ሕክምናን ከትምህርት፣ የቡና ንግድን ከቤተሰብ

ሴቶች በማንኛውም የሥራ ዘርፍ ተሰማርተው መስራት እንደሚችሉ በተለያዩ መስኮች ተሰማርተው ውጤታማ ከሆኑ ሴቶች መረዳት ይቻላል። ይህን የሚያደርጉት ደግሞ በቤት ውስጥ ኃላፊነት ተጠምደው ውለው እያደሩም ነው። አደባባይ እንዳይወጡ፣ በየትኛውም ሥራ ተሰማርተው እንዳይሰሩ በሚያደርጉ ተጽእኖዎች ሳቢያ የሥራ ተሳትፏቸው እንዲጠብ ተደርጎ የኖረ ቢሆንም፣ ይህን አመለካከት ሰብረው በመውጣት በተሰማሩባቸው መስኮች ውጤታማ የሆኑ በርካታ ሴቶችን በአብነት መጥቀስ ይቻላል።

ሴቶች በራሳቸው በቀጥታ ከሚያበረክቱት ድርሻ በዘለለ በየትኛውም የወንዶች ስኬት ውስጥ ሰፊ ተሳትፎ አላቸው። ‹‹ከእያንዳንዱ ስኬታማ ወንድ ጀርባ አንዲት ሴት አለች›› የሚባለውም በዚሁ ምክንያት ነው። ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ ይህ አስተዋጿአቸው በይፋ እውቅና ሲሰጠው አይስተዋልም። ያም ቢሆን ሴቶች በማንኛውም የሥራ መስክ የጀርባ አጥንት ሆነው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን ለማሳካት የሚቀድማቸው የለም። በተለይም በግብርናው ዘርፍ ሴቶች ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ስለመሆኑ መረጃዎች ያመላክታሉ።

there isn?ˉt any reason not to have one of our company website on your wrist.we have top quality see this site.compared to various other brandnames for sale reddit contains a large reputation.

ከግብርና ሥራ አንዱ በሆነው በቡና ሥራ ተሰማርተው የኢትዮጵያን ቡና ከምርት ጀምረው ለዓለም ገበያ በማስተዋወቅ ረገድ ጉልህ አበርክቶ ያላቸው ሴቶች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም። ከእነዚህ መካከልም የጡዊ አማሮ ቡና ላኪ ድርጅት መስራችና ባለቤት ወይዘሮ ቅድስት ብሩ አንዷ ናት። ቡና አምራች ከሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች አንዱ በሆነው ደቡብ ክልል ጌዲኦ ዞን ዲላ ከተማ ተወልዳ ያደገችው ወይዘሮ ቅድስት፤ የሕይወት ጥሪዋ ከሆነው የሕክምና ሙያ ወጥታ ወደ ቡና ሥራ ተሰማርታም ውጤታማ መሆን ችላለች።

ወይዘሮ ቅድስት ከሕክምና ሙያ ወጥታ ወደ ቡና ሥራ የገባችው በቤተሰቦቿ ምክንያት ነው። የዛሬዋ የስኬት ገጽ እንግዳችን ለበርካታ ዓመታት ካገለገለችበት የሕክምና ዘርፍ ወጥታ ከምርት ጀምሮ ባለው ሂደት ቡናን አዘጋጅታ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እያቀረበች ትገኛለች።

የሕክምና ሙያ ነብሷ አጥብቃ የምትሻው የሙያ ዘርፍ እንደሆነ የጠቀሰችው ወይዘሮ ቅድስት፤ በነርሲንግ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪዋን በያዘች ማግስት በቅዱስ ጳውሎስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከስድስት ዓመታት በላይ አገልግላለች። ወላጅ አባቷ ያቀረቡላትን የንግድ ሥራ አሻፈረኝ በማለት ነበር ያኔ በእጅጉ አጥብቃ ትወደው ወደ ነበረው የሕክምና ዘርፍ የገባችው። በሕክምናው ዘርፍ ሕዝቧን ማገልገል በመቻሏ ደስተኛ ነበረች።

