ኢሬቻ የሰላም በዓል ፤ በሰላም እንዲከበር

አንድ ሰው ተወልዶ አድጎ ትልቅ ሰው ሆኗል ለመባል የልጅነት ፣ የአፍላነት እና የወጣትነት ጊዜያትን ያልፋል፤ በዚህ የህይወት ዑደት ውስጥ የዚህ ሰው አስተሳሰብ እና ማንነት በብዙ መንገድ ይቀያየራል፡፡ በዘመን በተተካ ቁጥርም ያለው አኗኗር ይቀየራል። በዚህ መሀል ግን ከዘመን ዘመን የማይለዋወጡ መንፈሳዊ ፣ማህበራዊ እና ባህላዊ እሴቶቻችውን ጠብቀው ከትውልድ ትውልድ የሚሻገሩ በዓላት አሉ። እነዚህ በዓላት በብዙዎች ዘንድ የአንድ ማኅበረሰብ ዋነኛ መገለጫም ተደርገው ይወሰዳሉ።

እኛ ኢትዮጵያውያን ከአኗኗራችን ባሻገር በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና የተሰጣቸው ብዙ በዓላት ባለቤቶች ነን፡፡ ከነዚህ በዓላት ውስጥ በአደባባይ የምናከብራቸው ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህ የአደባባይ በዓላት መሠረታቸው ሃይማኖት ቢሆንም በውስጣቸው የተለያዩ እሴቶች አሏቸው።ማህበራዊ ግንኙነትን በማጠናከር ባህላዊ እሴቶችንም በማንጸባረቅ፣ታሪካዊም ይዘት ኖሮአቸው፣ በየዓመቱ በድምቀት ይከበራሉ፡፡በነዚህ በዓላት ላይ ለመታደም ከተለያዩ የዓለም ክፍል ሁሉ ሳይቀር ከየአቅጣጫው ይሰባሰባሉ፡፡

እንዲህ ሕዝብን በማሳተፍ የሚከበሩ በዓላት በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረው መስቀል፣ የኦሮሞ ማኅበረሰብ በልዩ ሁኔታ የሚያከብረው ኢሬቻ ፣ ጊፋታ (የወይላይታ ዘመን መለወጫ) እና የያሆዴ (የሀዲያ የዘመን መለዋጫ) ጥቂቶቹ ናቸው። የመስቀል በዓልም ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ትውፊቱን ጠብቆ ከዓመት ዓመት ይከበራል። በተለይም በመስቀል ዋዜማ የሚከበረው ደመራ በእምነቱ ተከታዮች ልዩ ስፍራ አለው፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት/ ዩኔስኮ/ ከማይዳሰሱ ቅርሶች ውስጥ የተመዘገበ ትልቅ በዓል ነው፡፡

እነዚህን በዓላት ባህላዊና መንፈሳዊ ይዘታቸውን እንደያዙ ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፉ አሁን ላይ ደርሰዋል። ካላቸው መንፈሳዊና ባህላዊ ክዋኔ የተነሳም ከእምነቱ ተከታይ አልያም ከአካባቢው ማኅበረሰብ ውጪ የሌሎችን ኢትዮጵያውያንና የውጭ ሀገር ዜጎችን ቀልብ በመሳብም በኩል ትልቅ ሚና አላቸውና እነዚህ ቱሪስቶችም ዓመት ጠብቀው ሀገራችን እንዲመጡ መልካም አጋጣሚ ይፈጥራሉ።

