የኢሬቻ እሴቶች በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ይገለጡ፤

 ከዚህ በቀደመ መጣጥፌ ሶስቱ አብርሃማዊ ዕምነቶች ማለትም ክርስትና ፣ እስልምና እና የአይሁድ ዕምነቶችን ከእነ በጎ ባህላቸው በተለይ ልሒቃን ወይም ጉልሀን ነን በምንል ዕቡያን ባለመገለጣቸው፣ በየዕለት ተዕለት ሕይወታችን ባለመታየታቸው ፣ በተግባር ስላልኖርናቸው ፣ ከዘመናዊው ትምህርት ጋር መሳ ለመሳ ስላላስኬድናቸው እንዲሁም ከምዕራብም ሆነ ከምስራቅ እንዳሉ በገለበጥናቸው ርዕዮተ ዓለሞች ስለደፈቅናቸው ሀገራችንን ዛሬ ለምትገኝበት ሁለንተናዊ ቀውስ ተዳርጋለች። ለዚህ ደግሞ ልሒቃን ተብዮዎች በአንድም በሌላ መልኩ ተጠያቂ ነን።

በዛሬ መጣጥፌም ልሒቃንን በእርግጥ ኢሬቻን እንኖረዋለን በሕይወታችን እንተረጉመዋለን ስል እጠይቃለሁ። መቼም አፋችንን ሞልተን እንዴታ አንልም። ሀገራችን የምትገኝበት ነባራዊ ሁኔታ ፀሐይ የሞቀው ፣ ዓለም ያወቀው ፣ የአደባባይ ሀቅ ነውና። በተፈጥሮዬ ጨለምተኛ የሚሉት አይነት ሰው አይደለሁም ። ሆኖም ባህላዊ ወረቶቻችንን መኖር በተግባር መግለጥ ካልጀመርን መጭው ጊዜ ከዚህ የከፋ እንደሚሆን እነግራችኋለሁ። ለዚህ ነው ቆም ብለን ከእያንዳንዳችን ዕምነትና ባህል አኳያ ራሳችንን ያለ ርህራሔ አናዘን መቤዠት የሚያስፈልገን። ለቀብድ ያህል ይሄን ካልሁ ወደ ገደለው።

ዓለም አቀፉ የእርቅ፣ የሰላም፣ የግልግልና የሽምግልና ረቡኒ (መምህር ) ፕሮፌሰር ሕዝቅያስ አሰፋ “የሰላምና ዕርቅ ትርጉምና መንገዶች” በሚለው ማለፊያ መጽሐፋቸው የሰላም የእርቅ አድማሶች በማለት በመጀመሪያ ሰው ከራሱ ጋር ከዚያ ከጎረቤቱ፤ ከማህበረሰቡ ጋር በመጨረሻም ከተፈጥሮ ጋር እርቅ፤ ሰላም ማውረድ እንዳለበት ይተነትናሉ። ሰሞኑን የሚከበረው የኢሬቻ በዓል ሰው በመጀመሪያ ከራሱ ጋር በመቀጠል ከጎረቤቱ ከዚያም ከተፈጥሮ ጋር የሚታረቅበት ማዕድ ነው።

ኢሬቻ ሰላም ፣ ፍቅር ፣ ይቅርታና አንድነት የሚፈፀምበት በመሆኑ አብሮነትን ስለሚያበረታታ አሳሳቢ ነው። ጥልን ቂምን ጥላቻን እያራገፈ መልካም መልካሙን ማለትም ሰላምን ዕርቅን የሚያጠናክር ስለሆነ በውስጠ ታዋቂ ሰላምን ይዟል። የኦሮሞ ባህልና ታሪክ ተመራማሪና ፀሐፊ ኦቦ ድርቢ ደምሴ ኢሬቻ ማለት ኦሮሞ ለምለም ሳርና አበባ ይዞ ፈጣሪን የሚያመስግንበት ክዋኔ ሲሆን በሀይቅ ፣ በወንዝ ፣ በምንጭ ወይም በውሃ ዳርና በተራራ ብቻ የተወሰነ ግን አይደለም ይላሉ።