ቤተሰቦቿ ቡና አምራችና አቅራቢ እንደመሆናቸው የቡና ሥራን በቅርበት እየተመለከተች ያደገችው ወይዘሮ ቅድስት፤ የሕክምና ሥራዋን እየሠራች የቤተሰቦቿን የቡና ንግድ ታግዝ ነበር። በምርትና አቅራቢነት የተሰማሩት ወላጅ አባቷ ቡናውን ወደ አዲስ አበባ አምጥተው በሚሸጡበት ወቅት ከሕክምና ሥራዋ ጎን ለጎን ቤተሰቦቿን ማገዟ ወደ ቡና ሥራ ውስጥ ቀስ በቀስ እንድትገባ አስገድዷታል።

በቡና ልማትና ኤክስፖርት ዘርፍ የተሰማሩት ወላጅ አባቷ የቡና ሥራውን እንድታግዛቸው ከፍተኛ ፍላጎት የነበራቸው መሆኑን ያስታወሰችው ወይዘሮ ቅድስት፤ በሙሉ አቅሟ ለማገዝ ወስና ከቡና ሽያጭ በተጨማሪ በቡና ዝግጅትና በቡና ቅምሻም እንዲሁ ያላትን ተሳትፎ ከፍ አድርጋለች። በዚህ ጊዜ ‹‹የነብስ ጥሪዬ ነው›› የምትለውን የህክምና ሙያ ገታ በማድረግ የሙሉ ጊዜ ሥራዋ አድርጋ ከምርት እስከ ኤክስፖርት ያለውን የቡና ሥራ ተቀላቅላለች።

ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ሙሉ ጊዜዋን ለሥራው የሰጠችው ወይዘሮ ቅድስት፤ እስከ 2008 ዓ.ም ድረስ በወላጅ አባቷ የቡና እርሻ በልማቱ በስፋት ተሰማርታለች፤ በኤክስፖርት ዘርፍ ላይ እየሰራች ትገኛለች። በአሁኑ ወቅት ግን የእርሻ ሥራው በተለያዩ ምክንያቶች መቋረጡን ጠቅሳለች። ይሁንና በ2012 ዓ.ም የቡና ፈቃድ በማውጣት ‹‹ጡዊ አማሮ ቡና ላኪ›› የተሰኘውን ኤክስፖርት ኩባንያ አቋቁማ እየሰራች ትገኛለች። ዘርፉ የምታውቀው በመሆኑ ብዙ እንዳልከበዳት የጠቀሰችው ወይዘሮ ቅድስት፤ መነሻዋን በደቡብ ክልል አማሮ በማድረግ ምርቱን አዘጋጅታ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ተሰናዳች።

በወቅቱ ቢሮ ከፍታ ሁለት ሠራተኞችን በመያዝ ወደ ሥራው የገባች ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ለ12 ሴቶችና ለአምስት ወንዶች በድምሩ ለ17 ሰዎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር ችላለች። በአማሮና ይርጋጨፌ አካባቢ የሚመረተው ቡና ታጥቦ፣ ደርቆና ተለቅሞ የሚዘጋጅበት ማጠቢያ ማሽን በመትከል የተዘጋጀ ቡና ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ታቀርባለች።

“የቡና ሥራን ከታች ከእርሻው ጀምሮ አውቀዋለሁ” የምትለው ወይዘሮ ቅድስት፤ የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ መሆን እንዲችል በጥራት መመረትና መዘጋጀት እንዳለበት ታስገነዝባለች። ለዚህም መንግሥትን ጨምሮ በዘርፉ የተሰማራ ማንኛውም ሰው ኃላፊነት እንዳለበት ገልጻለች። በተለይም የቡና ዋጋ በዓለም ገበያ እየወረደ ባለበት በአሁኑ ጊዜ ተወዳዳሪ ለመሆንና ከፍ ያለ ዋጋ እንዲያወጣ ለማድረግ ቡናውን በጥራት ማዘጋጀት እንዳለ ሆኖ በሀገር ውስጥ የሚገዛበት ዋጋና ኤክስፖርት የሚደረግበት የተመጣጠነ መሆን እንዳለበት ገልጻለች።

