በኢትዮጵያ ሰብዓዊነትና መደጋገፍ ባህል መሆኑን የሚያሳዩ እጅግ በርካታ አብነቶችን መጥቀስ ይቻላል። የሀገሪቱ ሕዝብ የተቸገረንና አቅም በማጣቱ ድጋፍ የሚሻን ወገን በቡድንና በተናጠል በመሆን የሚደግፍባቸው የተለያዩ አደረጃጀቶች ባለቤት ነው። ከእነዚህ መንገዶች መካከል እቁብ፣ እድር እና የመሳሰሉት ዘመናትን ያስቆጠሩ እሴቶቹ ይጠቀሳሉ። “ወገን ለወገኑ ደራሽ ነው” የሚል የቆየ ብሂልና በጎ ልምድ ያለው ኢትዮጵያዊ የጎረቤቱን እና የአካባቢውን ልጅ እንደራሱ ልጅ ቆጥሮ የማሳደግና የማስተማር ባህል አለው።
ዛሬ ይህንን እሴት የሚጋራ አንድ ሀገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅት ስለሚሰራው ምግባር ሰናይ ተግባር ጥቂት ዳሰሳ ለማድረግ ወድደናል። ይህ ሀገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅት በኢትዮጵያዊ የበጎነት ስሜትና የመተጋገዝ መንፈስ ላለፉት 22 ዓመታት ጎዳና ለመውጣት የተገደዱ ሴቶችን፣ ሕፃናትን፣ አረጋዊያንን ጨምሮ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ውስጥ የወደቁ የማህበረሰብ ክፍሎችን እየደገፈ፣ በሁለት እግራቸው እንዲቆሙ ምክንያት እየሆነ ይገኛል።
ድርጅቱ ‹‹ኒው ላይፍ›› ይባላል። የዝግጅት ክፍላችን ያነጋገራት የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሄለን ጥላሁን ‹‹ድርጅታችን ጎዳናዎች የሰዎች መኖሪያ ሳይሆኑ መረማመጃዎች ናቸው ብሎ ያምናል።›› ትላለች፡፡ ሥራ አስኪያጇ ለሰው ልጅ ክብር እንደሚገባም ጠቅሳ፣ ‹‹ማንም ሰው ጎዳና ላይ መኖር የለበትም ብለን ራዕይ ይዘን ነው ድርጅቱን ለመመስረት የተነሳ ነው›› በማለት ትገልጻለች። ድርጅቱ ሴቶች ሕፃናትና ወጣቶችን አምራች ዜጋ ለማድረግ ዋና ግብ አስቀምጦ ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት መመስረቱን ታስታውሳለች።
በተለይ የአዲስ አበባ ከተማ ጎዳና ላይ በሚኖሩ ሕፃናት፣ ሴቶችና እናቶች ተጨናንቋል የምትለው ሥራ አስኪያጇ፣ ይህ አሃዝ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱንም ትናገራለች። በተለይ ኒው ላይፍ በተመሰረተበት ወቅት የነበረው ጎዳና ላይ የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር አሁን ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ማሻቀቡን ጠቅሳለች።
የማህበረሰቡ ክፍል የሆኑት እነዚህ ዜጎች ጎዳና እንዲወጡ ከሚገደዱባቸው ዋንኛ ምክንያቶች ውስጥ የኑሮ ውድነት፣ ጦርነት፣ የቤተሰብ ልጆችን በኃላፊነት የማሳደግ አቅም ማጣት፣ የተሻለ ሕይወት ይኖራል የሚል የተሳሳተ ግምትና የግንዛቤ እጥረት እንደሚጠቀሱ ትገልፃለች። በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ሴቶችና ሕፃናትን ሳይጨመር ከ100 ሺህ በላይ ሕፃናት መኖራቸውን መረጃዎችን ዋቢ አርጋ የምትጠቅሰው ወይዘሮ ሄለን፣ ይህም የጎዳና ሕይወት ምን ያህል አስከፊ ደረጃ እየደረሰ መሆኑን ያሳያል ትላለች።
