የሀገራችን የትምህርት ጉዳይ ሁሌም ቢሆን የመነጋገሪያ አጀንዳ ነው፡፡ ከታች እስከ ላይ እንዳነጋገረ አለ። በሁሉም የትምህርት እርከኖች ላይ እንዳወያየ ነው። በሁሉም የትምህርት ይዘቶች ላይ ውዝግብ ነበር፤ አሁንም አልተፈታም – አለ።
በተለይም፣ የትምህርት ጥራት ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ እየሆነ ከመምጣቱ የተነሳ «የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ጥራት ምክር ቤት» የሚል እስከ ማቋቋም ድረስ ተሄዶ እንደነበር እናስታውሳለን። ዛሬ ምን ደረጃና ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ግልፅ አይደለም እንጂ፣ በወቅቱ እንደተገለፀው ከሆነ የምክር ቤቱ ዓላማና ተልዕኮ ግሩምና አሻጋሪ ይመስል ነበር።
ይህ በዓይነቱ ልዩ የሆነ፣ ለትምህርት ጥራትና አግባብነት ጉልህ አስተዋፅኦ ያለው፤ ከሥርዓተ ትምህርት ቀረጻ ጀምሮ ተማሪዎችን ለማብቃት በጋራ መሥራት ድረስ እንደሚዘልቅ ተገልፆለት የነበረው ተቋም (የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ጥራት ምክር ቤት) ከ200 በላይ የሙያ ማኅበራትን ያካተተ ሲሆን በትምህርት ጥራትና አግባብነት ላይ አተኩሮ የሚሠራ እንደሆነም በምስረታው ወቅት ተገልፆ ነበር። ይሁን እንጂ፣ አሁን አሁን ስለዚህ ምክር ቤት እየተሰማ ያለ ምንም ነገር የለም።
ለውጡን ተከትሎ ኢትዮጵያ ሳይንስንና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን በኃላፊነት የሚመራና የሚያስተዳድር ተቋም (የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር) ምስረታ ተቋሙ በፍጥነት ወደ ተግባር በመግባት በርካታ ሥራዎችን ሲያከናውን የነበረ ሲሆን፣ አንዱም የልየታ ሥራ (Higher Education Differentiation) እንደነበር የምናስታውሰው ነው። በተለይም እንደ አንድ የሚዲያ ተቋም ይህ ጋዜጣም አስፈላጊውን ትኩረት በመስጠት ሰፊ ሽፋን ሰጥቶ የዘገበው መሆኑም የሚረሳ አይደለም። አሁን፣ ጊዜው ደርሶ መርሐ ግብሩ ወደ መሬት የመውረጃው ወቅት እንደመሆኑ መጠን፣ በጉዳዩ ላይ የተወሰነ ወቅታዊ ሃሳብ በማከል ሂደቱን ማሳየት ይገባል፡፡
በወቅቱ (ጥቅምት፣ 2013 ዓ.ም) የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር (አሁን ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ተዋህዷል) ሚኒስትር በነበሩት ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ ዩኒቨርሲቲዎቹን በትኩረት መስክ መለየት (Differentiation ይሉታል) የሀገሪቱን ብልጽግና ለማሳካት እንደሚረዳ ተገልፆ ነበር፡፡ «ተቋማቱ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ በመወጣት አርአያ ሆነው የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የሚፈልገውን ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ማፍራት» ያለባቸው መሆኑም እንደዚያው።
የዚሁ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት ዶ/ር ሙሉ ነጋ በበኩላቸው የዩኒቨርሲቲዎች ልየታ ዋና ዓላማ ዩኒቨርሲቲዎቹን ለማበላለጥ ሳይሆን ከነበራቸው የትኩረት አቅጣጫ በመነሳት የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ ማድረግ መሆኑን ተናግረው ነበር።
በዚህ በልየታ አሠራር መሠረትም በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ 7 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአምስት የትኩረት መስኮች የተለዩ ሲሆን፥ በዚህም የምርምር፣ አጠቃላይ፣ የአፕላይድ ሳይንስ፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ እና የቴክኒካል ዩኒቨርሲቲዎች ተብለው መመደባቸውም አይዘነጋም።
በትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ-ካርታ ጥናት ውጤት መሠረት 8 የምርምር፣ 15 የአፕላይድ ሳይንስ፣ 2 የሳይንስና ቴክኖሎጂ እና ቀሪዎቹ 21ዱ የአጠቃላይ ዩኒቨርሲቲ ተብለው መለየታቸውም ይታወቃል።
በምርምር ዩኒቨርሲቲነት የተመደቡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም፥ አዲስ አበባ፣ አርባ ምንጭ፣ ባህርዳር፣ ጎንደር፣ ሀረማያ፣ ሀዋሳ፣ ጅማ እና መቐለ ናቸው። አክሱም፣ አምቦ፣ አርሲ፣ አሶሳ፣ ደብረብርሃን፣ ደብረማርቆስ፣ ዲላ፣ ድሬዳዋ፣ ጅግጅጋ፣ ኮተቤ፣ ሰመራ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ወልቂጤ፣ ወለጋ እና ወሎ ዩኒቨርሲቲ የአፕላይድ ዩኒቨርሲቲዎች ተብለዋል።
አዲግራት፣ ቦንጋ፣ ቦረና፣ ቡሌሆራ፣ ደባርቅ፣ ደብረታቦር፣ ድምቢዶሎ፣ ጋምቤላ፣ እንጅባራ፣ ጂንካ፣ ቀብሪደሃር፣ መዳወላቡ፣ መቅደላአምባ፣ መቱ፣ ሚዛን ቴፒ፣ ኦዳ ቡልቱም፣ ራያ፣ ሰላሌ፣ ዋቸሞ፣ ወራቤ እና ወልዲያ ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ አጠቃላይ ዩኒቨርሲቲዎች ሆነዋል። የአዳማ ሳይንስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እና የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲነት ተለይተዋል።
በቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ ስር ደግሞ የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ተመድቧል።
በተደጋጋሚ እንደተገለፀው፣ ይህንን ውሳኔ ለማሳለፍ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ መሠረት በማድረግ ጥናቱን አካሂዷል። ይህንንም የልየታ ምክረ ሃሳብ በተቻለ ፍጥነት ወደ ተግባር ለመቀየር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተከታታይ ውይይቶች መደረጋቸውም እንዲሁ በወቅቱ ተገልፆ እንደነበር ይታወቃል።
ባለፈው አመት «በሀገሪቱ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ከሚቀጥለው በጀት ዓመት አንስቶ የሚያቀርቧቸው አዳዲስ የግንባታ ፕሮጀክቶች የሚጸድቁላቸው፣ ትምህርት ሚኒስቴር ከሰጣቸው የልህቀት ማዕከልነት ልየታ ጋር ከተስማማ ብቻ» ነው የሚል የትምህርት ሚኒስቴርን አቋም መስማታችን በራሱ የሚነግረን እውነት ቢኖር የልየታ መርሐግብሩ (ተቋማቱን በልህቀት ማዕከልነት መመደቡ) ወደ ኋላ የማይመለስ መሆኑን ነውና የመርሐግብሩን ውጤታማነት ከወዲሁ እንድንጓጓለት ያደርገናል።
ይህ የልየታ መርሐግብር ታስቦበት የተገባበት ስለመሆኑ ሌላው ማሳያ (ደረጃ) «ታንዳርድ» የተሠራለት (ያለው) መሆኑ ሲሆን፤ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ለልህቀት ማዕከልነት የተቀመጠውን መስፈርት(ስታንዳርድ) ለማሟላት የሚቀራቸውን መሠረተ ልማት ለመለየት፣ የመሠረተ ልማት ልየታ ለማካሄድ ይቻል ዘንድ ቡድን መዋቀሩን መስማታችን፤ ለተግባራዊነቱም በሚኒስቴሩ የአስተዳደርና መሠረተ ልማት ዘርፍ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በኃላፊነት መመደቡና የመሳሰሉት የሚነግሩን ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ነው።
የትኩረት መስኮቹ ከነማብራሪያዎቻቸው፤
ከላይ፣ የቀድሞው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በ2012 ዓ.ም የከፍተኛ ትምህርት ሥርዓት ልየታ (Higher Education Differentiation) በሀገሪቱ የሚገኙ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎችን በአምስት ዋና ዋና የትኩረት መስኮች የምርምር፤ አፕላይድ ሳይንስ፣ ኮምፕሬሄንሲቭ፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም ቴክኒካል በሚል መለየቱ የሚታወስ ሲሆን፤ እንደሚከተለውም አብራርቷቸው (www.moshe.gov.et www.facebook.com/SHE.Ethio) ነበር።