ከዓለም ገበያ ጋር እኩል መወዳደር እንዲቻል ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ በተጨማሪ ጥራትና ዋጋ ላይ መሰራት እንዳለበት የምታስገነዝበው ወይዘሮ ቅድስት፤ ምርቱን በሁለት መንገድ ለገበያ እንደምታቀርብም ነው የምትገልጸው። አንደኛው አቅርቦት ነው፤ ይህም ማለት ቡናውን በማዘጋጀት ለላኪዎች ማቅረብ ነው። ሁለተኛው ዝግጅቱን የጨረሰ ቡና በቀጥታ ወደ ውጭ ገበያ መላክ ሲሆን፣ ይህንንም ማድረግ መቻሏን አስረድታለች።

እሷ እንዳለችው ፤ የቡና ማጠቢያና ማዘጋጃው ያለው በደቡብ ክልል አማሮና ይርጋጨፌ ነው። ቡናውን ከአካባቢው አርሶ አደሮች በቀጥታ ታገኛለች። አማሮ፣ ይርጋጨፌና ወናጎ በሚባሉ አካባቢዎች ከሚገኙ 86 ቡና አምራች አርሶ አደሮች ጋር ትስስር መፍጠርም ችላለች። እነዚህ አርሶ አደሮች በቋሚነት ያመረቱትን ቡና ለእሷ ያቀርባሉ። በተጨማሪም ሌሎች አርሶ አደሮች በወቅቱ ባለውና በተተመነው ዋጋ መሰረት ተገቢውን ክፍያ ፈጽመው ቡና በመረከብ ከአርሶ አደሩ የሰበሰቡትን ቡና በአካባቢው በሚገኘው የቡና ማጠቢያና ማበጠሪያ ማሽን አጥበው አድርቀውና ለቅመው ካዘጋጁ በኋላም እንደወቅቱ ገበያ በሚያዋጣት መንገድ ቡናውን ለገበያ ታቀርባለች።

የዓለም የቡና ዋጋ እነሱ ገዝተው ካዘጋጁበት ዋጋ ጋር ተመጣጣኝ ከሆነ በቀጥታ ኤክስፖርት እንደሚልኩ የጠቀሰችው ወይዘሮ ቅድስት፤ 70 በመቶ የሚሆነው ገበያ አውሮፓ ሀገራት ቤልጅየም፣ ጀርመንና ፈረንሳይ መሆኑን ነው የገለጸችው። አሁን አሁን ደግሞ ወደ ኤዥያ ሀገራት ጭምር ገበያዋን እያሰፋች ትገኛለች። ጡዊ አማሮ ቡና ላኪ በዓመት በአማካኝ ከ1000 እስከ 1500 ቶን ቡና የማዘጋጀትና የማቅረብ አቅም እንዳለው የጠቀሰችው ወይዘሮ ቅድስት፤ ከ300 እስከ 350 ቶን ያህል ቡና ደግሞ ለውጭ ገበያ እያቀረበች መሆኑን አጫውታናለች።

ወደፊትም አዳዲስ የገበያ ዕድሎችን ለማግኘት በሀገር ደረጃ የተለያዩ ጥረቶች እንደሚደረጉ ያመላከተችው ወይዘሮ ቅድስት፤ አዳዲስ የገበያ ዕድሎችን ለማግኘት ዓለም አቀፍ በሆኑ ኤክስፖዎች ላይ መሳተፍ አንደኛው አማራጭ እንደሆነ ነው ያስረዳችው።

