‹‹ምክክሩ የሚሠራው ወቅታዊ ስሜቶችን ለማረጋጋት ሳይሆን የተፈጠሩበትን ገፊ ምክንያቶች ለይቶ መሠረታዊ መፍትሔ ለማምጣት ነው›› -አቶ ጥበቡ ታደሰ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቃል አቀባይ

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ የታወጀበት አንዱ ምክንያት መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አካታች ሀገራዊ ምክክሮችን በማካሔድ የተሻለ ሀገራዊ መግባባትን ለመገንባት በማስፈለጉ ነው፡፡ በሒደትም የመተማመንንና ወሳኝ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተቀራርቦ የመሥራት ባህልንም ለማጎልበት ታስቦ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ሲያከናውን የነበረውን ሥራ ሰሞኑን አንዱ ባለድርሻ አካል ለሆነው መንግሥት ገለጻ ማድረጉ ይታወቃል፡፡ ኮሚሽኑ በእስካሁኑ ሒደት ስለሠራቸው ሥራና በቀጣይ ስለሚያከናውነው ተግባር አስመልክቶ አዲስ ዘመን ከኮሚሽኑ የሚዲያ ኮሙኒኬሽንና አጋርነት ዘርፍ አስተባባሪ እና የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ከሆኑት ከአቶ ጥበቡ ታደሰ ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተው አጠናቅሮ አቅርቧል፡፡ መልካም ንባብ፡፡

አዲስ ዘመን፡በቅርቡ ኮሚሽኑ የደረሰበትን የሥራ ሒደት ለመንግሥት አቅርቧል፤ የነበረው ግብረመልስ ምን ይመስል ነበር?

አቶ ጥበቡ፡ ሰሞኑን ከመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ኮሚሽኑ ውይይት ነበረው:: ከዚህ የተነሳ ኮሚሽኑ ለመንግሥት ሪፖርት አቀረበ ተብሎ ሲዘገብ አስተውለናል:: ነገር ግን ያቀረበው ለመንግሥት ሪፖርት አይደለም:: ምክንያቱም ኮሚሽኑ ተጠሪነቱ ለኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው:: ስለሆነም ሪፖርት የሚያቀርበው ለኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች እና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነው እንጂ ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለካቢኔያቸው የማቅረብ ኃላፊነት የለበትም:: ስለዚህ አንዱ መታረም ያለበት ጉዳይ ነው ብለን እናምናለን:: መንግሥት እንደ አንድ ባለድርሻ አካል የሀገራዊ ምክክሩ አካል ነው:: ለምሳሌ መምህራን፣ ሲቪል አካላት፣ ፖለቲከኞችና ሌሎችም እንደሆኑት ሁሉ መንግሥትም አንዱ ባለድርሻ አካል ነው:: ኮሚሽኑም ከእነዚህ ባለድርሻ አካላት ጋራ በጋራ የሚሠራቸው በርካታ ሥራዎች አሉት::

ልክ ከሌሎቹ ባለድርሻ አካላት ጋር እንደምናደርገው ውይይት ከመንግሥትም ጋር በተካሄደው ውይይት አንዳንድ የሚነሱ ጥያቄዎችን ተቀብሎ ኮሚሽኑ ማብራሪያዎችን ሰጥቷል:: ከፍተኛ አመራሩም እስካሁን የተሠሩ ሥራዎችን አድንቀው ኮሚሽኑ ጥሩና መልካም ጅምር ላይ እንዳለ ጠቅሰው ሥራውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ግብረ መልስ ሰጥተዋል:: ኮሚሽኑ በሚያደርገው ሥራ እንደ አንድ ባለድርሻ አካል መጫወት ያለበትን ሚና ለመጫወት ቁርጠኛ መሆኑን ገልጿል::

አዲስ ዘመን፡እንደ አንድ ባለድርሻ አካል ከመንግሥት ጋር ባደረጋችሁት ውይይት የጠበቃችሁት ምላሽ እንዴት ይገለጻል?

አቶ ጥበቡ፡ እንደተጠበቀው መልካም ነው:: መንግሥት ሲባል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ብቻ ሳይሆኑ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ መንግሥት በፌዴራልም በክልልም ደረጃ ያሉ የሥራ ኃላፊዎች ናቸው:: ስለዚህ ባከናወንናቸው ሒደቶች በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አካላት እስካሁን በታየው ትብብራቸው በጣም አበረታች ነው:: መደገፍ ባለባቸው ሁሉ በመደገፍ ላይ ናቸው:: በዚህኛውም መድረክ ላይ የታየው ነገር ተመሳሳይ ነው:: እንዲህ ሲባል የኮሚሽኑ ገለልተኝነትና ነፃነት እንደተጠበቀ ነው:: የተገለጸውም በቀጣይም የሚጠበቅባቸውን ለማድረግ ነው::

አዲስ ዘመን፡ኮሚሽኑ በአሁኑ ወቅት እየተገበራቸው ያሉ ሥራዎችና የደረሰበት ውጤት እንዴት ይገለጻል?

