ራሄል ሞገስ ትባላለች። በተለምዶ ‹የሚጥል ሕመም› ተብሎ በሚጠራው ሕመም ከተያዘች 11 ዓመት ሆኗታል። በሳይንሳዊ መጠሪያው ኢፕሊፕሲ ተብሎ የሚታወቀው ይህ የሚጥል ሕመም ሕክምና እንዳለው በመገንዘቧ ክትትሏን የጀመረችው በቶሎ ነበር። ‹‹አንዳንድ ሠዎች ርኩስ መንፈስ ነው። ርግማን ነው ይበሉ እንጂ የሚጥል ሕመም እንደሌሎቹ የጤና ችግሮች ነው። ሕክምናና መድኃኒትም አለው።›› የምትለው ራሄል፤ የታዘዘላትን መድኃኒት በአግባቡ በመውሰዷ አሁን ላይ ሕመሟን ተቆጣጥራዋለች። ይህም ብዙ ለውጦችን በራሷ ላይ እንድታይ አስችሏታል። በአካውንቲንግ ተመርቃም በአሁን ወቅት በሽያጭ ሠራተኛነት ሕይወትዋን እየመራች እንደምትገኝ ታስረዳለች።
ራሄል ከህመሙ ጋር በነዚያ 11 ዓመታት ውስጥ ብዙ ፈተናዎችን አሳልፋለች። ከዚህ ቀደም ተቀጥራ በሠራችባቸው ቦታዎች ብዙ ፈተናዎች ገጥሟታል። በህመሟ ምክንያት ስትወድቅ ‹‹ባንቺ ምክንያት ገበያ ተመልሷል።›› ተብላለች። አንዳንድ አሠሪዎቿም ፈቃድ ይከለክሏታል። ችግሯንም አልተረዱላትም ነበር። ‹‹ብዙ ፈተናዎች ይኑሩ እንጂ ዋናው በጥንካሬ ማለፍ ነው።›› ትላለች።
‹‹መውደቅ ለእኔ የሆነ የታወከ ነገር በአምስት ደቂቃ ውስጥ ሲስተካከል ማለት ነው።›› ስትል ይህን የጤና ችግር የምትገልፀው ራሄል፤ ሌሎች ታማሚዎች መድኃኒታቸውን በሰዓት ከወሰዱ፣ ክትትላቸውን በሚገባ ካደረጉ፣ ራሳቸውን ከጭንቀት ካራቁ ብሎም የሕክምና ባለሙያዎች የሚሏቸውን ከሰሙ ለውጥ ማምጣት እንደሚችሉ ልምዷን ታጋራለች።
አቶ ዐቢይ አስራት በኬር ኢፕሊብሲ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው። ማዕከሉ ከተመሰረተ ስምንት ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፤ በነዚህ ዓመታት ውስጥ የሚጥል ህመም (ኢፕሊብሲ) በኅብረተሰቡ በኩል የሚፈለገውን ያህል እንኳን ባይሆን የተሻለ አመለካከት እንዳለው ያወሳሉ። ማዕከሉ ግንዛቤ ከመስጠት በተጨማሪ የሚጥል ሕመም ላለባቸው ታማሚዎች የተሻለ የሕክምና ዕድል ኖሯቸው አገልግሎት እንዲያገኙ እና መድኃኒቶቹም እንደልብ የሚገኙ ባለመሆናቸው ለታማሚዎች በሚገባ እንዲደርሱ ለማድረግ ዓላማ አድርጎ እየሠራ ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪም በማዕከሉ ውስጥ የሕክምና አገልግሎት እንዲደረግላቸው ማድረግን ያካተተ ሲሆን፤ በወር አንዴ ነጻ የሕክምና አገልግሎት ይሰጣል።
