ኢሬቻ የፍቅር ፣ የወንድማማችነት እና የአንድነት በዓል

ኢሬቻ ኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ጥንታዊና ነባራዊ ሃይማኖታዊና ባህላዊ የበዓል አከባበር ሥርዓት ሆኖ የዘለቀ በዓመት ሁለት ጊዜ የሚከበር በዓል ነው። ክረምት ሲገባና መስከረም ሲጠባ (ቢራ) የሚከበር ነው። መስረም ሲጠባ የሚከበረው በዓል በሐይቆች በወንዞች ዳር ሆኖ አደይ አበባ፣ ለምለም የወይራ ቀንበጥ፣ እርጥብ ሣር (በአፋን ኦሮሞ ጂደ ይባላል) ተይዞ የሚከበር ባህላዊ ኩነት ነው።

በይበልጥ መስከረም ሲጠባ የሚከበረው ከመስቀል ደመራ በኋላ ባሉት እሁድ መካከል ነው። በቢሾፍቱ በሆራ አርሰዲ ማለትም በአርሰዲ ሐይቅ የአዲሱ ዘመን ኢሬቻ ሚሊዮኖች በተገኙበት በድምቀት ይከበራል። ይህም በብዛት ከጨለማው ክረምት ወደ ቢራ (ሲነበብ ይጠብቃል ) ፀደይ ላሸጋገረ ዋቃን (ፈጣሪን) ምስጋና የሚቀርብበት ነው።

በዝናቡ ምክንያት በወንዞች ሙሌት የተለያዩ ሰዎች፣ ወዳጅ ዘመዶች እንዲሁም በእርሻ ተወጥረው ዘመድ ለመጠየቅ ላልቻሉ ፋታ የሚያገኙበት እና የሚገናኙበትና የሚጠያየቁበት ወቅት በመሆኑ ፈረንጆች የምስጋና ቀን እንደሚሉት ዓይነት Galataa Waqaa (thankfulness of God) ይቆጠራል።

ሲያከብሩም ከላይ እንደጠቀስነው አበባውን እርጥብ ሣሩን የወይራ ቀንበጡን ይዘው ምስጋና በማቅረብ ነው። በዚሁ ኢሬቻ አካባበር ከየአካባቢው የመጡ ኦሮሞዎች ምስጋናቸውን በደስታ በባህላዊ ዘፈኖች፣ ጭፈራዎች በውዝወዜ በግጥሞች በምሳሌያዊ አባባሎች ይገልፃሉ።

አፈንዲ ሙተቂ ባወጡት አንድ የምርምር ጽሑፍ ፤ ኢሬቻ በሐረርጌ ኦሮሞዎች እሬሳ በመባል እንደሚታወቅ ይገልፃሉ። በሁለቱ በዓላት የሚከበሩባቸውን ወቅቶች፣ የየበዓላቱን ዓላማ እና በዓላቱ የሚከበሩባቸውን ዐውዶች ያጠኑ ምሁራን በዓላቱ በጥንት ግብጻዊያንም ይከበሩ እንደነበረ ይናገራሉ።

ይሁንና ተመራማሪዎቹ ‹‹የበዓላቱ ምንጭ ጥንታዊት ግብጽ ነች ወይንስ ከግብጽ በታች የሚኖሩት የኩሽ (ኑቢያ) ሕዝቦች?›› የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ተቸግረዋል። ጥያቄውን አስቸጋሪ ያደረገው የግብጻዊያኑ እምነት ብዝሀ አማልክት (Polytheism) የተቀላቀለበት መሆኑ ነው። በአፋን ኦሮሞ ዋቃ ቶኪቻ ሲባል አንድ አምላክ ማለት ነው። ኩሻዊያኑ ግን “ዋቃ”፣ “ዋቅ፣ “ዋቆ” እያሉ በተቀራራቢ ቃላት ከሚጠሩት አንድ አምላክ በስተቀር ሌሎች አማልክት የሏቸውም።