አቶ ጥበቡ፡ እስካሁን ከተሠሩ በርካታ ሥራዎች በርካታ ጉዳዮችን ለማከናወን ጥረት ተደርጓል:: እኛ ሥራ የምንሠራው በአራት ምዕራፍ ከፍለን ነው:: የቅድመ ዝግጅት፣ የዝግጅት፣ የሒደትና የትግበራና የክትትል ምዕራፍ በሚል ነው:: አሁን ባለው ሁኔታ የቅድመ ዝግጅቱ እና የዝግጅቱ ምዕራፍ ተጠናቅቆ የሂደት የምንለው ሦስተኛው ምዕራፍ ላይ እንገኛለን:: የቀረን ነገር ቢኖር ወደአራተኛው ምዕራፍ መሸጋገር ነው::

በአሁኑ ወቅት የሠራችሁት ምንድን ለተባለው የተያዘው ዓመት 2016 ዓ.ም እንደመሆኑ የበጀት ዓመቱን እቅድ በመተግበር ጀምረናል:: ከዚህ አኳያ በሀገራዊ ምክክር ላይ የሚሳተፉ ተሳታፊዎች እስካሁን የለየናቸው ክልሎች እንደተጠበቁ ሆነው ተሳታፊዎች ባልተለዩባቸው ቀሪ ክልሎች ለመለየት ትኩረት አድርገን እየሠራን ነው:: እነዚህም የአፋር፣ ሱማሌ፣ አማራ፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ኢትዮጵያና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ናቸው::

የመጀመሪያ ሥራችን እንደሚታወቀው ተሳታፊ የሚለየው ኮሚሽኑ ብቻ አይደለም:: የተለያዩ ተባባሪ አካላት አሉ:: ስለዚህ በእነዚህ ክልሎች እየሠራን ያለው ተባባሪ አካላትን የመለየት እና የማሰልጠን ሥራ ነው:: ሁለተኛው በሀገራዊ ምክክሩ ዙሪያ ግንዛቤ መፈጠር ስላለበት ኅብረተሰቡ በሚሳተፍበት ጊዜ አውቆና ተረድቶ መሳተፉ ውጤት ስለሚያመጣ ግንዛቤ የሚፈጥሩ በየክልሉ በሚነገሩ የተለያዩ ቋንቋዎች አማካይነት የማዘጋጀትና ተደራሽ የማድረግ ሥራ ትኩረት ሰጥተን የምንሠራው ነው:: ሥራው የሚሠራው ከተለያዩ አካላት ጋር አጋርነትን በመፍጠር ነው:: ስለዚህ የተሳታፊ ልየታ ከምንሠራቸው ክልሎች ያሉ ባለድርሻ እና የመንግሥት አካላት ጋር በመሆን ሥራ እየሠራን ነን::

ሌላው ትኩረት ሰጥተን እየሠራን ያለነው ሥራ ደግሞ እስካሁን ተሳታፊዎችን ከለየንባቸው ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በክልልና በከተማ አስተዳደር ደግሞ የሚሳተፉ የተለያዩ ተሳታፊዎች አሉ:: እነርሱ የሚወከሉት ከተቋማት፣ ከማኅበራትና ከመሳሰሉት ስለሆነ የተወከሉትን ሰዎች የማሰባሰብና መረጃዎችን የማጠናከር ሥራ በተመሳሳይ ጊዜ እየሠራን ነው:: ከዚያ በተጨማሪ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ግንኙነቶቻችንን የማጠናከር ሥራ በትኩረት እየሠራን እንገኛለን::

ሌላው ትኩረት ሰጥተን እየሠራን ያለነው የአጀንዳ ሐሳቦችን የመሰብሰብ ሥራ ነው:: አጀንዳ የሚሰበሰበው ደግሞ አንድም ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ወኪሎቻቸውን መርጠው በእነርሱ በኩል በኮሚሽኑ አስተባባሪነት የሚካሔዱ መድረኮች ላይ ነው:: ከእነዚያ መድረኮች አጀንዳ ይሰበሰባል:: በሌላ መንገድ ደግሞ የአጀንዳ ሃሳቦች የምንሰበስብበት መንገድ በቀጥታ በዚያ መንገድ የመሳተፍ ዕድሉን ያላገኙ ሰዎችም ሆኑ ተቋማት ጭምር የአጀንዳ ሃሳብ አለን በማለት በሚመጡበት ጊዜ በቢሮዎችና በተለያዩ የቴክኖሎጂ አማራጮች የማሰባሰብ ሥራዎችን እየሠራን ነው::

ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች አጀንዳ የምንሰበስብበት መንገድ አሁንም ትኩረት ሰጥተን እየሠራን ያለነው በጥናት ነው:: አንድ ኮሚሽኑ ይህን ለማካሄድ ያለው በዝግጅት ላይ ነው:: ሁለተኛ ነገር ከዚህ ቀደም በተለያዩ ተቋማትና የተለያዩ ግለሰቦች ያካሄዷቸው ጥናቶች ካሉ፤ የሚዲያ ተቋማትም ጭምር ከዚህ በፊት ሲዘግቧቸው የነበሩ ጉዳዮችን በማጥናት ከእነዚያም ደግሞ ጥሩ የአጀንዳ ሃሳቦችን መሰብሰብ ስላለብን እሱንም እንዲሁ ትኩረት ሰጥተን እየሠራን ነው::

በቀጣይ በሚደረገው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይና በሀገራዊ ምክክሩ ላይ ያለውን ሒደት የሚያመቻቹ አመቻቾችን እንዲሁ የማብቃትና የመለየት ሥራ ያስፈልጋል:: በተለይ በኢትዮጵያ ከሚገኘው የዩኒቨርሲቲ ተቋማት ጋር በመተባበር ይህን ሥራ ሊሠሩ የሚችሉ በገለልተኝነት፣ በታማኝትና በግልጸኝነት ሊሠሩ የሚችሉ የተለያዩ ምሁራንንም ጭምር ለማሳተፍ ጥረት እየተደረገ ነው::

በቀጣይ የሚኖሩን ሥራዎች አጀንዳ ማሰባሰቡ፤ መቅረጹና ምክክር ማካሄዱ ናቸው:: እነዚህ በሥርዓት መመራት ያለባቸው ናቸው:: ለምሳሌ ተሳታፊዎቹን የምንለየው ራሱ ኮሚሽኑ በቀረጸው ተሳታፊዎችን የመለያ ሥነ ዘዴ በመጠቀም ነው:: ልክ በተመሳሳይ ሌሎችንም ኹነቶች የምንመራበትን ሥርዓት የመቅረጽ ሥራዎችም እየተሠሩ ነው:: ስለዚህ ከእነዚህ ተጨባጭ ሁኔታዎች ተነስተን የ2016 በጀት ዓመት እቅዳችንን አዘጋጅተን በዚያ እቅድ መሠረት እየተተገበሩ ያሉ ተግባራት ናቸው::

አዲስ ዘመን፡የተቀሩት ተሳታፊዎች ያልተለዩባቸው ክልሎች ተሳታፊዎቹን እስከመቼ ለመለየት አቅዳችኋል?

አቶ ጥበቡ፡ የሥራው ባህሪ በራሱ ሒደት ነው:: ሁለተኛ ነገር ደግሞ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን የሚያሳትፍ ነው:: ሦስተኛ ነገር ደግሞ ሥራው መሬት ላይ በሚወርድበት ጊዜ አካታችና አሳታፊ መሆን ስላለበት የሚሠራው በሥርዓት ነው:: ስለዚህ ይህን ጉዳይ በዚህ ጊዜ አከናውኗል ማለት የሚያስችል ሁኔታ ላያጋጥም ይችላል:: ምክንያቱም መሬት ላይ በተጨባጭ የምናያቸው አንዳንድ ፈታኝ የሆኑ ሁኔታዎች ስለሚኖሩ ነው:: አሁንም የተፈጠሩ አሉ፤ ምናልባትም ወደፊትም የሚፈጠሩ ይኖራሉ:: ከዚህ አኳያ እኛ በጥቅሉ እየሠራን ያለነው በእቅዳችን መሠረት ነው::

ዋናው ግን እንደ አንድ መነሻ እየሠራን ያለነው በዚህ በ2016 በጀት ዓመት አጋማሽ ላይ ምክክሩን መጀመር ነው:: ምክክሩን እንጀምራለን ካልን ምክክሩ ከመጀመሩ በፊት መከናወን ያለባቸው የያዝናቸው እቀዶች መጠናቀቅ አለባቸው:: ምክከሩን በአጋማሽ ላይ እናካሂዳለን ካልን አሁን ካለንበት ወር ተነስተን በቀሩት ጥቂት ወራት ተሳታፊ ያልለየንባቸውን ክልሎች ለይተን የማጠናቀቅና አጀንዳዎችን ማሰባሰብን መጀመር አለብን:: በተጨማሪም አጀንዳዎቹ መቀረጽም አለባቸው:: ወደምክክሩ የሚገባው ከዚያ በኋላ ነው:: ስለዚህ ሥራዎቹ ከዓመቱ አጋማሽ በፊት ተጠናቅቀው ምክክሩ በዓመቱ አጋማሽ ላይ መጀመር አለበት::

አዲስ ዘመን፡በኮሚሽኑ አማካይነት የሚካሔደው ውይይት አሁን በሚታዩ ወቅታዊ ስሜቶች ተጽዕኖ ስር ይወድቃል የሚል ስጋት ይኖር ይሆን?

