በምገባ ተቋማት ዙሪያ የከተማ አስተዳደሩና የባለሀብቶች በጎ ተግባር እውቅና ሊሰጠው ይገባል !

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ 102 ሺህ ዜጎች በቀን አንድ ጊዜ ራሳቸውን መመገብ እንደማይችሉ የከተማ አስተዳደሩ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ በ2014 ዓ.ም ባካሄደው ጥናት ማስታወቁ ይታወሳል። ከሁለት ዓመት ወዲህም ቢሆን ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ አዲስ አበባ የመጡ ችግረኞች በመኖራቸው ቁጥሩ ከዚህ ከፍ እንደሚል መገመት አይከብድም ፡፡

በየመንገዱ የምናያቸው ረሃብ ያጠወለጋቸው አዛውንቶችና ሕጻናት ፤ በየገባንባቸው ምግብ ቤቶች በር ላይ የምናስተውላቸው ፍርፋሪ የሚቃርሙ ወገኖች ስናይ ችግሩ የቱን ያህል የገነገነ እንደሆነ ለማወቅ አስቸጋሪ አይሆንም፡፡

ይህን ችግር ለመቅረፍ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል። በተለይም ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ባለሀብቶችን በማሳተፍ እያስገነባቸው ያሉ የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከላት ተጠቃሽ ናቸው።

እነዚህ ተቋማት በቀን አንድ ጊዜ መመገብ የማይችሉ የበርካታ አቅመ ደካሞችን ችግር እያቃለሉ ስለመሆናቸው በተጨባጭ እያየነው ያለው በጎ ተግባር ነው፡፡ ቀጣይነቱም ለብዙዎች እፎይታ እንደሚሆን ይታመናል።

ከተጀመሩ እስከ አሁን በእነዚህ ሰው ተኮር ሥራዎች ተጠቃሚ የሆኑ እናቶች የሚሰጡትን አስተያየት መስማት አንጀት ያላውሳል፡፡ በተደረገላቸው በጎ ተግባር የሚሰማቸው የደስታ ሲቃ፣ ደስታቸውን ለመግለጽ ፣ ለምስጋና ቃላት ሲያጥራቸው ማየት ሆድ ያባባል፡፡

ይህ የከተማ አስተዳደሩ ሥራ የሰው ሕይወት ላይ ነው የተሠራ ፤ ሕይወት የማዳን የመታደግ ሥራ ከመሆኑ አንጻር እየቀረበለት ያለው ምስጋና ተገቢው ስለመሆኑ ብዙም ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም ። ከዚህ ይልቅ ከፍ ያለ እውቅና እና ከበሬታ ሊሰጠው የሚገባ ነው።

በርግጥ ይህን የከተማ አስተዳደሩን በጎ ተግባር ለማመስገን የግድ የተራበ መሆንን አይጠይቅም ፤ አዕምሮው ጤናማ የሆነ ሰው እነዚህ ዜጎቻችን በማእከላቱ ያገኙት እፎይታ የቱን ያህል እንደሆነ ለመገንዘብ አይከብደውም። የእነዚህን ሰዎች ችግር ለመረዳት ጤነኛ ህሊና ያለው ሰው መሆን በቂ ነው ።

ከሰው ልጅ መሠረታዊ ፍላጎቶች ሁሉ ቀዳሚው ምግብ ነው፡፡ ሌላው ቀጥሎ የሚመጣ ነው፡፡ ልብስ በሉት መጠለያ ከምግብ በኋላ የሚመጡ ናቸው፡፡ ጎዳና ላይ እንኳን ለማደር ዋናው የሚበላ ሲኖር ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የከተማ አስተዳደሩ ሥራ ከፍ ያለ እውቅና ሊሰጠው የሚገባ ነው፡፡

ይህ የከተማ አስተዳደሩ ሥራ ሊደነቅ የሚገባው የዛሬዎቹን ሰዎች በመመገቡ ብቻ አይደለም፡፡ ታሪክ በመፍጠሩ ነው፤ እንዲህ አይነት ሥራዎች እንዲኖሩ አዲስ ሰዋዊ ሥራ በማስተዋወቁ ነው፡፡ አዲስ አበባ ይህን ሰዋዊ ሥራ ስትጀምር በታሪክ የመጀመሪያዋ ነው፡፡ ከዚህ በፊት እንዲህ አይነት ነፃ የምገባ ማዕከል አልታየም፡፡ የትምህርት ቤት የተማሪዎች ምግባም አልነበረም፡፡ እነዚህ ሰው ተኮር ሥራዎች ሰው ይፈጥራሉ፡፡

ይህንን የከተማ አስተዳደሩን እና የባለሀብቶችን ሰዋዊ ሥራ ያዩ ሌሎች ባለሀብቶችም እና ታዋቂ ሰዎች እንዲህ አይነቱን በጎ ነገር ለማስቀጠል ይነሳሳሉ፤ ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡ ይሄም የከተማ አስተዳደሩን የበጎ አድራጎት ሥራ ተደራነሽት እንዲሰፋ፣ እንዲያድግ ያደርገዋል ፡፡ በዚህም በምገባ ማዕከላት ውስጥ ሁሉም ዝቅተኛ ኑሮ ያላቸው ዜጎች ገበተው መመገብ የሚችሉበትን እድል ይፈጥሯል ፡፡

