«ቡቺ፣ ቦቢ፣ …» የሚሉት መጠሪያዎች በእኛ ሀገር ለውሾች ስያሜ ይውላሉ። የእነዚህን መጠሪያዎች ትርጉም በትክክል ለማወቅ አስቸጋሪ ቢሆንም፤ ውሾቹም ለምደዋቸው ሲጠሩበት ከተፍ ይላሉ። እነ «ቡቺ» ስለለመዱ እንጂ፤ የውሾቹ ባለቤቶች ያሻቸውን ስም በመጠሪያነት ሊሰጧቸው ይችላሉ። በሌላው ዓለም ግን ለውሻዎ ያወጡለት ስም ምናልባትም ተቀባይነት የሌለውና ቅጣት ሊያስከትል የሚችልም ይሆናል። ኦዲቲ ሴንትራል ከሰሞኑ እንደዘገበው፤ አንድ ቻይናዊ ለሁለት ውሾቹ ባወጣላቸው ስሞች ምክንያት ለአስር ቀናት በእስር እንዲቆይ ተደርጓል።
ነዋሪነቱን በምስራቅ ቻይና ያደረገው የ30ዓመቱ ጎልማሳ የሚያሳድጋቸውን ሁለት ውሾች «ቼንዋን» እና «ዤጉዋን» በሚል የሰየማቸው ሲሆን፤ በማህበራዊ ድረገጽ ላይም ይህንኑ ይለጥፋል። ለውሾቹ እንደ ቀልድ ያወጣላቸው ስም እንደሚያስቀጣው ያላወቀው ግለሰብም፤ በማህበራዊ ድረገጾች መታየት እንደጀመረ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሊያውለው ችሏል። ምክንያቱ ደግሞ ስሞቹ የሀገሪቷ መንግሥት እና ሰራተኛው ጋር ተያያዥነት ያለው በመሆኑ ነው። አንድ የፖሊስ ኃላፊ እንደገለጹት ከሆነም፤ ስሙን ለውሻ መጠሪያነት ማዋል መንግሥትን እና ሰራተኛውን የሚያስተዳድረውን አካል ይጎዳል።
ስም አውጪው ግለሰብ በበኩሉ «ህጉን አላውቀውም፤ ይህን መሰል ስም ማውጣቴም ህገወጥ መሆኑን አላወቅኩም ነበር» ሲል ነው ቃሉን የሰጠው። ይህንን ተከትሎም ዣንግያንግ በተባለው ከተማ ባለው ማረፊያም ለአስር ቀናት ያህል በእስር ላይ ለመቆየት ተገዷል። ግለሰቡ እንዲህ ባለ ስም በቁጥጥር ስር በመዋሉም አብዛኛው የማህበራዊ ድረገጽ ተጠቃሚ ተስማምቶበታል። ሌሎች በበኩላቸው ነገሩ ግር ስላሰኛቸው «የትኛው ስም ተፈቅዷል፤ የትኛውስ ክልክል ነው?» ሲሉ ጥያቄ ማንሳት ጀምረዋል። እኛም ጥያቄ አለን፤ በእርግጥ ወንጀል ያሰኘው መጠሪያው ለእንስሳት በመዋሉ ነው ወይስ ሰውም ቢጠራበት ያስቀጣው ይሆን?
አዲስ ዘመን ግንቦት 12/2011
ብርሃን ፈይሳ