የበዓላቱን ታሪካዊ ፣ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ እሴቶቸቸውን በጠበቀ መልኩ በየዓመቱ እንዲቀጥል ማድረግ የሚጠይቀው ሥራ ወይም ዝግጅት ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ በተለይም ይዘታቸውን ጠብቀው መከበራቸው ከሁሉ በላይ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡ በዓላቱ የአብሮነት ፣የብዝሃነትና የወንድማማችነት መገለጫ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በተለያየ እምነት ፣ የባህል ልዩነት ያላቸው ወጣቶች በዓላቱ የሚከበሩባቸውን አካባቢዎች በጋራ በማፅዳት ለበዓላቱ አከባባር ያላቸውን አጋርነት ሲገልጡ ማየት እየተለመደ መጥቷል። ይህም ከተለያየ ቤተሰብ የተገኘን ፣ የራሳችን እምነት እና ባህል ያለን ብንሆንም በመከባበር እና በተቀራረበ የአብሮነት መንፈስ ያደግን ጥሩ ጉርብትና ያለን ሕዝቦች መሆናችንን ያሳያል፡፡

እንዲህ ያለው የመተባበርና የመከባበር መንፈስ በዓሉን ለሚያከብር ማኅበረሰብ ብቻ ሳይሆን፣ ከውጪ ሆኖ ለሚመለከትም ትልቅ መልእክት በማስተላለፍ ፋይዳው የጎላ ነው፡፡ በዓሉ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከናወን በተለያየ መልኩ ጥረት የሚያደርጉ ወጣቶች እና በጎ ፍቃደኞች፣ ፕሮግራሙ ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ በተለያየ መንገድ የሚሳተፉ አስተባባሪዎች የበዓሉ ተሳፊዎች እና የፀጥታ አካላት ቅንጅትና ተናቦ መስራት ለበዓላቱ አከባበር ስኬታማነት ትልቅ አቅምም ነው፡፡

እንደ ቀደሙት ወቅቶች ሁሉ የእነዚህ ሁሉ አካላት ትብበር እና መናበብ ታክሎበት የመውሊድና የመስቀል ደመራ በዓላት ያላቸውን ታሪክ ፣ ባህል እና ሃይማኖታዊ ትውፊት ይዘው በሰላም እና በድምቀት ተከብረዋል። ለዚህም የበዓሉ ባለቤት የሆነው መላው ሕዝባችን ትልቁን ድርሻ ወስዷል። ምስጋናም ሊቸረው ይገባል፡፡

በርግጥ ሀገራት በጊዜ ሂደት የተለያዩ ፖሊሲዎችን ይከተላሉ ያሻሽላሉ፡፡ በዚህ መሃል የሕዝባቸውን አኗኗር የሚቀይሩ እና የሚያቀሉ ከዓለም ጋር እኩል የሚያስኬዱ ሥርዓቶችን ይዘረጋሉ፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም እንደ ሀገር ልዩ የሚያደርጋቸውን ባህላዊ፣ ማኅበራዊና መንፈሳዊ እሴቶችን አጉልተው ለማሳየት ይጥራሉ። ይህ ዓለም አቀፋዊ እውነታ ነው።

እኛም እነዚህ በዓላት ከሀገራችን አልፈው ስማችንን በበጎም ሆነ በመጥፎ ለማስጠራት ያላቸውን አቅም በመረዳት ከፍ ባለ የኃላፊነት መንፈስ ስናከብራቸው ቆይተናል። የእኛነታችን መገለጫ የሆነው የኢሬቻ በዓልም በተመሳሳይ ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲከበር የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ያሉትን አካላት ማገዝና ለሰላሙ ተባባሪ መሆን ይጠበቃል፡፡

ኢሬቻ የምስጋና በዓል ነው። “ኢሬቻ ማለት ዋቃ (ፈጣሪ) የፈጠረውን ማመስገን ማለት ነው” የኦሮሞ ሕዝብ ምድር እና ሰማይን ለፈጠረው ፤ ከዘመን ወደ ዘመን በሰላም ላሸጋገረው ፈጣሪው /ዋቃ ምስጋናውን የሚያደርስበት በዓል ነው። ማኅበራዊ ደረጃ እና የእድሜ ልዩነት ሳይፈጠር የኦሮሞ ሕዝብ ለዘመናት በጋራ ሲያከብር የቆየ ዛሬም እያከበረው ያለ በዓል ነው።

