የኢትዮጵያ አየር መንገድ የስኬት ምስጢር

ዓለም የተጨነቀችበት ግዜ ነበር። ሰው ሁሉ በሩን ዘግቶ ጎዳናዎች ጭር ብለው የሞት መንፈስ የረበበበት ወቅት። የኮሮና (የኮቪድ 19) ወረርሽኝ ከወደ ቻይና ተነስቶ በመላው ዓለም በመስፋፋቱ ምክንያት የሰው ልጅ ይገባበት ጥግ የሚፈልግበት አስቸጋሪ ወቅት። መንገዶች ተዘግተው፣ መዝናኛ ስፍራዎች በራቸውን ጠርቅመው የመንግስትና የግል ድርጅቶች ሰራተኞቻቸውን ወደ ቤታቸው ሸኝተው እጃቸውን አጣጥፈው የተቀመጡበት አስቸጋሪ ግዜ። በወቅቱ እጅግ ጥቂት የሚባል በጥንቃቄ የተሞላ እንቅስቃሴ ብቻ ይደረግ የነበረበት የፈተና ዘመን።

በዚህ የኮቪድ ዘመን አገራትን ከአንዱ ጫፍ ወደ አንዱ ጥግ በማገናኘት፣ የገቢና የወጪ ንግድን በማቀላጠፍ ወደር የማይገኝላቸው ታላላቅ አየር መንገዶች የእንቅስቃሴ ገደብ ውስጥ ገብተው ወረርሽኙ ካደረሰው የሰው ልጅ ሕልፈትና ማሕበራዊ ቀውስ ባሻገር ከፍተኛ ኪሳራ አስተናገዱ። በወረርሽኙ ምክንያት ለወራት የዓለም አቪዬሽን ኢንዱስትሪ ክፉኛ ተመታ። በእውነቱ በሺዎች የሚቆጠሩ አየር መንገዶች የኢንፌክሽኑን ስርጭት ለመግታት የጉዞ ገደቦችን ሲያስተዋውቁ እና ድንበሮቻቸውን ሲዘጉ በሺዎች የሚቆጠሩ አየር መንገዶች በረራቸውን ለማቆም እና ስራቸውን ለመሰረዝ ተገደዱ።

የእርምጃዎች መጥፎ ውጤት በዋነኝነት የተሰማው ከወረርሽኙ በኋላ ታላላቅ አየር መንገዶች የደረሰባቸውን ጫና ይፋ ሲያደርጉ ነበር። በተለይ አፈጻጸማቸው እያሽቆለቆለ መምጣቱን እና ኪሳራን ለማወጅ መገደዳቸውን ይፋ ያደረጉ በርካቶች ነበሩ። ለምሳሌ ቨርጂን አውስትራሊያ፣ ፍላይቤ እና ኮምፓስ አየር መንገድ ክፉኛ ወድቀዋል፤ የአስተዳደር ጫና ውስጥ ገብተዋል። በተለይ በይፋ ኪሳራ ማወጃቸው ኮቪድ 19 ዓለም አቀፍ ስጋት መሆኑ ካበቃ በኋላ እንኳን መነጋገሪያ ነበር።

በምሳሌነት የጠቀስናቸውና ተጨማሪ በርካቶች በአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ የሚሳተፉ አየር መንገዶች በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ሲፍረከረኩ ነበር። ይሁን እንጂ ብርቅዬ የምስራቅ አፍሪካ ፈርጥና የአፍሪካ ኩራት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተቃራኒው ጫናውን ተቋቁሞ “በዚህ ችግር ተጠልፎ ይወድቃል” በማለት የተነበዩለት ብዙሃን አሳፍሮ ግዙፍ ስኬት ማመዝገብ ቻለ። እንደ ታሪክ የምናወራው ይህ ስኬት ከረጅም ዓመታት በፊት የተከሰተ አይደለም። ይህ ታሪክ ከሁለትና ሶስት ዓመታት በፊት የተከሰተ በኢንዱስትሪው ወስጥ ብዙሃንን ያነጋገረና ለኢትዮጵያ አየር መንገድ አድናቆትን ያስገኘ የቅርብ ግዜ ትዝታ ነው።

