ኢሬቻ- ታላቅ የምስጋና በዓል!

 በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ በየዓመቱ በወርሃ መስከረም ከሚከበሩ በዓላት መካከል አንዱ የኢሬቻ በዓል ነው፡፡ ኢሬቻ ደግሞ የምስጋና በዓል ነው፡፡ ይሄም ዘመንን በዘመን ለለወጠለት፤ ጨለማውን ጊዜ በብርሃን ለተካለት፤ ከባዱን የክረምት ወር አሳልፎ ለጸደዩ ላሸጋገረው፤ የደፈረሰውን ወንዝ አጥርቶ፣ ጉልበተኛውን ወንዝ ገርቶና አጉድሎ ከወዳጅ ዘመን የሚገናኝበትን ወቅት ስላመጣለት ለፈጣሪው ምስጋናን የሚያቀርብበት በዓል ነው፤ኢሬቻ፡፡

ማኅበራዊ ደረጃ እና የእድሜ ልዩነት ሳይፈጠር የኦሮሞ ሕዝብ ለዘመናት በጋራ ሲያከብር የኖረው ይሄ የምስጋና ማቅረቢያው የኢሬቻ በዓል፤ የማኅበረሰቡ ባህል እና ፍልስፍና፣ ወግና ሥርዓት በሚንጸባረቅባቸው ከፍያሉ ትውፊቶች የዳበረ ነው። የሰላም፣ የመተሳሰብ፣ የመደጋገፍ፣ የፍቅር፣ የአብሮነት፣ የወንድማማችነት፣ የእኩልነት፣ የአመስጋኝነት፣ ስለ ፈጣሪ ክብር በአንድ ቆሞ ምስጋናን የማቅረብ ልዕልና መገለጫ አውድም ነው፡፡

የኦሮሞ ሕዝብ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ባይተዋር አለመሆኑን፤ ከቀደምቶቹ ቀድሞ ዴሞክራሲን በራሱ አውድ ሲተገብረው መኖሩን ለዓለም ያሳየበት፣ እንዲሁም የማይዳሰስ ቅርስ ተደርጎ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ የተመዘገበው የገዳ ሥርዓት አንዱ አካል የሆነው የኢሬቻ በዓል፤ በዚሁ ልክ በዘመናት ሂደት ውስጥ እሴቱን ጠብቆ ከትውልድ ትውልድ ሲወራረስ፣ ዛሬም ይሄንኑ ልዕልናውን እንደጠበቀ ከፍ ባለ ድምቀት እየተከበረ ይገኛል፡፡

የኢሬቻ በዓል ዛሬ ላይ የኦሮሞ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያውያን የወል ሀብት ወደመሆን እየተሸጋገረ ያለ፤ በዚህም ትልቅ የሀገርና የዓለም ሀብት መሆን የሚችልና፣ ራሱን ችሎም በዓለም አቀፍ ቅርስነት መመዝገብ የሚገባው ሀብት መሆኑ እየተገለጠ ነው፡፡ ይሄንኑ ታሳቢ በማድረግም የዓለም ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብም ሰፋፊ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡

ኢሬቻ የዓለም ቅርስ ሆኖ ሊታወቅ ይገባል የሚባለውም ያለምክንያት አይደለም። ምክንያቱም ኢሬቻ – በዓሉ የተጣላ የሚታረቅበት፣ ቂሙን ትቶ በነጻ ልቦና ፈጣሪ ንጹህ ወዳደረገው የውሃ አካል ሄዱ ንጽህናውን የሚያጸናበት እሴት ያለው ሀብት ነው። ከዚህም ባለፈ የኦሮሞ ሕዝብ ከራሱ አልፎ ለመላው የሰው ልጅ ሰላምና ደኅንነት ፈጣሪውን የሚለምንበት፤ የሚያመሰግንበት በዓል በመሆኑ ነው።

ኢሬቻ ፈጣሪን ከማመስገንና ከእርቅ ባለፈም፤ እንደ ሀገር የኢትዮጵያዊነት አንድ ትልቅ እሴት በመሆን ሀገራዊ አንድነትን በማጽናት የሚኖረው ፋይዳ የላቀ ነው። በተለይም በሀገራዊ የማንነት ግንባታ ሂደት ውስጥ ሊኖረው የሚችለውም አስተዋጽኦ የጎላ ነው።

በዓሉ በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ የሚታደሙት፤ ሴቶች፣ ወንዶች፣ ህጻናት፣ ወጣቶች፣ ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች እና ሃደ ሲንቄዎች በውብ አለባበስ ደምቀው፤ ልብን በሚሰርቅ ዜማ ታጅበው የሚያከብሩት የውበት ሰገነት የሆነ በዓልም ጭምር ነው፡፡

አደይ አበባ እና ርጥብ ሳር ተይዞ በአባ ገዳዎች እና ሃደ ሲንቄዎች ‘መሬሆ’ እየተባለ ውብ ዝማሬ የሚሰማበት፤ ወጣቶች ባህላዊ ጭፈራ እና ዘፈን የምስጋና ቀናቸውን የሚያደምቁበት፤ ባህላዊ የጥበብ መድረክ መሆኑም የቱሪዝም መስህብ በመሆን በኢኮኖሚ ፋይዳው፤ መልካም ገጽታን በመገንባትም ዲፕሎማሲያዊ አበርክቶው ሲታይ እንደ ሀገር የሚኖረው ፋይዳም የጎላ ነው፡፡

በዚህ መልኩ የአብሮነት፣ የሰላምና ወንድማማችነት ድባብን ተላብሶ የሚከበረው፤ ባህላዊ እና የውበት መገለጫ እሴት ምንጭ የሆነው የኢሬቻ በዓል ከሀገር አልፎ ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኝ እየተደረገ ካለው ጥረት መልካም የሚባል ቢሆንም፤ በዓሉ የቱሪዝም ምንጭ፣ የሀገር ገጽታ መገንቢያ አውድ ሆኖ እንዲያገለግል ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ያስፈልጋል፡፡

ከሁሉም በላይ ደግሞ የቀደመ ባህል እና ሥርዓቱን ጠብቆ እንዲከበር ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ፡፡ ለዚህም መላው ሕዝባችን፤ በተለይ ደግሞ የኦሮሞ ማኅበረሰብ የበዓሉ እሴት ሳይበረዝ እንዲቀጥል በዓሉን በፍቅር፣ በሰላምና በአንድነት ሊያከብረው ይገባል። ለኅብረብሔራዊ አንድነት ግንባታና አብሮነት ካለው አስተዋጽኦም አኳያ፤ ባህላዊ እሴቶቹ ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፍ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት! መልካም የኢሬቻ በዓል!

አዲስ ዘመን መስከረም 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You