አቶ ጥበቡ፡ በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ የሚፈጠር ጫና ይኖራል ብለን አንገምትም:: በእቅዳችን መሠረት ሥራችንን ለማከናወን በሚደረግ ጥረት የራሱ ተግዳሮት ሊመጣ ይችላል:: ነገር ግን አንዱ መገንዘብ ያለብን እውነታ አሁን በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ማድረግ ያስፈለገበት አንዱ ተጨባጭ ምክንያት አሁን በተለያዩ አካባቢዎች ይታያሉ ያልሻቸው ስሜቶች ምናልባትም በእኛ እምነት ከስሜትም ከፍ ያሉ የሀገርን ህልውና የሚፈታተኑ አሳሳቢ ችግሮች አሉ::

አንዱ ምክክሩ በተጨባጭ አስፈላጊ የሚያደርገው በኢትዮጵያ ውስጥ እንደዚህ ዓይነት አውዶች በመኖራቸው ነው:: ስለዚህ እዚህም እዚያም የሚታዩ ችግሮችን እኛ የምናያቸው ውጤቶች መሆናቸው ነው:: በመሆኑም ሀገራዊ ምክክሩ የሚሠራው ወቅታዊ ስሜቶችን ለማረጋጋትና ለማከም ሳይሆን የተፈጠሩበትን ገፊ ምክንያቶች ለይቶ መሠረታዊ መፍትሔ ለማምጣት ነው::

ከዚህ አኳያ አሁን ላይ የሚታዩ ግጭቶች የተለያዩ ገፊ ምክንያቶች ቢኖሯቸውም ዋንኛው ምክንያት ብለን የምናምነው እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮቻችን ላይ ያሉን አለመግባባቶች ናቸው ወደዚያ የሚያደርሱን:: እነዚህን አለመግባባቶች ደግሞ ለመፍታት የምንጠቀምበት አንዱ አማራጭ የኃይል አማራጭ ይሆንና እንዲህ ዓይነት ነገሮችን ይፈጥራሉ ማለት ነው:: ስለዚህ ከዚህ በመነሳት በሀገር ደረጃ ያሉ መሠረታዊ ጉዳዮቻችን ላይ ያሉ አለመግባባቶችን መፍታት ነው:: ከዚህ አኳያ በየወቅቱ የሚታዩ ነገሮች የእኛ አሠራር ላይ ከጊዜ አኳያ እቅዳችንን ሄድ መለስ እንድናደርገው ያስገድዱን ካልሆነ በስተቀር በራሳቸው የሚፈጥሩት የተለየ ጫና አይኖርም::

ከዚያ በተጨማሪ አንድ መታየት ያለበት ምክክር ኮሚሽኑም ሆነ አዋጁም ጭምር መጨረሻ ላይ እንዲያሳካቸው ከሚፈለጉት ዓላማዎች መካከል አንዱ የምናየው ወቅታዊ ችግሮች ዘላቂ በሆነ ሁኔታ መፍታት የሚያስችልና አስተማማኝ የሆነ ሠላም የሚረጋገጥበትን የፖለቲካና ማኅበራዊ መደላድል መፍጠር ነው:: ስለዚህ ይህንን ዓላማ ይዞ የተንቀሳቀሰ ኮሚሽን ወቅታዊ የሆኑ ችግሮችን ዘላቂ በሆነ ሁኔታ ለመፍታት የሚያስችሉ ሥራዎችን እንዲሠራ ኃላፊነት የተሰጠውና እሱንም ለመተግበር እየተንደረደረ ያለ ተቋም በእነዚህ ሊፈቱ በሚችሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ተጽዕኖ ስር የሚወድቅበት ዕድል ይኖራል ተብሎ አይታሰብም::

አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዝሃነት መገለጫው ቢሆንም አንዱ ሌላውን በሚገባ ያውቀዋል የሚል እምነት የሌላቸው አካላት አሉ፤ ይህ ከሆነ ለሥራችሁ እንቅፋት ሊሆን ይችላል ተብሎ ይታሰባል?

አቶ ጥበቡ፡ ለሀገራዊ ምክክሩ ብዝሃነት እንቅፋት ሊሆን የሚችልበት ዕድል የለውም:: ብዝሃነት በራሱ ጸጋ ነው:: እንዴት መያዝ እንዳለብን ያለማወቅ ሁኔታ ነው ችግር የሚፈጥርብን እንጂ ብዝሃነት በራሱ ችግር የለበትም:: ነገር ግን እንዳልሽው ያለመግባባት ወይም ደግሞ ያለመተዋወቅ ችግሮች አሉ መባሉ ትክክል ነው:: ነገር ግን እሱ በኮሚሽኑ ሥራ ላይ ችግር አይሆንም:: ምክንያቱም በእውነትም ስለማንግባባና ስለማንተዋወቅ ነው ችግሮች እየተፈጠሩ ያሉት:: ስለዚህ ይህ ኮሚሽን የመጣውና ሥራውን እየሠራ ያለው ይህንን ችግር ለመቅረፍ ነው:: በመሆኑም ያለመግባባቱና ያለመተዋወቁ ችግር በራሱ ችግር አይደለም::

