ኢትዮጵያውያን ከመቼውም ጊዜ በላይ የሚናፍቁት ጉዳይ ቢኖር ሰላምን ነው፡፡ ምንም እንኳ የኑሮ ውድነቱ ከጊዜ ወደጊዜ እያሻቀበ ቢመጣም ከሰላም መስፈን እንደማይበልጥም አሳምረው ያውቃሉ፡፡ ታድያ ለዚህ ሰላም መስፈን ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ድርሻ መኖሩን እምብዛም ትኩረት ሲሰጥ አይስተዋልም፡፡ በደጅ ባለውና በተዘረጋው የሰላም አጀንዳ ተዋናይ ለመሆን መዘጋጀት ብልህነት ነው፡፡ ይህ የሰላም አጀንዳ ደግሞ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ይዞ የቀረበው ታላቅ ጉዳይ ነው፡። ከዚሁ ጉዳይ ጋር ተያይዞ አዲስ ዘመን የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር እና እንዲሁም የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ከሆኑት ከፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ጋር ቆይታ አድርጓል፤መልካም ንባብ፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ እየታየ ያለው ችግር ከየትኛው የተሳሳተ ትርክት የሚመነጭ ነው ይላሉ?
ፕሮፌሰር በየነ፡– ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ችግር አንድ አይነት ብቻ አይደለም።ችግሮቻችን አንድ፣ ሁለት፣ ሶስት… እየተባሉ የሚቆጠሩ ናቸው። አንዳንዱ ችግር በአንዳንድ ወቅት ገንፍሎ የሚወጣ ነው።እሱንም ችግር እንለዋለን። ቀጥሎ ደግሞ ፈረንጆች (Moving Target) ተንቀሳቃሽ ኢላማ የሚሉት የቸገረ አይነት ሁኔታ ደግሞ ነው።ተንቀሳቃሽ ኢላማ መምታት አስቸጋሪ ነው።ተንቀሳቃሹን ነገር አነጣጥሬዋለሁ ብለን ልንመታው ስንል ወዲህ ወዲያ ስለሚንቀሳቀስ ዒላማችን ውስጥ ለማስገባት ያስቸግራል። ልክ እንደዛው ሁሉ የኢትዮጵያ ችግሮች እንደተንቀሳቃሽ ኢላማ ናቸው። አነጣጥሮ ለመምታት ተንቀሳቃሽም በመሆናቸው በጣም ከባድ ነው።ስለዚህ በዚህኛው ችግር ላይ አተኩር እስኪ እስካልተባልኩ ድረስ ለጠየቅሽኝ ጥያቄ ምላሼ የሚሆነው ጠቅለል ያለ ነው፡፡
ያም ሆኖ ግን እኛ ኢትዮጵያውያንን ለየት የሚያደርገን በችግሮቻችን ውስጥ ሆነን ማለፍ እንችልበታለን።አሁንም ቢሆን ስለምንችል በችግር ውስጥ እያለፍን ነው።የእኛ አይነት ችግር የደረሰበት ሌላ ሀገር ቢሆን እስካሁን ተበታትኗል፡፡
ደርግ ወድቆ ኢህአዴግ የገባ ጊዜ በሽግግር መንግስት ወቅት በቻርተር ኮንፍረንሱ ላይ ብዙዎችን የማግኘት እድል ነበረኝ።አንድ በጣም ያስገረመኝ የኦጋዴን ነጻ አውጪ ድርጅት የሚባለውን የሚመሩ በጉባኤው ውስጥ የነበሩ ሰው የተናገሩት ነገር ነው። ሰውዬው በአጼ ኃይለስላሴም ዘመን የነበሩ ናቸው። በወቅቱ በነበረው የአስተዳደር ሥርዓት ውስጥም የሰሩ እንደመሆናቸው ብዙ ነገር የሚያውቁ ናቸው።‹‹ልጅ በየነ፣ አሁን ሱማሊያም ተቸገረ፤ እያንዳንዱ የጎሳ መሪ ሀገሪቱን የምመራው እኔ ነኝ እያለ ነው፤ ኢትዮጵያም ተቸገረች።መንግሥትም ወድቋል።ሱማሊያም ፈረሰች፤ ኢትዮጵያ ግን ያልፈረሰችው ለምንድን ነው? ሲሉ ጠይቀውኝ እራሳቸው መልሰው፤ ኢትዮጵያ ግን መንግሥት እንኳ ሳይኖር ሕዝቡ ሰላም ነው፤ በየጎሳ መሪው ተከፋፍሎ ሀገር አልተበታተነም። ኢትዮጵያ ቋሚ መንግሥት ለዘመናት ያለባት ሀገር ናት።ሕዝቡ መንግሥታዊ አስተዳደርን ያውቃል።ስለዚህ ስልጣን ላይ ያለው ቢፈልግ አንዱ ሌላውን ይገለብጣል፤ ሌላኛው ደግሞ ሌላውን ይገድላል እንጂ ሀገሪቱን ግን ሕዝቡ ያስቀጥላል አሉኝ።
በእርግጥም ባለው ባህላዊ እሴት በመታገዝም ኢትዮጵያ ሳትበታተን እንድትቆይ ያደረገው ሕዝቡ ነው። ሁሉም እንደየመልካም እሴቱ አካባቢውን በመጠበቁ ነው። በየድንበሩም ያለ እንዲሁ ሀገሩን በንቃት ጠብቆ ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያ የዚህ የትጉህ ሕዝብ ሀገር ናት፤ ችግሮች ይመጣሉ፤ ይሄዳሉ።የሚራኮቱት ገዥዎቹ ናቸው። በመሆኑም ይህንን ለይተን ካጤንን በኢትዮጵያ ውስጥ የሚያጋጥሙን ችግሮች ጨርሶ ተስፋ ሊያስቆርጡን አይችሉም።ኢትዮጵያ በሕዝቦቿ እጅ ውስጥ ናት።
