ኢትዮጵያ ያሏትን የተፈጥሮ ሃብቶች በመረዳት እና ጥቅም  ላይ በማዋል ለትውልድ የሚተርፍ ሥራ መሥራት ይገባል!

ኢትዮጵያ የበርካታ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ቅርሶች ባለቤት ነች፡፡ የተፈጥሮ ሃብቶቹ ከኤርታኢሌ እስከ ዳሎል፤ ከራስ ዳሽን እስከ ታችኛው ኦሞ ሸለቆ ድረስ የተዘረጉ ናቸው። ከእነዚህም መካከል አስደናቂ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ የአየር ንብረት፣ ብርቅዬ የዱር እንስሳት፣ እንዲሁም የሰው ዘር መገኛ ስፍራዎች ተካተውበታል።

እነዚህ ደግሞ ኢትዮጵያን ለቱሪስት መዳረሻነት ከሚያበቋት ነገሮች መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸው። ኢትዮጵያ በዓለም ቅርስነት 13 ቅርሶችን በማስመዝገብ ከአፍሪካ ቀዳሚ አገር የነበረች ሲሆን ሰሞኑን ደግሞ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክንና የጌዲዮ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ መልክዓ ምድር፣ በማስመዘገብ በዩኒስኮ የተመዘገቡ የቱሪስት መስህቦችን 15 በማድረስ በአፍሪካ ቀዳሚነቷን ማረጋገጥ ችላለች፡፡

በተለይም ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ ግንባታዎች በስፋት በመከናወን ላይ ናቸው፡፡ ሀገራዊ ለውጡ ዕውን ከሆነበት 2010 ጀምሮ የተፈጥሮ ሃብቶችን በማወቅ፤ በመለየት፤ በማልማትና በመጠቀም ረገድ እመርታዊ ለውጦች ታይተዋል፡፡ በአጠቃላይ ወቅቱ ለቱሪዝም ዘርፉ ትንሳኤ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡

በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሀሳብ አፍላቂነት እና መሪነት ለዘርፉ የተሰጠው ልዩ ትኩረት የሚያበረታታ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገበታ ለሸገር፤ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ በሚል ማዕቀፍ በሀገራችን የሚገኙትን የቱሪዝም መዳረሻዎች በዘመናዊ መልክ እንዲለሙ እና ለቀረው ዓለም እንዲተዋወቁ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ተቀርፀው ወደ ስራ ተገብቷል፡፡ መዲናችን አዲስ አበባን ጨምሮ በአራቱም ማዕዘናት ሃብቶችን በመለየትና በማልማት የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እጅግ በርካታ ሥራዎች ተከውነዋል፡፡

በገበታ ለሸገር የቱሪስት መዳረሻዎች ግንባታ የአንድት፤ የወንድማማች እና የእንጦጦ ፓርኮች ለአዲስ አበባ ድምቀት ሆነዋታል፡፡ ለወትሮው በቱሪስት መተላለፊያነት የምትታወቀው አዲስ አበባ የቱሪስቶች መቆያ የመሆን ዕድልም አግኝታለች፡፡ በገበታ ለሀገር ፕሮጀክትም የጎርጎራ፤ የኮይሻ እና የወንጪ የቱሪስት መዳረሻዎች ለኢትዮጵያ የቱሪዝም ዕድገት ተጨማሪ ዕድሎችን ፈጥረዋል፡፡

ሰሞኑን ደግሞ በደቡብ ምዕራብ ክልል ቤንች ሸኮ ዞን የ‹‹ገበታ ለትውልድ›› ውጥን አካል የሆነውን ‘የደንቢ ሐይቅ ሎጅ’ የመሰረት ድንጋይ የማስቀመጥ ተግባር ተከናውኗል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን የጅማ ከተማ በአዲሱ ገበታ ለትውልድ ከተመረጡ ቦታዎች ውስጥ አንዷ ሆናለች፡፡ የጅማ ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት የከተማውን ገጽታና የአኗኗር ዘይቤ በእጅጉ እንደሚለወጥም ታምኖበታል።

ሚዛን አማን ላይ የሚሠራው አዲስ ሪዞርትና ኮይሻ አካባቢ የሚሠራው ፕሮጀክት ከጅማ ከተማ በቅርብ ርቀት የሚገኙ ናቸው፡፡ እነዚህ ቦታዎች የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶችን ቆይታ ያማረ በማድረግ የአካባቢው ሕብረተሰብ ከዘርፉ ገቢ እንዲያገኝ የሚያስችሉም ናቸው፡፡

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የታደለችና በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ስንሄድ ያልተነኩ እምቅ ሀብቶች በስፋት የሚገኙባት ሀገር ነች። እነዚህ የተፈጥሮ ሃብቶች በአግባቡ ከታወቁ እና ጥቅም ላይ መዋል ከቻሉም የኢትዮጵያ የብልጽግና መሰረትና የሕዝቦቿም የኑሮ መሰረቶች ይሆናሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሰሞኑን በጅማና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብቶችን ሲጎበኙ ባስተላለፉት መልዕክት ‹‹ሀገሩን ያላወቀና ሀብቱን በአግባቡ ያልተጠቀመ የባከነ ነው›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

አባባሉ ትልቅ እውነት አለው፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ ያላትን ዕምቅ የተፈጥሮ ሃብቶች በአግባቡ በማወቅ፣ በመጠቀምና በመጠበቅ ለትውልድ የሚተርፍ ሥራ መሥራት የእያንዳንዱ ዜጋ ግዴታ ሊሆን ይገባል፡፡ በየአካባቢው ያለውን እምቅ አቅም የተረዳ ዜጋ ለመገፋፋትና ለመጣላት የሚሆን ጊዜ ስለማይኖረው ለልማትና ዕድገት ይተጋል፡፡ ራሱን ቤተሰቡንና ሀገርንም ይለውጣል። በአጠቃላይ ያለንን እምቅ ሀብት ሥራ ላይ አውለን የኢትዮጵያን ብልጽግና ማረጋገጥ ይገባል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎንም ለቱሪዝም ዘርፉ እንቅፋት የሆነውን ጦርናትና ግጭት በማስወገድ ኢትዮጵያ ያላትን ዕምቅ የተፈጥሮ ሃብቶችን እንድትጠቀም ማድረግ ም ወቅቱ የሚጠይቀው ትልቅ ጉዳይ ነው!

አዲስ ዘመን መስከረም 23/2016

Recommended For You