የእሬሳ እና የደራራ በዓላት በጥንቱ ዘመን ከኦሮሞ ሕዝብ በተጨማሪ የምሥራቅ ኩሻዊያን (Eastern Cushitic People) በሚባሉት የቤጃ፣ የሳሆ እና የሶማሊ ሕዝቦችም ይከበሩ እንደነበረ ተረጋግጧል። እነዚህ ሕዝቦች ቀደም ብለው የእስልምናን እምነት በመቀበላቸው በዓላቱን ማክበሩን ትተውታል። ይሁንና እንደነርሱ የኩሻዊ ቋንቋ ተናጋሪ የሆነው የአፋር ሕዝብ እስከ ቅርብ ዘመን ድረስ የኢሬሳን በዓል ያከብር እንደነበረ ልዩ ልዩ ጥናቶች ያስረዳሉ።

በኢሬቻ ዙሪያ ጥናት ያደረጉ የተለያዩ ምሁራን፤ የኦሮሞ ሕዝብ ምድር እና ሰማይን ለፈጠረው ፈጣሪው ዋቃ ምስጋናውን ለማድረስ የኢሬቻ በዓልን እንደሚያከብር በዚህ ላይ አባ ገዳዎች፣ ሃደ ሲንቄዎች እና የማኅበረሰቡ ባህላዊ መሪዎች እንደሚታደሙ ይጠቅሳሉ። በአጠቃላይ ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ ከክረምት ወደ ፀደይ በሰላም ላሸጋገረው አምላክ ምስጋና የሚያቀርብበት በዓል እንደሆነ ይናገራሉ ።

የኦሮሞ ታሪክ ምሁሩ ዲሪቢ ደምሴን አነጋግሮ ቢቢሲ ባሰራጨው ዘገባ ፤ ‹‹ኢሬቻ ማለት ዋቃ (ፈጣሪ) ማለት ሲሆን በዓሉም ፈጣሪን ማመስገን ነው፤ በዓሉም ማኅበራዊ ደረጃ እና የእድሜ ልዩነት ሳይፈጠር በኦሮሞ ሕዝብ ለዘመናት በጋራ ሲያከበር ቆይቷል።

ኢሬቻ የዘመን መለወጫ በዓልም እንደሆነ፤ የኦሮሞ ሕዝብ ክረምቱን በማለፉ በኢሬቻ ቀን ምስጋናውን ለፈጣሪ እንደሚያቀርቡ፤ በክረምት ወራት ተራርቆ ሳይገናኝ የቆየ ዘመድ አዝማድ መስከረም ላይ ይገናኛል። ሕዝቡም ክረምቱን በፈጣሪ ፍቃድ የሞላው ውሃ ጎድሎ ከዘመድ አዝማድ አገናኝን ብሎ ምስጋና ያቀርባል።

የአንትሮፖሎጂ ባለሙያው ገመቹ መገርሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው ፤ ‹‹ክረምት ሌሊት ነው። ሌሊት ደግሞ ጨለማ ነው። ጨለማ ለአውሬ እንጂ ለሰው ልጅ አይሆንም። ጨለማው ሲነጋ ደግሞ ብርሃን ነው፤ ብርሃን ሲሆን ሃሳብ የለም ደስታ እንጂ። ‹‹መስከረም ጠባ ማለት ይህ ነው ›› በማለት የኦሮሞ ሕዝብ ከክረምት መገባደድ በኋላ የኢሬቻ በዓልን የሚያከብርበትን ምክንያት ያስረዳሉ።

