
አዲስ አበባ:- የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ቀጣናዊ ትስስራቸውን በማጠናከር ለቀጣናው ሠላምና ዕድገት በጋራ ሊሠሩ እንደሚገባ የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ዋና ጸሐፊ ገለጹ። የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የድንበር መሬት ፍኖተ ካርታ ሊዘጋጅ ነው።
18ኛው የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ የሚኒስትሮች ስብሰባ ትናንት ሲካሄድ የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ሠላምና ዕድገት ማረጋገጥ የዕለት ተዕለት ተግባር ሊሆን ይገባል።
በቀጣናው የሚገኙ ሀገራት በታሪክና በባህል የተሳሰሩ እንደመሆናቸው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነታቸውን ማጠናከር፣ የተፈጥሮ ሀብትን በጋራ ማልማትና የድንበር ላይ ንግድን ማሳለጥ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
የሚኒስትሮቹ ስብሰባ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና የድንበር መሬቶች ጉዳይ አንዱ አጀንዳው መሆኑንም ዶክተር ወርቅነህ አንስተዋል።
የድንበር መሬት ፍኖተ ካርታ ለአካባቢ ብልጽግና፣ ለሠላም መስፈንና ለአጠቃላይ ዕድገት ወሳኝ በመሆኑ የድንበር መሬት ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑንም ገልጸዋል።
በቀጣናው ሀገራት የሚዘጋጀው ፍኖተ ካርታ በአፍሪካ ቀንድ ድንበሮች አካባቢ ልማትን ለማፋጠን፣ የድንበር መሬትን ለማልማት፣ የጋራ ራዕይና ስትራቴጂ ለማዘጋጀት እንደሚጠቅም ተናግረዋል። የተገለሉ ማኅበረሰቦችንም ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማስፈን የላቀ ድርሻ እንደሚኖረውም አስገንዝበዋል።
በሀገራቱ መካከል የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የድንበር መሬት ፍኖተ ካርታ ለማዘጋጀት ቁርጠኝነቱ አለ ያሉት ዶክተር ወርቅነህ፤ ትግበራውን ዕውን ለማድረግ አሳታፊነትን መሠረት ያደረገ ሥራ ማከናወን ተገቢ ነው ብለዋል።
የድንበር ኬላን የንግድ መሸጋገሪያ፣ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የማኅበራዊና ባህላዊ ትስስር ማጠናከሪያ፣ ፖለቲካዊ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ማዕከል ሆኖ እንዲያገለግል መሥራት ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።
የግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንቶች በኢትዮጵያ ለማስፋፋት የአውሮፓ ኅብረትና አባል ሀገራት ሂደቱን በአወንታዊ እንደሚደግፉም አስታውቀዋል።
በቀጣናው የጋራ ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶችን ለመፍታትና ሀገራዊ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ትኩረት ማድረጉንም ጠቁመዋል።
የፍኖተ ካርታውን ዓላማ ከግብ ለማድረስ መተባበር፣ መሠረተ ልማቶችን ማሻሻል፣ ቀጣይነት ያለው ሠላም ግንባታ ማስፋፋት እንደሚገባም አመላክተዋል።
18ኛው የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ኢትዮጵያን፣ ኬንያን፣ ሶማሊያን፣ ጂቡቲን፣ ኤርትራን፣ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳንን በአባልነት ያቀፈ ሲሆን ከየካቲት 2015 ዓ.ም ጀምሮ የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭን ኢትዮጵያ በሊቀመንበርነት እየመራች ትገኛለች።
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን መስከረም 23 ቀን 2016 ዓ.ም