ለክብረ በዓላቱ ብቻ ሳይሆን ለእሴቶቻቸውም

የመጠቅለያው ማብረቅረቅ፤ የስጦታውን ዋጋ እንዳያሳንስ”፤

የስጦታ መጠቅለያ ከዋናው ይዘት ደምቆ የመልእክቱን ዋጋ እንዳያደበዝዝ ወይንም መሠረታዊው ጉዳይ ላይ ማተኮር ሲገባ ማጀቢያው ላይ ብቻ ቀልብንና አመኔታን ሙሉ ለሙሉ መጣል እንደማይገባ ለመግለጽ ሲፈልጉ ብዙ ሀገራት ከላይ የተጠቀሰውን መሰል አነጋገር በየቋንቋቸው አዳብረዋል። በእኛም ቋንቋ ውስጥ ቢሆን “ጋባዧ ዋንዛ፤ የምትወደሰው ብሳና” የሚሉት ዓይነት ተቀራራቢ ብሂላዊ አነጋገር እንዳለን ልብ ይሏል።

በዚህ ፀሐፊ እምነት የሀገራችን በዓላት በሙሉ በአግባቡ ተሰንደው ተደራጅተዋል ለማለት በፍጹም የሚያስደፍር አይደለም። ለምሳሌ፡- ከዓመት ዓመት በካሌንደር ከሚዘጉት አሥራ ሦስት ያህል ሕዝባዊና ሃይማኖታዊ ብሔራዊ በዓላቶቻችን ውጭ ምን ያህል የማሕበረሰብና የአካባቢ ወይንም መንፈሳዊና ባህላዊ በዓላት እንዳሉን ለመዘርዘር የተመዘገቡ በቂ መረጃዎችን ያለ ድካም ለማግኘት ስለሚያዳግት “በየአካባቢው የሚከበሩት በዓላት ብዛታቸው ይህን ያህል ይሆናል” ብሎ ለመወሰን በእጅጉ ያዳግታል።

በየብሔረሰቡ፣ በማሕበረሰቡ፣ በየጎጡና በየመንደሩ ውስጥ ካሌንደር መዝግቦላቸው እውቅና አለማግኘታቸው እንጂ በርካታ የአካባቢ በዓላት ከብሔራዊ በዓላት ባልተናነሰ ደረጃ (ምናልባትም ባይበልጡ) በልዩ ድምቀትና አጀብ ሲከበሩ ይስተዋላል። ለጊዜው ስለይዘታቸው ለማመስገንም ሆነ ለመኮነን የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ስላይደለ በጥልቀት አንተነትናቸውም።

ዋናውና ሊታወስ የተፈለገው መሠረታዊ ጉዳይ በብሔራዊ ደረጃም ይሁን በየአካባቢው ባህልና እምነት መሠረት በተወሰኑ የዐውዳዊ ትእይንቶች ማዕረጋቸው ከፍ ያሉ ሃይማኖታዊ ወይንም ባህላዊ በዓላት የመከበራቸው ፋይዳ ትርጉሙና ግቡ ምንድን ነው የሚለው ይሆናል። በዓላቱ በቁጥር ምን ያህል እንደሆኑ እንገምት ብንል መነሻ የሚሆነን ተቀራራቢ ግምት ለማግኘት ስለምንቸገር የምንግባባው “በመቶዎች ምናልባትም በሺህዎች” ሊገመቱ ይችላሉ በሚል ጥቅል አገላለጽ መደምደም እንችላለን። እነዚህ የሀገራችን ልዩ መገለጫ የሆኑ ባህሎችና በዓላት ምን አበርክተውልን ምን ነሱን? በጥሞና ልናስበብት ይገባል።

በየሃይማኖቶቹ የሚዘከሩና የሚወደሱ በዓላትን እንኳን ብንመለከት እንደ ቀኖናቸው፣ ዶግማና እምነታቸው ብዛታቸው ከዓመት ዓመት ሺህ ምንተ ሺህ ሊባሉ የሚችሉ ዓይነት ናቸው። ያውም በድርብና በድርብርብ በዓልነት።

