በሀገሪቱ የለውጥ መንፈስ በዜጎች ሕይወት ውስጥ አቅም ገዝቶ መንቀሳቀስ ከጀመረበት ጊዜያት አንስቶ የለውጥ ባህሪ ነውና ሀገር እንደ ሀገር ብዙ ዋጋ ለመክፈል ተገዳለች። ለቀደመው የፖለቲካ ሥርዓት አልገዛም ከማለት ጀምሮ ፣ መላው ሕዝባችን የለውጡ ተስፈኛ በመሆን ከፍ ያለ መስዋዕትነት የጠየቁ ታሪካዊ ክስተቶችን ለማስተናገድ የተገደደባቸው ሁኔታዎች ብዙ ናቸው።
እንደሀገር ቀደም ባሉት ጊዜያት ከነበሩን የለውጥ ተሞክሮዎቻችን በመነሳት ፣ ለውጡን ያልተገባ ዋጋ መክፈያ ሳይሆን የተሻለ ማትረፊያ ለማድረግ በለውጥ ኃይሉ በኩል የተደረጉ ጥረቶች ፣ ይዘናቸው ከመጣናቸው የኃይል እና የሴራ ፖለቲካ ምክንያት ብዙ ፈተናዎችን አስተናግዷል።
በአንድ በኩል የለውጡ መንፈስ ያልጣማቸው ፣ ራሳቸውን አልፋና ኦሜጋ አድርገው የሚቆጥሩ ኃይሎች፤ በሌላ በኩል በየዘመኑ ሀገራዊ ክፍተቶችን አነፍንፈው የክፍተቱ ተጠቃሚ ለመሆን የሚጥሩ ታሪካዊ ጠላቶቻችን በጋራ ሆነው በፈጠሩብን ሀገራዊ የህልውና ስጋት ሳንወድ በግድ ወዳልተፈለገ የግጭትና የጦርነት አዙሪት ተመልሰን ልንገባ ተገደናል።
በዚህም በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችን ለሞት እና ለአካል ጉድለት ፣በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ለስደትና ለመፈናቀል፣ ለረሀብና ለእርዛት ፣ ሌሎች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደግሞ ለስነልቦና ቀውስ የተዳረጉበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ችግሩም ሆነ ከችግሩ በስተጀርባ ያሉ ገዥ ምክንያቶች ምንነት ለመላው ዓለም ያልተሰወረ፤ የአደባባይ ምስጢር ነው።
ይህ በሆነበት ሁኔታ አንዳንድ የዓለም አቀፍ ኅብረተሰብ ክፍሎች፤ የተሻሉ ነገዎችን አምጦ ለማዋለድ ባደረገው ጥረት ባልተገቡ ምክንያቶች ያልተገቡ ዋጋዎችን ለመክፈል ለተገደደው ሕዝባችን ፈጥኖ ከመድረስ ይልቅ የተስፋ ቀናቶችን ባልተገቡ ምክንያቶች እያበከነበት ይገኛል። ይህ ድርጊቱም ከሁሉም ይልቅ ከሰብዓዊነት አንጻር ጥልቅ ጥያቄን ሊያስነሳ የሚችል ነው።
አሁን በችግር ውስጥ ያለው ሕዝባችን የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አንድ ነው፤ ከችግሩ መውጣት እንዲችል የሚያስችለውን የትኛውንም አይነት ድጋፍ የማግኘት የሞራል ብቻ ሳይሆን የሕግም መብት አለው። ይህንን መብቱን በማስከበር ሂደት ውስጥም የሀገራት መንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ያላቸው ኃላፊነት መተኪያ የሌለው ነው።
በተለይም እንደ የዓለም የምግብ ድርጅትን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ራሳቸውን ከየትኛውም የፖለቲካ ተጽእኖ ነጻ በማድረግ የዕለት እርዳታ ለሚፈልጉ ዜጎቻችን ተገቢውን ድጋፍ የማድረግ ግዴታ አለባቸው። ይህንን ኃላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው ለሚፈጠረው ሰብአዊ ቀውስ ተጠያቂ ሊያደርጉት የሚችል አካልም ሊኖር አይችልም
በእያንዳንዷ ችግር ዙሪያ ተጠያቂነትን ለመፍጠር የሚደረግ ጥረት የርዳታ ተቋማቱ ኃላፊነት ሳይሆን ለዚህ የተቋቋሙ ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊነት ነው። እንዲህ ዓይነቱን የማጣራት ሂደት የችግሩ ባለቤት ያልሆነውን ሕዝብ በመቅጣት ውጤታማ ማድረግ አይቻልም። ውጤታማ አደርጋለሁ ብሎ መንቀሳቀስም ከተቋማዊ ስልጣንና ኃላፊነት በአደባባይ ማፈንገጥ ነው።
ይህን ዓለም አቀፋዊ እውነታ ተሳቢ በማድረግም ዓለም አቀፍ የምግብ ድርጅትን ጨምሮ፤ ራሳቸውን ዓለም አቀፍ የርዳታ ድርጅት አድርገው በመሰየም የሚንቀሳቀሱ ተቋማት ካለፈቃዱ በከፋ ችግር ውስጥ ለሚገኛው ሕዝብ በትንሹ የዕለት ደራሽ እርዳታዎችን በማቅረብ ከፊቱ ከሚጠብቀው አደጋ መታደግ ይጠበቅባቸዋል።
ይህን ላለማድረግ የሚቀርብ የትኛውም ዓይነት ምክንያት በተቋማቱ ላይ የሰብአዊነት ተጠያቂነት የሚያመጣና የሞራልም ሆነ የሕግ ተጠያቂነትን የሚያስከትል ይሆናል!
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 28 ቀን 2016 ዓ.ም