ወቅቱ አውሮፓውያን አፍሪካን በቀኝ ግዛት ስር ለማድረግ ዓይናቸውን ወደ አህጉሪቱ ያማተሩበት የታሪክ ምዕራፍ ነበር። በወቅቱ አብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት በአውሮፓውያን እጅ ሲወድቁ፣ ኢትዮጵያን ለመውረር ቀይ ባሕርን ያቋረጠችው ጣሊያን ግን ዕቅዷ ሳይሳካላት ቀርቷል።
በ1888 አ.ም (ከ1895 እስከ 1896 እ.ኤ.አ.) ዓድዋ ላይ የጣሊያንን ጦር የገጠመው የኢትዮጵያ ሰራዊት ድል ማስመዝገቡ፣ ድሉ የአፍሪካ ብሎም የመላው ዓለም ጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ድል መሆኑ ሲታወቅ፤ ጣሊያን የሽንፈት ፅዋ ተጎንጭታ የኢትዮጵያን ምድር ለቃ ወጥታለች።
ነገር ግን በዚህ በዓድዋ ሽንፈት ቂም የቋጠረችው ጣሊያን ከአርባ አመታት በላይ የጦርነት ድግስ በኋላ ዳግም ተመልሳ በመምጣት በኢትዮጵያ ላይ በዓለም አቀፍ ሕግ በተከለከሉ የጦር መሣሪያዎች ሳይቀር በመጠቀም በኢትዮጵያውያን ላይ ወረራ አካሂዳለች።
በወቅቱም ኢትዮጵያ ለዓለም መንግሥታት ማህበር (League of Nations) ወረራው ተገቢ አይደለም ብላ አቤት ብትልም አጋርነት ካሳዩ ጥቂት አገራት ውጪ ሰሚ አላገኘችም ነበር።
የመንግሥታቱ ማህበር ከተመሠረተ ከአምስት ዓመታት በኋላ የተካሄደውን ይህን ወረራ ለመቀልበስ / ለአምስት አመታት/ የኢትዮጵያ መንግሥትና መላው ሕዝብ ታላቅ ተጋድሎ አድርገዋል።
ከዚህ ወስጥ የየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም ክስተት አንዱ ነው። በዕለቱ ለኢጣሊያ ንጉሣዊ ቤተሰብ አንድ ልዑል በመወለዱ ምክንያት በጄነራል ግራዚያኒ ትዕዛዝ በቀድሞው የገነተ ልዑል ቤተመንግሥት /በአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ/ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፤ ለፋሺስቶቹ ያደሩ ከሀዲ ባንዳዎችና መኳንንት፤ የፋሺስት ባለሥልጣናትና ወታደሮች እንዲሰበሰቡ ተደርጎ ነበር።
ከተሰብሳቢዎቹ ጋር ሰርገው የገቡት አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ለፋሺስቶቹ ባደሩ ከሀዲ ባንዳዎችና መኳንንቶች፤ እንዲሁም በፋሺስት ባለሥልጣናት ላይ የእጅ ቦምቦችን በመወርወር ጉዳት ማድረሳቸውን ተከትሎ ጭፍጨፋው ከግቢው ተጀም ሯል።
በዕለቱ በግቢው ውስጥ የነበሩ ከሦስት መቶ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ተጨፈጨፉ፤ የተማሩ ወጣቶች፣ የጦር መኮንኖችና ካህናት፣ መነኮሳት በሙሉ ከከተማው እየተለቀሙ እንዲጨፈጨፉ ተደረገ። የከተማዋ ነዋሪዎች እቤት ውስጥ እንዲገቡ እየተደረገ ከውጭ ተቆልፎባቸው ቤንዚን እየተርከፈከፈ በእሳት እንዲቃጠሉ ሆነ።
ኢትዮጵያውያንን በአካፋ፣ በዶማ፣ በመጥረቢያ በተገኙበት እየቆራረጡ አዲስ አበባን በደም ጎርፍ እንድትጥለቀለቅ ሆነ። ፋሽስቶች በሦስት ቀናት ውስጥ ብቻ ከአዲስ አበባንና አካባቢዋ ከ30ሺህ የሚበልጥ ሕዝብ ፈጁ።
የበቀል እርምጃው በአዲስ አበባ ብቻም ሳይሆን አብርሃ ደቦጭ፤ ሞገስ አስገዶምና አባሪዎቻቸው ተሸሽገውበታል ወደ ተባለው፣ ደብረሊባኖስ ገዳምም ደርሶ ቀሳውስትና ምዕመናን እንዲገደሉ ተደረገ። በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ አሰቃቂና አሳዛኝ ከሆኑት ጭፍጨፋዎች መካከል አንዱ የሆነው የየካቲት 12 ጭፍጨፋ በ20ኛው ክፍለ ዘመን ከነበሩ አስከፊ ክስተቶች መካከል ይጠቀሳል።