በየአካባቢው የሚከበሩ ባህላዊ እምነቶችም እንዲሁ በቁጥራቸው ብዛት ብቻ ሳይሆን በይዘታቸውና በአከባበራቸው ሥርዓት ጭምር እንዲህ ነው ብሎ ስለ ብዛታቸውና ዓይነታቸው አፍ ሞልቶ ለመናገር ትናንት ስለምን እንዳልተቻለ፤ ዛሬም ለምን እንደማይሞከር ምክንያት ለመስጠት መጣደፍ በባህር ውስጥ የመዘፈቅ ያህል ሊከብድ የሚችል የተግዳሮት ፈተና ነው።

ባህል፣ በዓላትና እሴት ቤተሰባዊ ዝምድናቸው እስከ ምን ድረስ ይዘልቃል? የሚለው ጥያቄ የዚህ ጽሑፍ ማዕከላዊ የመወያያ ጭብጥ ነው። ቀጥሎ በምልዓትም ባይሆን በመሠረታዊ ደረጃ ሦስቱን ጽንሰ ሃሳቦች ለመነካካት ቢሞከርም በተለየ ምልከታ ግን “እሴት” የሚለው ዋና ሃሳብ ከባህልና ከበዓላት ጋር ያለውን መስተጋብር ዘርዘር አድርገን ለማሳየት እንሞክራለን።

ባህልና በዓላት ምንና ምን ናቸው?

ባህል አንድ ሕዝብ ወይንም ወገን ለረዥም ዘመናት የእኔ ብሎ አክብሮ የያዘው ማሕበረሰባዊ ሀብቱና መገለጫው ነው። የሰውን ልጅ ሰብዓዊና ምክንያታዊ ፍጡር እንዲሆን ካስቻሉት ዋና ባህርያቱ መካከልም አንዱና ቀዳሚው ባለ ባህል የመሆን ብቃቱ ነው። ባህል በጥቅሉ ቁሳዊና መንፈሳዊ፣ የሚጨበጥና የማይጨበጥ ተብሎ ሊመደብ ይችላል።

የዘርፉ ባለሙያዎች የሰው ልጅ ከባህሉ ጋር ያለው ትስስርና ቁርኝት እጅግ የጠበቀ እንደሆነ አስረግጠው የሚናገሩት በበቂ ማስረጃ እየተነተኑ ነው። ሰው ያለ ባህል ልኑር ቢል ከሰብዕና ደረጃ ዝቅ ሊል እንደሚችልም ይከራከራሉ። ባህል በማሕበረሰቡ የእምነት፣ የአምልኮና ሌሎች ክንውኖች ጎልቶ ይንጸባረቃል። ክፉና ደግ፣ ቸርና ንፉግ፣ ቆንጆና አስቀያሚ፣ ርሁሩህ እና ጨካኝ ወዘተ. የመሳሰሉ ብያኔዎች የሚሰጡት አብዛኛውን ጊዜ በባህሉ መስፈርት መሠረት ነው።

ባህል በዕድሜ ማነስና ከፍታ፣ በጀግንነትና በፍርሃት፣ በአዋቂነትና ባለማወቅ ወዘተ. ሊገለጽና ሊንጸባረቅ ይችላል። ለምሳሌ፡- የሃይማኖት መሪዎች፣ የዕድሜ አንጋፋ አባቶችና እናቶች፣ ጀግኖች አርበኞች፣ የኪነ ጥበባት ባለሙያዎች፣ በሥነ ምግባር የተመሰገኑና አንቱታ ያተረፉ አርአያ ሰብ ግለሰቦች፣ በታሪክ የሚወሱ ተጠቃሾች፣ የመልካም ሥነ ምግባር አስተማሪ በሆኑ የተረት ገጸ ባሕርያት ሳይቀር ባህል ጎልቶ ሊንጸባረቅ ይችላል።