‹‹ዜጎችን ከጎዳና የማንሳት ሥራ ጊዜ ሊሰጠው የማይገባና ክቡር የሰው ልጅ ሕይወትን ገፅታ በእጅጉ የሚያበላሽ ነው›› ስትል ገልጻ፣ ለበርካታ ዓመታት በጎዳና ላይ የሚገኙ ሕፃናትን፣ ወጣቶችን በማንሳትና ከማህበረሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉ በመሥራት የሚታወቀው ድርጅቱ፣ ዋናው ትኩረቱን ይህን ማድረግ የፈለገበትን ምክንያት ትገልፃለች።
ሥራ አስኪያጇ እንዳለችው፤ ‹‹ኒው ላይፍ›› ጎዳና የወጡ የማህበረሰቡ አካል የሆኑ ሕፃናትና ወጣቶችን ለማቋቋም አልሞ የተመሰረተው በሁለት ባለትዳሮች ነው። እነሱም ሰላማዊት ቡቻና ብርሃኑ ጣሰው ይባላሉ። በወቅቱም ድርጅቱ በጎዳና ላይ ያሉ ልጆችን በመሰብሰብ የምግብ፣ የንፅህና እና የሥነ ምግባር ትምህርትን ጨምሮ በርካታ ድጋፎች ያደርግ ነበር። በተጨማሪ ድርጅቱ የተለያዩ የእጅ ሥራ ሙያዎችን በማስተማር ራሳቸውን እንዲችሉ እድል ይፈጠር ነበር።
በጊዜው ‹‹ኒው ላይፍ›› ባደረገው ድጋፍ ምክንያት አሁን ላይ ከጎዳና ተነስተው ኢንጂነር፣ ዶክተር፣ መምህር፣ በተለያዩ የሥራ መስኮች እስከ ማናጀርነት የሥራ መስክ የደረሱ እንዲሁም የራሳቸውን የግል ሥራ መስርተው ውጤታማ የሆኑ በርካታ ውጤታማ ሰዎች መፈጠራቸውን የምትገልጸው ወይዘሮ ሄለን፤ አሁንም ድረስ ይህንን በጎ ምግባሩን አጠናክሮ መቀጠሉንና በጎዳና ሕይወት ውስጥ ያሉ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎችን የሚታደግ ሥራ እንደሚሰራም ትናገራለች።
“የሚውሉበትንና የሚያድሩበትን አካባቢ መሠረት አድርጎ ማህበረሰቡ የሚሰጣቸው አመለካከት፣ የሚፈጥርባቸው ተፅእኖ እንጂ፣ በመርህ ደረጃ በጎዳና የሚኖሩ ዜጎች በቀዳሚነት ፍቅርን ይፈልጋሉ” የምትለው የኒው ላይፍ ሥራ አስኪያጇ ወይዘሮ ሄለን፤ በተገቢው መንገድ ማህበረሰቡ ቢያቀርባቸውና ቢደግፋቸው እንደማንኛውም ዜጋ ለውጥ ማምጣት የሚችሉ መሆናቸውን ትገልፃለች። ከዚህ መነሻ ድርጅታቸው እነዚህን ዜጎች በሚኖሩበት ቦታ በመሄድ እንደ እህትና ወንድም ፍቅር በመስጠት እና ችግራቸውን ቀርቦ በመረዳት ድጋፍ ለማድረግ እንደሚጥር ትናገራለች።
እንደ ሥራ አስኪያጇ ገለፃ፤ ‹‹ኒው ላይፍ›› በጎዳና ላይ የሚኖሩ ዜጎችን በተከታታይ በማግኘት ፍቃደኛ እስኪሆኑ ድረስ አቅርቦ በማነጋገር የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ ያደርጋል። ከዚህ በመቀጠልም ወደሚያዘጋጀው ማዕከላት በማስገባት የባህሪ ለውጥ ለማምጣት የሚረዱ ስልጠናዎችን በባለሙያዎች ይሰጣል። በተለይ እነርሱ በማህበረሰቡ፤ ማህበረሰቡ በእነርሱ ላይ ያላቸውን አሉታዊ አመለካከት የሚያሻሽሉ ግንኙነቶችና ሥልጠናዎችንም በመስጠት ግንኙነቶችን ለማሻሻል ይሰራል።