1. የምርምር ዩኒቨርሲቲ
በዚህ ምድብ ስር የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በድኅረ-ምረቃ ትምህርት እና ምርምር ላይ ያተኩራሉ፤ ከቴክኖሎጂ ሽግግር እና ከድኅረ-ምረቃ ሥልጠና ጎን ለጎን በተለይ የምርምር አቅምን፣ የምርምር አፈፃፀምን እና የመምህራን ምርምር ውጤታማነትን ማሳደግ ላይ በትኩረት ይሠራሉ።
2. አፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ
የአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲዎች ሙያ-ተኮር የትምህርት መርሐግብሮች ያሏቸው ሲሆኑ፣ በእነዚህ ተቋማት ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች የንድፈሃሳብ ዕውቀታቸውን እንዴት ተግባር ላይ ማዋል እንዳለባቸው እውቀት ይዘው ይወጣሉ፡፡ በብሔራዊ እና ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ውስጥ የተለያዩ ፕሮጄክቶች፣ የሥራ ምደባዎች እና የሥራ ላይ ልምምዶች በእነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚሰጡ የዲግሪ መርሐ-ግብሮች አካላት ናቸው፡፡
3. አጠቃላይ ዩኒቨርሲቲ
በዚህ ምድብ ስር ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች አጠቃላይ የማስተማር፣ ምርምር እና የማኅበረሰብ ተሳትፎ የሚከናውንባቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ናቸው። የዶክትሬት፣ የማስተርስ እና የመጀመሪያ ዲግሪ መርሐግብሮችን የሚያካትቱ ሲሆን፣ ማስተማር እና ምርምር ላይ በተመጣጠነ መልኩ ይሠራል።
4. የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች
የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲና የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎችን የሚያቅፍ ይሆናል።
5. የቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ፤
የኢትዮጵያ ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲዎች በዚህ ስር የሚካተቱ ናቸው፡፡
በወቅቱ ከተገኘ መረጃ ለመረዳት እንደሚቻለው፣ በየዩኒቨርሲቲዎቹ የሚሰጡ የትምህርት መስኮችን በተመለከተ ባጠቃላይ ባሉ 47 ዩኒቨርሲቲዎች ከ200 በላይ የቅድመ-ምረቃና ከ450 በላይ የሁለተኛ ዲግሪ እንዲሁም ከ200 በላይ የሦስተኛ ዲግሪ የትምህርት መስኮች ይሰጣሉ::
አሁን ምን እየተደረገ ነው?
በትምህርት ሚኒስቴር የአካዳሚክ ጉዳዮች መሪ ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት ዶ/ር ኤባ ሚጀና ሰሞኑን ከመገናኛ ብዙሃን ጋር በጽሕፈት ቤታቸው ባደረጉት ቆይታ ወቅት እንደገለፁት፣ በተጀመረው ዓመት የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ለተመደቡበት የትኩረት መስክና ተልዕኮ የዝግጅት ሥራ ቅድሚያ ይሰጣሉ፡፡ በ10 ዓመታት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ወደ ትኩረት መስክና ተልዕኮ እንዲሸጋገሩ የትግበራ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ የመጀመሪያው ምዕራፍ ሥራ ተጀምሯል።