አስቀድሜ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ችግሮች ብዙ ናቸው፤ በአሁኑ ጊዜ ሀገሪቷን መረጋጋት የሚያሳጡ እንቅስቃሴዎች በየቦታው አሉ፤ በእርግጥ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። ድሮም የሚከሰት ነው።ይሁንና ሀገር እስከመበተን የሚያደርሱ አይሆኑም፤ ራሳቸው ይከስማሉ።በእርግጥ ነገሮች በተጋጋሉበት አካባቢ ችግር መኖሩ አይቀሬ ነው። የቀረው ደግሞ የሁልጊዜ ሂደቱን ይቀጥላል። የዚህች ሀገር ባለቤት ሕዝቡ ነው የሚል መንፈስ ስላለ ኢትዮጵያ ልትበታተን አትችልም፡፡
አንዳንዶቹ እዚህም እዚያም የሚነሱ ችግሮችን በማየት ብቻ በቃ ኢትዮጵያ ትበተናለች ይላል።የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊበትናት ከሚያስበው አካል በላይ ግንዛቤ ያለው ስለሆነ ይህ አባባል እኔን ብዙ አያሳስበኝም። መንግሥት እንኳ ባይኖር ባለው መልካም እሴት እየተመራ የሚኖር ሕዝብ ነው።ጎረቤታችን ሱማሊያ ስትበታተን ኢትዮጵያ ምን ሆነች? ምንም።
ስለዚህ አሁን እየሆነ ያለው ነገር በእኔ እምነት ዘላቂ ችግር ሳይሆን ጊዜያዊ ነው። ትልቁ ችግር በዚህ መንፈስ ተነሳስተው ‘እኛም ይሳካልናል’ የሚል ምኞት ያላቸው የሚመስሉ እዚህም እዚያም ጦርነት እያጫሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሰላም ወጥቶ እንዳይገባ የእንቅስቃሴ አድማሱን እያጠበቡ መምጣታቸው ነው።
ለችግሩ መንስኤ የሆነው ትርክት የቱ ነው ወዳልሽው ስመጣ ሁሉም የጎበዝ አለቃ ለመሆን መሯሯጡ ነው። በኦሮሚያ ውስጥ ያሉ ጎረምሶችም ያው የጎበዝ አለቆች ናቸው፤ በተመሳሳይ አማራ ክልልም ያሉት እንደዛው የጎበዝ አለቆች ናቸው። እነዚህን ሕዝቡ በትዕግስት የሚያስተምርበት ሁኔታ ቢኖር ጥሩ ነው። የሀገሪቱ መከላከያ ደግሞ ድጋፍ እየሰጠ ቢንቀሳቀስ ሰላሙ ይመጣል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ ይህ ከሆነ መፍትሔ ይመጣል የሚል እምነት አለኝ።
ሕጋዊ መብት ያለው በዴሞክራሲ የሚያምነው አካል ነው። ዴሞክራሲያ ሒደት ደግሞ የሕዝብ ይሁንታን ያገኘ አካል ሲሆን፣ ይኸው አካል አገሪቷን ይምራ።እንዲህ ማለት ደግሞ የተደራጁና ዴሞክራሲያዊ የሆኑ አካላት ተፎካክረ ሕዝብን ማወክ ሳይጠበቅባቸው ተወዳድረው ይሁንታን ካገኙ አገር ማስተዳደር ይችላሉ። የሚይዙት ጥያቄ በአንድ ቀን እንደማይፈታ ሁሉ እነርሱም ወደስልጣን ማማ መጥተው አገር ማስተዳደር ከፈለጉ ሒደቱን ጠብቀውና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ተወዳድረው ሊሆን ይገባል። ሁላችም በሰላማዊ አግባብ ጥያቄ የምንፈታበት ልቦና ቢሰጠን መልካም ነው፤ የብዙዎቹ የጸጥታ መደፍረስ ምክንያቱ የስልጣን ፍላጎት ነው።
ሌላው የከፋው ነገር በየቦታው አትንኩኝ ባይነትና እልኸኝነት መኖሩ ነው። እንዲያ ከሆነ ደግሞ ማን ለማን በቀላሉ ይበገራል የሚለው መጤን ያለበት ነው። ምክንያቱም ያለውን ችግር ለመፍታት በሚደረገው ሒደት አልንበረከክም የሚለው ነገር ትልቅ ፈተና ነው። ከዚህ የተነሳ የግጭቶቹ መንስኤ ይህና ያኛው ነው ብለን የምንናገረው ሳይሆን በርከት ያለ ነው ብሎ መናገሩ ይሻላል። ለምሳሌ አንዱ ዘንድ የወሰን ጉዳይ ሊሆን ይችላል፤ ያልተፈቱ ጥያቄዎች አሉ።እነዚያን ለመፍታት ግን መደማመጥ ያስፈልጋል።ማንም ቢሆን መሬቱን ተሸክሞ የሚጓዝ አይኖርም፤ መሬቱ ይኖራል፤ ሰዎች ደግሞ እያለፉ ትውልድ ይተካል።ስለዚህ ሁኔታዎችን አስፍቶ ማየቱ የተሻለ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ለዘመናት የነበሩ ችግሮች ሳይፈቱ ዛሬ ላይ ደርሰዋል።ለዚህ ምክንያቱ ምንድን ነው ይላሉ?
