ከውጪ ኢንቨስትመንትና ኢንቨስተሮች ጋር ሊታሰቡ የሚገባቸው ጉዳዮች

የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ወደ ሀገር ውስጥ በመሳብ ሂደት እንደ ሀገር ሊገኙ የሚችሉ መልካም እድሎች የመኖራቸውን ያህል፤ በዛው ልክ ሊታሰቡ የሚገባቸው ሥጋቶች መኖራቸው መዘንጋት የለውም። ምክንያቱም የውጪ ኢንቨስተሮች በአንድ ሀገር ሲሰማሩ ከጋራ ተጠቃሚነት የኢኮኖሚ ጉዳያቸው ባሻገር፤ የራሳቸውን ትርፍ ማግኘትና ሀብታቸውን ማሳደግ፣ ጥሬ እቃን በርካሽ ማግኘት፣ ርካሽ ጉልበትን ለመጠቀም፣ ብዙ ሕዝብ ባለበት ሀገርና አካባቢ ሰፊ ገበያን ፍለጋና ዋጋ የሚያወጡ መረጃዎችን በስለላ መልክ ለማሰባሰብም ዓላማ አድርገው ነው።

ከነዚህ በተጨማሪ ደግሞ የውጪ ባለሀብትም ሆኑ መንግሥታት በሀገራቸው ለማስቀመጥ ኪራይ የሚክፍሉበትን የተትረፈረፈ ገንዘብ ወይም ሀብት ከኪራይ ክፍያ ነጻ በሆነና በተከታታይ ጥቅም በሚሰጥ መልኩ ለማዋል ሲሉ በሌሎች ሀገራት ለረጅም ጊዜ ጥቅም ሊያገኙ በሚችሉበት መልኩ ኢንቨስት ያደርጋሉ። ይህ ገንዘብ የማሸሹ ፍላጎት የሚመነጨው በበለጸጉ ሀገሮች ሀብታሞች ገንዘባቸውን ለማስቀመጥ ኪራይ ስለሚከፍሉ የሚያገኙት ወለድ ከዜሮ በታች(negative interest rate) በመሆኑ ነው።

ከዚህም ሌላ በዓለም ዙሪያ ባለው የዋጋ ግሽበት (ኢንፍሌሽን) ምክንያት የገንዘባቸው የመግዛት አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ እንደሚሄድ ስለሚያውቁ በኢንቨስትመንት ስም ገንዘባቸውን ወደ ውጪ በማሸሽ ኢንቨስት ያደርጋሉ። ከነዚህም በተጨማሪ ከሚደረገው ኢንቨትመንት ጋር በተያያዘ የውጪ ኢንቨስተሮች ለዜጎቻቸው ለሚፈጥሩት የሥራ እድልም ከፍተኛ ቦታ ይሰጡታል።

እነዚህንና ሌሎች አላማዎችንና ፍላጎቶችን መሰረት ባደረገ መልኩ የውጪ ሀገር ኢንቨስተሮች በሌላ ሀገር ገንዘባቸውን ኢንቨስት ያደርጋሉ። እናም የውጪ ኢንቨስተሮች ሌላውን የመርዳት ፍላጎታቸው ለሽፋን ካልሆን በስተቀር እጅግ በጣም አነስተኛ ነው። ስለሆነም የውጪ ኢንቨስትመንት ጥቂት ጥቅሞች ሊኖሩት ቢችሉም፤ በአብዛኛው በርካታ ጉዳቶች እንዳለው በሰፊው ይታመናል።

