ሀገራዊ አቅሞቻችንን በሚገባ ማወቅ ለኢትዮጵያ ብልጽግና መሠረት ነው!

 የአንድ ሀገርና ሕዝብ የወደፊት ዕጣ ፈንታ በዋናነት የሚወሰነው ያ ሕዝብ /ሀገር ስላለው ሀብትና አቅም ተገቢው እውቀት ሲኖረውና እና ይህንን ዕውቀት ወደሚጨበጥ ተስፋ መለወጥ የሚያስችል መነቃቃት መፍጠር ሲችል እንደሆነ ይታመናል። አሁን ላይ ስለማደጋቸው ብዙ የሚነገርላቸው ሀገራትና ሕዝቦችም እውነታ ከዚህ የተለየ እንዳልሆነ የታሪክ መዛግብት ያመላክታሉ።

እነዚህ ሀገራት ዛሬ ላይ የደረሱበት የዕድገት ደረጃ ለመድረስ እንደ ሀገር ያላቸው ተፈጥሯዊ ፣ ማህበራዊና ሰብዓዊ ሀብቶቻቸውን አግባብ ባለው መንገድ ትኩረት ሰጥተው ለማየት ረጅም ርቀት ተጉዘዋል። በዚህ ሂደት ያገኟቸውን አቅሞች በማጎልበት የሀገርና የሕዝብ ተጨባጭ ተስፋ የሚሆንበትን መልካም አጋጣሚ ፈጥረዋል። ዜጎችም ያላቸውን አውቀው ባላቸው መጠን እንዲያስቡ ማድረግ የሚያስችል ሥርዓትም መፍጠር ችለዋል፡፡

አንዳንድ ሀገራት ከራሳቸውም ባለፈ ባህር ማዶ ተሻግረው የሌሎችን አቅም በማጥናት ተጠቃሚ ለመሆን የሄዱበት ሆነ እየሄዱበት ያለው መንገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸውን ተጠቃሚነት እያጎለበተላቸው ለዜጎቻቸው ከትናንት የተሻለች ዛሬን ፈጥረዋል። ነገዎቻቸውን ከዛሬ በተሻለ ተስፋ የሚጠብቁበትን ማንነትም ገንብተዋል።

እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ ሀገር የህልም ችግር ያለብን ሕዝቦች አይደለንም። ትናንት የትልቅ ታሪክ ባለቤት ከመሆናችን የተነሳ ከፍያሉ ህልሞችን ለማለም ብዙ ተግዳሮቶች የሚፈታተኑን አይደለንም። ከዘመን ዘመን ከትውልድ ትውልድ የሚሻገሩ ታላላቅ ሕልሞች ባለቤቶች ነንና። እያንዳንዱ ትውልድ ከትናንት ታሪኩ እየተነሳ የበለጸገች ታላቅ ሀገር የመፍጠር ራዕይ ሰንቆ የህይወት ጉዞውን ለመጓዝ ሞክሯል።

ይህም ሆኖ ግን “በየዘመኑ ትልቅ እንደሆንን ትልቅ እንሆናለን” ከሚለው ትውልዳዊ መፈክር ባለፈ እንደሀገር ወደ አሰብነው ለመድረስ ሳንችል ዘመናት ተቆጥረዋል። ካሰብነውና ካለምነው ይልቅ ያላሰብነውና ለማሰብ የሚከብደን እጣ ፈንታችን ሆኖ ብዙ ዋጋ ከፍለናል። በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሳይቀር ባልተገቡ ስያሜዎች ለመጠራት ተገደናል።