ፕሮፌሰር በየነ፡- በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ያመለጡ መልካም አጋጣሚዎች የሚባሉ ነገሮች አሉ። አንድ የኢትዮጵያ ወዳጅና የኢትዮጵያ ታሪክ አዋቂ ኢትዮጵያን ያመለጡ ሰባት ያህል መልካም አጋጣሚዎች ነበሩ ብለው ያስቀመጧቸው አሉ። እርሳቸው በሙያቸው የማኅበረሰብ አጥኚ (ሶሲዮሎጂስት) ናቸው።ኢትዮጵያዊ አይደሉም፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ መጥተው አርሶ አደሩ መሃል ኖረው ታሪክ ሲያጠኑ ነበር። እኚህ ምሁር ኢትዮጵያን በደንብ የሚያውቁ ናቸው ከሚባሉ ዓለም አቀፍ ምሁር መካከል አንዱ ነበሩ።
እኚህ ባለሙያ ኢትዮጵያ ያመለጣት መልካም አጋጣሚ ብለው ካስቀመጧቸው ጥቂቱ ለምሳሌ የአጼ ኃይለስላሤ ሥርዓት በሌላ ሲተካ የደርግ ጎረምሳ መኮንኖች የፈጠሩት ችግር ከመኖሩ አስቀድሞ ደርግ ሲያደርግ የነበረው አካሔድ ጤነኛ ነበር። ምክንያቱም ደርግ በወቅቱ ሲንቀሳቀስ የነበረው ‹‹ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም›› በሚል መርህ ነበር። በሂደት ግን መርዝ የበላ እንስሳ ይመስል መክለፍለፍ ጀመረ። ግድያው፣ ማሰቃየቱና ሌላው ሌላው መንጸባረቅ መጀመሩ የሚታወስ ነው። በዚያን ጊዜ ሰላማዊ ሽግግር ተብሎ የተጀመረው ነገር ቢኖርም በወቅቱ ንጉሱን እጅ በመንሳት የተጀመረው ብልጠት እያደር ከረር እያለ መምጣቱ አይዘነጋም።በሒደትም “ጠቅላይ ሚኒስትር ይቀየር እስኪ” በሚልም ጥያቄ ቀረበ። ለውጡ ሲመጣ እኔም በወቅቱ ትምህርቴን አጠናቅቄ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተቀጠርኩበት ጊዜ ነበር። እኛም በወቅቱ ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት አሁኑኑ ካልሆነ ብለን ሀገሩን አቀጣጠልነው።በዚህ ጊዜ ደርግም ደነገጠ።
በወቅቱ ሁኔታው ተረጋግቶ ቢሆን ኖሮ በሰላማዊ መንገድ ወደሽግግሩ ይመጣ ነበር። ነገር ግን እሱ ደፈረሰ። ጦሱ የብዙዎቹን ዜጎች ሕይወት የቀማ ሆነ።ከዚያ ጦስ የተራረፍነው ጥቂቶች አሁንም አለን፡። በወቅቱ የተፈጠረው ሁኔታ (The Crime and the Nation) የሚባለው አይነት ነው። እጅግ በጣም አዋቂና ለኢትዮጵያ ታላቅ ርእይ ያላቸውን ዜጎችን ሁሉ የፈጀ ነበር።
ቀጥሎ ደግሞ ደርግ ሲወድቅ ጥቅም ላይ ሳይውል የቀረው መልካም አጋጣሚ አውሮፓ ላይ የተደረገው ኢህአዴግ፣ ደርግ እና ሻዕቢያ ለውይይት የተቀመጡበት አጋጣሚ ነበር።እዛ ውይይትና ምክክር ላይ ሳይግባቡ ቢቀሩም ሰላማዊ በሆነ አግባብ ከደርግም ሆነ ከኢህአዴግም እንዲሁ ከሀገር ሽማግሌም ማለትም በወቅቱ እነፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሐቅ ሁሉ የነበሩበት ነበር።