ልጅ ሲወለድ፣ አዲስ ቤት ሲሰራ፣ ሙሽራ ሲወጣ፣ በዘር ወቅትም፣ ወዘተረፈ ኢሬቻ ይደረጋል በማለት ከማህበረሰቡ የዕለት ተዕለት ሕይወት ጋር ምን ያህል የተቆራኘ እንደሆነ ያስረዳሉ። የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑት ኦቦ ሙሉጌታ ደበበ (ፒ ኤች ዲ) በሌላ በኩል ኢሬቻ የገዳ ሥርዓት አንዱ አንጓ ነው ይላሉ። በማሳያነት ከሚጠቀሱት አበይት ምክንያቶች ቀዳሚው የሥርዓቱ ክዋኔ በቃሉና በአባ መልካ አጋፋሪነት መመራቱ ነው በማለት በዋቢነት ይጠቅሳሉ።

ኢሬቻ በኦሮሞ ማህበረሰብ ዘንድ በዓመት ሁለት ጊዜ እንደሚከወንና የመጀመሪያው በበልግ በተራራ ላይ አምላክን የሚያመሰግንበትና ዝናብ የሚለማመንበት ሲሆን ቱሉ ኢሬቻ ይሰኛል። ኦቦ ድርቢ ቱሉ ኢሬቻ መሬት አፏን ከፍታ የበልግ ዝናብን የምትጠብቅበት ወቅት ስለሆነ ፈጣሪን ዝናብ የሚለማመኑበት ጊዜ መሆኑን ይገልጻሉ። ለምለም ሳርና አበባ ተይዞ በሀይቅ፣ በወንዝ፣ በምንጭ ዳር የተከበረው የምስጋና በዓል ደግሞ መልካ ኢሬቻ በመባል እንደሚታወቅ ኦቦ ሙሉጌታ ያብራራሉ።

ፈጣሪ ዝናብ ስለሰጠ ከክረምት ወደ ብራ ስለ አሸጋገረ የሚመሰገንበት እንዲሁም አዝመራው ደርሶ ተሰብስቦ ወደ ጎተራ እንዲገባ የሚለመንበት መሆኑን አክለው ይገልጻሉ። በፕሮፌሰር የሰላም አድማስ እይታ መሠረት ኢሬቻ ሦስቱንም የሰላም አለባውያን በአንድነት የያዘ የእርቅ፣ የሰላም ገበታ ነው ማለት ይቻላል። ጥያቄው እየኖርናቸው ነው ወይ !? የሚለው ነው። ለማንኛውም ሦስቱን የሰላም አድማሶች ከኢሬቻ እሴቶች አንጻር አንድ በአንድ እናመሳክር፦

1ኛ . ከራስ ጋር ሰላም ፤

ዓለም አቀፍ አሸማጋይ እና የሰላም አባት ፕሮፌሰር ሕዝቅያስ ከፍ ብሎ በጠቀስሁት መጻሐፋቸው ገፅ – 102 ላይ”ውስጣዊና መንፈሳዊ ሰላም ከራስ ጋር ሰላም ማውረድ ፣ መታረቅ ነው። ከፈጣሪ ጋር ሰላም ከማውረድ ጋር ትስስር አለው። ውስጣዊ ሰላም ከሌሎች ጋር ለሚመሰረት ሰላም ወሳኝ ነው። ውስጣዊ ሰላም ያለው ሰው ምን ያህል ከሌሎች ጋር በሰላም እንደሚኖር እና ሰላም እንደሚያካፍል ይታወቃል። ውስጣዊ ሰላም ያላቸው ሰዎች አስታራቂና ሰላም ገንቢም ናቸው። ሰላማቸው ወደሌሎች ይፈሳል። ከራሱ ጋር የታረቀና ውስጣዊ ሰላም ያለው ሰው የሕይወትን መስተጋብር የተገነዘበ ስለሆነ ከማህበረሰቡና ከተፈጥሮ ጋርም ሰላምና እርቅን ያወረደ ነው። ከራስ ጋር የሚፈጠር ሰላም ለሰላም አድማሶች መነሻም ውጤትም ነው ። …”