ባህል ከቤተሰብ፣ ከማሕበረሰብ፣ ከሃይማኖት ተቋማትና ልምምዶች፣ ተምሳሌትነት ካላቸው ምልክቶች፣ ከትምህርት ሥርዓትና ከሀገረ መንግሥት የፖለቲካ አስተዳደር ወዘተ. ጋር ተሸርቦና ተጋምዶ ህልውና የሚሆን መንፈሳዊና ቁሳዊ የኅብረተረሰብ ሀብት ነው። ቁሳዊ ባህል በአመጋገብ፣ በመጠለያ አገነባብና በአኗኗር ዘይቤ፣ ለውበት ማድመቂያነት በሚውሉ ማጌጫዎች፣ ለግብርና በሚውሉ ቁሳቁሶች፣ እጀ ጠቢባን በሚገለገሉባቸው መሳሪያዎችም ወዘተ. ሊገለጽ ይችላል።

ማሕበራዊ ባህል በሰው ለሰው ግንኙነት ይወከላል። ለምሳሌ፡- ጓደኝነት፣ ቤተሰባዊና የእርስ በእርስ ግንኙነቶች በአብነት ሊጠቀሱ ይችላሉ። ፍልስፍናዊ ባህልም እንዲሁ ከአእምሯችን፣ ከስሜታችን፣ ከመንፈሳዊ ሕይወት አቋማችን ጋር የተያያዙና በሌሎች ላይ ተጽእኖ የምናሳድርበትን የግል መንፈሳዊ አቋምና ፍልስፍና አካቶ የያዘ ነው።

በዓላት በአንጻሩ ከባህል ውስጥ የሚያዘመሩ “ምርቶች” ናቸው። ባህልና በዓላት ብዙ ጊዜያት መስመራቸው እየደበዘዘ አንድም ሁለትም ሆነው በተለዋጭነት ሲገለጹና ሲተዋወቁ ይስተዋላል። በቀላል ማሳያ ለማመልከት ያህል ባህል በአጥር በተከበበ ሰፊ የመኖሪያ ግቢና ቤት ሲመሰል በዓላት ደግሞ የቤቱ አንድ ክፍል ወይንም ክፍሎች እንደሆኑ ቢታሰብ ጥቂትም ቢሆን ውስብስቡን ጽንሰ ሃሳባቸውን ለመረዳት ያግዝ ይመስለናል።

ያልጠለለው “የእሴት” ድንጋጌ፤

ትርጉሙ ተዛብቶ አገልግሎት ላይ ከሚውሉ የቋንቋችን “ድፍርስ” ጽንሰ ሃሳቦች መካከል አንዱ እሴት በቀዳሚነትና ያለማስተዋል ተደጋግሞ ሲንገላታ እንመለከታለን። በብዙ መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ “የመሥሪያ ቤታችን እሴቶች” ተብለው የሚዘረዘሩ እጅግ አማላይና አስጎምጅ ቃላትን በየግድግዳው ላይ በወርቃማ ቀለም ታትመው ማንበብ የተለመደ ነው። “ግልጽነት፣ ቁርጠኝነት፣ አጋርነት፣ ጥራት፣ ቅልጥፍና፣ ውጤታማነት፣ ቅንነት፣ ታማኝነት፣ ባለጉዳይን ማክበር፣ የሙያ ሥነ ምግባር ወዘተ.” የሚሉት እነዚህን መሰል የቃላት ድርድሮች በሙስናና ባለጉዳይን በማንገላታት ተለይተው በሚታወቁ መንግሥታዊና ሕዝባዊ ተቋማት ሳይቀር በተቋማቱ ሰሌዳ ላይ በጉልህ ፊደላት ተቀርጸው ማንበብ የባህል ያህል ተቆራኝቶናል።

የእሴት ትርጉም ከላይ ከጠቃቅስናቸው እውነታዎች በእጅጉ የተለየ ነው። እሴት ከባህል ውስጠኛው ክፍል ተፈልቅቆ የሚወጣና በጣዝማ ማር የሚመሰል የተፈተነ ተግባር ነው። ጣዝማ ማር አገልግሎቱ አንድም ለጥፍጥና አንድም ለመድኃኒትነት እንደሚውል ትንሽ ትልቁ ያውቀዋል። ይህንን ጠነንና ጠንከር ያለ ገለጻ ፈታ አድርጎ ማብራራቱ አስፈላጊ ስለሆነ በጥቂቱ እናፍታታው።