ኮሚሽኑ እንዲቋቋምና ሀገራዊ ምክክር ሊያመጣ የተፈለገበት ምክንያት ይኸውም በሚገባ ያለመተዋወቃችን የፈጠራቸውና የወለዳቸው ብዙ ችግሮች ስላሉ ነው::

ላለመተዋወቃችንና በአግባቡ ላለመግባባታችን ብዙ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ:: ነገር ግን በእርግጥ እንድንግባባ እና እንድንተዋወቅ ተሠርቷል ወይ የሚል ጥያቄ ያስነሳል:: ይሁንና በአብዛኛውን ነገሮች የሚያተኩሩት ልዩነቱ ላይ ነው:: መግባባት ወይም መተዋወቅ ማለት ሰዎች ከሰዎች ጋር አብረው ማዕድ ስለተጋሩና ስለተጫወቱ ተዋወቁ ወይም ተግባቡ ማለት አይደለም:: መግባባት ከእዚህ አለፍ የሚል ጉዳይ ነው:: ስለዚህ መግባባትንና መተዋወቅን ለመፍጠር ቁጭ ብሎ መወያየትንና መመካከርን እንዲሁም ልብ ለልብ መነጋገርን ይጠይቃል:: ቀደም ሲል ለመግባባት የሚያስችሉ መድረኮችም አልነበሩም:: ይሁንና ሰዎች ወደመተዋወቁና መግባባቱ እንዲመጡ መሠራት ያለበት ሥራ ባለመሠራቱ ነው ይህ ውጤት ሊመጣ የቻለው:: እንደሚባለው ማንም ቢሆን የሚያጭደው የዘራውን ነው:: በመሆኑም አሁን የምናያቸው ያለመተዋወቅና ያለመግባባቶች ተዘርተው እየታጨዱ ነው ብሎ ማሰብ ይቻላል::

ከዚህ አኳያ ሲታይ አንዱ ሀገራዊ ምክክሩን አስፈላጊ የሚያደርገው ነገር በኢትዮጵያ ውስጥ ይህ እውነት በመኖሩ ነው:: በትክክል ልብ ለልብ የመተዋወቅና የመግባባት ችግር ስላለ ሰው ከሰው ጋር፤ አንዱ ብሔር ከሌላው ጋር ችግር ስላለበት ይህ ኮሚሽን እንዲወለድና ሥራዎችን እንዲሠራ ማድረግ ተችሏል::

በዚህ ላይ መያዝ ያለበት አንዱ ቁም ነገር ምክክር የሚደረገው በተግባቡ ሰዎች መካከል አይደለም:: በተግባቡ ሰዎች መካከል ምንም ምክክር አያስፈልግም:: ምክክር የሚያስፈልገው ባልተግባቡና መሠረታዊ ልዩነቶች ባላቸው ሰዎች መካከል ነው:: ይሁንና ሕዝቡ መግባባት የማይችለው ብዝሃነት ስላለው አይደለም:: ብዝሃነት ላለመግባባት ምክንያት አይደለም:: ብዝሃነት ተይዞ ግን ቁጭ ብሎ በመነጋገርና ልብ ለልብ በመደማመጥ እንዲሁም አንዱ የሌላው ጫማ ውስጥ ገብቶ ሁኔታዎችን በማየት ደረጃ ላይ መግባባት መፈጠር ነው እንጂ ብዝሃነት በራሱ ችግር አይሆንም:: በተለያየ ቦታ ያለው የእርስ በእርስ አለመግባባት ምክክር ኮሚሽኑ ላይ የሚያሳድረው ምንም ዓይነት ጫና የለም::

አዲስ ዘመን፡የፖለቲካ ስብራት የፈጠረው አለመግባባት በምክክር መድረኩ መጠገን የሚቻለው እንዴት ነው? ከታሪክ የተወረሱ ዕዳዎችስ የሚፈቱት በምን ዓይነት አካሔድ መሆን አለበት? እንደ ሀገር መግባባት ያልተደረሰባቸውን የትርክት መንስዔዎችስ በምክክር የሚፈቱት እንዴት ነው?

አቶ ጥበቡ፡ እየታዩ ያሉ አለመግባባቶች እንዳሉ ሆነው እኛ አተኩረን የምንሠራው ብዙ ምክንያቶችና ብዙ መገለጫዎች ሊኖሩ ይችላል:: እኛ ግን በአብዛኛው ዋና ትኩረታችን እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ አለመግባባቶች ላይ ነው:: እነዚህ አለመግባባቶች በአጭር ጊዜ የተወለዱ ሳይሆኑ ለዘመናት የነበሩ ሲከማቹ ቆይተው ዛሬ የደረሱበት ደረጃ ላይ የደረሱ ናቸው::

