የበርካታ ተፈጥሯዊና ማኅበራዊ እሴቶች ባለቤት የሆነው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ለእርሻና ለእንስሳት እርባታ ምቹ ሥነምህዳር ያለበት ክልል ነው:: ለክልሉና ለሀገራዊው ምጣኔ ሀብት ስትራቴጂክ ፋይዳ ካላቸው የግብርና ምርቶች መካከል ቡና፣ ቅመማ ቅመም፣ የቅባት እህሎችና ማር በስፋት ይመረትበታል:: በዚህም ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ በውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይም የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል:: ክልሉ በተለያዩ የሰብል ዓይነቶች፣ የቅባት እህሎች፣ በሆርቲካልቸር እንዲሁም በሥራ ሥር ምርቶች ይታወቃል::
ክልሉ ከፍተኛ የዝናብ መጠን ከሚያገኙ የሀገሪቱ ክልሎች መካከል አንዱ ሲሆን፤ ይህም ክልሉ ከዓመት ዓመት አረንጓዴ ሆኖ እንዲታይ ከማድረጉም ባለፈ ለግብርና ሥራ ያለው አበርክቶ የጎላ ነው::
የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አሸናፊ ክንፉ እንደሚሉት፤ ክልሉ በግብርናው ዘርፍ በ2015/16 ዓ.ም የመኸር ወቅት አጠቃላይ 323 ሺ 294 ሄክታር መሬት በአዝዕርት ሰብሎች ለማልማትና ከዚህም ሰባት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት አቅዶ ሲሠረ ቆይቷል:: በምርት ዘመኑ በክልሉ 322 ሺ 911 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈን ተችሏል::
ክልሉ በማሳ ሽፋን ከዕቅድ በላይ መሄድ የሚችልበት ዕድል እንደነበረው ጠቅሰው፣ በወርሃ ነሐሴ ዝናብ ከመቋረጡ ጋር በተያያዘ በተገቢው መንገድ ማሳዎችን በዘር መሸፈን እንዳልተቻለ ምክትል የቢሮ ኃላፊው ይናገራሉ:: ከዝናቡ መቋረጥ ባለፈም ከተዘሩት ሰብሎች ውስጥ ስምንት ሺ ሄክታር ያህል ሰብል መበላሸቱንና በሌላ ሰብል እንዲተካ መደረጉን ገልጸዋል::
እሳቸው እንዳሉት፤ በመኸር ወቅት በዋናነት 10 ሺ ኩንታል ምርጥ ዘር ለማቅረብ የታቀደ ሲሆን፤ የተመሰከረለት ዘርና ምርጥ ዘር ተደምሮ 15 ሺ 765 ኩንታል ምርት ጥቅም ላይ እንዲውል ተደርጓል:: 36 ሺ 356 ሄክታር መሬት የሚሸፍን የአፈር ማዳበሪያ ጥቅም ላይ ውሏል::
ከአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትና ስርጭት ጋር ተያይዞ በሀገሪቱ ያሉት ችግሮች እንዳሉ ሆነው 72 ሺ ሄክታር መሬት የሚሸፍን የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ ተቅዶ እንደነበር አስታውሰዋል:: የዩሪያ ማዳበሪያ በየጊዜው እየታየ የሚጨምር መሆኑን ወይም በማሳ ላይ ተጨምሮ ያልተጠናቀቀ መሆኑን ጠቅሰው፣ ጥቅም ላይ የዋለው 36 ሺ 356 ሄክታር መሬት የሚሸፍን የዩሪያ ማዳበሪያ ቁጥሩ ሊጨምር እንደሚችል ነው ያስረዱት::
በበልግ ወቅትም እንዲሁ በክልሉ ሰፊ ማሳ በዘር የተሸፈነ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አሸናፊ፤ እንደ ክልል 325 ሺ 556 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈን እንደተቻለ ተናግረዋል:: ይህም በመኸር ወቅት በዘር ከተሸፈነው ጋር ሲደመር በአጠቃላይ 650 ሺ ሄክታር አካባቢ የሚደርስ ማሳ በአዝዕርት ሰብል ብቻ የተሸፈነበት አግባብ ስለመኖሩ አመላክተዋል::