የባህል ተመራማሪዎች ባህልን የሚመስሉት ከቀይ ሽንኩርት ጋር እያመሳሰሉ ነው። ቀይ ሽንኩርት ቢልጡት የሚወጣው ልጣጭ እንጂ “ሥጋና አጥንት” የሚባል ባህርይ የለውም። አንዱ ልጣጭ ሲገፈፍ የሚከተለው ሌላ ልጣጭ ነው። ሽንኩርቱን እስከ መጨረሻው ልጠን እንጨርሰው ብንል ልጣጭ ከመግፈፍ ውጭ ምንም የተለየ አካል ማግኘት አይቻልም።

ባህል በሽንኩርት የተመሰለበት ዋና ምክንያት አንድን ግለሰብ ወይንም ማሕበረሰብ ዘልቀን ውስጡን “እየላጥን” እንፈትሽ ብንል በንብርብሩ ውስጥ የምናገኘው የቤተሰብን ተጽእኖ፣ የአካባቢ ወግና ሥርዓትን፣ የእምነት ተቋማት ያሳደሩትን የሕይወት ፍልስፍናና መርህ፣ በትምህርት ሥርዓቱ የተቀረጸን የአኗኗር ሥርዓት፣ የሀገረ መንግሥቱ ፖለቲካና መንግሥታዊ ሥርዓት ያሰመራቸውን መስመሮች፣ ከፍ ሲልም የዓለም አቀፍ ዋና ዋና ተጽእኖ ፈጣሪ አካላት ያተሙትን አሻራ ነው። እነዚህ ሁሉ ተጽእኖ ፈጣሪ አካላት አሻራቸው ደምቆ የሚታየው የማሕበረሰቡ አባላት ልብ ተቀልብ ሆነው ተምረው ሕይወታቸውን ሊመሩበት በይሁንታ ስለተቀበሏቸው ነው።

እሴት ግን ከእነዚህ ንብርብር እውነታዎች የተለየ ነው። በንብርብር ከተመሰለው ከባህሉ ጠሊቅ ክፍል ስለሚቀዳም እውቀቱ የሚገኘው እየተለማመዱት ሳይሆን ሳይታወቅና በረቀቀ መንገድ ስሜትና መንፈሳችንን ገዝቶ ስለሚያስገብረን ነው። ይህንንም ረቀቅ ያለ ገለጻ በቀላል ምሳሌ ለማስረዳት እንሞክር።

በብሔራዊ ደረጃ የሚከበሩት ሕዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓላቶቻችን የራሳቸው የአከባበር ባህልና ወግ አላቸው። መስቀልም ሆነ መውሊድ፣ ፋሲካም ሆነ አረፋ ወይንም ሌሎቹ ሲከበሩ በልዩ ሁኔታ የሚታወቁባቸው መለያ አላቸው። የምዕመናን አመጋገብ፣ አለባበስ፣ የግብዣው ዓይነትና የአደባበይ ትዕይነቶች ሁሉ እንደ በዓላቱ ባህል ሊለያይም ሊመሳሰልም ይችላል። ነገር ግን ከአልባሳቱና ከአመጋገቡ፣ ከአደባባይ ትዕይነቱና ከድምቀቱ ባሻጋር አክባሪው ምዕመን ተነፋፍቆ ሲገናኝና ማዕድ አብሮ ሲቆርስ የሚታየው አርቴፊሻል ያልሆነ ፍቅርና መከባበር፣ አንተ ትብስ፣ አንቺ ትብስ መተሳሰብ፣ የተጣለው እንዲታረቅ ሁኔታው ሲያስገድድ፣ የተቸገር ሲረዳና ነፍሱና ስሜቱ ሲረሰርስ የሚሰተዋለው ያ መልከ ብዙ መገለጫ ሌላ ሳይሆን በበዓላቱና በባህሉ ውስጥ ያለው እሴት ጎልቶ የመውጣቱ ምልክት ነው።