ለዚህ ደግሞ በዋነኛነት እንደ ችግር የሚጠቀሰው ከራሳችን ተርፎ ለብዙዎች የሚተርፍ ተፈጥሯዊ ፣ ማኅበራዊና ሰብአዊ ሀብት ባለቤት የመሆናችንን እውነታ በአግባቡ አለማወቃችን፤ ለዚህ የሚሆን የትውልዶች መነቃቃት የሚፈጥር የአስተሳሰብ መሰረት መገንባት አለመቻላችን እንደሆነ ይታመናል። በተለይም እንደ ሀገር ይህን አእምሮ አለመፍጠራችን ከትናንት የተሻለች ሀገር እንዳንፈጥር ተግዳሮት ሆኖብናል።

ይህ ችግር ከሁሉም በላይ የተሻለች ሀገር ለመፍጠር የሚያስፈልገንን ሀገራዊ ሰላም ተጨባጭ ለማድረግ ትልቁ ፈተና ከሆነ ሰነባብቷል፤ ከዚህም ባለፈ ዜጎች ነገዎቻቸውን ባሰቡ ቁጥር ተስፋቸውን ባህር ማዶ እንዲያደርጉ ፣ በዚህም ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍሉ እያደረጋቸው ይገኛል።

በዚህ መልኩ ወደ ፊት ዋጋ ለመክፈል የተዘጋጁ ዜጎችም ቁጥር እንዲህ በቀላሉ የሚሰላ ነው ተብሎም የሚገመት አይሆንም። በቀደሙት ዘመናት እንደ ሀገር ያለንን አቅም አለመረዳታችንም ሆነ ለዚህ የሚሆን ሀገራዊ መነቃቃት አለመፍጠራችን፤ የቱንም ያህል ዋጋ ያስከፈለን ቢሆንም አሁን ላይ በችግሩ ዙሪያ የተሻለ ግንዛቤ መፍጠር ከቻልን እንደ ሀገር የሚኖሩን ነገዎች ብሩህ ስለመሆናቸው ብዙም ለጥያቄ የሚቀርብ አይደሉም። የማወቃችንን ያህል መለወጣችንም የማይቀር ነው።

ከዚህ አንጻር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይህንን እውነታ ታሳቢ አድርገው በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሰሞኑን ያደረጓቸው ጉብኝቶች እና በጉብኝቶቹ የፈጠሩት አቅምን የማወቅ መልካም አጋጣሚ እንደሀገር ለጀመርነው የብልጽግና ጉዞ ስኬታማነት ትልቅ ጉልበት እንደሚሆን ይታመናል።

በተለይም የክልል መንግሥታት የክልሎቻቸውን አቅም በአግባቡ ማወቅ የሚያስችል ወጥነት ያለው የአሰራር ሥርዓት በመፍጠር የዜጎቻችንን ነገዎች ብሩህ ለማድረግ የተጀመረው ሀገራዊ ንቅናቄ ትርጉም ያለው ውጤት እንዲያስመዘግብ ከቢሮ ያለፈ ስ ምሪቶች እንደሚያስፈልግም ያሳየ ነው።

በክልሎች የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ቢሆኑ በሀገር ዕድገት ውስጥ ተጨባጭ ሚና እንዲኖራቸው፤ በየአካባቢው የሚገኙ ሀገራዊ አቅሞችን በመለየት ለዜጎች የተሻለች ሀገር ለመፍጠር ትልቅ ኃላፊነት እንዳለው ተቋም ከፍ ባለ የኃላፊነት መንፈስ ሊንቀሳቀሱ ይገባል።

ባለሀብቶቻችንም ቢሆኑ እነዚህን አቅሞች በማወቅ በራሳቸውም ሆነ ከሌሎች ሀገራት ባለሀብቶች ጋር በመተባበር ለማልማት ግንባር ቀደም መሆን ይጠበቅባቸዋል ፤ በዚህም ለራሳቸው ፣ ለልጆቻቸውና ለልጅ ልጆቻቸው፤ ከዛም ባለፈ ለሀገርና ለመጪዎቹ ትውልዶች የበለጸገች ሀገር ለመፍጠር በሚደረገው ሁለንተናዊ ርብርብ የዜግነት ድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል!

አዲስ ዘመን  መስከረም 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You