ያኔ ውይይቱ ተሳክቶ ቢሆን ኖሮ ወያኔ በብልጠት ያደረገው አካሄድ በለዘበ እና በቁጥጥር በዋለ ነበር።ችግሩ ምንድን ነው ያልሽ እንደሆነ የአሸናፊ ፍትህ (Victor’s justice) የሚሉት ነገር አለ። ይህ አይነቱ አካሔድ ረግጦ ይዞ ልግደልህ አይነት ነው። ተሸናፊው ምንም የማለት መብት የለውም። እነዚህ መጥተው የደርግ ሰራዊትንም የጦር ኃይሉንም ወንጀለኛ የማድረግ አባዜን ተያያዙት።ይህ ጨርሶ ፍትህ ወይም መልካም የሚባል አልነበረም፡፡
እኔ በወቅቱ በሽግግሩ ውስጥ የነበርኩ እንደመሆኔ ሁኔታውን አውቃለሁ። የማያውቁ ሰዎች የሚናገሩት የተለያየ ነገር ነው። በወቅቱ እዚህም እዚያም ኢትየጵያን ነጻ አውጪ ነን እያሉ የመጡ ነገሮች ኢትዮጵያን ነጻ ማውጣት ሳይሆን ፍላጎታቸው መበታተን ነበር። ሁሉም በየፊናው እንደጥሩ አጋጣሚ ሲጠቀምበት የነበረው የመንግሥትን መውደቅ ነበር። የተወሰዱ እርምጃዎች ሁሉ የብልጠት ነበሩ። ይህን የብልጠት አካሄዳቸውን ያልተገነዘቡ ሁሉ የሚያውሩላቸው ሌላ ነገር ነው። የነበሩ መልካም አጋጣሚዎችን የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ሳይጠቀሙባቸው የባከኑ ናቸው።
ሕዝቡ ደግሞ ዝም ብሎ “እመራሃለሁ” የሚለውን ሁሉ ያዳምጣል።የሚያስቸግሩት ስልጣኑን እኛ ካልያዝን በሚል ነፍጥ አንግበው ጫካ የገቡ ካልሆኑ በስተቀር የቀረው ሕዝብ የሚለው ነገር የለውም። ሕዝቡ በትክክል የሚመራውን ካገኘ አካባቢውን እየጠበበቀ ምርቱን ማምረት ይያያዛል። ስለዚህ እየተንከባለለ የሚመጣ ችግር የበዛው ያመለጡ አጋጣሚዎች ስላሉ ነው።ቢያንስ እየፈተናቸው እንሔድ ነበር።ነገር ግን ችግሩን የመፍታት ብቃት ያላቸው የፖለቲካ መሪዎች ባለመኖራቸው እዚህ መድረስ ተችሏል።
ኢህአዴግ ሴረኛ ለመሆኑ ዋናው ምክንያት ጉድለቱን ለመሙላት ሲል ነው።ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመምራት ብልጠትን መጠቀም የግድ ነበር።እኔ በበኩሌ እንደእዛ ማድረጋቸው አያስደንቀኝም። ሁሌም በቁጥር አነስ የሚለው ወገን ደግሞ ብልጠትን ቢያካትት አይገርምም።የተወሰዱትን የብልጠት እርምጃዎች ጊዜው የፈጠረው በመሆኑ ምንም ማድረግ አይቻልም። እንደእዛ ካላደረጉ እነርሱም የበላይነቱን ይዘው አይቆዩም ነበር።
አዲስ ዘመን፡- ብልጽግና የነበሩትን ችግሮቸች በግልጸኝነት ለመፍታት ቢሞክርም ሕዝቡ ግልጸኝነትን ተቀብሎ ማዳበር ባለመቻሉ ችግርተከስቷል። ስለሆነም መፍትሔው ምንድን ነው ይላሉ?