ለምሳሌ፣ በ1883 ስምንት ሀገሮች ባደረጉት የአፍሪካን እንከፋፈል ስሌትና ስምምነት በአፍሪካ አህጉር ሰፊ ሰብዓዊ ጉዳት አድርሰዋል፡፡ የተፈጥሮ ሀብት ምዝበራም ፈጽመዋል፡፡ እነዚህ የዛን ጊዜው ቅኝ ገዢ ሀገራት ታዲያ ዛሬም በአብዛኛው በባለሀብቶቻቸው አማካይነት ወደ አፍሪካ ሀገሮች ገንዘባቸውን የሚልኩ ሆነዋል።ይህንን አይነት ድርጊት በጥቅሉ በርካታ ቁጥራቸው የማይናቅ ባለሙያዎችና አዋቂዎች በጥንቃቄ ያልተወሰነ ከሆነ፤ ቀደም ሲል በጦርነት የነበረውን የቅኝ አገዛዝና ሀብት የመዝረፍ ድርጊት የሚተካ ዘመናዊ የሆነ የኢኮኖሚ ቅኝ አገዛዝ (Economic Colonialism) ነው ይሉታል።

እናም ይህንን ብሂል በሚያንጸባርቅ ወይም በሚመስል አግባብ ድርጊቶች በትርፍ መልክ አንዳንዴ ማቆሚያ በሌለው ወይም የረጅም ጊዜ ውስብስብ ውለታን መሰረት በማድረግ ሀገሮች የሚወጣው የውጪ ምንዛሬና የሚፈጽሟቸው ድርጊቶች እጅግ በጣም የከፉ ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ በዚህ አይነቱ ውል ውስጥ ሀገራችን በ1897 ዓ.ም በመግባት ከአዲስ አበባ ጂቡቲ በተዘረጋው የባቡር ሃዲድ በጦርነት ሊያገኙት ያልቻሉትን የሀገራችንን ሃብት በእንቨስትመንት ስም የፈረንሳይ መንግሥት ሚሲዮናዊያን ከሆኑ ከእነዚያ ሁለት ፈረንሳዊያን ጋር በተደረገ ውል ለመቶ ዓመታት ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ ሀገራችን እንድትከፍል አድርገዋታል።

በመሆኑም ከሀገር በቀል ኢንቨስተሮች ጋር ሲነጻጸር የውጪ ኢንቨስተሮች የተገኘውን ትርፍ መልሰው እዚሁ ሀገር ውስጥ እናጥፋ ወይም ኢንቨስት እናድርግ ስለማይሉ፤ የተገኘውን የምርት ውጤትና ጥቅም (Newly Created Wealth) በተለያየ መልኩ ማለትም በትርፍ፣በዲቪዴንድ፣በሮያሊቲ፣ በደመወዝና በሌላ መልኩ በውጪ ምንዛሬ ከሀገር እንዲወጣ ያደርጋሉ። ዋናው አላማቸው ትርፍ ማግኘት ስልሆነም ትርፋቸውን እንደ የሀገር ውስጥ ኢንቨስተሮች መልሰው በሀገር ውስጥ ተከታታይና ተደጋጋፊ በሆኑ ሥራዎች ላይ አያውሉም። ስለሆነም የተመረተው ወይም በሀገር ውስጥ ጉልበትና ጥሬ እቃ የተፈጠረው ሀብት ተከታታይ እድገት (Extended Reproduction) ማስገኘት አይችልም ማለት ነው።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሁኔታ እጅግ በጣም አስፈላጊ ሳይሆን የሚመጣ የውጪ ኢንቨስትመንት ሀገር ቤት ያሉትን ተመሳሳይና እያደጉ ያሉ ኢንዱስትሪዎችን ወይም ተመሳሳይ ሥራ የሚሰሩትን ሌሎች ድርጅቶችን በተለያየ መልኩ የሚሰጡትን አገልግሎቶች በመሻማት የማቀጨጭ ወይም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደግሞ ከነአካቴው የመተካትና ከገበያ የማውጣት ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ። እንደዚሁ ደግሞ ነባር፣ ተመሳሳይና ተቀራራቢ ድርጅቶች ላይ በሚፈጥሩት ጫና ሀገር በቀልና ባህላዊ ምርቶችን ቀስ በቀስ ከገበያ ሊያወጣቸው ይችላሉ።