ኢሬቻ ከመደረጉ በፊት ከራሱ ጋርም ሆነ ከሌሎች ጋር የተቀያየመ የተጋጨ ካለ እንዲወጣ ሽማግሌዎች በኦሮሞኛ “እውነትን ከአምላክ ፆታን ከምድር መደበቅ አይቻልም። በውሻም ሆነ በልጅ ምክንያት የተጋጨ ካለ ከፈጣሪ ጋር እንዳያቀያይመን ይውጣ” በማለት እንደሚያግባቡ ይህን ሳያደርጉ ቢቀሩ ደግሞ በማህበረሰቡ ዘንድ እንደሚያስወቅሳቸው ኦቦ ድርቢ ያስረዳሉ። የሀገር ሽማግሌዎች ቢያንስ በመጋቢትና በመስከረም በዓመት ሁለት ጊዜ እርቅ የማውረድ የመሸምገል አጋጣሚ እንዳላቸው ይገልጻሉ። መልካ ኢሬቻም ሆነ በወርሀ መጋቢት የሚከበረው ቱሉ ኢሬቻ ላይ ተሳታፊ ለመሆን ከራስ ጋር መታረቅ ሰላም ማውረድ ማህበራዊ ቅድመ ሁኔታ እንደሆነና በዓሉ ቤትን ራስን በእርቅ የማፅዳት፤ የጥል ግድግዳን የማፍረስና ፋይል ዘግቶ ወደ አዲስ ምዕራፍ የመሻገሪያ ድልድይ መሆኑን ኦቦ ሙሉጌታ አክለው ያብራራሉ።

2ኛ . ማህበራዊ ሰላም፤

ፕሮፌሰር ሕዝቅያስ ስለ ሁለተኛው የሰላም አድማስ ገፅ – 103 ላይ ማህበራዊ ሰላም ከራስ ጋርና ከተፈጥሮ ጋር ከሚደረግ ሰላም ጋር ጥብቅ ትስስር አለው። ይህ ማለት ግን ማህበራዊ ሰላም ከሌለ ውስጣዊ ሰላም አይኖርም ወደሚል መደምደሚያ አያደርስም። ሆኖም ብጥብጥና ሁከት ባለበት ውስጣዊ ሰላምን ማስፈንንም ሆነ ማስቀጠልን ፈታኝ አያደርገውም ማለት አይደለም። ሌላው ማህበራዊ ሰላም ከተፈጥሮ ጋር ከሚደረገው ሰላም ጋር ጥብቅ ትስስር ያለው መሆኑን መገንዘብ ነው። ግጭትና ጦርነት በተደጋጋሚ የተካሄደባቸው አካባቢዎች የሚገኝ የተፈጥሮ ሀብት ስለሚጎዳ ደኑም ስለሚጨፈጨፍ አካባቢው ይራቆታል።

በዚህም ሥነ ምህዳሩ ስለሚዛባ የከባቢ አየር ለውጥን ያስከትላል። ለዚህ ነው የማህበራዊ ሰላም መኖር ለፍጥረትና ለአካባቢ ጥበቃ ዋስትና ተደርጎ የሚወሰደው። ፕሮፌሰር እንደሚሉት ከራስ ጋር የሚፈጠር ውስጣዊ ሰላም ከጎረቤትና ከማህበረሰብ ጋር የሚደረግ እርቅ መሠረት ነው። በኢሬቻ ለመታደም ከራስ ጋር መታረቅ ማህበራዊ ቅድመ ሁኔታ ነው። ከራሱ ጋር ሰላም ያለው ደግሞ ከጎረቤቱ ጋር የመጋጨት አጋጣሚው ዝቅተኛ ነው።