ፕሮፌሰር በየነ፡– እኔ የፖለቲካ ስብዕና አለኝ ብዬ አስባለሁ።አስቀድሜ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ያመለጡን የፖለቲካ አጋጣሚዎች የምንላቸው አሁንም ቢሆን አሟጠን ስላልተጠቀምናቸው ነው የሚል እይታ አለኝ።ለምሳሌ እኛ አሁን እየሰራን ያለነው ከብልጽግና ፓርቲ ጋር በትብበብር መንፈስ ነው።ለኢትዮጵያ እና ለሕዝቧ በሚበጅ ጉዳይ ላይ በትብብር እንሰራለን፡፡
እንዲህ ሲባል ግን መስመራችንን ትተናል ማለት አይደለም። ይህች ሀገር ትንሽ እፎይታ ያስፈልጋታል። በአመራርነቱ ቆንጮ ላይ ያለው አካል መልካም አስተሳሰብ ያለው እና ለሕዝቡም ለሀገሪቱም የሚበጅ ነገር እፈልጋለሁ ብሎ በተግባርም እያስመሰከረ እስከሔደ ድረስ ያንን ማመን የሚከብድ አይሆንም።እንደእዛ ካልሆነ ሌላ አጀንዳ ነው ማለት ነው። ዝም ብሎ ግርግር መፍጠር እና እከሌ እንዲህ አለ፤ እከሊት እንዲህ አለች እየተባባሉ ለመኖር ካልሆነ በስተቀር ማለት ነው።እኛ ያንን አልመረጥንም።ምክንያቱም ለሕዝባችንም አይበጅም በሚል ነው።
ችግሩ አሁን የደረሰበት ሊደርስ የቻለው ብልጽግናን ያቋቋሙ መልካም አስተሳሰብ ያላቸው መሪዎች በመቸኮላቸው ነው እላለሁ።ከኢህአዴግ ወደ ብልጽግና ሲሸጋገሩ በነበረው ጊዜ ፍጥነቱ በጣም የበዛ ከመሆኑ የተነሳ የጥይት ያህል የተወነጨፈ ነበር። በዚህ ፍጥነት ውስጥ አንድ ያመለጠ አጋጣሚ እንዳለ እረዳለሁ።ትንሽ የሽግግር ጊዜ ያስፈልግ ነበር። ሕወሓትም አኩርፎ መሽጎ ነበር። መመሸግ ብቻ አልነበረም። ጥቃት እስከማድረስ መክፋቱ የሚታወቅ ነበር።የዚያን ያህል ዝግጅት ላይ ሳይደረስ ሁኔታዎችን ለመግታት ሲባል የተናደደ ንዴቱ እስኪበርድለት ጊዜ አልተሰጠውም።
በወዲያኛው በኩል ያሉ ሰዎች በፖለቲካው ጥርሳቸውን የነቀሉ ናቸው። አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ ያቋቋሙ አይነት አይደሉም። በፖለቲካው ዘርፍ ጠንከር ያሉ እንደመሆቸው ከእነርሱ ጋር መወያያት እንደሚያስፈልግ ግንዛቤው ቢኖር ጥሩ ነበር።እዛ ላይ መቻኮል ታይቷል ባይ ነኝ። መቻኮል ባይኖር ኖሮ የደረሰውን አደጋ በትንሹም ቢሆን መቀነስ እንችል ነበር።
አሁን ባለው ሁኔታ ምን ማድረግ ይቻላል ላልሽው አንደኛ የሀገርንና የሕዝብን ጥቅም አስበልጦ የማየትን አካሄድ ማዕከል ማድረግን መልመድ አለብን። የተናደዱ፣ የተቆጡ እንዲሁም ተበደልን ያሉ ወገኖች ሁሉ ፍልስፍናዊ የሆነ አመለካከት ያስፈልጋቸዋል ባይ ነኝ።ዝም ብሎ የጎበዝ አለቃነት የትም የሚያደርሰን አይደለም። ምክንያቱም ከዚህች ሀገር ጋር የየዕለት ግንኙነት የሌላቸው ስንትና ስንት ሺ ኪሎ ሜትር ላይ ተቀምጠው በሀገሪቱ ላይ የሚወነጭፉት ነገር ብዙ ነው። የሚገድሉት ሆነ የሚያድኑት እንዲሁም የሚያፈርሱትና የሚገለብጡት ጉዳይ መብዛቱ ለመቆጣጠር ፈታኝ ነው። በመሆኑም ጊዜውን አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡
በእርግጥ ሰለጠኑ በሚባሉ ሀገራትም ዘንድ እንዲህ አይነቱ አካሄድ እየፈተናቸው መሆኑ የሚታወቅ ነው።እነርሱም በጋለ ምጣድ ላይ የመቀመጥ ያህል ጉዳዩ አንገብጋቢ እየሆነባቸው መጥቷል።ስለዚህ በኢትየጵያ መንግሥት ላይ ብቻ የደረሰ አድርጎ ማየት የለብንም። ሁላችንም ጉዳዩን ሰፋ አድርገን ለማየት መሞከር አለብን።እንዲያም ሆኖ እኛ ከሀገራችን ውጪ ሌላ አማራጭ የለንም የምንለው ወገኖች፤ የተሻለውንና ሰላማዊ በሆነው ጉዳይ ላይ ልናተኩር ይገባል።
በዚህ ሀገር የማያባራ ጥያቄ አለ። ነጻ አውጪው ከመብዛቱ የተነሳ መቼ ነጻ ወጥተን እንደምናልቅ አይገባኝም። አንዳንዱም ገና ነጻ አልወጣሁም ይላል።ተማርን እውቀት አለን የሚሉትም ዘላለም ነጻ አልወጣንም ሲሉ ይደመጣል።ማን ከማን ነጻ ይወጣል? ማንስ ማንን ነጻ ያወጣል? ከዚህ መንፈስ መውጣትም መዳንም አለብን።ለዚህ ደግሞ ትዕግስት ያስፈልጋል፡፡
በዚህ ዘመን ትዕግስት የሚታጣ ከሆነ መሳሪያ የሚያቀብል ሞልቷል።ሰርቶ የመኖር መላ ለጠፋበት አካል ደግሞ ይህ የሚመረጥ ይሆናል።እያወኩን ያለው ከዚህ የተሻለና የጠለቀ አጀንዳ የሌላቸው ናቸው።በአሁኑ ወቅት ሮጥ ብሎ ዘመድ ጠይቆ መምጣት ዝም ብሎ የሚወሰን ነገር አልሆነም።
እኔ ለምሳሌ በቅርቡ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ሠራተኞችን ይዤ ለመዝናናትም ዓመታዊ ጉባኤ ለማካሄድም ወደ አርባምንጭ ተጉዤ ነበር። ወደ አርባምንጭ የመሄዳችን ነገር በአንጻራዊነት የሰላሙ ነገር ይሻላል በሚል ነው።ይሁንና ከሠራተኛው ውስጥ ፈርቶ የቀረ ነበር።ስለዚህ የእንቅስቃሴ ነጻነታችንን መነጠቅ አንሻም።በፍርሃት ቆፈን ውስጥ መውደቅም ጤንነት አይደለም።በፍርሃት ቆፈን ውስጥ ስንወድቅ ለሌላው የልብ ልብ ለመስጠት እንገደዳለን።ስለዚህ ሰው በእልኸኝነት እንቀስቃሴ መጀመር አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ስራውን የጀመረው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከዚህ አኳያ ተስፋውና ተግዳሮቱ ምንድን ነው?