የውጪ ኢንቨስተሮች ዋነኛ አላማቸው ትርፍ በመሆኑ የዜጎችን መብትና ጥቅም የሚጎዳ ሥራ ሊሠቸሩ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ለዜጎች የጡረታ ጥቅም አለማስከበር እንደ ትልቅ ጉዳት ሊቆጠር ይገባዋል። በዜጎች ላይ ብቻ ሳይሆን ትርፍን ከማሳደግ ዋነኛ አላማቸው የተነሳ በአካባቢ የአየር ሁነታና የተፈጥሮ ሀብት ላይ ጥፋትና ብከለት ሊፈጥሩ ይችላሉ።

በተለይ የኢንዱስትሪ ምርት አምራች የሆኑ የውጪ ኢንቨስተሮች ምርት በሚመረትበት ጊዜ የሚወጣው ፍሳሽም ሆነ ጭስ ወይም ሌላ ነገር በአየር ጠባይና የአካባቢ ብክለት በቀላሉ የሚያስከትሉ ሊሆኑ ይችላሉ። ከዚህ ጋር በተያያዘ አስፈላጊ ቁጥጥርና ክትትል ካልተደረገ በአካባቢ ነዋሪዎች፣ እንስሳትና የተፈጥሮ ሀብት ላይ ከፍተኛ ችግር ማስከተል እንደሚችሉ በማወቅ ጥንቃቄ መደረግ አለበት።

ሌላው እጅግ የከፋ የሚሆነው፣ የውጪ ኢንቨስትሮች ችግር የውጪ ምንዛሪ ላይ ጫና ሊፈጥሩና እጅግ አስፈላጊ ለሆኑ ግብአቶች መግዣ የሚውል የውጪ ምንዛሪ ሚዛን ሊያዛቡ መቻላቸው ነው። ለኢትዮጵያ የውጪ ምንዛሪ ማለት ጠንካራና ዘመናዊ የሀገር መከላከያ ማለት ነው። አስፈላጊና በቂ መድኃኒቶች፣ ነዳጅ፣ ማዳበሪያ፣ የሕክምና መሳሪያዎችና ለትምህርት ዘርፍ የሚውሉ በርካታ ግብአቶች ማለት ነው። በርካታ ማሽነሪዎችንና የእርሻ መሳሪያዎች ማቅረብ ማለት ነው፡፡ ተሽከርካሪዎችንና የመለዋወጫ እቃዎቻቸውን ማቅረብ ማለት ነው፡፡ አልባሳትንና የሕንጻ ግብአቶችን፣ የኤሌክትሮኒክስና የቤት ውስጥ ፍጆታ እቃዎችንና ሌሎች በርካታ በውጪ ገንዘብ የሚገዙ እቃዎችን ለሕዝብ ማቅረብ መቻል ማለት ነው።

ከእነዚህ በተጨማሪ ሀገራችን የውጪ ምንዛሪ ለበርካታ ጉዳዮች አንገብጋቢ በሆነ ደረጃ ትፈልጋለች። ስለሆነም ከውጪ ኢንቨስተሮች ጋር የሚደረገው ስምምነት በክፍያ በኩል አስገዳጅ፣ የጊዜ ገደብና ቅጣት ያለው ከሆነ ሊሰጠው ከሚገባ ቅድሚያ የተነሳ በሀገራችን የውጪ ምንዛሪ ፍላጎት ላይ ከፍተኛ ጫናን ይፈጥራል። ስለሆነም ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎች አስፈላጊ ግዢዎች ላይ ከፍተኛ ጫናን ይፈጥራል። ስለሆነም ትርፋቸውን በውጪ ምንዛሪ የሚወስዱ ነገር ግን ወደ ውጪ የሚሸጥ ምርት የማያመርቱ የውጪ ድርጅቶችን ወደሀገር በመጋበዝ ጉዳይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል ማለት ነው።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ መልኩ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የውጪ ኢንቨስተሮች ሲመጡ ሌሎች የራሳቸው ዜጎች እዚህ የሚሠራውን ሥራ የሚሠሩት ወይም የሚያስተባብሩት በውጪ በሀገራቸው ሆነው ነው። በውጪ ምንዛሪ የሚከፈሉትም እዚህ ከሚሰራው ሥራ ትርፍ ነው። ኢንቨስት አድራጊው ድርጅት ወደ ውጪ የሚሸጥ ምርት የማያመርት ከሆነ ይህንንም ክፍያ ከፋዮች የእኛው የቡና ገበሬዎችና ሌሎች ወደ ውጪ የሚሸጡ ምርት አምራቾች ናቸው ማለት ነው። ስለሆነም የነዚህንም አይነት ኢንቨስተሮች የውጪ ገበያ ፈልገው ምርታቸውን በመሸጥ የውጪ ምንዛሬ የሚያስገኙ ስለመሆናቸው ከስምምነቱ በፊት እርግጠኛ መሆን ይገባናል።

