በዚህ ወቅት የአትክልት ዋጋ መናርም ሆነ የጥራት መጓደል በተለየ ሁኔታ ሸማቹን እያማረረው ነው፡፡ በተለይ የሽንኩርት ዋጋ የማይቀመስ ሆኗል፡፡
ቀይ ሽንኩርት በአዲስ አበባ ከተማ ለሸማቹ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርብ ተደርጎ በተመቻቸው በእሁድ ገበያ አንድ ኪሎ ከ70 እስከ 80 ብር፣ ነጋዴዎች ደግሞ ከ120 እስከ 130ብር በኪሎ እየተሸጠ ነው። ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ምርቱ ከሚገኝበት ስፍራ በኪሎ እስከ 75 ብር እየቀረበ እንደሆነም መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ለቀይ ሽንኩርት ዋጋ መናርም ሆነ የጥራት መጓደል በዋናነት በክረምቱ ዝናብ ውሃ መብዛት እንደምክንያት የሚነሳ እንደሆነ ቢጠቀስም ሰው ሠራሽና የተለያዩ ችግሮች መኖራቸው ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ይገልጻሉ፡፡
በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የሰጡን የመቂ ባቱ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾች ኅብረት ሥራ ዩኒየን ሥራ አስኪያጅ አቶ ኩምሣ ጉዲና እንዳብራሩት፤ ቀይ ሽንኩርት አሁን እንደተከሰተው የዋጋ መናር የተጋነነ ባይሆንም በክረምት ወቅት የሽንኩርት ዋጋ ከወትሮ ው ጊዜ ይጨምራል፡፡
አንዱ ምክንያት ደግሞ የክረምት ወቅት ለሽንኩርት ልማት ምቹ አለመሆኑ ነው፡፡ሽንኩርት ቶሎ ይበሰብሳል፤ ፈንገስ በሚባል በሽታም ይጠቃል፡፡ በዚህ ምክንያት አልሚዎች በክረምት ቀይ ሽንኩርትን ለማምረት አይነሳሱም ፤ምርቱም ይቀንሳል፡፡
ሌላው ለምርቱ መቀነስ ምክንያት የሆነው ደግሞ አልሚዎች በክረምቱ መሬታቸውን ለጤፍ፣ ለበቆሎ፣ ለስንዴና ለተለያየ የሰብል ልማት ማዋላቸው ነው። ክረምት ሲመጣ በሽንኩርት ላይ የጥራት መጓደል ይታያል፤ ይህም ውሃ ከመብዛት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ አሁን ላይ ወደ ገበያ እየገባ ያለውም ውሃ በማይተኛበት መሬት ላይ የተመረተ ሽንኩርት ነው፡፡
የ2015 የክረምት ወቅት ዝናብ በከፍተኛ ሁኔታ በመብዛቱ ለምርት መቀነስ በከፍተኛ ሁኔታ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ዝናቡን ተቋቁመውና ማሣቸው ላይ ውሃ የማይተኛ አርሶአደሮች አምርተው ወደ ገበያ ባቀረቡት ምርት ላይ ደግሞ ደላሎች ጣልቃ በመግባት ችግሩን አባብሰውታል፡፡ የአየርፀባይና ሰው ሠራሽ ችግሮች ለዋጋ መናር ድርሻ እንደነበራቸው አቶ ኩምሣ ያስረዳሉ፡፡