የሆልቲካልቸርና ቋሚ ሰብሎች ሲጨመሩ ደግሞ በበልግና በመኸር ወቅቶች በሰብል የተሸፈነው መሬት ወደ ዘጠኝ መቶ ሺ ሄክታር መሬት የሚደርስ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አሸናፊ፤ በዚህም በክልሉ አጠቃላይ በአዝዕርት ሰብሎችና በሆልቲካልቸር ምርቶች ጭምር በዓመት እስከ ዘጠኝ መቶ ሺ ሄክታር መሬት የሚሸፈን እንደሆነ ተናግረዋል:: በመሆኑም በሁለቱ የምርት ወቅቶች በጠቅላላው ከ85 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ከክልሉ የሚገኝ መሆኑን አመላክተዋል::
የምርት አሰባሰብን አስመልክቶ አቶ አሸናፊ ሲያብራሩ፤ በበልግና በመኸር የተገኘው ምርት በተመሳሳይ ወቅት የሚሰበሰብበት ጊዜ ስለመኖሩ ጠቅሰው፤ ከመስከረም ወር ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ጊዜያት ምርት እንደሚሰበሰብ ነው ያስረዱት::
እሳቸው እንዳሉት፤ በበልግ ወቅት ከተመረተው ምርት 11 ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ በመኸር ወቅት በዘር ከተሸፈነው ማሳ ደግሞ ሰባት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል:: በድምሩም በ2015/16 ከአዝዕርት ሰብሎች ብቻ 18 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ የሚጠበቅ መሆኑን ተናግረዋል::
አቶ አሸናፊ እንዳሉት፤ በክልሉ በየዓመቱ የሚገኘው ምርት ለገበያ በሚቀርብበት ጊዜ በሀገሪቱ ገበያ ላይ ከፍተኛ ድርሻ አለው:: ክልሉ ከአዝዕርት ሰብሎች በተጨማሪ በሆርቲካልቸር ዘርፍ ዕምቅ አቅም አለው:: በተለይም ሙዝ፣ አቦካዶና ማንጎ በአካባቢው በስፋት ይመረታሉ:: የክልሉ የሙዝ፣ የአቦካዶና የማንጎ ምርት ከአካባቢው ገበያ አልፎ ለማዕከላዊ ገበያ እየቀረበ የሚገኝ ሲሆን፤ ይህም ክልሉ በኢኮኖሚ ውስጥ ያለው ድርሻ ከፍተኛ እንዲሆን አድርጎታል ነው ያሉት::
በምርት ዘመኑ በክልሉ ያጋጠሙ ችግሮች ስለመኖራቸው አቶ አሸናፊ ጠቅሰዋል:: በተለይም የዝናብ እጥረትና ከዝናብ እጥረቱ ጋር ተያያዥ የሆኑ የበሽታና የተባይ መከሰት አጋጥሞ እንደነበር አስታውሰው፣ በክልሉ የተከሰተው የበሽታና የተባይ ክስተት በወረርሽኝ ደረጃ አለመሆኑን ተናግረዋል:: ይህም በሰብል ላይ ያደርስ የነበረውን የጉዳት መጠን የቀነሰው መሆኑን ገልጸዋል:: ችግሩ የተከሰተውም በቡቃያ ወቅት መሆኑን አስታውቀው፣ በዚህ ወቅት የተከሰተውን በሽታና ተባይ የመከላከል ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል:: አሁንም በቡቃያ ደረጃ ባሉት ሰብሎች ላይ የክትትልና የቁጥጥር ሥራ እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል::
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በተፈጥሮ የታደለ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከበልግና ከመኸር ወቅት በተጨማሪ በመስኖ ልማት ሥራስ ምን ምን ተሠራ፤ ምንስ ውጤት ተገኘ ስንል ላነሳነው ጥያቄ እንደ ክልል በቅርቡ የበጋ መስኖ ስንዴ እና ሆርቲካልቸር ልማት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑንም አቶ አሸናፊ ይናገራሉ:: በተለይም በበጋ መስኖ ስንዴ ላይ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በክልሉ በስድስት ዞኖች ማለትም ከፋ ዞን፣ ዳውሮ ዞን፣ ቤንች ሸኮ ዞን፣ ኮንታ ዞን፣ ሸካ ዞንና ምዕራብ ኦሞ ዞን ላይ የበጋ መስኖ ሥራ መጀመሩን ነው የጠቀሱት::