በነዚህ አይነት ሊታዩ በሚችሉ ውሳኔዎች በሀገራችን በርካታ ፋብሪካዎች ለውጭ ሀገር ኢንቨስተሮች ተሸጠዋል። ይሄ ለአጭር ጊዜ ጥቅም ሲባል፣ የመሐከለኛና የረጅም ጊዜ እዳና ግዳጅ ሳይታሰብ ወይም በደላላዎች ጫና ሊሆን ቢችልም፤ በዚህ ግን ሀገራችን በርካታ ግዴታዎች ውስጥ የገባች መሆኑ ይታወቃል።

ለምሳሌ ያህል፣ ለውጪ ኢንቨስተሮች በርካታ የቢራ ፋብሪካዎች ተሸጠዋል። ከተሸጡት የቢራ ፋብሪካዎች መሃከል የበደሌ ቢራ ፋብሪካ ከ12 ዓመታት ገደማ በፊት የተሸጠው በ310 ሚሊዮን ዶላር ነው። ለምን ለውጪ ኢንቨስተር መሸጥ አስፈለገ? ከሽያጩ በኋላ ለገዥው ድርጅት በሀገር ውስጥ ለሚሸጠው ምርት በተከታታይ በውጪ ምንዛሪ የሚከፈል ክፍያ ስላለ በሽያጩ ገንዘብ ሌላ ምን የውጪ ምንዛሬ የሚያስገኝ ኢንቨስትመንት ተደረገበት? ባለፉት 12 ዓመታት በውጪ ምንዛሪ ለገዢው የተከፈለው ገንዘብ ከተገዛበት ዋጋ ጋር ሲነጻጸር ምን ያህል ነው ? ወደ ውጭ ሀገር የሚሸጥ ምርት ያመርታሉ ወይ? ከሌሎች ከፍ ባለ ጠርሙስ የሚሸጡት ቢራ በሌሎች አምራቾች ላይ ምን ተጽእኖ ይፈጥራል? የዚህ አይነቱ ምሳሌ ምን ያስተምረናል? የሚሉት ጥያቄዎችና ሌሎች ጉዳዮች በተለያየ መልኩ መመርመርና ለሌሎች ውሳኔዎች መሰረትና መማሪያ መደረግ አለባቸው እላለሁ።

በዚህ ረገድ የውጪ ኢንቨስትሮችን ሳያስገባ የኢትዮጵያ መንግሥት ካደረጋቸውና እያደረገ ካላቸው ሥራዎች ውስጥ የኢትዮጵያ አየር መንገድና የዓባይ ግድብ እራስን በራስ የመቻል ውሳኔዎች ለበርካታ የሀገራችን ድርጅቶች የይቻላል አራአያና መማሪያ መሆን እንዳለባቸው መታወቅ ይገባዋል። ስለእነዚህ ሁለትና ሌሎች ተመሳሳይ ድርጅቶች፣ ሌሎች ድርጅቶች ሁሉ እንዲሰሙ ድምጻችንን ከፍ አድርገን መናገር ይኖርብናል።

እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ በዱቤ ወይም ተብድሮ መግዛት እያለ ለብዙ ሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶችንና ብዙ የውጪ ምንዛሪ የማያስገኙ ድርጅቶችን አገልግሎቶች ለውጪ ኢንቨስተርስ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል አሳልፎ መሸጥ ከራሳችን ጠንካራ ድርጅቶች ለመማር ካለመቻል ወይም ለመማር ፈቃደኛ ካለመሆን ወይም በደላላዎች ግፊት የተደረጉ ውሳኔዎች ሊሆኑ ይችላሉ ማለት ይቻላል።

ለምሳሌ ያህል አቶ ግርማ ዋቄ፣ አቶ ተወልደ እና ሌሎችም በተለያየ መልኩ የውጪ ኢንቨስተሮች ሳያስገቡ አውሮፕላኖች ከቦይንግ ከኤርባስ በዱቤም ይሁን በብድር ገዝተው እጅግ በጣም የተዋጣለት ሥራ የሚሰሩና የመሩ መሆኑ እየታወቀ፤ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን 40 በመቶ ወይም የ28 ሚሊዮን ደንበኞቹ መጠቀሚያ የሆነውን አገልግሎቱን ለምን ለውጪ ኢንቨስተሮች እንደሸጠ ስንጠይቅ በርካታ መልሶች ሊኖሩት ቢችልም፤ የመጀመሪያው መልስ ግን ከኢትዮጵያ አየር መንገድ መማር አለመቻሉን ወይም ለመማር አለመፈለጉን እንገነዘባለን፡፡

ይህንንም የምለው በዓለም በቻይና፣ በአሜሪካ፣ በደቡብ ኮሪያ በእንግሊዝና በሌሎች ሀገሮች እጅግ በጣም ዘመናዊ ተወዳዳሪና ተፎካካሪ የሆኑ የቴሌኮሙኒኬሽን ታወሮችና መሳሪያዎች በሰፊው የሚያመረቱ፣ የሚሸጡና የሚከራዩ መሆናቸው የሚታወቅ ስለሆነና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሥራ አፈጻጸም ለኢትዮጵያ ቴሌኮምም ሊሰራ እንድሚችል ስለማምን ነው። ምክንያቱም ከነዚህ ወደ 28 ሚሊዮን ከሚሆኑ ደንበኞች በየወሩ የሚሰበሰበው በአብዛኛው በብር ሲሆን፤ ለውጪ ኢንቨስተሮች የሚከፈለው ግን በውጪ ምንዛሪ ነው።

ይህ በወራዊ፣ በመንፈቃዊና ዓመታዊ ተሰለቶ ወደ ውጪ ምንዛሪ ከተለወጠ በኋላ የኢትዮጵያ ቴሌኮም በአገልግሎቱ ከሚያገኘው የውጪ ምንዛሪ ገቢ ጋር ማወዳደሩ ለወደፊት ለሌሎች ሃገራዊ ዉሳኔዎች ጥቅም ያለዉ ይመስለኛል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ይህ ዉል ለእኔ ከላይ እንደጠቀስኩት እንደ የ1897 ከአዲስ አበባ ጂቡቲ የባቡር መንገድ ግንባታ ዉልና ስምምነት መጪዉን ትዉልድ ጭምር ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍል ይመስልኛል። ኢትዮጵያ ለኬንያ የምትሸጠዉ የመብራት ሃይል በአብዛኛው የማምረቻ ምርት (Producer Good) ሲሆን፤ እየገዛን ያለነው ግን በአብዛኛው የፍጆታ ምርት (Consumer Good) ነዉ። በመሆኑም በርካታ የሀገራችን ድርጅቶች ከዚህ አይነቱ ዉሳኔ መማርና መራቅ አለባቸዉ እላለሁ።