ሥራ አስኪያጇ እንዳብራራቸው፤ በመጀመሪያው ሶስት ሳምንት ወደ ማዕከሉ የሚገቡ ጎዳና ላይ የሚኖሩ ዜጎች የሚረጋጉበት እና የለመዱትን ያልተገባ ባህሪ /‘ሱስ’/ እንዲቀንሱ የሚደረግበት ነው”፡፡ ይህንን እርከን ሲያልፉ ልዩ ልዩ ሥልጠናዎችን በመስጠት የሕይወት ክህሎት እንዲያገኙ በማስቻል ቤተሰብ ያላቸውን ወደ ቤተሰባቸው መመለስ፣ የተጣሉትን በማስታረቅ፣ የተጠፋፉትን በማገናኘት፣ ቤተሰብ የሌላቸውን ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በማገናኘት ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉና አምራች ዜጎች እንዲሆኑ ልዩ ልዩ ሥራዎችን ያከናውናል።
የማህበረሰቡ አካል የሆኑት በጎዳና ላይ የሚኖሩ ዜጎች አስቀድመው ወደዚህ ሕይወት ውስጥ እንዳይገቡ የመከላከል ሥራ ካልተሰራ የችግሩን ምንጭ ማድረቅ አይቻልም፡፡ በዋናነት ይህንን ችግር ለመቅረፍ መሥራት ያለበት በማህበረሰቡ ውስጥ መሆኑን ኒው ላይፍ አምኖ፣ አዲስ ስትራቴጂክ እቅድ ነድፎ እየሰራ ነው። በእቅዱ መሠረትም በቀዳሚነት ዜጎች ወደ ጎዳና ከመውጣታቸው በፊት የመከላከል ሥራ ላይ አተኩሮ እየሰራ ይገኛል።
“ልጆቿን ብቻዋን የምታሳድግ እናት እዚያው ማህበረሰቡ ውስጥ እያለች ወደ ጎዳና ሳትወጣ ልንደርስላት ይገባል” የምትለው የኒው ላይፍ ሥራ አስኪያጅ፤ እነዚህን መሰል እናቶች ልጆቻቸውን እንዲያስተምሩ፣ በኢኮኖሚ የገቢ ምንጭ እንዲያገኙና የማህበረሰቡ ጠንካራ አካል እንዲሆኑ መሥራት ከምንም ነገር በላይ ወደ ጎዳና የሚወጡ ዜጎችን ቁጥር እንደሚቀንሰው ትናገራለች።
ሥራ አስኪያጇ እንዳለችው፤ ‹‹ኒው ላይፍ›› በቅርብ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ በተፈጠሩ ግጭቶችና የሰላም እጦት ከልዩ ልዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን የመደገፍ ሥራም ይሰራል፡፡ በተለይ ከፕላን ኢንተርናሽናል ጋር በመተባበር 21 ሺ አካባቢ ከሚደርሱ በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገኙ ስደተኞችን መካከል እርሱ መደገፍ የሚችለውን ያህል በመለየት (አካል ጉዳተኛ ሴቶች፣ እናቶች እና አቅመ ደካሞችን፣ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶችን) እየረዳ ነው። እነዚህን ዜጎች አቅማቸው በፈቀደው መጠን መደገፍ መቻሉ ነገ ደጋፊ አጥተው ጎዳና እንዳይወጡና እንዳይበተኑ ማድረግ ያስችላል፡፡ ይህን መሰሉ ተግባርም የድርጅቱ የቅድመ መከላከል ተግባሩ ነው፡፡
“ኒው ላይፍ 30 ሺህ የሚደርሱ ዜጎች ላይ በጎ ተፅእኖ መፍጠር ችሏል” የምትለው ሥራ አስኪያጇ፤ ከጎዳና አንስተው ዩኒቨርሲቲ ለመግባት አንድ ዓመት ከቀራት ተረጂ አንስቶ በርካታ ችግሮችን ውጣ ውረዶችን እንዲያልፉ ድጋፍ እስካደረጉላቸው በርካታ ሺህ ወጣቶች ድረስ በጎ ተፅእኖ መፍጠር መቻሉን ትናገራለች። “ኢትዮጵያውያን የት ቦታ መርዳት እንዳለባቸው ላይገነዘቡ ይችላሉ፤ እንጂ ንፉግ አይደሉም” በማለትም እነዚህን ወገኖች ከማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስብራታቸው እንዲያገግሙ ለማድረግ እጃቸውን በቀናነት የሚዘረጉና ድርጅታቸውን የሚደግፉ ብዙሃን እንዳሉም ትገልፃለች።