“ክረምት ለሊት ነው። ለሊት ደግሞ ጨለማ ነው። ጨለማ ለአውሬ እንጂ ለሰው ልጅ አይሆንም። ጨለማው ሲነጋ ደግሞ ብርሃን ነው፤ ብርሃን ሲሆን ሃሳብ የለም ደስታ ይሆናል። መስከረም ሲጠባ ማለት ይህ ነው” በማለት የኦሮሞ ሕዝብ ከክረምት መገባደድ በኋላ የኢሬቻ በዓልን ያከብራል።

በኢሬቻ በዓል ላይ የኦሮሞ ሕዝብ ለመላው የሰው ልጅ ሰላምና ደኅንነት ፈጣሪውን ዋቃን ይለምናል፤ ያመሰግናል። “የተጣላ ታርቆ፣ ቂሙን ትቶ በነጻ ልቦና ፈጣሪ ንጹህ ወዳደረገው የውሃ አካል ይሄዳል። ኢሬቻ ቀልብ የሚነጻበት ቦታ ነው።

የኢሬቻ በዓልን ለማክበር የሚወጣ ታዳሚ እንደ ሳር ወይም አበባ ያለ እርጥብ ነገር በእጁ ይዞ መምጣት ይጠበቅበታል፤ ይህም “ፈጠሪያችን ሆይ አንተ ያጸደቅከው ነው አብቦ ፍሬ ያፈራው” የሚለውን ትልቅ መልእክት ለማስተላለፍ ነው።

በዓሉ የሰላም፣ የፍቅር፣ የተጣላ የሚታረቅበት፣ የተራራቀ የሚገናኝበት በመሆኑ ከጸብ ይልቅ ፍቅርን፣ ከጥላቻና ከመራራቅ ይልቅ አንድነትን በማጉላት ኢትዮጵያዊነታችንን ይበልጥ የምናጠናክርበትና የምናሳይበት ሊሆንም ይገባል፣

“እንኳን ሰው፤እቃ ከእቃ ይጋጫል” እንደሚባለው፤ አዎ! ሰው አብሮ በመኖር ሂደት ውስጥ ይጋጫል፣ እንደ ሕዝብም የማያግባቡን ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን በዚህ ዓይነት በዓላችን ላይ ከማያግባቡን ይልቅ በሚያስማሙን ነገሮች ላይ ትኩረት በማድረግ፤ ችግራችንን ወደጎን ትተን በፍቅር በመተሳሰብና በይቅርታ በመተላለፍ በሰላም ማክበር ይጠበቅብናል፣አንዳንድ የእኩይ ተግባር ነጋዴዎች አብሮ የኖረን ሕዝብ ለማቃቃር በናፍቆት የሚጠብቃቸውን የአደባባይ በዓላቱን ለማደብዘዝ በጠቅላላው ኢትዮጵያዊ መገለጫዎቻችንን ለማኮሰስ ሊጥሩ ይችላሉ፣ ነገር ግን እኛ አስተዋይ በመሆን ችግር ቸርቻሪዎችን ወደጎን ብለን፣በዓሉ በሰላም ይከበር ዘንድ የበኩላችንን መወጣት አለብን፣

ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነን ደግሞ ያለፉት የመውሊድና የደመራ በዓላት ናቸው፣ የበዓሉ ታዳሚ በሰላም ወጥቶ በሰላም ወደቤቱ ለመመለሱ ትልቁን ድርሻ የያዘው እራሱ ታዳሚው ነው፡፡ኢሬቻም በሚከበርባቸው ሁለት ቀናት የበዓሉ ታዳሚዎችን ጨምሮ መላው ኢትዮጵያዊ አንድ በመሆን የጸጥታ ኃይሎችን በመደገፍ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል፡፡

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን መስከረም 25/2016

Recommended For You