ሆኖም ከጎረቤቱ ጋር ወይም ከሌላ ሰው ጋር ግጭት ቢፈጠር የሀገር ሽማግሌዎች በቱሉ ወይም በመልካ ኢሬቻ የማስታረቅ መልካም አጋጣሚም ኃላፊነትም ስላለባቸው ማህበራዊ ሰላምን ከመታወክ ይታደጉታል። ለዚህ ነው የሥነ ማህበረሰብ አጥኚዎች መጀመሪያ ከራስ በመቀጠል ከጎረቤት ጋር የሚፈጠር ሰላም ከተፈጥሮ ጋር ለሚደረስ ሰላም መደላድል እንደሆነ የሚያስረዱት። ታላቁ መጽሐፍስ “እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት።”አይደል የሚለው ! ?

3ኛ. የተፈጥሮ ሰላም፤

ፕሮፌሰር በገፅ – 104 ላይ “የተፈጥሮ ሰላም ከማህበራዊ እና ከውስጣዊ ሰላም ጋር ጥብቅ ትስስር አለው። ከተፈጥሮ ጋር ሰላም፣ እርቅ ማውረድ አካላችን ከታነፀበት ምድር ጋርም መታረቅ ነው። ከተፈጥሮ፣ ከዩኒቨርስ ሥርዓትና ኃይል ጋር መንሰላሰል የውስጣዊ ሰላም ምንጭ ነው። …የተፈጥሮ ፍቅርና እንክብካቤ ለማህበራዊ ሰላም መስፈን የማይተካ ሚና እንዳለው የተለያዩ ጥናቶች ያረጋግጣሉ። …” ኢሬቻ ከሁለቱ የሰላም አድማሶች ይልቅ ከተፈጥሮ ጋር ለሚደረግ እርቅ ያደላል ቢባል ማጋነን አይሆንም።

በቱሉ ኢሬቻ ፈጣሪውን ለበልግ እርሻ፣ ለከብቶች ግጦሽና ለውሃ ዝናብ የሚለምንበት መሆኑ መልካ ኢሬቻው ደግሞ ፈጣሪው ዝናብ ስለሰጠው፣ ከክረምት ወደ ብራ ስላሸጋገረው የሚያመሰግንበት በሌላ በኩል ያልተሰበሰበውን እህል በአደራ የሚሰጥበት የአምላክን ጥበቃ የሚለማመንበት መሆኑ በተለይ ለምለም ሣርና አበባ ይዞ ውሃ ዳር ፈጣሪ የሚመሰገንበት መሆኑ ከተፈጥሮ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ መሆኑን ያሳያል። ይሁንና ኢሬቻ ደረጃው፣ ስፋቱ፣ ጥልቀቱ በየሰላም አድማሱ የተለያየ ቢሆንም ሰው ከራሱ፣ ከጎረቤቱ በመጨረሻም ከተፈጥሮ ጋር በአንድ የእርቅ ፣ የሰላም፣ የመቀባበል ፣ ወዘተ… ማዕድ ቀርቦ የሚቋደስበት ስለመሆኑ አያጠያይቅም።

ፕሮፌሰር ሕዝቅያስ”…በተለያዩ ማህበረሰቦች ሀገር ግንባታ Nation Building በመሀላቸው ያለውን ልዩነት አጥብቦ ግድግዳዎችን አፍርሶ የጋራ ማንነት መገንባት ነው። …” ይላሉ። የሀገር በቀል እውቀቶችና የባህል ተመራማሪው አቶ አብዱልፈታህ አብደላ ይሄን የፕሮፌሰር ሃሳብ ይጋራሉ። በዓሉ በአዲስ አበባ ሌሎችን የማህበረሰብ ክፍሎች ባሳተፈ አግባብ መከበሩ ለሀገረ ግንባታ መሠረት ጥሏል ማለት ይቻላል ሲሉ ዘላቂ ፋይዳውን ያመላክታሉ። የጋራ የሆኑ እሴቶችን ባህሎችን እያጎለበትን እያሳደገን በሄድን ቁጥር መተዋወቅ፤ መከባበር ፤ መቀባበል ስለሚጨምር እኔነት በእኛነት እየተተካ ስለሚሄድ ለሀገርም ሆነ ለሀገር መንግሥት ግንባታ እርሾ እንደሚሆን ተመራማሪው ያስረዳሉ።

ዛሬ ከምንገኝበት መንታ መንገድ ላይ የደረስነው ባህሎቻችንን እሴቶቻችንን ለሀገር መንግሥትም ሆነ ለሀገር ግንባታ ባለማዋላችን ነው ሲሉ አቶ አብዱልፈታህ ይሞግታሉ። ኦቦ ሙሉጌታ በበኩላቸው እንደ ዓድዋ ያሉ የድል በዓሎቻችን ፣ ኢሬቻ ፣ ሻደይ፣ አሸንዳ፣ ፍቼ ጨምበላላ ፣ ጊፋታ ፣ ወዘተረፈ አንድ የሚያደርጉን ባህሎች በበዙ ቁጥር ኢትዮጵያዊነታችን ይጠናከራል። ከተገኘንበት ብሔር ይልቅ ኢትዮጵያዊነታችን እየገዘፈ ይሄዳል። እየተዋሀድን ፣ እየተቀባበልን፣ እየተከባበርን በሄድን ቁጥር እየተዋደድን እንሄዳለን አንድነታችንም በዚያው ልክ ይጎለብታል ሲሉ ይጠቁማሉ።

እንደ መውጫ

መስቀልንም ሆነ ኢሬቻም ወይም ጊፋታ ፣ መስቀላዮም ሆነ ፍቼ ጨምበላላ አሸንዳ ሻደይም ሆነ ሶለል ፣ ወዘተረፈ ሲከበሩ በተቻለ መጠን ከፖለቲካዊ አንድምታ ጋር ላለማቆራኘት ጥረት ሊደረግ ይገባል። በተወጠረች ፖለቲካዊ ገመድ በጥበብ በማስተዋል መጓዝ ግድ ይለናል። እሴቶቻችን ባህሎቻችን በራሳቸው ሙሉ፣ ጮኸው የሚናገሩ፣ ከሩቅ እንደ ቀስተ ዳመና ደምቀው የሚታዩ ስለሆኑ ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ ማጋጌጪያ አያሻቸውም። ቱባ መሆናቸው በራሱ ሙሉኡ አድርጓቸዋልና። አቶ አብዱልፈታህ ኢሬቻ ከበርካታ ዓመታት በኋላ ወደ አዲስ አበባ ይዞልን የሚመለሰው ምስጋናን፣ ይቅርታን ፣ ሰላምንና አንድነትን እንጂ ሌላ አጀንዳን ሊሆን አይገባም ይላሉ።

ሆኖም የክልል ሰንደቅ አላማ እና የፓርቲ አርማ በማንገብ ፖለቲካዊ ቡልኮ መደረቡ ተገቢ አይደለም። ይህ ከኢሬቻም ሆነ ከሌሎች በዓላት እሴቶች ጋር የሚጣረስ ከመሆኑ ባሻገር አቃፊነቱ ላይ ጥያቄ ፣ ብዥታ ፣ ግርታ ሊያስነሳ ይችላል። ከባህላዊ ፣ እሴታዊ አንድምታው ይልቅ ፖለቲካዊ ቱማታው ላይ ጊዜያዊ ነጥብ ለማስመዝገብ የሚደረግ መሽሎክሎክ ፊት ሊነሳ ይገባል።