በጊዜው ኢትዮጵያውያንን ለዚህ ሁሉ ግፍ እና በደል የዳረጋቸው የሰሩት ጥፋት ኖሮ ሳይሆን በአንገዛም ባይነታቸው ብቻ በወራሪ ኃይሎች እንደ በደል ተቆጥሮ ነበር። ይህ አሰቃቂ ክስተት ከተፈጠረ ዘንድሮ ሰማንያ ስድስተኛ ዓመቱን በአዲስ አበባ ስድስት ኪሎ በሚገኘው የሰማእታቱ መታሰቢያ ሀውልት የአበባ ጉንጉን በማስቀመጥ ታስቦ ውሏል።
ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን በዘመናት ሁሉ ለነፃነት እና ለፍትህ የከፈሉት ዋጋ እጅግ ብዙ ነው። ዘመናዊ መሣሪያ እስከ አፍንጫው የታጠቀን ጦር በአንድነታቸው ተማምነው፣ በጊዜው ኋላ ቀር በሆነ መሣሪያ ይዘው፣ በአይበገሬነት ተፋልመው ጠላትን መርታት ችለዋል።
ዛሬ ላይ በቀድሙት አባቶቻችን ዘንድ የነበረው አንድነት እና ህብረት ከብዙዎቻችን ላይ እየጠፋ፣ ወይም እየቀነሰ ስለመሄዱ በብዙ መልኩ እንታዘባለን። የአሁኑ ትውልድ የቀደመ የአገሩን አኩሪ ባህልና ታሪክ የዘነጋ ሁሉ እስኪመስል ድረስ ሁኔታዎች አሳሳቢ እየሆኑ ነው።
ለአገርና ሕዝብ እዚህ ግባ የሚባል ፋይዳ በሌላቸው ጉዳዮች ተጠምዶ ሲውል እናያለን። ዛሬ ዘመን ተቀይሯል። የአሁኑ ትውልድ ተጋድሎ ማሸነፍ የሚጠበቅበት ግን ደህነትን እና ኋላ ቀርነትን ነበር።
የቀደሙ አባቶቹ በዘመናቸው የገጠማቸውን እና “ባሪያ ላድርግህ” ያላቸውን ጠላት ተዋግተው ድል በማድረግ ዛሬ ላይ ልጆቻቸው በኩራት የሚናገሩትን ታሪክ መፃፍ ችለዋል።
ታዲያ ዛሬ አገሪቱን እና ሕዝቦቿን ከያዟት የድህነት አረንቋ ማውጣት እና የቆየ መጥፎ ገፅታዋን መቀየር የዚህ ትውልድ የቤት ሥራ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ እውነት ነው። ነገር ግን፣ ዛሬም ኢትዮጵያን በዓለም ማህበረሰብ ፊት አንገት ያስደፋትን ድህነት እና ኋላቀርነት ማሸነፍ አልቻለችም።
ሰፊ እና ለእርሻ ተስማሚ የሆነ ድንግል መሬት፣ የተፈጥሮ ሀብት፤ እንዲሁም ሰፊ ቁጥር ያለው አምራች የሰው ኃይል ይዛ ዛሬም በድህነት የመዳከሯ ምክንያት በዋናነት በአሁኑ ትውልድ ያለ ደካማ የሥራ ባህል እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ።
የዚህ ዘመን ትውልድ ባለፈ እና የእርሱ አሻራ ባልሆነ የስልጣኔ እና የገድል ታሪክ ብቻ መኩራራትን ሥራው አድርጎ፤ ለአገር በማይበጁ ጥቃቅን ጉዳዮች ተጠምዶ ጊዜውን እያጠፋ ካለፉት አባቶቹ በአደራ የተረከባትን አገር ዛሬም ሰቅዞ ከያዛት ድህንነት እና ኋላቀርነት ማውጣት አልቻለም።
አገር የሚገነባው በትውልድ ቅብብሎሽ፣ ያለ መሰልቸት በሚሠራ ሥራ እንደሆነ እሙን ነው። የዛሬው ትውልድ እርሱ በኩራት እንደሚያወራላቸው፣ እንዳለፉት አባቶቹ በመልካም ለመነሳት (ስም ከመቃብር በላይ እንዲሉ) ብቻ ሳይሆን፤ በሚመጣው ትውልድ በመጥፎ ታሪኩ ላለመወቀስ ብሎም በጀግኖች የሕይወት መስዋዕትነት የቆየች አገሩን ከያዛት ድህነት ለማላቀቅ፤ ብሎም ኃላፊነት እና አደራውን ለመወጣት መሥራት እንደሚጠበቅበት አያጠያይቅም እላለሁ። የአባቶቹን አሻራ ማስቀጠል ከወጣቱ ይጠበቃልና!!!
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን የካቲት 21 ቀን 2015 ዓ.ም