አለመግባባቶቹን የፈጠራቸው የፖለቲካ ስብራቶች ወይም ፖለቲካው አካባቢ ያሉ ቀውሶች የራሳቸው ሚና አላቸው:: ነገር ግን ምናልባት ዋነኛ ምክንያት ናቸው ብሎ መውሰዱ ተገቢ ላይሆን ይችላል:: በተጨማሪ ከዚህ ጋር ተመጋጋቢ ሆኖ የሁሉም ድምር ውጤት ሊሆን ይችላልና:: አሁንም ያለው ሆነ ቀደም ሲል የነበረው የፖለቲካ ሥርዓታችን የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ አበርክቷል::

ሌላው ያነሳሽው ታሪኮቻችንን በተለያየ መንገድ የምንረዳበት ሁኔታ አለ፤ እንዳልሽውም መግባባት ላይ ያልደረስንባቸው ትርክቶችም አሉ:: ሆነ ተብለውም ለተለየ ዓላማ የሚሰራጩ ጉዳዮችም አሉ፤ እነዚህና መሰል ነገሮች ተደማምረው አሁን ለተፈጠረው ነገር አስተዋጽኦ አበርክተዋል ብለን እናምናለን::

እንደ ሀገር ከምክክር ኮሚሽኑ ጋርም ተያይዞ ተመካክረን ልንሻገራቸው ከምንችላቸው ሃቆች መካከል የጠቀስሻቸው ነገሮች ናቸው:: አንደኛ የፖለቲካ ሁኔታችን መሻሻልና መለወጥ አለበት:: ሁለተኛ ደግሞ ታሪኮቻችን ላይ ለመግባባት ጥረት መደረግ አለበት:: እንዲሁም በተዛባ ሁኔታ የሚፈጠሩ ትርክቶች የሆነ ቦታ ላይ ተግትተው መልክ መያዝ መቻል አለባቸው:: ትናንት ነበሩ። ዛሬም አሉ፤ መፍትሔ ካልተገኘ ደግሞ ነገም ይቀጥላሉ ማለት ነው:: ስለዚህ ሥራዎች የሚሠሩት ከእንደዚህ ዓይነት እሽክርክሪት ውስጥ ለመውጣት ነው::

ከዚህ አኳያ ምናልባት በምክክር ኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ እንደዓላማ ከተቀመጡ ነገሮች አንዱ እነዚህን የጠቀስሻቸውን ሁኔታዎች መቀየር ነው:: አንዱ በምክክር ሒደቱ እንደርስበታለን ተብሎ የጠቀመጠው ዓላማ መተማመን የሰፈነበት እና አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት የመፍጠር ጉዳይ ነው::

ሁለተኛው ደግሞ እንዳልሽው ሲንከባለሉ የመጡ ውስጣዊ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የሚያስችል የፖለቲካ ሥርዓት ማዳበር አንዱ ከምክክሩ የሚጠበቅ ጉዳይ ነው::

ስለሆነም የኮሚሽኑ እንቅስቃሴ አሁናዊ ምልክቶችን ተከትሎ ሳይሆን መሠረታዊ ችግሮችን በመለየት ፈውስ ማምጣት ነው:: ታክሞ በማገገምና በመፈወስ መካከል ልዩነት አለ:: ስለዚህ እኛ በዋናነት የምናተኩረው የችግሩን ምንጭ በምክክር ሒደት በማግኘት ከዚያ አዙሪት ለመውጣት ሁነኛ መፍትሔ የመፈለግ አቅጣጫን ተከትለን በመሥራቱ ላይ ነው::

በምክክሩ ሒደት ይህንን እንዴት እውን እናደርጋለን ለሚለው ጥያቄሽ እኛ የምናስበው በመጀመሪያ እነዚህ ጉዳዮች አጀንዳ ሆነው ይመጣሉ ብለን እንጠብቃለን:: በእርግጥ ሊመጡም ላይመጡም ይችላሉ:: አጀንዳ ሆነው ከመጡ ምክክር ይደረግባቸዋል:: ስለዚህ በምክክር ሒደቱ ደግሞ እነዚህ ጉዳዮች ወደመግባባት ይመጣሉ ተብለው ይጠበቃሉ:: ይህ ዝርዝር ነገሮችን የሚጠይቅ አንዳንዶቹ በአጭር ጊዜ፤ ሌሎቹ ደግሞ በተራዘመ ጊዜ ሊስተካከሉ የሚችሉ ጉዳዮች ናቸው:: ምክንያቱም እነዚህ ለረጅም ዓመታት ሲከማቹ የነበሩ ጉዳዮችን በአንድ ጀምበር የሚፈታበት ተዓምራዊ የሆነ ነገር ካልተፈጠረ በስተቀር ሊሆን ስለማይችል አንዳንዶቹ በአጭር ጊዜ ሊፈቱ ይችላሉ፤ ሌሎቹ ደግሞ በረጅም ጊዜ ትግበራ ሊፈቱ ይችላሉ:: ስለዚህ የእኛ ተስፋ ጉዳዮቹ ላይ ምክክር በማድረግ ከእነዚህ አዙሪት ውስጥ የምንወጣበትን ነገር ሕዝቡ መክሮ እዚያ ደረጃ ላይ ይደርሳል የሚል እምነት አለኝ::

አዲስ ዘመን፡ኮሚሽኑ ከሕዝብና ከመንግሥት ጋር ተሰናስሎ የሚሠራው ሥራ ስኬታማ ይሆን ዘንድ ከሕዝብም ሆነ ከመንግሥት የሚጠበቀው ምንድን ነው?