እንደ አቶ ዐቢይ ገለፃ፤ በማዕከሉ አንድ ሺህ የሚሆኑ አባላት ያሉ ሲሆን፤ ለአባላቱ በጎ ፈቃደኛ የሆኑ ኒውሮሎጂስቶች (የነርቭ ስፔሻሊስቶች) ሕክምና እንዲያገኙ ይደረጋል። በኢትዮጵያ ያለው የኒውሮሎጂ ባለሙያ ቁጥር አናሳ በመሆኑ ለሚሊዮን ሕዝብ መድረስ አይችሉም። በተለይም የሕጻናት ኒውሮሊጂስት ቁጥራቸው ከአምስት የማይበልጥ ቢሆኑም የተሻለ ሕክምና ሕፃናትን ጨምሮ ለአዋቂዎችም እንዲያገኙ ይደረጋል።
ከዚህ ጎን ለጎንም የሚጥል ሕመም ያለበት ሠው፤ ሕመሙ ያለበትን ደረጃ ሊገልጽ የሚችል እና ከየትኛው አንጎል ክፍል ነው የሚነሳው ብሎ የሚለካ ማሽን በማዕከሉ የሚገኝ ሲሆን፤ ታማሚዎቹ ነጻ ምርመራ እንዲያገኙ ያደርጋል። ከዚህ በተጨማሪም የኤም አርአይ ምርመራ ከዲያግኖስቲክ ማዕከላት ጋር በመነጋገር በነጻ እንዲያገኙ ሁኔታችን ያመቻቻል። ከሕክምናው በተጨማሪም መድኃኒቶቹ እንደልብ የሚገኙ ባለመሆናቸው እና አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ዋጋቸው ውድ መሆኑን ተከትሎ አቅም ለሌላቸው ታማሚዎች ማዕከሉ መድኃኒቱን በመግዛት ይሠጣል። ዓመታዊ የጤና መድህን ክፍያ በመክፈል እገዛ ያደርጋል።
ሲስተር ሜሮን ሽመልስ በኬር ኢፕሊብሲ ኢትዮጵያ በማኅበረሰባዊ ግንኙነት ታማሚዎችን በማየት እንዲሁም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በማዕከሉ ትሰጣለች። እንደ እርሷ ገለፃ፤ አብዛኛው የሚጥል ሕመም ያለበት ሠው ሕመሙ ምን እንደሆነ ግንዛቤው የለውም ። እንደውም ‹‹እንደ ልክፍት ወይም አውድቅ ይዞኛል›› የሚል አመለካከት ነው ያለው። ገና ወደ ማዕከሉ ሲመጡ ይድናል የሚል ተስፋም የላቸውም። ይህንን ተከልትሎም ማዕከሉ የሕክምና ድጋፍ እንዲያገኙ፣ ሕመሙን መቆጣጠር እና መዳን እንደሚችሉ ግንዛቤ ይሰጣል።
ሌላው በማዕከሉ ለታማሚዎች የሥነ ልቦና ድጋፍ ስለሚደረግላቸው ሥራ አግኝተው አግብተው ወልደው ሕይወታቸውን እየመሩ ያሉ ብዙ ናቸው የምትለው ሲስተር ሜሮን ሽመልስ፤ በተለይም ዘወትር ረቡዕ የሚሠጠው የምክር አገልግሎት (የቡና ጠጡ ፕሮግራም) ቋሚ መሆኑን ታስረዳለች። በዚህም የህመሙ መንስኤ ምንድነው? እንዴት እንቆጣጠረው? የሚለውን ጨምሮ ለወደፊት ሕይወታቸው የሚያግዛቸው ምክር ይሰጣል።