ከሀገራዊ ፣ ከቀጣናዊ ፣ ከአህጉራዊና ከዓለም አቀፋዊ ስትራቴጂና ሕልማችን አንጻር አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳይኖረው ሃይማኖትንና በዓላትን ለአማኙና ለተከታዩ መተው ሊበረታታ ይገባል። በነገራችን ላይ ሃይማኖትንና ባህልን ከፖለቲካ ጋር የማጣቀስ አባዜያችን ትናንት የተጀመረ አይደለም። የዋለ ያደረ አባዜ እንጂ። ይህ ቅርሻ በዜጎች መካከል መጠራጠርን፣ ልዩነትን የሚያነብር ስለሆነ ሰከን ብሎ ማሰብ ይገባል። ለብሽሽቅ፣ ለእልህ ፖለቲካ በር እንዳይከፍት ጥንቃቄ ማድረግም ያስፈልጋል።

ከሁሉም በላይ ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ላልገነባች ሀገርና ሕዝብ ፖለቲካዊ ትክክለኝነት Po­litical Correctness የልብ ትርታዋ ሊሆን በተገባ። ሆኖም በገዥው ፓርቲም ሆነ በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአፍ ወለምታ፣ ግራ ቀኙን ካለማመዛዘን፣ የመራጭን constituency ቀልብ ለመግዛት ፣ “የአንቂን” Activist ቡራኬ ለማግኘት የሚፈፀሙ ፖለቲካዊ ስህተቶች ሀገርን ያልተገባ ዋጋ ሲያስከፍሉት ኑረዋል።

አንዳንድ ፖለቲከኞቻችን ለጭብጨባ ተሟጋች ነን ባዮች ለሰብስክራይብና ለላይክ ሲሉ በስሜት ከመጋለብ ዛሬም ሳይረፍድ ራሳቸውን በልጓም ፣ በልባብ ሊገቱ ይገባል። ወደ መነጋገሪያው ቀርቦ አንደበትን ከመክፈት በፊት ሁለት ሦስቴ ማሰብና ከስሜታዊነት መታቀብ ያስፈልጋል። ገና ብዙ ያልተሻገርናቸው ሸለቆዎች፣ ገደሎች አሉብንና በእንቅርት ላይ … እንዳይሆን አበክረን ልንጠነቀቅ ይገባል። ከጊዜያዊ ድል ዘላቂውን የሀገርና የሕዝብ ጥቅም ማስቀድም ትልቁን የተስፋ ስዕል አሻግሮ ማየት ያስፈልጋል።

ታዋቂው አሜሪካዊ የጥቁሮች መብት ተሟጋችና የሰላማዊ ትግል ሐዋርያ ማርቲን ሉተር ኪንግ “… እያንዳንዳችንን በቀጥታ የሚጎዳ ሁላችንንም በተዘዋዋሪ ይጎዳል። …”ሲል የተናገረው ሰሞነኛውን አውድ ይዋጃል ብዬ ስለአሰብሁ አጋርቼ ፤ በመጀመሪያ ኦቦ ድርቢ በመቀጠል ኦቦ ሙሉጌታ ታች አምና ባስተላለፉት አባታዊና ወንድማዊ ዘመን ተሻጋሪ ምክር መጣጥፌን ልቋጭ ። “… ባለቤቱ የእኔ ነው በማለት ትልቅ ቦታ የሰጠውን በማጣጣል ጣትን መቀሰር አይገባም ።”

ከሁሉም በላይ ኢሬቻንም ሆነ መስቀልን በዓመት አንድ ጊዜ በአደባባይ ማክበር ብቻ ሳይሆን በዕለት ተዕለት ኑሯችን እንተርጉማቸው። እንኑራቸው። በልካቸው እንገኝ። ልካቸው ሰላም ፣ እርቅ ፣ ይቅርታ፣ መቀባበል ፣ መግባባት ፣ አብሮነት ፣ አንድነትና ሰው ሆኖ መገኘት ነውና ።

ፈጣሪ የከርሞ ሰው ይበለን !

አሜን ።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)

አዲስ ዘመን መስከረም 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You