በበጋ መስኖ ከሰባት ሺ 140 ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ ሰብል ለመሸፈን አቅደው እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህ መጠን ከክልሉ ካለው እምቅ አቅም ጋር ሲነጻጸር እጅግ ዝቅተኛ ነው ይላሉ:: ለዚህም ዋነኛ ችግር የሆነው በክልሉ የመስኖ መሠረተ ልማት አለመልማቱ ዋነኛ ችግር መሆኑን ተናግረው፣ የመስኖ መሠረተ ልማት ባልተሟላበት ደግሞ በበጋ መስኖ አዝዕርቶችንም ሆነ የሆርቲካልቸር ልማት ማካሄድ አዳጋች መሆኑን ተናግረዋል::
ይሁንና በቀጣይ ክልሉ ሙሉ አቅሙን ተጠቅሞ በበጋ መስኖ የተለያዩ ምርቶችን ማምረት እንዲችል አስፈላጊዎቹ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ነው አቶ አሸናፊ የተናገሩት፤ በዚህም ለልማት አስፈላጊ የሆኑ ፓምፖችን ጨምሮ የማሳ ልየታ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አቶ አሸናፊ ገልጸዋል:: ከዚሁ ጋር በተያያዘም የጋራ የንቅናቄ መድረክ በመፍጠር ለአርሶ አደሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎች እንደሚሰጡ ጠቅሰው፣ በቀጣይ ክልሉ ሙሉ ለሙሉ ወደ በጋ መስኖ ልማት እንደሚገባም ጠቁመዋል::
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሦስት ሺ ሄክታር በመስኖ ሊለማ የሚችል መሬት እንዳለው የጠቀሱት አቶ አሸናፊ፤ ክልሉ በመስኖ ሊለማ የሚችል ሰፊ የመሬት ሽፋን ቢኖረውም በአካባቢው የመስኖ መሠረተ ልማት የተሟላ ባለመሆኑ የበጋ መስኖን በሙሉ አቅሙ መጠቀም አልቻለም ብለዋል:: ከመስኖ መሠረተ ልማቶች በተጨማሪም የመስኖ ልማት ሊከናወን በሚችልባቸው አካባቢዎች የመንገድ ችግር መኖሩን ጠቅሰው፤ በተለይም በመስኖ ሊለማ የሚችል ሰፋፊ መሬት ባለበት በኦሞ ዞን አካባቢ መንገድ አለመኖሩን ነው ያመላከቱት::
እሳቸው እንዳሉት፤ ከኦሞ ወንዝ በተጨማሪም በሸካ፣ ዳውሮና በሌሎች አካባቢዎች ጭምር ትላልቅ ወንዞች ይገኛሉ:: አካባቢዎቹ የበጋ መስኖ ሊለማባቸው የሚችሉ ሰፋፊ መሬቶች አላቸው:: ነገር ግን ወደ አካባቢው ለመድረስ የመንገድ እና የመስኖ አውታሮች አልተዘረጉም:: ለዚህም የክልሉ መንግሥት ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመሆን መሠረተ ልማቱን ለማሟላት ጥረት እየተደረገ ይገኛል::
ይሁንና ለጊዜውም ቢሆን በአካባቢው በሚገኙ የመሠረተ ልማት አውታሮችና በባህላዊ መስኖ ተጠቃሚዎች በፓምፖች በመታገዝ ከባዶ በመነሳት የበጋ መስኖ ስንዴ እየለማ ነው ያሉት አቶ አሸናፊ፤ በተለይም በ2015/16 የተሻለ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል::
እሳቸው እንዳሉት፤ ባለፈው ዓመት በበጋ መስኖ 3500 ሄክታር መሬት በዘር የተሸፈነ ሲሆን፣ አሁን ግን ይህን አሀዝ በእጥፍ ለማሳደግ እየተሠራ ነው:: በቀጣይም የመንገድ መሠረተ ልማቶች ሲሟሉና የመስኖ አውታሮች ተዘርግተው ምቹ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ አሁን ካለው በእጥፍ በመቶ ሺ የሚቆጠር ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴና ሌሎች ሰብሎች ሊለሙ እንደሚችሉ ነባራዊ ሁኔታው ያሳያል::