እንደ ሲስተር ሜሮን ገለፃ፤ ሁለት ዓይነት የሚጥል ሕመም አለ። አንደኛው ጄነራል ሲዢር የሚባለው በአንጎል ግራ እና ቀኝ በኩል የነርቭ ሴሎች በአንድ ጊዜ እኩል የሆነ የኤሌክትሪክ ንዝረት ወደ መላው የአንጎል ክፍል የሚረጭ ሲሆን፤ ምልክቶቹም ወድቆ መንቀጥቀጥ፣ አረፋ መድፈቅ ፣ አልፎ አልፎ ሰገራ እና ሽንት መልቀቅ ያጋጥማል። ሁለተኛው ደግሞ ፎካል ሲዢር ነው። ይህም ከአንጎል ክፍል የሚጀምር ወደ ሌላ የአንጎል ክፍል የማይሰራጭ ሲሆን ፤ አካላዊ እና ስሜታዊ ተፅዕኖዎችን ያስከትላል። ምልክቶቹም ለተወሰነ ሰከንድ የሰውነት ክፍል መድረቅ፣ድንገተኛ የመረበሽ ስሜት እና መሰል ምልክቶች ናቸው። በመሆኑም በዚህ ጊዜ መደረግ ያለበት የእርዳታም ይሁን የጥንቃቄ መረጃ እንዲኖራቸው ይደረጋል።
‹‹የሚጥል ሕመም በንክኪ አይተላፍም። ከሌላ አእምሮ ሕመም ጋር የማይያዝ መሆኑን ሠዎች ሊረዱት ይገባል። ልክ እንደማንኛውም የነርቭ ሕመም ሕመም ነው። በቂ ሕክምና፤ በቂ መደኃኒት አለው። ስለዚህም ሀኪም አቁሙ እስኪል ድረስ መድኃኒቱን በሚገባ መውሰድ ያስፈልጋል።›› በማለት ሲስተር ሜሮን ሙያዊ ምክራን ገልፃለች።
በሚጥል ሕመም ብዙ ችግሮች የደረሰባት ራሄል አሁን ላይ ሠርታ ትገባለች። ልምዷንም ወደ ማዕከሉ ለሚመጡ አባላት ታካፍላለች። ሕብረተሰቡም እንደ ማንኛውም ሕመም ሕክምና እንዳለው ማወቅ ይኖርበታል ባይ ናት። የሚጥል ሕመም ኖሮባቸው ከቤታቸው ያልወጡ ይኖራሉ። ስለዚህም ልጆቹን ቤት ቆልፎ ከማስቀመጥ ይልቅ ወደ ሕክምና እንዲሄዱ፣ መድኃኒታቸውን በአግባቡ እንዲወስዱ፣ ትምህርት እንዲማሩ፣ ሥራ እንዲሠሩ ማድረግ ይገባል። ለዚህ ደግሞ ቤተሰብም እራሱን ማሰር የለበትም በማለት ትመክራለች።
‹‹ለሚጥል ሕመም በተለምዶ ክብሪት ማጨስ፣ ውሃ መስጠት፣ እንጨት እንዲነክሱ ማድረግ እና መሰል ድርጊቶች የሰዎችን ሕይወት እስከማሳጣት ይደርሳል›› ያሉት አቶ ዐቢይ፤ ስለዚህም ማዕከሉ የግንዛቤ ሥራዎችን በሥፋት እንደሚሰራበት ይገልጻሉ። ሌላው የሚጥል ሕመም ምን ሰዓት ላይ እንደሚነሳ ባለመታወቁ ለታማሚዎች የማይደገፉ ሥራዎች መኖራቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል። ለአብነትም መኪና ማሽከርከር፣ አብዝቶ እሳት አጠገብ ከሚሠሩ ሥራዎች፣ በማሽን በመታገዝ ከሚሠሩ ሥራዎች ራሳቸውን ማራቅ ይኖርባቸዋል።
ማዕከሉ ለወደፊት ብዙ ራዕይ እንዳለው የሚገልጹት ሥራ አስኪያጁ፤ የመድኃኒት እጥረት፣ ማዕከሉ በኪራይ ቤት አገልግሎት ለመስጠት መገደዱ እና ድጋፎችን እንደልብ አለመገኘቱም ሥራቸውን ፈታኝ እንዳደረጉ ያስረዳሉ። አያይዘውም የኢትዮጵያ የነርቭ ሕክምና ማህበር እና ሌሎችም ለሚያደርጉት የበጎ አድራጎት ድጋፍ በማመስገን የመድኃኒት አምራቾች እና አቅራቢ ድርጅቶች ድጋፋቸውን እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።
እየሩስ ተስፋዬ
አዲስ ዘመን መስከረም 24 ቀን 2016 ዓ.ም