የአየር መንገዱ ስኬት በዚህ ብቻ የሚገለፅ አይደለም። ለበርካታ አስርት ዓመታት ምቹ አጋጣሚ በነበረበት ወቅት ብቻ ሳይሆን በፈተና ግዜም አውሎ ንፋሱን መቋቋም የጠንካራ ተቋማት መገለጫ እንደሆነ አንዱ ማሳያ መሆን ችሏል። ይህ ስኬቱ ደግሞ በዓለማችን ላይ አሉ ከሚባሉ አየር መንገዶች ውስጥ አንዱ አድርጎታል። ብዙዎች ሊወዳጁት አብረውት ሊሰሩ የሚሹ ናቸው። በየዓመቱ በሚደረጉ የእውቅናና የሽልማት ስነስርዓቶች ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድን አናጣውም። የቅርብ ግዜውን እናንሳ ብንል እንኳን ሁለት ታላላቅ ስኬቶች ማስመዝገቡን እንረዳለን።

የመጀመሪያው ከአውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር 2020 ጀምሮ እስካሁን ድረስ “የአፍሪካ ምርጡ አየር መንገድ” የሚል ሽልማትን “Busi­ness Traveller Awards” ማግኘቱ ሲሆን ሌላው ደግሞ ከቀናት በፊት የሰማነው ከመጀመሪያዎቹ ዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር /IATA/ የደኅንነት አመራር ቻርተር ፈራሚዎች አንዱ መሆኑን ነው። የደህንነት አመራር ቻርተር ስምንት ዋና ዋና የደኅንነት አመራር መርሆዎችን በመተግበር የደኅንነት ባህል ለማጠናከር ያለመ እንደሆነ የሚታወቅ ነው። እነዚህ ስኬቶች አየር መንገዱ እያስመዘገባቸው ከሚገኙ በርካታ ዓለማቀፍ ድሎች ውስጥ በምሳሌነት የሚጠቀሱ ናቸው።

የአየር መንገዱ በአስቸጋሪ ግዜያቶች ሳይቀር የሚያስመዘግባቸው ስኬቶች ስንመለከትና “ለመሆኑ የስኬት ሚስጥሮቹ ምን ይሆኑ” ብለን መጠየቃችን አይቀርም። በተለይ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ትላልቅ ተቋማት ልክ እንደ አየር መንገዱ የስኬት ማማ ላይ እንዲቀመጡ መሰል የአሰራር ስርዓት ለመዘርጋት በተምሳሌትነት ለመውሰድ ስንሻ ይህንን ጥያቄ ማንሳታችን አይቀርም። ይህ ጥያቄ በእኛ በኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ብዙ የተባለለትና የተመረመረ ጉዳይ ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስኬት በሁለት ምክንያቶች ሊወሰድ እንደሚችል የዚህ ፅሁፍ አዘጋጅ ያምናል። የመጀመሪያው የአየር መንገዱ የጠራ “ራዕይ” እና በመንግስት የእለት ተእለት ስራዎች በሚያከናውንበት ወቅት የሚያገኘው ነፃነት ነው። መረጃዎችን ስንመለከት የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር የ2025 ሊያሳካው ያስቀመጠውን ራዕይ በ2018 ላይ እንዳሳካው እንመለከታለን። ከዚያ አልፎ 2025 ሳይደርስ በ2035 ያስቀመጠውን ራዕይ ለማሳካት እቅድ መንደፉን መረጃዎች ያሳዩናል።

አየር መንገዱ በኢትዮጵያ መንግስት ባለቤትነት ቢታወቅም በባለሙያዎች መመራቱ፣ ፍፁም ሙያዊ ስነ ምግባር፣ የአገልግሎት ሰጪነት ስሜት የተላበሱ ሰራተኞች ማካተቱ ለስኬቶቹ ዋና ምንጭ እንደሚሆኑ መገመት አያዳግትም። የአቪዬሽን ንግዱ እንደማንኛውም ኮርፖሬሽን በጥልቅ እንