ኢሬቻ ከመልካ እና ቱሉ የተጋመደ፤ለሰላምም የተወደደ

የኦሮሞ ሕዝብ ፍቅር፣ ወንድማማችነት እና ዕርቅን በሚገነቡ ባህላዊ ዕሴቶች እጅጉን የበለጸገ ሕዝብ ነው፡፡ ከእነዚህ ድንቅ ባህላዊ ዕሴቶች መካከል አንዱ የኢሬቻ በዓል ነው ፡፡ ኢሬቻ – የምስጋና፣ የዕርቅ እና የሰላም ፣ የፍቅር፣ የይቅርታ እና የአንድነት በዓል ነው። ሁሉን አስተካክሎና ውብ አድርጎ የፈጠረ ፈጣሪ የሚመሰገንበት ፣ ቀጣዩ ጊዜ ብሩህ እንዲሆን መልካም ምኞት የሚቀርብበት ፤ ትናንትን የማመስገኛ እና ነገን ሰላም የማድረጊያ በዓል ነው።

ክረምት መውጣቱን ተከትሎ በበርካታ የኦሮሞ ሕዝብ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል የራሱ የሆኑ ምስጢራዊ ይዘቶች እንዳሉት ይነገራል፡፡ ይኼም ኢሬቻ የተፈጥሮ (የፍጥረታት ሕግና ሥርዓት) በዓል እንደሆነ ይገለጻል ፡፡ በመሆኑም “መልካና ቱሉ “የራሳቸው ክብር፣ ሕግ እንዳላቸው ስለሚታመን ኢሬቻ የፈጣሪ ‘ዋቀ” ሥርዓት ሕግና ትዕዛዝ የሚሞላበት እንዲሁም ቀጣይነት እንዲኖረው የሚከበር በዓል ነው ፡፡

በወርሃ መስከረም የሚከበረው ኢሬቻ ክረምት አልፎ ወደ በጋ ሲሻገር ምሥጋናና ምልጃ የሚቀርብበት ሲሆን ፤ በበዓሉ በዋዜማው የሙዳ ሥርዓት (Sirna Mudda) ይከናወናል፡፡ በአባ ገዳዎችና በአባ መልካዎች የሚከናወኑ የምሥጋና መስዋዕቶች፣ ጸሎት፣ ምርቃትና ዕርቅ በሐይቁ ውሃ መጠመቅ የሥነ ሥርዓቱ አካል ናቸው ፡፡ በዕለተ ቀኑ ክብረ በዓሉ ሲከበር ልጃገረዶች ‹‹ማሬዎ ማሬዎ›› እያሉ የሚዘምሩት፣ ይኼም ማለት ሁሉም ነገር የተፈጥሮ ሥርዓትን ጠብቆ ዞሮ መምጣቱን ለመግለጽ እንደሆነ ጥናቶቹ ያስረዳሉ ፡፡

በዚህ በዓል በፈጣሪና ፍጥረት መሀል ያለው ሥርዓት ሳይቋረጥ ሒደቱን ጠብቆ በመካሄዱ የሚከበር የምሥጋናና የምልጃ በዓል እንደሆነ ለማስረዳት ነው፡፡ ምልጃውና ምሥጋናው ክረምትና በጋ ፣ ቀን ሌሊት፣ ብርሃንና ጨለማ፣ ልጅነትና እርጅና እንዲሁም ሕይወትና ሞት የማያቋርጡ ሒደቶች እንደሆኑ ለማሳየት ነው፡፡ አባ ገዳዎችና አባ መልካዎች ወንዙ ዳር ሆነው ታላቅና ታናሹን እንደ ቅደም ተከተላቸው ይመርቃሉ፡፡ መልዕክት ያስተላልፋሉ። ‹‹ኢሬቻ ሰላም ነው፣ ሰላም ጥልቅ ትርጉም አለው፣ ሰው ከሰው ጋር፣ ሰው ከራሱ ጋር፣ ሰው ከተፈጥሮ ጋርና ሰው ከፈጣሪው ጋር ሰላም ሊኖረው ይገባል፤›› የሚለው ጽንሰ ሐሳብ የክብረ በዓሉ ጭብጥ ነው፡፡

በገዳ ሥርዓት በግልጽ እንደተቀመጠው፤ የኢሬቻ በዓል የኦሮሞ ኅብረ ባህል የኦሮሞ ብዝኃነትና አንድነት በአንድ ቦታ የሚታይበት ልዩ በዓል የሆነው ኢሬቻ በዓመት ሁለት ጊዜ ይከበራል፡፡ አንደኛው ኢሬቻ ቢራ ወይም ኢሬቻ መልካ ሲሰኝ፣ ይኼም የክረምት ወቅት አልፎ መፀው ሲገባ የሚከበር ነው። በአብዛኛው ከመስከረም እስከ ኅዳር ድረስ ይከበራል። በመስከረም አጋማሽ ላይ ከሚከበረው ከመስቀል በዓል ማለትም አይኖ ወይም ጉባ ኮርማ በኋላ እሑድ ቀን ላይ ይከበራል፡፡