ለዚህም በቡና ሥራ ላይ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን ሴቶችን ብቻ ያቀፈው ማህበር “women in coffee Ethiopia” ትልቅ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጻለች። እሷ እንዳለችው ማህበሩ፤ የማህበሩ አባል የሆኑ ሴቶች ዓለም አቀፍ በሆኑ ኤክስፖዎች ላይ ተሳትፈው ቡናቸውን መሸጥና ማስተዋወቅ እንዲችሉ በሚያደርገው እገዛ በቡና ሥራ የተሰማሩና አባል የሆኑ ሴቶች የኢትዮጵያን ቡና በተለያዩ የዓለም ሀገራት ተንቀሳቅሰው እየሸጡና እያስተዋወቅ ይገኛሉ።

በተለየ መንገድ ከሴት ቡና አልሚዎችና አቅራቢዎች ብቻ የመግዛት ፍላጎት ያላቸው ዓለም አቀፍ ቡና ገዢዎች ስለመኖራቸው የጠቀሰችው ወይዘሮ ቅድስት፤ ለዚህም ማኅበሩ መኖሩ ጠቃሚ እንደሆነ ነው ያስረዳችው። ሴት ቡና አልሚዎችን ላኪዎችንና አቅራቢዎችን ብቻ ፈልገው የሚመጡ ዓለም አቀፍ ቡና ገዢዎች በማኅበሩ አማካኝነት በቡና ሥራ የተሰማሩ ሴቶችን በቀላሉ ማግኘት እየቻሉ እንደሆነ ጠቅሳ፤ በዚህም ተጠቃሚ እንደሆነች ነው የገለጸችው። ከሴት ቡና ላኪ መግዛት ፈልጎ ከጀርመን ለመጣ ቡና ገዢ መሸጥ የቻለችበትን ሁኔታም ጠቅሳለች።

ወይዘሮ ቅድስት እንዳብራራችው፤ ማኅበሩ በቡና ሥራ የተሰማሩ ሴቶች ዓለም አቀፍ በሆኑ ኤክስፖዎች ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ ብርቱ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። አሁን ላይ ደግሞ በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ዓለም አቀፍ የቡና ኤክስፖ አዲስ አበባ ላይ ማዘጋጀቱ ይዞን ከሚመጣው የገበያ ዕድል በተጨማሪ በርካታ ጠቀሜታዎች ይኖሩታል። ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የተወጣጡ ቡና ገዢዎች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ብቻ ሳትሆን የቡና መዳረሻ እንደሆነች ጭምር የሚረዱበትና ቡናውን ከምርቱ ጀምረው በመረዳት መግዛት የሚችሉበትን እድልም ይፈጥራል።

ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ ቡና ገዢዎች ከሴት ቡና አምራችና ላኪዎች ጋር በቀላሉ መቀራረብ የሚችሉ በመሆኑ በቡና ሥራ ላይ የተሰማሩ ሴቶች ንግዳቸውን ለማሳደግ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። ከዚህ ቀደም በቡና ሥራ የተሰማሩ ሴቶች በተለያዩ ዓለም ሀገራት ተዘዋውረው ቡና የሚሸጡበትና የሚያስተዋውቁበት መንገድ ረዥምና ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቅ ነበር፤ አሁን ላይ ግን ዓለም አቀፍ የቡና ኤግዚቢሽን በቡና መገኛ ሀገር ኢትዮጵያ ላይ መካሄዱ ለዘርፉ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል። ወይዘሮ ቅድስት እንደ ሀገርም ሆነ በግሏ ከኢግዚቢሽኑ ትልቅ ውጤት ትጠብቃለች።