በቅርብ ጊዜ እራሱን እያስተዋወቀ የሚገኝ አንድ የገበያ ማዕከልም በቀጥታ ከአርሶአደሩ ተቀብሎ አንዱን ኪሎ በ25 ብር እንደሚያቀርብ በማስታወቂያ እያስነገረ ነው፡፡ ድጅቱ አቀርበዋለሁ ያለው ዋጋ አሁን በአብዛኛው በገበያው እየቀረበ ካለው ዋጋ ጋር ሰፊ የሆነ ልዩነት መፈጠሩ በሸማቹ ዘንድ እያነጋገረ ነው፡፡ስለዚህም ሁኔታ አቶ ኩምሣ በሰጡት ማብራሪያ በቦታው ተገኝተው ባያረጋግጡም የድርጅቱ ማስታወቂያ ከእውነት የራቀ ነው ብለዋል፡፡
በከፍተኛ ሁኔታ ሽንኩርት አምራች በሆነው ስምጥ ሸለቆ አካባቢ ከገበሬ ማሣ ላይ ባለፈው ረቡዕ አንድ ኪሎ እስከ 75 ብር ነው የተሸጠው፡፡ አከፋፋዩና ቸርቻሪው ጋር ሲደርስ ደግሞ ዋጋው ይጨምራል፡፡ ማስታወቂያ ያስነገረው ድርጅት ከየት እያስመጣ እያቀረበ እንደሆነም አብሮ ግልጽ ቢያደርግ እውነታውን ማረጋገጥ ይቻል እንደነበር ነው የገለጹት፡፡
እንደ አቶ ኩምሣ ማብራሪያ ሽንኩርት ከዚህ በኋላ በዋጋም በጥራትም መሻሻል እንደሚያሳይ ይጠበቃል፡፡ እስከ ዛሬ ባለው ተሞክሮ ክረምቱ ሲያበቃና መሬቱን ለሰብልና ለተለያየ ልማት ያዋለው አርሶአደር ምርቱን ከሰበሰበ በኋላ ሽንኩርትን ጨምሮ የተለያዩ አትክልቶችንና ፍራፍሬዎች ወደ ማልማት ፊቱን ስለሚያዞር ምርቱም ይጨምራል፡፡
የክረምቱ መውጣትም ለምርቱ ጥራት መሻሻል ያግዛል። ሸማቹም በዋጋና በጥራት ተጠቃሚ ይሆናል። እንዲያውም በተቃራኒው በበጋው በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚመረት ገበያው ወርዶ አርሶአደሩ በገቢ ተጠቃሚ የማይሆንበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ነው ከዚህ ቀደም የነበሩ ተሞክሮዎች የሚያሳዩት፡፡
ዩኒየኑ የልማት ወቅቶችን ተከትሎ ለአባላቱ ዘርና የተለያዩ የግብርና ግብአቶችን በማቅረብና የአባላቱን ጥያቄ መሠረት ያደረጉ ምላሾችን በመስጠት እያገዘ መሆኑን የገለጹት አቶ ኩምሣ በሽታ የሚቋቋም የሽንኩርት ዘር በማቅረብ ምርታማነትን ለማሳደግ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ብለዋል፡፡
ዩኒየኑ በገበያ ትስስር በኩልም ሥራዎችን በመሥራት በተለይም የገበያ ትስስር ከፈጠረባቸው ዩኒቨርሲቲዎችና የኢትዮጵያ አየርመንገድ ይጠቀሳል፡፡ በተለይም ለኢትዮጵያ አየርመንገድ ሽንኩርት በማቅረብ የረጅም ጊዜ ደንበኛ መሆኑንና በዚህ ረገድም የውጭ ምንዛሪን በማስቀረት አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሆነ አስረድተዋል።