አቶ ጥበቡ፡ ሀገራዊ ምክክር እንደ ስሙ ሀገራዊ ነው:: ስለዚህ ባለቤቱ ሕዝቡ ነው:: ለሆነ አካል የተሰጠ አይደለም:: ሀገራዊ ነው ካልን በውስጡ በርካታ ባለድርሻ አካላት አሉ ማለት ነው፤ ከዚህ ውስጥ አንዱና ዋነኛው ደግሞ ኅብረተሰቡ ነው:: ሁለተኛ ደግሞ መንግሥት ነው:: ቀጥሎ የተለያየ የፖለቲካ ድርጅቶችና ሊሒቃን ናቸው:: ከዚህ አኳያ ያሉት የተለያዩ አካላት ናቸው::

ምክክሩ አለመግባባቶችንና ግጭቶችን ለመፍታት በባሕሪው ትንሽ ለየት የሚያደርገው ምክክር ሒደት ላይ ተሸናፊና አሸናፊ የሚባል ነገር አለመኖሩ ነው:: ሁሉም አሸናፊ ሆኖ የሚመጣበት መድረክ ነው:: አሸናፊ ሆነው የሚወጣው ነገር ደግሞ እውነት ነው፤ እውነት ደግሞ የሕዝብ ሐቅ ነው:: ስለዚህ ከዚያ አኳያ ሁሉም በእውነት ስለእውነት በጋራ ችግሩ ላይ ተነጋግሮ በጋራ መፍትሔ ላይ መድረስ ይቻላል ብለን እናምናለን:: ስለዚህ ባለድርሻ አካላቱ እስካሁን ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ላደረጋቸው ጥረቶች ድጋፋቸው እጅግ የሚደነቅና የሚበረታታ ነው:: ሕዝቡ እንደ ሕዝብ በሔድንባቸው ቦታዎች ላይ ሲያሳየን የነበረው ነገር እጅግ በጣም የሚደነቅ ነው:: የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሙያ ማኅበራትና ሌሎች የተለያዩ ተቋማት በሀገራዊ ምክክር ላይ ያላቸው ተስፋ እና የሚያደርጉት እገዛ በጣም የሚበረታታና መጠናከር ያለበት ነው:: ይህም በቀጣይ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንፈልጋለን::

ከዚህ በመለስ ከኅብረተሰቡ አንዱ የሚጠበቀው ነገር ጫናዎች ቢኖሩበትም እነርሱን ተጋፍቶ በምክክር ሒደቱ ላይ ያለውን ተሳትፎ ሊያጠናክር ይገባል:: የምክክር ሒደቱ ደግሞ ውጤት እንዲያመጣ የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያበርክት ይጠበቅበታል::

ከዚያ በተጨማሪ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትም እስካሁን ሲያደርጉ የነበሩትን አስተዋፅኦ መቀጠል ይኖርባቸዋል:: ከመንግሥትም አኳያ መወጣት የሚጠበቅበትና በአዋጁም የተቀመጠ ተግባራት አሉ:: እስካሁን ባለው ሁኔታ ኮሚሽኑ ገለልተኛነቱንና ነፃነቱን በጠበቀ ሁኔታ እየተደረጉ ያሉ ድጋፎች በጣም የሚያበረታቱ ናቸው:: ይህንኑ ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠልና በምክክር ሒደቱ መጨረሻ ላይ ምናልባት የሚገኙ ምክረ ሃሳቦችን ተቀብሎ የመፈጸም ኃላፊነት የመንግሥት እንደመሆኑ መጠን ለዚህም ከወዲሁ መዘጋጀት አለበት::

ምሁራኑና የፖለቲካው ማኅበረሰብ አካባቢም እንዲሁ እንደማንኛውም ባለድርሻ አካል በንቃት የመሳተፋቸው ነገር እንደተጠበቀ ሆኖ ተሳትፏቸው ጥናቶችን በማድረግ ሊሆን ይችላል፤ ምናልባትም በአካሄዳችን የታሪክ ችግሮች ሊኖሩ ስለሚችሉ እነዚያን በመንቀፍም ከኮሚሽኑ ጋር የቅርብ ግንኙነት በመፍጠር ችግሮቹ እንዲፈቱ በማድረግ የበኩላቸውን ሚና መጫወትና ጉዳዩ ውጤት እንዲያመጣ አስተዋጽኦ ማበርከት አለባቸው ብለን እናስባለን::

ከሚዲያም በተመሳሳይ ከጥበብ ማኅበረሰቡም ኅብረተሰቡ በጉዳዩ ላይ ግንዛቤ እንዲኖረው በማድረግና በተሻለ ንቃት በመሳተፍ ያላቸውን ክህሎት ተጠቅመው ደግሞ ተገቢውን ኃላፊነታቸውን ቢወጡ መልካም ነው ብለን እናስባለን::

አዲስ ዘመን፡ኮሚሽኑ በተያዘው ዓመት የሚያካሒደው ውይይት ለሁሉም ችግር ቁልፍ ነው የሚሉ አካላት አሉ፤ ለዚህ ምላሽዎ ምንድን ነው?

