ምርትና አገልግሎትን ለማስተዋወቅ እንዲሁም ጠንካራ የገበያ ትስስር ለመፍጠር ኤግዚቢሽኖችና ባዛሮች ትልቅ ድርሻ አላቸው፡፡ በተለይም ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽንና ባዛሮች አገርን ከማስተዋወቅ ባለፈ የገበያ ትስሰር በመፍጠር፣ የልምድ ልውውጥና የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ ጉልህ አበርክቶ እንዳላቸው ይታመናል፡፡ ኤግዚቢሽንና ባዛሮች በተለያዩ ጊዜያት ሲካሄዱ መመልከት መቻላችንም በዚሁ ምክንያት ነው። ከሰሞኑም በአይነቱ ለየት ያለና በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄድ የቡና ኤግዚቢሽንና ኮንፍረንስ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው ይህ <<ውሜን ኢን ኮፊ>>/ሴቶች በቡናው ዘርፍ ሊባል ይችላል/ የተሰኘው ዓለም አቀፍ የቡና ኤግዚቢሽንና ኮንፍረንስ፣ እ.ኤ.አ ከመጪው ጥቅምት 16 እስከ 22 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ይካሄዳል፡፡ ኤግዚቢሽንና ኮንፍረንሱ የ‹‹ውሜን ኢን ኮፊ›› ኢትዮጵያ ማሕበር እና የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን በጋራ የሚያዘጋጁት ነው፡፡
ማሕበሩ በቡና አምራችነትና በቡና የእሴት ሰንሰለት ውስጥ ተዋናይ የሆኑ ሴቶችን በማደራጀት ከዘርፉ ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ የሚሠራ ማሕበር ነው፡፡ ማሕበሩ ከመንግሥትና ከሌሎች አቻ አካላት እንዲሁም በአገር ውስጥና በውጭ አገር ከሚገኙ ማሕበራት ጋር ተባብሮ ለመሥራት የተቋቋመ ሲሆን፤ ከተመሰረተበት 2009 ዓ.ም ጀምሮ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ በቡና ልማትና ግብይት ዘርፍ ለተሰማሩ ሴቶች ድጋፍና እገዛዎችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በተለይም በቡና ሥራ የተሰማሩ ሴቶች በተለያዩ ዓለም አገራት ተዘዋውረው ዓለም አቀፍ በሆኑ ኤግዚቢሽኖችና ኮንፍረንሶች ተሳትፈው የኢትዮጵያን ቡና መሸጥና ማስተዋወቅ የሚችሉበትን ዕድል በመፍጠር ሰርቷል፡፡
በአሁኑ ወቅትም በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደውን ዓለም አቀፍ የቡና ኤግዚቢሽንና ኮንፍረንስ በኢትዮጵያ ለማካሄድ ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡ የዚሁ የቡና የኤግዚቢሽንና ኮንፍረንሱ ዋና ዓላማ ምንድ ነው? ምን አስተዋጽኦ ያበረክታል? የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት ከውሜን ኢን ኮፊ ኢትዮጵያ የቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሳራ ይርጋ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡
እሳቸው እንዳሉት፤ ዓለም አቀፍ የቡና ኤግዚቢሽንና ኮንፍረንሱ የኢትዮጵያ ቡና ከምርቱ ጀምሮ እስከ ሲኒ ድረስ ያለው ሂደት የሚተዋወቅበትና ቡና ለኢትዮጵያውያን ምን ማለት እንደሆነ ማሳያት ያስችላል፡፡ በወቅቱ በሚፈለገው ግብይት የገበያ ትስስር መፍጠር፣ የልምድና የዕውቀት ሽግግር ማድረግና ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ብቻ ሳትሆን የቡና ቱሪዝም መዳረሻ ጭምር መሆኗን ማሳየት ደግሞ ሌላው የኤግዚቢሽንና ኮንፈረንሱ ዋና ዓላማ ነው፡፡