ዩኒየኑ ከ1994 ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ 153 መሠረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበራትንና በነዚህ ማኅበራትም ከ9ሺ በላይ አርሶአደር አባላትን ይዞ በዚህ ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንና በአብዛኛውም የአትክልት ልማት እንደሚያከናውን የነገሩን አቶ ኩምሣ አርሶአደሩ ልማቱን በማሳደግ ተጠቃሚ ለመሆን ፍላጎቱ ከፍተኛ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
አቶ ኩምሣ በዘርፉ ተግዳሮት ናቸው ያሏቸውንም እንዳነሱት ለልማቱ የሚውሉ ግብአቶች ዋጋ እየናረ መምጣት ነው፡፡ በየጊዜው እየተስፋፋ የመጣውን በሽታ ለመቋቋም ኬሚካሎች ያስፈልጋሉ፡፡ የኬሚካሎች ዋጋ መናር አልሚውን አርሶአደር እየፈተነው ነው፡፡ ዩኒየኑ ኬሚካሎች በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርብበትን ሁኔታ በማመቻቸት በተቻለ መጠን ጥረት እያደረገ ቢሆንም በተቃራኒው ከውጭ ምንዛሬ ጋር በተያያዘ በምርት ላይ የዋጋ ጭማሪ ማስከተሉን ተናግረዋል፡፡
ሌላው ዘርፉን እየፈተነው ያለው አጋጣሚዎችን ተጠቅሞ በመካከል ላይ ሆኖ የዋጋ መናርን እያስከተ ያለው ደላላ ጣልቃ ገብነት ነው፡፡ የምርት እጥረት ሲያጋጥም ችግሩን የበለጠ እያባባሰው እንደሆነ ያመለከቱት አቶ ኩምሣ ደላሎች ከመካከል ወጥተው አልሚውና ሸማቹ በቀጥታ የሚገናኙበት መንገድ እንዲፈጠር መንግሥት በዚህ በኩል በትኩረት መሥራት ይኖርበታል ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ኩምሣ ማብራሪያ የዩኒየኑ አባላት ሽንኩርትን ጨምሮ የተለያዩ አትክልቶችን በአመት ከአንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ የማምረት አቅም አላቸው፡፡
የሽንኩርት ዘር ከውጭ በማስመጣት ለአልሚዎች በማሰራጨት ላይ ከሚገኙ ዘር አከፋፋይ ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው ማርቆስ ዘር አስመጪ ድርጅት ውስጥ ባለሙያ የሆነችው ቅድስት ዓለሙ በበኩሏ እንዳስረዳችው፤ ቀይ ሽንኩርት በባህሪው እርጥበትም ቅዝቃዜም የአየር ፀባይ የሚፈልግ ቢሆንም ለምርት ሊደርስ ሲል ግን ውሃ እንደማይፈልግ አስረድታለች፡፡ በዚህ ወቅት ክረምቱ ለሽንኩርት ምርት ማነስና ለጥራት መጓደል አንዱ ምክንያት እንደሆነና ካለፈው አመት ጀምሮ የሽንኩርት ልማት መረበሹን ጠቅሳለች፡፡
ባለሙያዋ እንዳስረዳችው ሽንኩርት በመስኖ በሚለማበት ወቅት ከተተከለ ከ85ኛው ቀናት በኋላ ወደ ማሳው የሚለቀቀው ውሃ መቋረጥ ይኖርበታል፡፡በዝናብ ወቅት ግን ውሃውን ማቋረጥ የሚቻልበት ዕድል ባለመኖሩ ከመበላሸት ማዳን አይቻልም፡፡
የነበረው የዝናብ ወቅት ሽንኩርት ከሚፈልገው የውሃ መጠን በላይ በመሆኑ ምርታማነቱ ላይ ተጽእኖ መፈጠሩን ገልፃለች፡፡ ይህም ለዋጋ ንረት እንደ አንድ ምክንያት ሆኖ ሰው ሠራሽ ችግር ተጨምሮበት የአንድ ኪሎ ሽንኩርት በተጋነነ ዋጋ እንዲሸጥ ሆኗል፡፡