ፕሮፌሰር በየነ፡- በሌሎችም ሀገራት አንዱ ሌላውን ከመበደሉ የተነሳ እስከ በቀል የሚያደርሱ ስሜቶች ይኖራሉ። በዚህ ጊዜ በመጀመሪያ እርቀ ሰላም ተብሎ በእኛ ሀገር ተሞከረ፡።በዚያን ጊዜ የኮሚሽኑ አባል ነበርኩ።ለሶስት ዓመት ያህል ያንን የእርቀ ሰላም መንፈስ ለማስረጽ ተሞከረ።ይሁንና በታሰበው ልክ ፈጥኖ ሊሄድልን አልቻለም።ምክንያቱም ኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ያላትና ሰፊ ሀገር እንደመሆኗ ለማዳረስ ችግር ነበር።አንደኛ የጥንት ሀገር እንደመሆኗ ጉዳዩ ከየት ነው የሚጀመረው የሚለው በራሱ አጠያያቂ ነበር።
በዚህች ሀገር ነው ታሪካዊ በደል ተበድለናል የሚለውም እየተንጸባረቀ ያለው። ከዚህ የተነሳ ስንቱ ተለይቶ ከተጋነነው ነጻ መውጣት ይችላል።ነገር ግን በአግባቡ አነጣጥሮ ትክክለኛ ሕመም ያለበት ካለ ለማዳን ጥረት ይደረጋል እንጂ በግለሰብ ደረጃ ያለው ችግር እየቆጠረ መፍታት አይቻልም።ከዚህ የተነሳ በወቅቱ ጉዳዩ ትንሽ አስቸጋሪ እንደሆነ ተረድቻለሁ።
በእርግጥ የአሁኑ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚለው እንመካከር ነው። እኔ የነበርኩበት ደግሞ ችግሩን እንፍታ ነበር። አሁን እየመራሁት ባለው የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት፣ ፈጥነን የዓለም አቀፉ ሁኔታ ምን ይመስላል በሚል አጥንተን ለዚህ ኮሚሽን አቅርበናል። የኢንስቲትዩቱ ተመራማሪዎች ብሔራዊ ውይይት የሚባለው ዓለም አቀፋዊ ገጽታው ምን ይመስላል? በአፍሪካ እና በሌላው የዓለም ሀገራት ምን ይመስላል? የሚለውን የዳሰሳ ጥናት አድርገን ለኮሚሽኑ አባል ማብራሪያ ሰጥተናል። የተጠረዘ ሰነድም ሰጥተናል። በዚህ መልክ ለተሞክሮ ይሆን ዘንድ ጥሩንም መጥፎውንም አጥንተን አቅርበናል፡፡
ስለዚህ ይህንን ሰፊ ማኅበረሰብ አገናኝቶ ለማወያየት አንደኛ ማኅበረሰቡን በትክክል የሚወክሉት ሕዝባዊ አመኔታ ያላቸው እንዲሆኑ ስብሰባዎችን ማካሔድ ያስፈልጋል።ምክንያቱም ከ120 ሚሊዮን በላይ የሆነውን ሕዝብ ማወያየት አይቻልምና ጉዳዩን በውክልና ማካሔድ ነው።
ይህ ሲደረግ አንዱ ተግዳሮት ሊሆን የሚችለው አንዳንዱ አካባቢ ተደራሽ ላይሆን መቻሉ ነው።እንዲህም ስል አሁን የጸጥታ ችግር ያለባቸውን አካባቢዎች ማለቴ ነው። እንዲያውም ዋና ውይይቱ የሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች ብዙ ችግር አለ።ያንን አካባቢ ሳንሸፍን ብንቀር ደግሞ ችግሩን ከመሰረቱ ፈትታን ማለት አይቻልም። ስለዚህ እነሱንም በማወያየት ወደሰላማዊ ሁኔታ ማምጣት ይመረጣል፡፡