አቶ ጥበቡ፡ ጥሩ ጥያቄ ነው:: እንደሚመስለኝ ኮሚሽኑ ለሁሉም ነገር ቁልፍ ነው ማለትም ሆነ ቁልፍ አይደለም ማለት ሁለት ጫፍ እና ጫፍ የወጡ ነገሮች ስለሚሆኑ ልክ ናቸው ብለን አናስብም:: ለሁሉም ችግር መፍትሔ ነው ማለትም በሌላ በኩል ደግሞ ጭራሽ አያሳካም ማለትም ችግር አለበት:: ስለዚህ እውነታውን የሚያሳዩት መሃል ላይ ያ ነገሮች ናቸው ብዬ አስባለሁ::

እንግዲህ የሀገራችን ችግር ብዙ ነው:: ዓይነቱም ምክንያቱም ብዙ ነው:: ስለዚህ ኮሚሽኑን የእነዚህ ሁሉ ችግሮች መዳኛ መንገድ ነው ብሎ መውስድ የራሱ ችግር አለበት:: በዚያው ልክ ደግሞ ሀገራዊ ምክክሩ እንዳይሳካ የሚሠሩ ወገኖች አይሳካም ብለው ቢያወሩና ቢገምቱ ላይፈረድባቸው ይችላል:: ምክንያቱም እንዳይሳካ መሥራት ሥራቸው ስለሆነ:: በዚህ መሃከል ደግሞ ቀደም ሲል የተፈጠሩ ችግሮች ጥንካሬያቸውን በማየት ሊገምቱ የሚችሉ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ::

ስለዚህ ከዚህ አግባብ በኢትዮጵያ የሚካሄደው ሀገራዊ ምክክር የሚያተኩረው ደጋግሜ እንደገለጽኩት እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ነው:: ከዚህ አኳያ የራሱ ውስንነት ሊኖረው ይችላል:: ሁሉንም ጉዳዮች ስለማይመለከት ከዚህ አኳያ ገደብ ይኖረዋል ማለት ነው::

ሌላው ለሁሉም ችግሮቻችን መፍትሔው ሀገራዊ ምክክር ብቻ ነው ማለት አይቻልም፤ ምክንያቱም አገልግሎት አሰጣጥንና አሠራርንም በማዘመን እና የፍትህ ሥርዓቱንና መሰል ጉዳዮችን በማሻሻል ደግሞ መመለስና መፈታት ያለባቸው ብዙ ችግሮች አሉ:: ስለዚህ እዚህ ሀገር ያሉ ችግሮች በጣም የተከማቹና የተወሳሰቡ ዓይነታቸውም መንስዔያቸውም የተለያየ ስለሆነ እንደየሁኔታቸው መፍትሔ መስጠት ያስፈልጋል እንጂ ለሁሉም ነገር ሀገራዊ ምክክሩ መፍትሔ ነው ማለት አያስደፍርም::

ነገር ግን አንድ ትልቁ ነገር እጅግ መሠረታዊ የሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አተኩረን መሥራት ማለት የእርሱ ቅርንጫፎች የሆኑ ይከስማሉ እንደማለት ነው:: ምክንያቱም የችግሩ ምንጭ ስለተመታ ሌላው ችግር በራሳቸው ጊዜ ሊፈቱ ይችላሉ:: ስለዚህ ከዚህ አግባብ ትልልቆቹ አጀንዳዎች ላይ መግባባት መቻሉ ለትንንሾቹ ጉዳዮች መፍትሔ ይሆናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን:: ትልልቆቹ አጀንዳዎቻችን ላይ መግባባት ላይ ከደርስን ሌሎቹም የሚፈቱ ስለሚሆን መንግሥትም የተረጋጋ ሥራ መሥራት የሚያስችለው ሁኔታ ከመፈጠሩም በተጨማሪ ሕዝቡም የተረጋጋ ኑሮ እንዲመራ ምክንያት ይሆነዋል የሚል እምነት አለን:: ከዚህ አኳያ ምክክሩ የሁሉም ችግሮቻችን መፍትሔ ባይሆንም ለዋና ዋና ችግሮቻችን ግን መፍትሔ ይሆናል ብለን እናምናለን::

አዲስ ዘመን፡ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ::

አቶ ጥበቡ፡እኔም አመሰግናለሁ::

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 28 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You