ሌላው ለኢትዮጵያ እጅግ አሳሳቢ የሚሆነው በባንኮች ዙሪያ ያለው የውጪ ባንኮች የመጋበዙ ፍላጎት፣ ጥረትና ሃሳብ ነው። የባንኮች እንቅስቃሴና ሥራ ለሀገር እድገት እጅግ በጣም አስፈላጊና ወሳኝ ነው። ለፋብሪካ መስፋፋት፣ ለእርሻ እድገት፣ ለንግድ እድገትና መጠናከር፣ ለግንባታ ሥራዎች መስፋፋትና እድገት፣ ፈጣን የሆነ የገንዘብ ዝውውር ለሚሹና ለሁሉም የምጣኔ/ኢኮኖሚ ዘርፎች ማደግ ብዙ የውጪ ምንዛሪ ዋጋ የማያስከፍሉ የሀገር በቀል ባንኮች ብዛትና ስርጭት እጅግ በጣም ወሳኝና አስፈላጊ ነው።

ስለሆነም በታከታታይ በቁጥርም ሆነ በአገልግሎት አይነት የሚያድጉ ባንኮች በብዛት ያስፈልጉናል። እነዚህም ሀገር በቀል ባንኮች በሥራቸውና በእድገታቸው ላይ ጫናና አላስፈላጊ ከሆነ የውጪ ተፎካካሪዎች ነጻ በመሆን ከሕዝባችን እድገት ጋር ማደግ አለባቸው። ከንግድ ባንክና ከልማት ባንክ በስተቀር የባንኮቻችን እድሜ 30 ዓመታት ገደማና ከዚያ በታች በመሆኑ ገና ታዳጊዎች ናቸው።

ስለሆነም እጅግ ብዙ እድሜና ብዙ ካፒታል ባካበቱ ዋናው ዓላማቸው ትርፍ፣ ለዜጎቻቸው የሥራ እድል ፈጠራና ወለድ አልባ የሆነ ገንዘባቸውን ማሸሻ ከሆኑ ባንኮች ጫናና አግባብ የሌለው ፉክክር ነጻ መሆን አለባቸው። ስለሆነም የውጪ ባንኮች ወደ ሀገራችን መጋበዝ በጥንቃቄና አስፈላጊነታቸውና የሥራ ድርሻቸውን በአግባቡ በበርካታ ባለሙያዎች የተለየ ፣ የተደገፈና የተረጋገጠ ምክንያታዊ መሆን ያስፈልገዋል። አለበለዚያ እጅግ አስከፊና ለትውልድ የሚተላለፍ ችግርና እዳ ውስጥ ልንገባ እንችላለን።

በዚህ ረገድና አቅጣጫ የሌሎችንም ሀገሮች ልምድ መመርመሩና ማየቱ እጅግ አድርጎ ይጠቅማል። ለምሳሌ ያህል፣ ናይጄሪያ ከፍተኛ የውጪ ንግድና የኢኮኖሚ ትስስር ከምእራባውያን ጋር ያላት መሆኑ ቢታወቅም 94 በመቶ የሚሆነው የባንክ አገልግሎታቸው ሀገር በቀል ለሆኑ ባንኮች ብቻ የተፈቀደና የተሰጠ ነው። ሌላው፣ በእስራኤል ያለው የውጪ ባንኮች ፖሊሲም ከዚሁ ጋር የሚመሳስልና የሚቀራረረብ ነው። በእስራኤል ሀገር ገና ከጅምሩ ማሳደግ የሞከሩት የራሳቸውን ባንኮች በመሆኑ ዛሬ 95 በመቶ የሚሆነው የባንክ አገልግሎት የሚሰጠው ሀገር በቀል ለሆኑ ባንኮች ብቻ ነው።