ድርጅቱ ‹‹ኒው ላይፍ›› በርካታ እናቶች በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ፣ ተደማጭነታቸው እንዲጨምር ማድረጉን የምትገልፀው ወይዘሮ ሄለን፤ አንድ እናት በኢኮኖሚ አቅሟ የጎለበተች ስትሆን የውሳኔ ሰጪነትና ቤተሰብን የመምራት ኃላፊነት የመውሰድ አቅም እንደምትፈጥር ትናገራለች። በዚህ ምክንያት ‹‹ኒው ላይፍ›› መሰል አቅም እናቶች እንዲኖራቸው እቅድ ነድፎ መሥራቱንና አሁንም ድረስ በዚህ ተግባሩ መቀጠሉን ትገልፃለች።
“ኢትዮጵያ ከናይጄሪያ ቀጥሎ ከአፍሪካ በርካታ ወጣቶች የሚገኙባት ሀገር ነች” የምትለው ሥራ አስኪያጇ፣ ይህንን አቅም በሥራ ፈጠራ፣ በልማት እና ለሀገር በሚጠቅም አቅም በሚፈለገው ልክ እየተጠቀምንበት እንዳልሆነ ትናገራለች። ይህንን ችግር ለመቅረፍም ድርጅታቸው እንደ አንድ ባለድርሻ አካል ወጣቶችን በተለያየ መልኩ በማብቃት ተግባር ላይ እየተሳተፈ መሆኑንም ትገልፃለች።
እሷ እንዳለችው፤ በቅርብ ጊዜ ውስጥም በአዲስ አበባ “በአዲስ ከተማና አራዳ ክፍለ ከተሞች” አራት ሺህ የሚደርሱ ወጣቶችን “በሥነ ምግባር የታነፁ፣ ራሳቸውን ጠቅመው ለሀገር የሚሆኑ ወጣቶች እንዲሆኑ” የሚያስችል ሥልጠናና የማብቃት ሥራ ተሰርቷል፡፡ ከዚህ ባሻገር 100 እናቶችን ከፕላን ኢንተርናሽናል ጋር በመሆን የራሳቸውን የንግድ ሃሳብ አውጥተው ሥራ እንዲጀምሩ አስችሏል። በቅርቡም በሰላም ላይ በመሥራት በሲቪል ሶሳይቲ ዘርፍ እየተሳተፈ ይገኛል።
‹‹ኒው ላይፍ›› የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅዶችን ነድፎ እየሠራ መሆኑን የምታነሳው ሥራ አስኪያጇ፤ ድርጅቱ በድጋፍ የሚቆም ሳይሆን ራሱን የቻለና ለኢትዮጵያውያን ምርኩዝ መሆን የሚችል ግዙፍ ተቋም እንዲሆን ታልሞ እየተሰራ መሆኑንም ትገልፃለች። ከዚህ መነሻ በአጭር ጊዜ ውስጥ ራሱን በራሱ የፋይናንስ አቅም እንዲፈጥርና ፕሮጀክቶችን እንዲተገብር የሚያስችል እንዲሆን እንደሚሰራ ትናገራለች።
በሁለተኛነት ትውልዱ በሥነ ምግባር፣ በእውቀት እና ክህሎት የተሻለ ሆኖ እንዲወጣ የሚያስችል ማዕከል የመገንባት ህልም እንዳለም ትገልፃለች። ይህ ሁሉ የሚሳካው ግን መንግሥት፣ ማህበረሰቡ እና እያንዳንዱ ዜጋ “ኒው ላይፍን” ልክ እንደራሱ አድርጎ ማገዝና መደገፍ፣ ለአላማው መሳካትም አብሮ መቆም ሲችል እንደሆነ ታመለክታለች። ለዚህም የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ድጋፍና እገዛ ጠይቃለች። ከዚህ መነሻ ‹‹ኒው ላይፍ›› በአሥር ዓመት ውስጥ የልህቀት ማዕከልና ለወገኑ የሚደርስ ትልቅ ማዕከል እንደሚሆን ሥራ አስኪያጇ ሄለን ቃል ገብታለች።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን መስከረም 25/2016