ለአንድ ሳምንት በሚቆየው ዓለም አቀፍ የቡና ኤግዚቢሽንና ኮንፍረንስ ቡናን መሸጥ፣ ማስተዋወቅና አዳዲስ ገበያን ማግኘት እንደሚቻል የጠቀሰችው ወይዘሮ ቅድስት፤ ቡና የኢትዮጵያውያን ሀብት መሆኑን ለሚመጡት እንግዶች የሚያሳዩበት እንደሆነ ተናግራለች። በተለይም በቡና ሥራ የተሰማሩ ሴቶች እንዲሁም ሀገሪቷም ከኤክስፖው ተጠቃሚ እንደሚሆኑና ትልቅ ዕድል እንደሆነ ጠቁማለች።

ሴቶች በማንኛውም መስክ ውጤታማ ሥራ ይሠራሉ የምትለው ወይዘሮ ቅድስት፤ በተለይም በቡና ሥራ ሴቶች ትልቅ ድርሻ አላቸው ነው የምትለው። ሴቶች ከእርሻ ሥራው ጀምሮ በለቀማ፣ በማጠብና በማቀነባበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸውና ለቡና ሥራ የጀርባ አጥንት እንደሆኑ ነው የገለጸችው። እሷ እንዳለችው፤ ሴቶች በቡና ሥራ ከ80 በመቶ በላይ ድርሻ ያላቸው ሲሆን፤ በተለይም በለቀማ ወቅት ቀይ ቀዩን ቡና ለይቶ በጥንቃቄ ለቅሞ በማቅረብ በኩል ሴቶች ይመረጣሉ።

ቡናን በማዘጋጀትና በመላክም እንዲሁ ሴቶች ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው የምትገልጸው ወይዘሮ ቅድስት፣ ይሁንና የልፋታቸውን ያህል ግን ተጠቃሚ አይደሉም ትላለች። ሴቶች በቡና ሥራ እያበረከቱ ባለው አስተዋጽኦ ልክ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ አስፈላጊና ተገቢ እንደሆነም ታመለክታለች። ለዚህም በዘርፉ የተሰማሩ ሴቶች በአንድነት ተጠናክረው መሥራት እንዳለባቸው ነው የገለጸችው።

በዘርፉ የተሰማሩ ሴቶች እንዲበራከቱ ከቅጥር ጀምሮ ዕድሉን ለሴቶች መስጠት በዘርፉ የተሰማሩትን ወደ ማኅበሩ በማምጣት ማኅበሩ በሚያዘጋጃቸው የተለያዩ ስልጠናዎች ተሳታፊ እንዲሆኑ መረጃ መስጠት እንደሚገባም ነው ያስገነዘበችው። መረጃ ሀብት ነው የምትለው ወይዘሮ ቅድስት፤ ሴቶች መረጃ ካገኙና ዕድል ከተሰጣቸው በማንኛውም መስክ መሥራት የሚጠበቅባቸው እንደሆነ ነው ያመላከተችው።

የነብስ ጥሪዬ የምትለውን የነርሲንግ ሙያ ወደ ጎን በመተው በቡና ሥራ የተሰማራችው ወይዘሮ ቅድስት፣ ዛሬም ድረስ ለሕክምና ሙያ ልቧ ክፍት እንደሆነና በቀጣይም የሕክምና ሥራዋን ጎን ለጎን የማስኬድ ዕቅድ እንዳላት አጫውታናለች። የሕክምና ሙያ ሰዎችን መርዳት ማገዝ በመሆን በእጅጉ የሚያስደስታት መሆኑን ጠቅሳ፤ ማኅበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድም ንቁ ተሳትፎ ያላት መሆኑን ገልጻለች። እሷ እንዳለችው ምርቱን በምታገኝበት አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎችን በተለያየ መንገድ የምታግዝ ሲሆን፤ በተለይም ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ በማሟላት እንዲሁም መንግሥት ለሚያደርገው ጥሪ ምላሽ በመስጠት ማኅበራዊ ኃላፊነቷን እየተወጣች ትገኛለች።

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን መስከረም 26/2016

Recommended For You