አንዱ እኔን የሚያሳስበኝ ነገር ለራሳቸው ሰላም አጥተው ሀገሪቷን ሰላም የነሱ አካላት እንዴት አድርገን እናካትት የሚለው ጉዳይ ነው።እነሱን ትተን ሌሎቻችን ተስማማን ብንል በጥባጭ ባለበት የጠራ ውሃ መጠጣት አይቻልምና ችግር ይሆናል።በእርግጥ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከቁጥር አንጻር ስናይ እነሱ ሚዛን የሚደፉ አይደሉም።እንደዛም የተወሰነ ሆነው ሳለ እየበጠበጡ ነውና ይህ እንዳልኩሽ አንዱ ስጋቴ ነው።
ሰፊው ሕዝብ እንኳ በውይይቱ ላይ በሙላት ይሳተፋል። ያለበትን የልቡን ችግር በግልጽ ይናገራል። መፍትሔም እንዲያገኙ ወደአደባባይ ያመጣል። ይህን እንደ አንድ ተስፋ መውሰድ ይቻላል። ነገር ግን በጥባጮች አሉ። እነዚህ በጥባጮች ደግሞ “እኛ ያልነው ካልሆነ በስተቀር ስንበጠብጥ እንኖራለን” የሚሉ አሉ።ከዚህ የተነሳ ተወያዮችንና የመወያያ አጀንዳዎችን ኮሚሽኑ እየለየሁ ነው ቢልም ከእነዚህ ከተለዩ አካላት ጋር ሰርገው ገብተው የታለመለት የምክክር መድረክ እንዳይሳካ የሚያደርጉ አይጠፉምና እዚህ ላይ ጥንቃቄ ማድረጉ ተመራጭ ነው። ምክንያቱም ሰርጎ ገቦች አዳራሽ ድረስ ገብተው ሃሳብ እንዳይደራጅ የማድረግ ሙከራ ሊኖራቸው ስለሚችል ማጤን ይገባል። አጀንዳው ስኬታማ መሆን የሚችለው ምክክሩ ላይ የጋራ ግንዛቤ መጨበጥ ሲቻል ነው። ይህ እንዳይሆን የሚያደርግ አካል ምክክሩን እንዳይቀላቀልና እንዳያውክ በሚል ስጋት አለኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ መፍትሔው ምን መሆን አለበት ይላሉ?
ፕሮፌሰር በየነ፡– እንደ እኔ አተያይ ሕልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርም ነው የምለው።ምክክሩ መካሄድ አለበት።እሱ ጥሩ ጅምር ነው።ምናልባትም ይህ መንፈስ አስተማሪ ሆኖ ሌሎቹም ልብ እንዲገዙ ይረዳ ይሆናል።ምክንያቱም ሕዝቡ ከእነርሱ ጋር እንዳይደለ ሊረዱ ይችሉ ይሆናል።ምናልባትም በዚህ አጋጣሚም በጥባጮች ሊጋለጡ ይችላሉ። ከዚህ በኋላ በዱር በገደሉ መረበሽ አያስችለው ይሆናል። ስለዚህ እስከተቻለ ድረስ ይህ ምክክር መካሄድ ይኖርበታል። ምክክሩን መቶ በመቶ ማዳረስ ስላልቻልን ዋጋ የለውም የሚል ስሜት ሊነግስ አይገባም።
ምክክር መካሄዱ የሚያሳጣን አንዳች ነገር የለም፤ ይልቁን የሚጨምርልን መልካም ነገር አለው።መቼም ሚዛን የሚደፋው የሕዝብ ቁጥር በዚህ ምክክር ላይ የተለየ አቋም ይኖረዋል ብዬ አልገምትም።ፀጥታውን ያደፈረሱብንን አካላት ፈርተን ይህን መልካም አጋጣሚ እንዲያመልጠን ማድረግ የለብንም።እስካስኬደን ድረስ መሄድ አለብን።ከዚያም በሒደት እየገመገምን ምን ማድረግ ይቻላል የሚለውን እያየን እንቀጥላለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- ዓለም አቀፉ ማኅብረሰብ ለምክክሩ ሒደት ታማኝ ይሆናል ብለው ያስባሉ? የመፍትሔስ አካል መሆን ይችላሉ?
