በዓላቱ የባህላዊ እሴቶቻችን ታላላቅ መገለጫዎች ናቸው!

የአንድ ሀገር ሕዝቦች እውነተኛ ብሄራዊ ማንነት የሚገነባው በዛች ሀገር ባሉ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማኅበራዊ ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ እሴቶች ድምር ውጤት ነው። እነዚህ እሴቶች ዘመናትን እየዋጁ እና በዘመናት እየተዋጁ ትውልዶች ከትናንት ዛሬ ፤ ከዛሬ ደግሞ ነገ የተሻሉ ቀናትን ተስፋ አድርገው መኖር እንዲችሉ ዋነኛ አቅም ሆነው ያገለግላሉ።

በተለይም ባለንበት ዘመን እነዚህ እሴቶች የአንድን ማኅበረሰብ ሁለንተናዊ አቅም በመገንባት ሂደት ውስጥ ካላቸው አስተዋጽኦ አንጻር ከፍ ያለ ትኩረት እየተሰጣቸው ይገኛል። እሴቶቹ ከባለቤቱ ማኅበረሰቡ አልፈው ዓለም አቀፍ እውቅና የሚያገኙበት እና አግባብ ባለው መንገድ የሚጠበቁበት አስቻይ ሁኔታም በስፋት እየተስተዋለ ነው።

ኢትዮጵያም እንደ ሀገር የብዙ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሀገር ከመሆን ባለፈ የብዙ ሺ ዓመታት የሀገረ መንግሥት ታሪክ ባለቤት በመሆኗ፤ ለሀገሪቱ ሕዝቦች የተሻሉ ነገዎችን መፍጠር የሚያስችሉ ብዛት ያላቸው ማኅበራዊ ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ እሴቶች ባለቤት ነች። እነዚህ እሴቶች እንደ ሀገር እስከዛሬ ለመጣችባቸው ረጅም የታሪክ ምዕራፎችም ዋነኛ አቅም ናቸው።

እያንዳንዱ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ ከራሱ አልፎ ከሌሎች ጋር በሰላም ፣ በፍቅር እና በአንድነት መኖር የሚያስችሉ በየራሳቸው ምሉዕ የሆኑ ማኅበራዊ ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እሴቶች አሉት። ከትናንት ዛሬ ራሱን ሆኖ መኖር የቻለው እነዚህ እሴቶቹ በሰጡት አቅም እና በገነቡበት ማንነት ነው። በቀጣይም ከራሱ ጋር ተስማምቶ የተሻሉ ነገዎቹን መፍጠር የሚችለው በነዚሁ እሴቶቹ እየተደገፈ እንደሆነም ይታመናል።

የታሪክ መዛግብት እንደሚያስረዱንና እንደሚያስተምሩን ፤ እንደ ማኅበረሰብ ነገን ብሩህ አድርጎ ለማሰብ ከሁሉም በፊት ከራስ ጋር መታረቅ ያስፈልጋል፤ ከዚህ የተነሳም በየትኛውም ሁኔታ ከራሱ ጋር የተጣላ/ ከማንነቱ ጋር ያልተስማማ / ማኅበረሰብ የተሻሉ ነገዎችን መፍጠር አይችልም። እነዚህን ቀናት ለመፍጠር የሚያደርጋቸው ያልተሳኩ ጥረቶችም የከፋ ዋጋ ከማስከፈል ባለፈ የሚያስገኙለት ፋይዳ የለም።

እነዚህ እሴቶች ለሰው ልጅ ተለዋዋጭ የውስጥ ፍላጎቶች በሂደት ተገዥ የሚሆኑ ፤ ዘመንን እየተዋጁና በዘመን እየተዋጁ የሚሄዱ ፤ በዚህም በራሳቸው የትውልዶችን የመሆን መሻት የማስተናገድ አቅም ባለቤት በመሆናቸው በየትኛውም መልኩ እነሱን ተቀብሎ ማስተናገድ ተፈጥሯዊ ሂደታቸውን ለተሻለ ተጠቃሚነት የማብቃት ያህል የሚቆጠርና የሚበረታታ ነው።

እኛም እንደ ሀገር ያሉንን ብሔር ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ማኅበራዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እሴቶች ተቀብለን የአደባባይ እውቅና የመስጠታችን ሂደት ፤ አንድም እንደሀገር ፈተና ለሆነብን ሰላም የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍያለ ነው። ከዛም ባለፈ መገንባት ለምንፈልገው የጋራ ሀገራዊ ማንነት አልፋና ኦሜጋ እንደሚሆን ይታመናል።

እንደ ሀገር የክረምቱን መገባደድ ተከትሎ ያከበርነው የቡሄ በዓል ፤ መስከረም ከጠባ ያከበርናቸው፤ ብሄራዊውን ጨምሮ የተለያዩ ብር ፣ ብሔረሰቦች የዘመን መለወጫ እና የመስቀል በዓላት የማንነታችን እሴቶች ናቸው። ለነዚህ እሴቶች የምንሰጣቸው እውቅና በአንድም ይሁን በሌላ የብሄራዊ ማንነታችን አቅም እና ጥንካሬ ምንጭ ነው።

በሳምንቱ መጨረሻም የምናከብረው የኢሬቻ በዓልም ከፍ ያሉ ማኅበራዊ እሴቶች ያሉት፤ እንደ ሌሎች የሀገራችን ብሔር ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ማኅበራዊ እሴቶች በብሄራዊ ማንነት ግንባታ ውስጥ ከፍ ያለ አበርክቶ ያለው ነው። የኢትዮጵያዊነት ሌላው ገጽታ ማሳያ ደማቅ ቀለም ፤ የአንድነቱ ማሰሪያ ጠንካራ ገመድ እንደሆነም ይታመናል።

የኢሬቻ በዓል ከክረምት ወደ መስከረም፣ ከጨለማ ወደ ፀሐይ መሸጋገሪያ ያለውን ብሩህ የዘመን ታሳቢ ተደርጎ ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት፤ በቀደሙት ጊዜያት ተቀያይመው የነበሩ ሰዎች ይቅርታ የሚጠያየቁበት እና ይቅር የሚባባሉበት፣ በጋራ የሚያመሰግኑበት በዓልም ነው። ይህም ሀገራዊ ሰብአዊ እሴቶችን ለማጎልበት ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል።

እንደ ሀገርም ማኅበራዊ ትስስር በመፍጠር የሕዝቦች አንድነትን ለማጠናከር እንዲሁም የግጭት ማስወገጃ ዘዴ ሆኖ ማገልገል የሚችል፤ ከኦሮሞ ሕዝቦች ባሻገር ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎችን በአንድነት አቅፎ የሚያሳትፍ ነው። የበዓሉ እሴቶች ለጀመርነው ሀገራዊ ልማት ስኬት የሚኖረው ፋይዳም ከፍ ያለ ነው።

ይህንን ታሳቢ በማድረግ ስለ ኢሬቻም ሆነ መሰል በዓላት በማኅበረሰቡ ውስጥ ትክክለኛ ግንዛቤ በመፍጠር፤ ባህላዊ እሴቶቻቸውን ጠብቀው ያለአንዳች የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት በሰላማዊ መንገድ የሚከበሩበትን ሥርዓት ማበጀት ፤ ለዚህ የሚሆን ቁርጠኝነት መፍጠር ያስፈልጋል።

አዲስ ዘመን መስከረም 25/2016

Recommended For You