በኤግዚቢሽንና ኮንፍረንሱ በዓለም አቀፍ ደረጃ በቡና እሴት መጨመር ላይ የተሰማሩ ሴቶች እንደሚሳተፉ ወይዘሮ ሳራ አስታውቀዋል። በኢግዚቢሽንና ኮንፍረንሱ የአንድ ሳምንት ቆይታ ኮንቬንሽን፣ ኤክስፖና ኦሪጅን ትሪፕ እንደሚከናወን አመላክተው፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ ቡና ከመነሻው ጀምሮ በማስተዋወቅና የገበያ ትስስር በመፍጠር በተለያዩ የአገሪቱ ቦታዎች የሚገኙ ቡና አብቃይ አካባቢዎች እንደሚጎበኙ ጠቁመዋል፡፡
ወይዘሮ ሳራ እንዳስታወቁት፤ የኢትዮጵያ ቡና ኤግዚቢሽንና ኮንፍረንስ ዋና ዓላማ የቡና መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ የቡና ቱሪዝም መዳረሻ እንድትሆን በማድረግ ዓለም አቀፍ ገበያውን በማስፋት የኢትዮጵያን ቡና ማስተዋወቅ ይሆናል፡፡ በዘርፉ የተሰማሩ ሴት ቡና አምራቾች፣ ነጋዴዎችና ላኪዎች በተለያዩ አገራት እየሄዱ የኢትዮጵያን ቡና እያስተዋወቁ ሲሸጡ የኖሩት ብዙ ዋጋ እየከፈሉ ነው፡፡ እንዲህ አይነት ሁነቶች ከአፍሪካ ውጭ በሆኑ አገራት የሚዘጋጁ በመሆናቸውም በዘርፉ የተሰማሩ ሴቶች ለከፍተኛ ወጪ ይዳረጋሉ፡፡
ይህንን በመረዳት መሰል ኤግዚቢሽንና ኮንፍረንስ የቡና መገኛ አገር በሆነችው ኢትዮጵያ እንዲካሄድ ማህበሩ ጥያቄ ማቅረቡን ነው ወይዘሮ ሳራ ያስታወሱት፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ መሰል ኤግዚቢሽኖችና ኮንፍረንሶች በየሁለት ዓመቱ በደቡብ አሜሪካ፣ በማዕከላዊ አሜሪካና አሜሪካ ላይ የሚካሄዱ ቢሆንም፣ በአፍሪካ አገራት ተካሂዶ አያውቅም፡፡ በዚህ መነሻነት ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት በማግኘቱ በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ ላይ ዓለም አቀፍ የቡና ኤግዚቢሽንና ኮንፍረንስ ለማካሄድ ዝግጅቱ ተጠናቅቋል፡፡
አፍሪካ ላይ ከላቲን አሜሪካ ያልተናነሰ ቡና አብቃይ አገራት ስለመኖራቸው የጠቀሱት ወይዘሮ ሳራ፤ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ መዲናዋ አዲስ አበባ ከተማ ዓለም አቀፍ የቡና ኤግዚቢሽንና ኮንፍረንስ ለመጀመሪያ ጊዜ ለማካሄድ ዝግጅቱ መጠናቀቁን ነው የተናገሩት፡፡ ይሁንና ብዙዎች በአፍሪካ አገር ላይ እንዲህ አይነት ሁነት ማዘጋጀት ይቻላል የሚል እምነት እንዳልነበራቸው አስታውሰው፤ እኤአ በ2021 በአፍሪካ መዲና አዲስ አበባ ከተማ ዓለም አቀፍ የቡና ኤግዚቢሽንና ኮንፍረንስ እንዲዘጋጅ ፈቃድ ማግኘት እንደቻሉና ከአንድ ዓመት በላይ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ሲሰራ መቆየቱን አስታውቀዋል፡፡
ወይዘሮ ሳራ እንዳሉት፤ ውሜን ኢን ኮፊ ኢትዮጵያ ማህበር ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመሆን ይህን ዓለም አቀፍ የቡና ኤግዚቢሽንና ኮንፍረንስ ለማዘጋጀት በርካታ ሥራዎች ሲሠራ ቆይቷል፡፡ የዝግጅት ሥራው ከአንድ ዓመት በላይ ጊዜ ወስዷል፤ በርካታ በቡና ልማትና ግብይት ዘርፍ የተሰማሩ ሴቶች ከፍተኛ ተሳትፎ አድርገውበታል፡፡ ከማህበሩ ሴት አባላት በተጨማሪ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የፋይናንስ ተቋማትና ሌሎች የተለያዩ አጋር አካላት ጭምር ባደረጉት ድጋፍ ዝግጅቱ ተጠናቅቆ ኤግዚቢሽንና ኮንፍረንሱ ሊካሄድ ጥቂት ቀናት ብቻ የቀሩት ሲሆን፣ እንግዶች እየተጠባበቁ ይገኛሉ፡፡
