ኢሬቻ የሰላም፣ የአንድነትና ወንድማማችነት ማጽኛ!

 በኢትዮጵያ በተያዘው መስከረም ወር በርካታ በዓላት ተከብረዋል። የአዲስ ዓመት፣ የመስቀል ደመራና የመውሊድ በዓላት በተከታታይ በደማቅ ሥነ ሥርዓትና ፍጹም ሰላም በሆነ መንገድ ተከብረዋል፣ የበርካታ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ማንነት መገለጫ የሆኑ አዲስ ዓመት በዓላትም በደማቅ ሥነ ሥርዓት ሲከበሩ ሰንብተዋል።

ሁሉም በዓላት የበዓላቱ ባለቤቶች፣ የፌዴራል መንግሥቱና የክልል መንግሥታትና የተለያዩ የአስተዳደር እርከኖቻቸውና በዓላቱ የሚመለከታቸው የተለያዩ ተቋማት በተለይም ሕዝቡ ባደረጉት ሰፊ ዝግጅትና ርብርብ በደማቅ ሥነ ሥርዓት በሰላም ተከበረዋል። በእዚህ ስኬት ውስጥ የጸጥታ ኃይሉ ተጠቃሽ ተግባር ያከናወነ ሲሆን፣ የሰላሙ ባለቤት የሆነው መላው ሕዝብ ያበረከተው አስተዋጽኦም ከፍተኛ እንደሆነ ይታመናል።

ኢትዮጵያውያን አሁን ደግሞ በሌላ ደማቅ የበዓል አውድ ውስጥ እየገቡ ናቸው። ይህ በዓል በኦሮሞ ብሔር ዘንድ በደማቅ ሥነ ሥርዓት የሚከበረው የኢሬቻ በዓል ነው። በዓሉ ዛሬ በአዲስ አበባ ሆራ ፊንፊኔ፣ በማግስቱ እሁድ ደግሞ በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዴ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች፣ ሌሎች ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም ዲያስፖራዎችና የውጭ ሀገር ዜጎች በተገኙበት ይከበራል። በበዓሉ ለመሳተፍ በብዙ ሚሊየኖች የሚቆጠር ሕዝብ ከሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች እንዲሁም ከውጭ ሀገሮች ወደ አዲስ አበባና ኦሮሚያ ክልሎች እንደሚተሙም ይጠበቃል።

ለበዓል አከባበሩ በኦሮሚያ ክልልና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኩል ዝግጅት ተደርጓል። ለእንግዶች አቀባበል በማድረግ፣ በጸጥታና ደህንነት፣ አደባባዮችን፣ ጎዳናዎችን፣ ወዘተ በማስዋብ በኩል ለሚከናወኑ ተግባሮች አስፈላጊዎቹ ዝግጅቶች ተደርገው ወደ ትግበራ ተገብቷል። በዚህም መሠረት ሆራ ፊንፊኔ የሚከበርባት የአዲስ አበባ ከተማ ጎዳናዎችና አደባባዮች በአባገዳ ባንዲራ እና በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ተንቆጥቁጠዋል። በቢሾፍቱና በመላ የኦሮሚያ ክልልም ተመሳሳይ ዝግጅት እንደሚደረግ ይጠበቃል።

የኢሬቻ በዓል በክረምቱ መውጣትና ብራ መሆን አዲስ ተስፋ በሚሰነቅበትና፣ ምድር አረንጓዴ በምትለብስበት፣ ቡቃያው በሚያብብበት በእዚህ የመስከረም ወቅት ላይ የሚከበርና የኦሮሞ ሕዝብ ለእዚህ የፈጣሪ ጸጋ ምስጋና ለማቅረብ ርጥብ ሣር ይዞ ወደ ውሃ አካላት የሚወጣበት ነው፤ ይህ ብቻም አይደለም፤ ተቀያይመው የቆዩ ሰዎች ይቅርታ የሚጠያየቁበት፣ ያለፈውን ትተው ፈጣሪያቸውን በጋራ የሚያመሰግኑበትም ነው።

የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም የተለያየ እምነት ተከታዮች የየራሳቸው በዓል ቢኖራቸውም፣ አንዱ የአንዱን በዓል በማክበር በእጅጉ ይታወቃሉ። በኦሮሚያ ክልል ሕዝብ ዘንድ በደማቅ ሥነ ሥርዓት የሚያከብረው የኢሬቻ በዓልም እንዲሁ፣ በመላ ኢትዮጵያውያን ዘንድ በተለያየ መልኩ የሚገለጽ እሴት እንደመሆኑ የመላ ኢትዮጵያውያንም የጋራ በዓል ነው።

በኢትዮጵያውያን ዘንድ የአንዱ ቤት በዓል ለሌላውም ቤት በዓል ነው፤ በዓል በር ተዘግቶ አይከበርም፤ ቤተሰብን ብቻ ሳይሆን ጎረቤትን ማኅበረሰብንም ታሳቢ ይደረጋል። አንዱ አንዱን እንኳን አደረሰህ ይላል፤ ለዚያውም መልካም ምኞት መግለጫውን ይዞ። ይህ ብቻ አይደለም፤ ቤት ያፈራውንም ያቋድሳል፤ አንድ ላይ ይዘፈናል፤ ይጨፈራል፤ ይመረቃል።

የኢሬቻ እሴት በእያንዳንዱ ቤት ያለና ሊኖር የሚገባም ነው። ሰላም፣ አንድነት፣ ወንድማማችነትና ምስጋና ሁሉም ቤት ይኖራሉ፤ ምረቃው ለቤተሰብ፣ ለአንድ ቡድን ተብሎ አይደለም የሚደረገው፤ ለመላ ኢትዮጵያውያንም ለሀገርም ነው። ይህም የበዓሉን ማህበራዊ እሴትነት በሚገባ ያመለክታል። ይህ ማኅበራዊ እሴት እንዲጠበቅ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት እንደመሆኑ ለበዓሉ በድምቀትና በሰላም መከበር አስተዋጽኦ ማድረግ ከበዓሉ ባለቤት ብቻ የሚጠበቅ ሳይሆን፣ የኢሬቻ እሴት በውስጡ ካለው እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊም ይጠበቃል።

ኢሬቻ በሰዎች መካከል ማኅበራዊ ትስስርንና አንድነትን የሚያጎለብት የሰላም፣ የወንድማማችነት አርማ ነው። ይህ ደግሞ እነዚህን እሴቶች አጥብቆ ለሚያቀነቅነው፣ ለሰላም ከፍተኛ ዋጋ ሰጥቶ እየሰራ ላለው የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲሁም የሰላሙ ባለቤት ለሆነው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል።

መንግሥት የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት በሰላም ስምምነት በመቋጨት ሰላምን ለማጽናት እየሰራ እንደመሆኑ ለሰላም የሚጠቅሙ የትኛቸውንም እሴቶች ይጠብቃል። ባለፉት በዓላት ወቅትም በዓላቱ በሰላም እንዲከበሩ ከሕዝቡ ጋር ሆኖ አጥብቆ ሰርቷል፤ በዚህም ውጤታማ መሆን ተችሏል።

የኢሬቻ በዓልም በደማቅ ሥነ ሥርዓትና በሰላም እንዲከበር የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ከሕዝብ ጋር በመሆን በትኩረት መሥራት ከጀመሩ ቆይተዋል። በዓሉን የሰላም ማጽኛ፣ አንድነት ይበልጥ የሚሰርጽበት፣ ወንድማማችነት የሚጎለብትበት ለማድረግ መሥራት ከመላው ሕዝብ እንዲሁም የሰላም፣ አንድነትና ወንድማማችነት እሴቶችን ከሚያቀነቅን ማንኛውም ወገን ይጠበቃል። በዓሉን የሰላም፣ አንድነትና ወንድማማችነት ማጽኛ ማድረግም ይገባል!

አዲስ ዘመን መስከረም 26/2016

Recommended For You