ፕሮፌሰር በየነ፡- ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሲባል በስደት ዓለም ያለው ዳያስፖራንም የሚያካትት ነው ባይ ነኝ። አብዛኛው ዳያስፖራ በጥባጭ ነው።በዛ በኩል አፍራሽ አስተሳሰብ ሊመጣ ይችላል።አንደኛ ከራሳቸው አልፎ የውጪውንም ማኅበረሰብ የማስተባበር ጥረት ያደርጋሉ።ለኢትዮጵያ የማይመጥን ገጽታ እያላበሱ ስሟን ለማጠልሸት ይሯሯጣሉ። ይሁንና ኢትዮጵያ እነሱ ከሚሏት በተቃራኒ ያለች ሀገር ናት፡፡
የዓለም አቀፉ ማኅብረሰብ ላልሽው እነርሱ ጉዳዩን የሚያዩት ከራሳቸው ጥቅም አኳያ ነው።አንድ ማወቅ ያለብን ነገር ቢኖር ከኢትዮጵያ ጋር መወዳጀት የማይፈልግ የውጭ ሀገር መንግሥት አለመኖሩን ነው። ኢትዮጵያ ዝነኛም ታሪካዊም ናት። ስለዚህ ከዚህች ሀገር ጋር ሁሉም መወዳጀት ይፈልጋል።እንዲያውም ወደእኔ ካልመጣሽ እየተባለ ለመወዳጀት የሚደረግ ሽሚያ ነው የሚበዛው እንጂ ሆነ ብሎ ኢትዮጵያን ለማፍረስና ለመበታተን የሚያስብም መንግሥት የለም ባይ ነኝ።ነገር ግን በዚህ ሁሉ ውስጥ ነገሮችን በጥንቃቄ ማጤኑ ተገቢ ነው።
ኢትዮጵያ ብትፈርስ የሚጠቀም አይኖርም። የኢትዮጵያ መፍረስ በብዙ የሚያጎድል እንደሆነ መንግሥታት አሳምረው የሚያውቁት ነው። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ፣ በጠቅላላ በአፍሪካ እንዲሁም በዓለም አቀፉ ዘንድ ተፈላጊ ሀገር ናት።
ለምሳሌ የቅርቡን ብቻ ማስታወስ በቂ ነው። በአህጉራችንም ሆነ በሌላ አህጉር በኢኮኖሚያቸው የሚበልጡና ሊመረጡ የሚችሉ ስንቶች እያሉ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል እንድትሆን መመረጧ ተፈላጊነቷን የሚያሳይ ነው። እንዲያውም እኔ ኢትዮጵያ ጠላቷ ታዋቂነቷ ነው ባይ ነኝ። ስለዚህ ኢትዮጵያን የሚፈልጓት ለማፍረስ ሳይሆን የራስ ለማድረግ ሊሆን ይችላል። በዚህ ውስጥ በሚደረግ ሩጫ ደግሞ መጎነታተል አይጠፋ ይሆናል እላለሁ፡፡
ኢትዮጵያ ደግሞ በስልት መጫወት ትችላለች። ከሁሉም ጋር በጋራ በሆነ ጉዳይ ላይ መስራት ነው። እኔ የምለው ኢትዮጵያ ውጭ ያሉ ልጆቿ የውጭ መንግሥታት በኢትዮጵያ ላይ እንዲያምጹ የሚያደርጉትን ልመና ማቆም አለባቸው። የኢትዮጵያ መንግሥት ሆነ ብሎ አንድን ማኅበረሰብ ሊጎዳ እንደተነሳ አድርገው ማሰባቸውን ማቆም ይጠበቅባቸዋል። በጣም የሚያስ ገርመኝ አንዳንዶቹ በደርግም ሆነ በኢህአዴግ ጊዜ በሀገራችን ዴሞክራሲ ይምጣ ብለን ስንታገል የነበሩና በቅርብ የማውቃቸው ጭምር ናቸው።
እነዚህ አካላት ማዕረጋቸው ፕሮፌሰር፣ ዶክተር የሚል ሆኖ አሁን እየጻፉ ያለውን ሳስተውል ይደንቀኛል።እነዚህ ምሁር የተባሉ አካላት በአሁኑ ወቅት በጡረታ እድሜ ላይ የሚገኙም ጭምር ናቸው።” ወደቀ” ሲባል “ተሰበረ” ለማለት መፍጠናቸው ያስገርመኛል። መንግሥት ሲባል ዝም ብሎ ያሰኘውን የሚናገር አይደለም። አቋም መውሰድ ካለበት እንኳን ግራ ቀኙን መዝኖ ነው እንጂ እነርሱ በጮኹ ቁጥር አይደለም።ለምሳሌ ከ40 ዓመት በላይ የማውቃቸው “ለኢትዮጵያ እንታገላለን” የሚሉ ታጋዮች፣ ቀደም ሲል ለዴሞክራሲና ለነጻነት ሲታገሉ የነበሩ ናቸው። አሁን ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ካልፈረሰ በሚል አሜሪካንንም ሆነ ሌላውን ሀገር የሚማጸኑ መሆናቸው ያስደንቀኛል።
ስለዚህ ለኢትዮጵያ አደጋ የሚሆኑት የገዛ ልጆቿ ናቸው ባይ ነኝ እንጂ በእውነቱ የአለም አቀፉ መንግስታት ኢትዮጵያ ደክማ፣ ፍርሳና ተበታትና ሊያዩዋት አይፈልጉም። ምክንያቱም ከዚህ ሊጠሙ አይችሉምና ነው። ኢትዮጵያ እንድትጠፋ መስራት ማለት ራሳቸውን እንደማጥፋት የሚቆጠር ነው። ኢትዮጵያ ብትፈርስ ከ120 ሚሊዮን በላይ የሆነው ሕዝቧ የሚሰደደው ወደእነርሱ ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያ እንድትፍረከረክ በፍጹም አይሹም።
አዲስ ዘመን፡- ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
ፕሮፌሰር በየነ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን መስከረም 24 ቀን 2016 ዓ.ም