በአዳዲስ አልባሳት ከመዋብ ባሻገር፣ ለድግስ ፋታ ከማጣት በበለጠ ሕያው ሆኖ በማሕበረሰቡ ውስጥ የሚስተዋለው መቀባበል፣ መከባበርና መደናነቅ፣ መረዳዳትና መደጋገፍ፣ ለታላላቆች የሚሰጠው አክብሮትና ምክራቸውንና ምርቃታቸውን ለመቀበል የሚደረገው እሽቅድምድም እርሱ ነው “እሴት” የሚባለው። ስለዚህም ነው እሴትን በጣዝማ ማር የመሰልነው። አንድም ለጥፍጥና አንድም ለመድኃኒት ይሆናል ብለን። እሴት የባህልና የበዓላት አስኳል ረቂቅ የአብሮነት ሀብት እንጂ እንደ ሌላው በአጀብ ብዛት የሚገለጽ የግል ጉዳይ ብቻ አይደለም።

ወደ ማጠቃለያ ሃሳባችን እናዝግም። ምናልባትም በበዓላት ብዛትና በኅብረ ባህሎች ፀጋ ኢትዮጵያችን ከበርካታ ሀገራት ቀድማ የምትጠቀስ ሳትሆን እንደማትቀር ብንገምት ላንሳሳት እንችላለን። ሌላው ቀርቶ በየሃይማኖታችን ውስጥ ያሉትን የየቀኑን ድርብርብ መንፈሳዊ በዓላት እንቁጠር እንኳን ብንል ቁጥራቸው የትዬለሌ ሆኖ እንደምንቸገር ከላይ በሰጠናቸው ትንታኔዎቻችን ውስጥ ጠቃቅሰን አልፈናል።

አብዛኞቹ የሀገራችን ባህሎችና በዓላት ህልውና የሆኑት በሃይማኖቶች ዙሪያ እንደሆነ ይታወቃል። የአብዛኞቹ ሀገራዊ እሴቶቻችን የሚዘመሩትም ሃይማኖቶቹ ባጎናጸፉን ፀጋዎች አማካይነት ነው። የትኛውም ሃይማኖት ደግሞ በምድርም ይሁን በሰማይ ከሰላምና በአብሮነት ከመኖር ውጭ ሌላ መልእክት የለውም። የአብዛኞቹ ሃይማኖቶች ማዕከላዊ መልእክት “ለአንተ/ቺ እንዲደረግልህ/ሽ የምትፈልገውን/የምትፈልጊውን እንዲሁ ለሌላው አድርግ/ጊ” የሚል መሆኑን ወርቃማ ሕግጋት የሚባሉት የየሃይማኖቶቹ ትምህርቶች በግልጽ ያስረዳሉ።

እንደዚህ በሃይማኖቶችና በበዓላት እሴቶች ደምቃለች በሚባል ሀገር መገዳደል፣ አንዱ አንዱን ማፈናቀል፣ ወንድም በወንድሙ ላይ ሰይፍ እየሳለ ለመጠፋፋት የደም ሸማ መጣጣል ከየትና እንዴት ሥር ሰዶ ሊያጨካክነን ቻለ? ይሉኝታ በሌለው ዘረፋ መበልጸግን ያስተማረን የየትኛው ባህላችንና በዓላቶቻችን “ክፉ እሴት” ነው። በዓላትን ስናከብር ተነፋፍቀን፣ ስንገዳደል ተጨካክነን፤ ምን ይሉት ክፉ ብሔራዊ ልክፍት ነው? ወደ ቀልባችን ተመልሰን ባህሎቻችንንም ሆኑ በዓላቶቻችን ልንፈትሽ ግድ ሊለን ይገባል። ሰላም ለሕዝባችን ለዜጎችም በጎ ፈቃድ።

 (በጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)

gechoseni@gmail.com

አዲስ ዘመን መስከረም 26/2016

Recommended For You