ይህ ዓለም አቀፍ የቡና ኤግዚቢሽንና ኮንፍረንስ በዋናነት ዓላማ አድርጎ የተነሳው ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ብቻ ሳትሆን የቡና ቱሪዝም መዳረሻ አገር መሆኗን ማስተዋወቅ ነው የሚሉት የቦርድ ሰብሳቢዋ፤ ሰዎች እንደ መካና እየሩሳሌም ኢትዮጵያን ለቡና ብለው ማየት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ ይህን ማድረግ ሲቻል የሚገኘው ውጤት እጥፍ ድርብ እንደሆነና በዘርፉ ትርጉም ያለው ውጤት ማምጣት እንደሚቻል አመልክተዋል፡፡ ከቡና የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ በተለያየ መንገድ ማሳደግ እንደሚቻል ጠቅሰው፣ በኤክስፖርት ከሚገኘው ገቢ በተጨማሪ ገዥዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በሚፈጥሩት የገበያ ትስስርና ግዢ ገቢ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡ እንግዶቹ በሚኖራቸው ቆይታም ገቢ እንደሚገኝ ነው ያመለከቱት፡፡
‹‹ቡና ትልቅ የቱሪዝም አቅም መሆን ይችላል›› ያሉት ወይዘሮ ሳራ፤ በዚህ የቡና ኤግዚቢሽንና ኮንፍረንስም ከተለያዩ የዓለም አገራት የሚመጡ በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ስለመኖራቸው ተናግረዋል፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ ለእነዚህ እንግዶች ቡና ከምርቱ ጀምሮ እስከ ስኒ ድረስ ያለውን ሂደት ለማሳየት ዝግጅት ተደርጓል፡፡ ለዚህም አራት ቦታዎች ተዘጋጅተዋል፡፡ አንደኛው ጉጂ ዞን ሀምበላ ላይ የሚገኝ የቡና ሎጅ ሲሆን፣ በእዚህ ቦታ ላይ ከቡና እርሻ በተጨማሪ የቡና ቅምሻም ይካሄዳል። ሌላው በንሳ ላይ የሚገኝ ሎጅ አርደንት ኮፊ ሲሆን፤ እሱም እንዲሁ የቡና እርሻና የቡና ማቀነባባሪያ ያለው ነው፡፡ ከፋ ላይ የሚገኙት ደሀብ ቡና እና ጋላኒ ቡናም እንዲሁ ትልቅ የቡና እርሻ ያላቸውና ቡና የማምረትና የማቀነባበር ሥራ የሚሠራባቸውና የሚጎበኙ ቦታዎች ናቸው፡፡
በዓለም አቀፍ የቡና ኤግዚቢሽንና ኮንፍረንሱ ላይ የሚሳተፉ እንግዶች በእነዚህ አራት ሳይቶች በሚያደርጉት ጉብኝት የኢትዮጵያን ቡና ከምርት ጀምሮ የማወቅና የመረዳት አጋጣሚን ይፈጥርላቸዋል። ይህም የገበያ ትስስር ለመፍጠር በር የሚከፍት በመሆኑ ‹‹በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ›› እንደሚባለው ከሚፈጠረው የገበያ ዕድል በተጨማሪ የኢትዮጵያ ቡናን ማወቅና መረዳት ይችላሉ፡፡ በተያያዘም ቡና ማለት ለኢትዮጵያውያን ምን ማለት እንደሆነና የሕይወት ዘይቤያቸው መሆኑን ጭምር በመረዳት የኢትዮጵያን ቡና በብዙ የሚተዋወቁበት ሰፊ ዕድል የሚፈጠርበት አጋጣሚ ይሆናል፡፡ በዚህም ሴቶች ትልቅ አበርክቶ አላቸው፡፡
ወይዘሮ ሳራ ጥናቶች ዋቢ አድርገው እንዳሉት፤ በአገሪቱ 70 በመቶ ያህሉ የግብርና ሥራዎች የሚሰሩት በሴቶች ነው፡፡ ከግብርና ሥራዎች አንዱ የሆነው የቡና ሥራም በአብዛኛው በሴቶች የሚሰራ ነው፡፡