በተጨማሪም የተመረጠ ዘር መጠቀም ላይ ክፍተት መኖሩንም ትገልጻለች፡፡ሽንኩርት የሚያመርተው አርሶአደር በገንዘብ አቅም ማነስ ይሁን ወይንም በግንዛቤ ክፍተት አብዛኛው ጥሩ ምርት የሚሰጥና በሽታ መቋቋም የሚችል ዝርያን ከመጠቀም ይልቅ በዋጋ አነስተኛ የሆነ ዝርያን መጠቀም ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ገልጻለች፡፡
ድርጅታቸውም ከውጭ ለሚያስመጣው ዘር በቂ የሆነ የውጭ ምንዛሪ እንደማያገኝና ይህም ለምርታማነት የራሱ አሉታዊ ጎን እንዳለው በመጥቀስ መንግሥት ለዘርፉ ችግር ትኩረት ቢሰጥ ችግሩ ሊፈታ እንደሚችል አስረድታለች፡፡
እንደ ባለሙያዋ ገለጻ፤ በአሁኑ ጊዜ ጥሩ ዝርያ ተብሎ የሚመረጠው የተዳቀለ (ኃይብሪድ) የተባለው የሽንኩርት ዘር ነው፡፡ በሽታን ስለሚቋቋምና ምርታማነቱም ጥሩ በመሆኑ ይመረጣል፡፡ በዚህም በዋጋ ከሌሎች ዝርያዎች ከፍ ይላል፡፡ ድርጅቱ በዘር ላይ የተጋነነ የዋጋ ንረትን ለመከላከል በተቻለ መጠን አልሚዎች በቀጥታ ከድርጅቱ ዘር እንዲያገኙ የዘር መሸጫ ቦታዎችን ምቹ ለማድረግ ጥረት አድርጓል፡፡ ድርጅቱ አቅርቦቱን የሚወስነው የገበያ ፍላጎትን በማጥናት ነው፡፡ ጥቅምት ወር የሽንኩርት ልማት በስፋት የሚካሄድበት ወቅት እንደሆነና ከዚህ በኋላም ዋጋው እየወረደ እንደሚሄድም ቅድስት ገልጻለች፡፡
የሽንኩርት የዋጋ መናርና የጥራት መጓደልን በተመለከተ በግብርና ሚኒስቴር በሆርቲካልቸር ልማት ሥራ አስፈጻሚ ሥር የአትክልት ዴስክ ኃላፊ ሰለሞን ከበደ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የሽንኩርት ልማት በኢትዮጵያ በስፋት የሚከናወነው በስምጥ ሸለቆዎች (ሪፍት ቫሊ)ሲሆን፣ ዝዋይ፣ መቂ፣ ባቱ ወረታ አካባቢዎችን ይሸፍናል።
አካባቢዎቹ የውሃ መገኛ ከመሆናቸው በተጨማሪ ለሽንኩርት ልማት ተስማሚ የአየር ፀባይ አላቸው፡፡ በተጨማሪም ከአማራና ከደቡብ ክልሎችም ተመርቶ ወደ መሃል ሀገርና የተለያዩ ገበያዎች ይቀርባል፡፡ በአመትም እስከ ሦስት ጊዜ ማምረት የሚቻልበት ዕድል ቢኖርም ክረምት ላይ ግን የማምረቱ ሁኔታ ይቀንሳል፡፡በክረምት ሽንኩርት በበሽታ የመጠቃት ዕድሉ ሰፊ ስለ ሚሆን አምራቹ አይበረታታም፡፡
በክረምቱ አነስተኛ ምርት በመኖሩ ፍላጎትና አቅርቦት ባለመጣጣሙ የዋጋ ንረት ይከሰታል፡፡ በተለይ ደግሞ መስከረም ወር በዓላት ስለሚበዛ ፍጆታውም ይጨምራል። ይህ አጋጣሚ ደግሞ ለደላሎች ምቹ ስለሚሆን ጫናውን ከፍ ያደርገዋል፡፡