የትምህርት ሚኒስቴር የዘርፉን ስብራቶች ለማስተካከል ከወሰዳቸው እርምጃዎች አንዱ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎችን በትኩረት መስክና በተልዕኮ ተለይተው እንዲሠሩ ማድረግ መሆኑን የሚናገሩት ዶ/ር ኤባ፣ በተለይ የተማሪዎችን ዕጣ ፈንታ በተመለከተ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት «የነበሩት (ነባሮቹ) በጀመሩት ይቀጥላሉ፤ በዚያውም ያጠናቅቃሉ። አዲስ ገቢዎችም በአዲሱ የትኩረት መስክ በመመዝገብ ትምህርታቸውን መከታተል ይጀምራሉ።» በማለት መልሰዋል።
በቅርቡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሳውላ ካምፓስ በቅድመ ምረቃ መርሐግብር ያሠለጠናቸውን 91 ወንድና 58 ሴት በድምሩ 149 የ6ኛ ባች ተማሪዎች ለ2ኛ ዙር መስከረም 13/2016 ዓ.ም ባስመረቀበት ወቅት በክብር እንግድነት የተገኙት ዶ/ር ኤባ «የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ብቁ እና በቂ የሰው ኃይልን ማፍራት እንዲሁም የዘመኑን ዕውቀት ተጠቅሞ ቴክኖሎጂን መፍጠር፣ ማሻሻል ብሎም ማላመድ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሀገራችን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ለመቀየር የትምህርትና ሥልጠና ተቋማት የለውጥ ሃሳቦችን በማፍለቅና በመተግበር አርአያ የሚሆኑ ዜጎችን ማፍሪያ፣ የዴሞክራሲያዊ አስተሳሰቦችና ቴክኖሎጂዎች መፍለቂያ እንዲሁም የባሕላዊ እሴቶች ማጎልበቻ ማዕከላት እንዲሆኑ ማድረግ አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑን» መናገራቸው ለአመታት በችግር ተተብትቦ የቆየው የትምህርቱ ሴክተር ከታሰረበት እየተፈታ ይሆን የሚል ጥያቄንም የሚያጭር ብቻ ሳይሆን፣ የሀገራችን መፃኢ ዕድል ብሩህ ይሆን ዘንድ ከወዲሁ የሚያመላክት ይመስላል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በርካታ ሪፎርሞች (ለውጦች) የተካሄዱ ሲሆን፣ ከ2012 ትምህርት ዘመን ጀምሮ በዩኒቨርሲቲ ትምህርት 3 ዓመት የነበረው ዝቅተኛ የቅድመ ምረቃ ፕሮግራም ቆይታ ወደ 4 ዓመት ማደጉ (ወይም፣ ወደነበረበት መመለሱ) አንዱ ነው።
ለትምህርት ጥራት ሲባል ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ለድህረ ምረቃና ሦስተኛ ዲግሪ የሚቀበሏቸውን ተማሪዎች በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አማካኝነት ትምህርት ሚኒስቴር የሚዘጋጀውን ፈተና በመውሰድ ማለፍ የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ ይህ ዘንድሮ የሚጀመር መሆኑን መሪ ሥራ አስፈፃሚው ዶ/ር ኤባ ለአዲስ ዘመን ገልፀዋል፡፡ «ይህ ብቻም አይደለም፣ ከዚህ አጠቃላይ ፈተናም በኋላ የትምህርት ክፍሎች የየራሳቸውን ፈተና በማውጣት የሚፈትኑና ያለፉትን የሚቀበሉ ይሆናል» ሲሉም አክለዋል።
በአጠቃላይ፣ የዛሬው ትኩረታችን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በትኩረት መስክ ልየታ ሥራ (Higher Education Differentiation) ላይ ሆነ እንጂ በትምህርቱ ዘትርፍ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ፤ ለውጦችም እየታዩ፤ በተለይም በባለ ድርሻ አካላት ዘንድ መነሳሳቶች እየተፈጠሩ ስለመሆናቸው በስፋት እየታየ ሲሆን፤ መገናኛ ብዙኃንም እነዚህን ለውጦች ወደ ሕዝብ ሲያደርሱ መቆየታቸው ይታወቃል። ከነዚህ መካከልም ይህ የልየታ መርሐግብር አንዱ እንደመሆኑ መጠን፣ ሁሉም ማስትሬትና ዶክትሬት ሰጪ፣ ሁሉም ኬሚስትሪ አስተማሪ ከመሆን ተላቅቆ፤ ሁሉም በሕግ አስመራቂ ከመሆን ወጥቶ፤ ሁሉም ካልተገባ ፉክክርና ግርግር ወጥቶ የራሱ የሆነ ትኩረትና ተልዕኮ ኖሮት – – – ዘንድሮ ወደ ተግባር መግባቱን ስንገልፅ ለመልካም አፈፃፀሙም መልካሙን ሁሉ እየተመኘን ነው።
ወግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 28 ቀን 2016 ዓ.ም