የእነዚህ ሁለት ሃገሮች በራስ መተማመንና ለራሳቸዉ በሚሰጡት ብሄራዊ ክብር (National Pride) ሀገሮቻቸው በውጪ ባንኮች እንዳይወረሩ በማድረጋቸው በበርካታ የዓለም የምጣኔ ሀብት ሙያተኞች ከፍተኛ ሙገሳ እንዲያገኙ ያደረጋቸው መሆኑ ይታወቃል። ሌላው በምሳሌነት ሊጠቀስ የሚችለው የአሜሪካ፣ የካናዳ እና የእንግሊዝ ነው። እነዚህ ሶስት ሀገሮች እጅግ በጣም የጠበቀ በርካታ የምጣኔና የፖለቲካ ትስስር ቢኖራቸውም፤ አንድም የአሜሪካ ባንክ በካናዳ ወይም የካናዳ ባንክ በአሜሪካ (ኒዮርክ ከተማ ውስጥ ካሉ ጥቂት ቅርንጫፎች በስተቀር) በሌሎች ከተሞች ቅርንጫፍ ከፍተው አይታዩም ወይም አይሰሩም። እንደዚሁ የአሜሪካ ባንኮች በእንግሊዝና የእንግሊዝ ባንኮች በአሜሪካ ከተሞች አይታዩም። ከነዚህ ሁኔታዎች ብዙ መማር የምንችል ይመስለኛል።

ከዚህ በተቃራኒ በርካታ የውጪ ባንኮች ወደ ሀገራቸው በመጋበዝ ከመበዝበዝ መውጣት ያቃታቸው በርካታ ሀገሮች መኖራቸውን አውቀን፤ በዚህ የውጪ ባንኮች ወደ ሀገር መግባት ግብዣ ዙሪያ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ ያለበት ጉዳይ ነው። እናም ውሳኔው የፖለቲካ ወይም የሎቢስቶች ጉዳይ ሳይሆን የባለሙያዎች ውሳኔ መሆን አለበት እላለሁ።

በአጠቃላይ የውጪ ኢንቨስትመንትና ኢንቨስተሮች ግብዣ ውሳኔ ከጥቅሙ ባሻገር ያሉ ጉዳዮችን በጥንቃቄ መመልከት፤ አስፈላጊነቱ ከተረጋገጠና ሌሎች አማራጮች አለመኖራቸው በባለሙያዎች ተመርምሮ፣ ምስክርነት ከተሰጠበት በኋላ የሚወሰን ካልሆነ በስተቀር ቅጥ ያጣ የረጅም ጊዜ እዳ ውስጥ ለመግባት ስምምነት እንደተደረገ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባዋል። ሀገራችን ከአቅማችንና እጅግ ወሳኝ ከሆነ ፍላጎታችን ውጪ በሆነ መልኩ የውጪ ኢንቨስተር ስትጋብዝ ጉዳቱ ከሚገኘው ጥቅም በጣም የበዛ ሊሆን ይችላል።

ስለዚህ የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ጥቅምና ጉዳቱ በሙያተኞች ስሌት በአሃዝ በተደገፈ መልኩ መመዘንና ሌሎች አማራጮች መኖር አለመኖራቸው መረጋገጥ አለበት። ከዚህም በተጨማሪ የዚህ አይነቱ ውሳኔ ከደላላዎች ወይም ከሎቢስቶች ነጻ በሆነ መልኩና በፖለቲከኞች ውሳኔ ብቻ ሳይሆን፤ ከላይ እንደጠቀስኩት በሙያተኞች ነጻ ውይይት ከተደረገበት በኋላ በጥንቃቄ ተገምግሞና ተመርምሮ የሚወሰን መሆን አለበት። ይህ ካልተደረገና ውሳኔዎች በችኮላና ጥንቃቄ ባልተሞላበት መልኩ በጥቂት ግለሰቦች ፍላጎት ከተወሰኑ ከላይ እንደጠቀስኩት ሀገራችን ለትውልድ የሚተላለፍ እዳና ለረጅም ጊዜ የውጪ ምንዛሪ የሚያስከፍለን አስገዳጅ ውል ውስጥ በቀላሉ ልትገባ ትችላለች እላለሁ።

 ጋሹ ሀብቴ (ዶ/ር)

Ghabte12@aol.com

አዲስ ዘመን  መስከረም 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You