ከጥቂት ጊዜያቶች ወዲህ የሽንኩርት ምርት እየቀነሰ መምጣቱን የገለጹት አቶ ሰለሞን፤ ለዚህም የአየር ፀባይና ሰው ሠራሽ ችግሮች እንደምክንያት ቢቀርቡም የፀጥታ መደፍረስም ተጨማሪ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል። ተግዳሮቶቹ የተለያዩ በመሆናቸው በጥናት ለይቶ መፍትሔ ማስቀመጥ እንደሚጠይቅም አመልክተዋል፡፡
እንደ አቶ ሰለሞን ማብራሪያ ሚኒስቴር መሥሪያቤቱ በክረምት ወቅት ምርቱ በሌሎች ሰብሎችና ተክሎች እንደሚሸፈን ደርሶበታል፡፡ በክረምት ጊዜ የሚስተዋለውን የምርት ማነስ ችግር ለመፍታት ውሃ መቋቋም የሚችሉ ዝርያዎች ማቅረብ እንደሚያስፈልግ ግንዛቤ ተይዟል፡፡
ዘላቂ መፍትሔዎችን ከመፈለግ ጎን ለጎን ሚኒስቴር መሥሪያቤቱ በቀጣይ ጊዜያቶች በበጋው የሆርቲካልቸር ልማት ምዕራፍ ዝግጅት በማድረግ ወደ ሥራ ገብቷል።ጥቅምት፣ ኅዳር፣ ታኅሣሥ የመጀመሪያው የምዕራፍ ዝግጅት ወቅቶች ሲሆኑ፣ በዚህ መልኩ እስከ ግንቦት ድረስ ባሉት ጊዜያቶች ሥራዎች ይሠራሉ፡፡ በዚህ የዝግጅት ምዕራፍ ከሚከናወነው ሥራ አንዱ የዘር አቅርቦትና ሥልጠና መሥጠት ነው፡፡ በዚህ መልኩ እስከ ግንቦት ወር ድረስ ባሉት ጊዜያቶች ሥራዎች ይሠራሉ፡፡
የሚኒስቴር መሥሪያቤቱ ዋና ተግባርና ተልዕኮም ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር የሚያስችሉ ተግባራትን ማከናወን ነው፡፡ በመሆኑም በልማቱ ላይ ለተሰማሩ ሁሉ ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ከክልሎች ጋር ይሠራል፡፡ በግል የሚንቀሳቀሱትንም ይደርሳል፡፡
ድጋፉም የዘር ግብአት የሚያቀርቡ ኩባንያዎች ዘሩን በአግባቡ እንዲያቀርቡ በማድረግ ችግሮች ሲያጋጥሙ ለመፍታት ጥረት ያደርጋል፡፡ በኩታገጠምም ምርቱን በስፋት ለማምረት ጥረት እንደሚደረግም ተናግረዋል፡፡
የቀይ ሽንኩርት ዝርያዎች በሀገር ውስጥና ከውጭ በግዥ የሚገቡ ሲሆን፣ በሀገር ውስጥ በምርምር እንዲቀርቡ በሚደረገው ጥረት ከመልካሳ ግብርና ምርምር ዝርያዎች ወጥተው ይሰራጫሉ፡፡ ዝርያዎቹ የተለያዩ ሲሆኑ፣ በስፋት የሚታወቁት እስከ አምስት የሚሆኑ ናቸው፡፡
ቀይ ሽንኩርትን ጨምሮ በሆርቲካልቸር እየተከናወነ ያለው ልማት እንደሀገር አበረታች መሆኑንና እያንዳንዱ ዋጋም በሌሎች ሀገራት ውስጥ እየተሸጠ ካለው ጋር በንጽጽር ሲታይ በኢትዮጵያ የአትክልት ዋጋ የተሻለ እንደሆነ አቶ ሰለሞን ይገልጻሉ፡፡
ወቅትን ተከትሎ ለሚፈጠር ችግርና አጋጣሚን ተጠቅመው ገበያው ላይ ንረት የሚፈጥሩትን ደላሎች ከመካከል ለማስወጣት ሰፊ ሥራ እንደሚጠይቅና ለዚህም መንግሥትና ባለድርሻ አካላት በጋራ በመንቀሳቀስ ለችግሩ የጋራ መፍትሔ መፈለግ ይኖርባቸዋል ሲሉ በጉዳዩ ላይ ሃሳባቸውን የሰጡት ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን መስከረም 29/2016