በውሜን ኢን ኮፊ ኢትዮጵያ ማሕበር አባል መሆን የሚችሉት በቡና ሥራ ውስጥ የተሰማሩ ሴቶች ስለመሆናቸው ገልጸው፤ እነሱም ቡና አምራቾች፣ ቡና ቆይዎች፣ ቡና አቀነባባሪዎች፣ ላኪዎችና ቀማሾች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ማህበሩ በቡና አምራችነት የተሰማሩ ሁለት ቡና አምራች ሕብረት ሥራ ማሕበራትን ጨምሮ በድምሩ 70 የሚደርሱ አባላት እንዳሉትም ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አሸት ቡና የሚደርስበት ወቅት እንደሆነ ያነሱት ወይዘሮ ሳራ፤ ጊዜው በእጅጉ ተመራጭ እንደሆነና እንግዶቹ የተንዠረገገውን የቡና ፍሬ በእርሻ ቦታ ላይ ማየት እንደሚያስችላቸውም ጠቁመዋል፡፡ ይህም የኢትዮጵያን ቡና ከመነሻው ጀምሮ ያለውን ሂደት አውቀውና ተረድተው እንዲገዙ እንደሚያስችል አመልክተዋል፡፡
የቦርድ ሰብሳቢዋ እንዳብራሩት፤ በአፍሪካ የመጀመሪያ በሆነው ዓለም አቀፍ የቡና ኤግዚቢሽንና ኮንፈረንስ ላይ በቡና ሥራ ላይ የተሰማሩ አካላት በሙሉ ይሳተፋሉ፡፡ ተሳታፊዎቹ በአጠቃላይ ከ50 የተለያዩ ዓለም አገራት ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ቢያንስ ከ33 አገራት ሁለት ሁለት ኃላፊዎችና አባላት ይገኛሉ። በዚህም መድረኩ ቡናውን ከማስተዋወቅ ባለፈ የገበያ ትስስር የሚፈጠርበት እንደመሆኑ በሚኖረው የአንድ ሳምንት ቆይታ በአንደኛው ቀን በሚኖረው መርሃ ግብር ሰፊ የገበያ ትስስር የሚፈጠር ይሆናል፡፡
በርካታ የዓለም አገራት የኢትዮጵያን ቡና እንደሚፈልጉትና እንደሚጠቀሙበት የጠቀሱት ወይዘሮ ሳራ፤ የዓለም አገራት የኢትዮጵያን ቡና ፈልገው መምጣት እንዲችሉ መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ በተለይም ሴቶች በቡና ምርትና ማቀነባበር እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች መሥራታቸው የሚኖረው አበርክቶ ትልቅ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ በቡና ሥራ የተሰማሩ ሴቶች ከኢኮኖሚው በተጨማሪ ማሕበራዊ ግንኙነቶችን የሚያጠናክሩበት በመሆኑ በቡና ሥራ ሴቶች ትልቅ ድርሻ አላቸው፡፡ ለዚህም ውሜን ኢን ኮፊ ኢትዮጵያ ማህበር በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን ዓለም አቀፍ የቡና ኤግዚቢሽንና ኮንፍረንስ በማዘጋጀት ኢትዮጵያ የቡና መገኛ አገር ብቻ ሳትሆን የቡና ቱሪዝም መዳረሻ ጭምር መሆኗን ያስተዋውቃል፡፡
ከ75 በላይ ግለሰብ አባላት እና ከ200 በላይ በቡና አብቃይ አካባቢ የተደራጁ ቡና አምራች ሴቶች አባላት ያሉት ውሜን ኢን ኮፊ ኢትዮጵያ ማህበር፤ በተጨማሪም በተለያዩ የአገሪቱ ቡና አብቃይ ክልሎች የሚገኙ በችግኝ ማፍላት፤ መሬት ማዘጋጀት፤ መትከል፤ መንከባከብ፤ ብሎም ፍሬውን በመሰብሰብ፤ በማዘጋጀትና ወደ ገበያ በማቅረብ፤ በማማከርና ስልጠና በመስጠት እንዲሁም አገልግሎት በመስጠት ሥራ ላይ የተሰማሩ ሴቶችንም አካትቷል፡፡
ማህበሩ አባላቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቁና ተወዳዳሪ ለማድረግ አቅዶ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ሲሆን፤ እቅዱን ዳር ለማድረስ በሚያደርገው ጥረት በአገር ውስጥ እና በውጭ ከሚገኙ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ይሠራል፡፡ ማህበሩ እኤአ ከሚያዚያ 2017 ጀምሮ የኢንተርናሽናል ውሜን ኢን ኮፊ አሊያንስ (IWCA) ቻፕተር አባልም ነው።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን መስከረም 23/2016