጨ ሲባል ደግሞ፤ ሌላ እሳት በሌላኛው የሰሜኑ ክፍል ተለኮሰ፤ እንደተለመደውም በሌሎች ትናንሽ እሳቶች ታጅቦ እነሆ ዋጋ እያስከፈለን አሁንም አብሮን አለ፡፡

ይሄንኑ እሳት እያነደድንና እየነደድን ከትናንት ወደ ዛሬ ተሻግረናል፤ ዘመንንም በዘመን ተክተናል፤ የበጀት ዓመት ቀይረን፣ የሕዝብ እንደራሴዎችም ከእረፍት ማግስት ወደ መምከሪያ አዳራሻቸው ተመልሰዋል፡፡ በመጀመሪያው የመሰባሰብ ዕለታቸውም አንዱ ጉዳይ ተደርጎ እንደ አቅጣጫ ሲነሳ የነበረው ይሄው የሰላም ጉዳይ ሲሆን፤ ሰላም ከሁሉም በፊት ቅድሚያ ሊሰጠው፣ ችግሮች በንግግር ሊፈቱና ዜጎች በተለይም በጦርነት ወቅት እጅጉን ለችግር ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከሚደርስባቸው ችግርና ሰቆቃ እፎይታን እንዲያገኙ መሥራት እንደሚገባ ነው አጽንዖት የተሰጠው፡፡

ምክንያቱም ጦርነት አውዳሚ ነው፡፡ ሀብት ያወድማል፤ የሰው ልጆችን ያለ ልዩነት ይበላል፡፡ ሀገር እንድትደማ፤ ዜጎች እንዲጎሳቆሉ ያደርጋል፡፡ ወጣቶች ለልማት ሳይሆን ለጦርነት፤ አዛውንት፣ ሴቶች፣ ሕጻናትና አካል ጉዳተኞች ከፍ ላለ ሰብዓዊም አካላዊም፣ ሥነልቦናዊም ችግር ይዳረጉበታል፡፡

በጥቅሉ ጦርነት ለሀገር ውድቀትን፤ ለዜጎች ሰቆቃን የሚያስታቅፍ ክፉ ተግባር ነው፡፡ በአንጻሩ ሰላም ለሀገር ልዕልናና ክብርን፤ ለዜጎች እፎይታና ሰርቶ በመልጸግን፤ አጠቃላይ ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ሁሉን አቀፍ ብልጽግናን የሚያጎናጽፍ ኃይል ነው፡፡ ይሄን ኃይልና አቅም የተሸከመችው የሰላም ርግብ ደግሞ በጥይት አሩሮች ድምጽ ተረብሻ ማረፊያ ስታጣ ደጋግሞ ተስተውሏል፡፡

እናም ይህች የሰላም ርግብ በመካከላችን ያለ ስጋት እንድታርፍ ማድረግ ከእኛ ከሁላችንም ኢትዮጵያውያን የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡ ይህንን እውን ለማድረግ ደግሞ ስለ ሰላም መናገር ብቻ አይበቃም፤ ስለ ሰላም መመኘት ብቻ ሰላምን አያመጣም፤ ስለ ሰላም ፈጣሪን መማጸን ብቻውን በሰላም ወጥቶ ለመግባት ዋስትና አይሆንም። ምኞትም፣ ልመናም፣ ጸሎትም የልብ ንጽሕናንና መሻትን፤ በመሻት ልክ ደግሞ ሆኖ መገኘትና ማድረግን አብዝተው ይፈልጋሉ፡፡ በመሆኑም ዛሬ ላይ አብዝተን ስለምንሻው ለሰላም ሁላችንም ልንሠራ፣ የሚፈልገውንም ዋጋ ልንከፍል ይገባል!

አዲስ ዘመን መስከረም 29/2016

Recommended For You