ለግብርና ሥራው ፈታኝ ከሆኑ ችግሮች መካከል ማዳበሪያ አንዱ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ አሸናፊ፤ የማዳበሪያ ችግር እንደ ሀገር ያለው እንዳለ ሆኖ በአሁኑ የዘር ወቅት ማዳበሪያን በወቅቱ ለማቅረብ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል:: ማዳበሪያ በክረምት የተገዛ መሆኑን ጠቅሰው፣ በጊዜው የሚደርስ እንደሆነ ያላቸውን ተስፋ ተናግረዋል::
ሌላው በክልሉ በዋናነት ከሚጠቀሱ ችግሮች መካከል ከፍተኛ የሆነ የዝናብ መጠን ያለበት ክልል መሆኑን የጠቀሱት አቶ አሸናፊ፤ በዚህ የተነሳ በክልሉ የአፈር አሲዳማነት ችግር እየተከሰተ ነው ብለዋል:: ለዚህም አፈሩ በኖራ እየታከመ ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ ከፌዴራል መንግሥት ጋር በጋራ በመሆን እየተሠራ ስለመሆኑ ተናግረዋል:: በክልሉ አልፎ አልፎ የሚከሰተው ተባይና በሽታን አስመልክቶም በወረርሽኝ መልክ የሚታይ እንዳልሆነ ያነሱት አቶ አሸናፊ፤ በ2014/15 በወረርሽን መልክ የተከሰተ በሽታና ተባይ አለመኖሩን ተናግረዋል::
በክልሉ አረሞችን በሰው ኃይል በእጅ የማረም ልምድ እንዳለም ጠቅሰው፣ አሁን ግን የተቀናጀ የአረምና በሽታ ቁጥጥር የሚል ሥርዓት ተዘርግቶ እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል:: በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከፍተኛ የንብ መንጋ ስለመኖሩ ጠቅሰው፣ ለዚህም ሲባል ክልሉ እንደ ሌሎች ክልሎች ኬሚካል ላይ ትኩረት የማያደርግና ኬሚካል የማይጠቀም መሆኑን አመላክተዋል:: ለባለሙያዎች ሥልጠና በመስጠት አረሞችን በእጅ የማረም ሥራ በስፋት እየተሠራ እንደሆነና ይህም የመሬቱን ለምነት እንዲሁም የአካባቢውን ባዮ ዳይቨርሲቲ ጠብቆ ለማቆየት ጠቃሚ እንደሆነ አስረድተዋል::
በክልሉ የተፈጥሮ ማዳበሪያን መጠቀም እየተለመደ መሆኑን የገለጹት አቶ አሸናፊ፤ በተለይም በተያዘው የመኸር ወቅት የተፈጥሮ ማዳበሪያን ለጥራጥሬ ሰብሎች በስፋት መጠቀም መቻሉን ተናግረዋል:: እሳቸው እንዳሉት፤ ባዮፈርቲላይዘር የሚባል በፋብሪካ የሚዘጋጅ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በክልሉ አገልግሎት ላይ እየዋለ ይገኛል:: ይህም ለሰብሎቹ የዩሪያ ፍላጎትን ሊያሟላ የሚችል በመሆኑ በስፋት ጥቅም ላይ እንዲውል እየተደረገ ነው::
ከዚህ በተጨማሪ ለሆርቲካልቸር ሰብሎች የኮምፖስት ዝግጅት በአርሶ አደር ደረጃ በስፋት እየተዘጋጀ እንደሆነ ያመላከቱት አቶ አሸናፊ፤ ‹‹አንድ አርሶ አደር አንድ የኮምፖስት ጉድጓድ›› በሚል መርህ የጋራ ግንዛቤ በመፍጠር በስፋት እየተሠራበት መሆኑን አስታውቀዋል:: በቀጣይም አርሶ አደሩን የማስተማርና ግንዛቤውን የማሳደግ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረው፣ በአሁኑ ወቅትም እንደ ክልል ቡናን ጨምሮ አንዳንድ ሰብሎች ሙሉ ለሙሉ በኮምፖስት እየለሙ እንደሆነ አቶ አሸናፊ አስታውቀዋል:: ይህ ጅማሮ በሌሎች ሰብሎችም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል::
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 28 ቀን 2016 ዓ.ም