የኦሮሞ ሕዝብ የኢሬቻ በዓልን ለማክበር ሲወጣ እንደ ሣር ወይም አበባ ያሉ እርጥብ ነገሮችን በእጁ ይዞ ይወጣል። ባለሙያው እንዳሉትና ቢሾፍቱ በተለያዩ ዓመታት በዓሉን ሲከበር በግሌ እንደታደምኩትም ‹‹ ቢራን በሪኤ አበቦን ደራሬ ›› እያሉ ሲዘፍኑ አይቻለሁ። በእኔ ግርድፍ ትርጉም ‹‹መስከረም ጠባ ኢዮሃ አበባ›› እንደ ማለት ነው።

ኢሬቻ ሲከበር ዋቄፈናን ጨምሮ ሁሉም የእምነት ተከታዮች ክርስቲያኑም ሙስሊሙም ኦሮሞዎች ይገኛሉ፤ በበዓሉ የሚገኙ የሌሎች ብሔር፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቁጥርም ሰፊ ነው። ኢሬቻ ጥላቻና ሽኩቻ አልባ የፍቅርና የሰላም በዓል ነው። መቃቃርና መናቆር በኢሬቻ አከባበር ቦታ የላቸውም። የብሔሩ አባላት ኢሬቻ ሲያከብሩ እርቅ ፈጽመው ሰላም ወርዶ ጠብ ተወግዶ ነው።

የኦሮሞ አባ ገዳዎች በሄደበት ሁሉ ሕዝቡን እያቀፉ እና እየደገፉ ባህሉን እያስተማሩ በሞጋሳና በጉዲፈቻ ሥርዓት የብሔሩ አባል ያደረጉት ቤት ቆጥሮ አይጨርሳቸውም። የብሔሩም ቁጥር የበዛው በዚሁ መንገድ መሆኑን የታሪክ ሰነዶች ይመሰክራሉ።

መስከረም ሲጠባ በምስጋና የሚከበረው ኢሬቻ ክረምት ከመግባቱ በፊት ልምላሜ በመማፀን ዋቃን ለመለመን በተራራ ላይ በመውጣት በቱለማ ኦሮሞዎች የሚከበር ኢሬቻ በሚል ሳሙኤል ለይኩን ከአምቦ ዩኒቨርሲቲ ያወጡት አንድ ጥናት ያሳያል። ጥሩነህ ረቡማ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሶሻል አንትሮፖሎጂ ዲፓርትመንት ለድኅረ ምረቃ ያወጡት አንድ ጥናትም ይህንኑ የሚያጠናክር ነው።

ሰፊ ተቀባይነት ያለው የኢሬቻ አከባበር በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኝ ነው። ኢሬቻን በተመድ የትምህርት የሳይንስና ባህል ድርጅት ዩኔስኮ ለማስመዝገብ ጥረት ሲደረግ ነበር። ጥረቱ እንዲሰምር የፌዴራል የቱሪዝምና የባህል ተቋማት እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት ምርምር ተቋማት ትኩረት ሰጥተው መሥራት ይጠበቅባቸዋል። ጽሑፋችንን የምናጠቃልለው በኢሬቻ ምርቃት ይሆናል።

 Biyyi biyya nagaa nuuf godhi……….godhi Waaq

ሀገሩን የሰላም ሀገር ያድርግልን ……አድርግልን ፈጣሪ

Xinnaa keenya nuguddisi…………guddisi Waaq

ሕፃናቱን ያሳድግልን ………….. አሳድግልን ፈጣሪ

Guddaan Keenya nuuf haabulu …..bulchi Waaq

ታላቃችን ይደርግልን ………….አድርግልን ፈጣሪ

Barri bara nagaa nuu ta’a…………….godhi Waaq

ዘመኑ የሰላም ዘመን ይሁንልን …………..አድርግልን ፈጣሪ

Barri kan quufaa fi gabbinaa nuuf haa ta’u ………

godhi Waaq

ዘመኑ የጥጋብና የፀጥታ ይሁንልን ፡፡ አድርግልን ፈጣሪ !

 ኃይለማርያም ወንድሙ

አዲስ ዘመን መስከረም 26/2016

Recommended For You