ኦሮሞ ከጥንት ጀምሮ የሚያከብረው መስቀል ‹‹እፋኖ›› ወይም ‹‹ጉባ ኦርማ›› በመባል ይታወቃል። ሁለተኛው የኢሬቻ ክብረ በዓል ኢሬቻ ቢራ (መልካ) በሐይቆች ወይም በወንዞች ዳር የሚከበር ነው፡፡ አደይ አበባ፣ ለምለም ሳርና ዘንባባ ተይዞ የሚከበር ሲሆን የመጪው ወቅት መለያው ነው ፡፡ ይኼም ከከባዱ የክረምት ወራት በሰላም ያሻገራቸውን ዘመድ አዝማድ መገናኘት በመቻላቸው፣ ክረምት የዘሩት የእህል ቡቃያ በማየታቸው ፈጣሪያቸውን ‹ያመሰግናሉ፡፡ ከዚያም መጪው የበጋ ወራት የሰላምና የጤና እንዲሆንላቸውና የበቀለው ቡቃያ ፍሬ እንዲያፈራ ይለምናሉ፡፡ የሁለቱም በዓላት የአከባበር ሥርዓትና ልማድ ተመሳሳይ ሲሆን የሚከበርበት ወቅት ይለያያል፡፡

መሠረቱን ምስጋና ሰላም ላይ ያደረገው የኢሬቻ በዓል የኦሮሞ ባህል ዋነኝ መሰረት ከሆነው የገዳ ሥርዓት የሚቀዳ ማህበራዊ እሴት እንደሆነ ይነገራል፡ ፡ በኦሮሞ ባህል ማዕከል የታሪክ ተመራማሪ የሆኑት አቶ አለማየሁ ኃይሌ በአንድ ወቅት ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፤”በገዳ ሥርዓት ውስጥ በርካታ ተቋማት (Institutions) ያሉ ሲሆን፤ ኢሬቻ ደግሞ አንዱና አንኳሩ ማኅበራዊ ተቋም (Institutions) ነው፡፡ ኢሬቻ የጋራ የምስጋና ቀን ነው፡፡ ኦሮሞ በጋራ ወደ አደባባይ ወጥቶ ፈጣሪውን የሚያመሰግንበት በዓል ነው፡፡

ፈጣሪ አምላክ ከዝናባማው፣ ከጭጋጋማውና ከጨለማው ወቅት ወደ ብራው ወቅት ስላሸጋገረ ተሰባስቦ ምስጋና የሚያቀርብበት ነው፡፡ ስለበደለው ነገር እርቅ የሚጠይቅበት እና እጅ የሚነሳበትም ነው” ሲሉ ክብረ በዓሉ ሕዝቦችን በማስተሳሰር ረገድም ከፍተኛ ሚና እንዳለው ያመላከቱት፡፡ በርግጥም ኢሬቻ ሰላም፣ ፍቅር ፣ ምሥጋና ምልጃ መገለጫዎቹ ናቸው ፡፡” ሰው ከሰው ጋር፣ ሰው ከራሱ ጋር፣ ሰው ከተፈጥሮ ጋር ፤ ሰው ከፈጣሪው ጋር ሰላም ሊኖረው ይገባል ›› የሚለው ጽንሰ ሃሳብ የክብረ በዓሉ ጭብጥ ነው ፡፡ ከበዓሉ የአከባበር ሥርዓትና ክንውንም የምንረዳው ይሄንኑ ነው፡፡

የኢሬቻ በዓልን ኦሮሞዎች የተለያዩ ሃይማኖቶች ተከታዮች የክርስትና እምነት ተከታዮች ፣ ሙስሊሞችና ዋቄፈታዎች በጋራ ያከብሩታል፡፡ ሰላም ብቻ፣ ፍቅር ብቻ፣ አንድነት ብቻ ፣ ልምላሜ የሚሰበክበት እንደመሆኑ፤ እነዚህ በዓሉ ባህላዊ ትውፊቶች አሁንም ድረስ ከመልካ እና ቱሉ ዘንድ እንደዘለቁ ናቸው፡፡

አልፎ አልፎ የምናስተውላቸው የበዓሉን ድባብ የሚያደበዝዙ ክስተቶች ቢኖሩም፤ በዓሉ በመላው የኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ የምስጋና በዓል በመሆን በድምቀት እየተከበረ ይገኛል፡፡ ስለዚህ በዓሉ ካለው ከፍያለ ማህበራዊ እሴት አኳያ ባህላዊ ቱፊቶቹን ጠብቆ ከትውልድ ትውልድ እንዲተላለፍ በተለይ የማኅበረሰቡ ሽማግሌዎችና አባገዳዎች ከፍያለ ኃላፊነት እንዳላባቸው ይታመናል።

በዓሉ እንደሀገር የሁላችን የጋራ በዓል ከመሆኑ አንጻር ሁላችን ልንከባከበው፣ እና ልናሳድገው ይገባል፡፡ለበዓሉ ድምቀት በመሆንም ኢትዮጵያዊ ቀለሙን ልናደምቀው ይገባል፡፡ የአንዳችን በዓል ለሌላችን ውበትና ድምቀት ነው። ብንነግድ እናተርፍበታለን፡፡ ብናስተዋውቀው እንታወቅበታለን፡፡ በዓሉ የሰላም፣ አንድነት ፍቅር መሆኑን ማሳየት ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁላችንም የሞራል ግዴታ አለብን፡፡ መልካም ኢሬቻ!

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

አዲስ ዘመን መስከረም 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You