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕ መድ (ዶ/ር) በተገኙበት በቅርቡ ለአዲስ ዓመት ስጦታ በተመረቀው 20ኛው የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል ብቻ ከ500 በላይ ለሚሆኑ አቅመ ደካሞች የተመጣጠነ ምግብ እንደሚያቀርብ ተነግሯል፡፡ በአጠቃላይ በአዲስ አበባ ከተማ ባሉ 20 የምገባ ማዕከላት ከ35 ሺህ በላይ ወገኖች አገልግሎት እያገኙ ነው።

በከተማ አስተዳደሩ “ የፕሮጀክቶች ሁሉ ሜጋ ፕሮጀክት” ተብሎ ስያሜ የተሰጠው የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከላት ፤ በእርግጥም የፕሮጀክቶች ሁሉ ሜጋ ፕሮጀክት መባሉ የሚያንሰው አይደለም። ዜጎች የትኛውንም ግዙፍ ፕሮጀክት ማየት የሚችሉትና ከዚያ ፕሮጀክት ተጠቃሚ የሚሆኑት መጀመሪያ መመገብ ሲችሉ ነው፡፡ ለእነዚህ በቀን አንድ ጊዜ መመገብ ለማይችሉ ዜጎች ከዚህ የምገባ ማዕከል በላይ ምንም አይነት ሜጋ ፕሮጀክት ሊኖር አይችልም፡፡

ማዕከላቱን ወደ ሥራ ለማስገባት ሲታቀድ፤ መጀመሪያ የተደረገው ከሆቴሎች ምግብ እንዲመጣ ማድረግ እንደነበር ይታወሳል፣ በኋላ ግን በኢትዮጵያውያን ተባባሪነት በምገባ ማዕከሉ ምግብ ማዘጋጀት ተቻለ፡፡ አሁንም ባለሀብቶቻችን ካሁኑ በተሻለ መተባበር ከቻሉ ይህ የከተማ አስተዳደሩ የበጎ አድራጎት ሥራ ከዚህም በላይ ሊያድግ እንደሚችል ተስፋ ሰጪ ነው፡፡

ይህ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰው ተኮር ሥራ ለእነዚህ ወገኖች ይደርስ ዘንድ የባለሀብቶች ሚና ቀላል አይደለም፡፡ እነዚህ ባለሀብቶች ለእነዚህ በቀን አንድ ጊዜ እንኳን መመገብ ለማይችሉ ወገኖች ደርሰውላቸዋል። ባለሀብቶቹ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ላሉ ወገኖች እንዲህ አይነት አርአያነት ማስጀመራቸው በታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ አለው፡፡ ምናልባትም ይሄ ነገር ባህልና ልማድ ይሆናል ማለት ነው፡፡ አንድ ባለሀብት ለወገኖቹ በዚህ አይነት መንገድ መድረስ እንደሚችል አሳይተዋል። ይህን ያስተዋሉና የሰሙ ባለሀብቶች የዚህ በጎ ተግባር አካል ለመሆን ይመኛሉ ማለት ነው፡፡

እነዚህ ባለሀብቶች ነገ በየትኛውም መድረክ ላይ ‹‹ሀብቴ ለሀገር ነው›› ብለው ቢናገሩ ያምርባቸዋል፡፡ ምንም እንኳን የሚያስገነቧቸው ሕንጻዎችም ሆነ ትልልቅ የንግድ ዘርፎችም የሀገር ሀብት ቢሆኑም፤ የበለጠ ግን የዕለት ጉርስ ያጡ ወገኖችን በእንዲህ አይነት መንገድ መድረስ ደግሞ የበለጠ የሀገር ውለታ ነው፡፡ ምክንያቱም ምንም ትርፍ የሌለው ለበጎነት ብቻ ተብሎ የሚደረግ ነው፡፡ በእነዚያ ትልልቅ የንግድ ዘርፎቻቸው መገልገል የማይችለውን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የህብረተሰብ ክፍልም ደረሱለት ማለት ነው፡፡ ወዲህ ደግሞ የቀጣይ መልካም ዜጋ እየፈጠሩ ነው ማለት ነው። በትምህርት ቤቶች ግንባታም ድጋፍ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

ይህ የከተማ አስተዳደሩ ሰው ተኮር ሥራ ቀደም ሲል በትምህርት ቤቶች የተጀመረው የተማሪዎች ምገባ ባዶ ምሳ ዕቃ ይዘው ይሄዱ የነበሩ ልጆች ዛሬ በነፃነት እንዲማሩ አስችሏዋል፡፡ ልጆቹ ትኩረታቸውን ትምህርታቸው ላይ እንዲያተኩሩ አድርጓቸዋል፡፡ ይህን አሠራር እናቶች ሲመርቁ ቆይተዋል፡፡

አሁን ደግሞ እነሆ በቀን አንዴ እንኳን መመገብ የማይችሉ እንዲመገቡ የሚያደርጉ የምገባ ማዕከላት እየተገነቡ ወደ ሥራ መግባታቸው እውነታ ለብዙዎች እፎይታ ፈጥሯል። ይህ የከተማ አስተዳደርና የባለሀብቶች በጎ ተግባር ሊመሰገን፣ ሊበረታታ እና እውቅና ሊሰጠው ይገባል!።

ሚሊዮን ሺበሺ

አዲስ ዘመን መስከረም 29/2016

Recommended For You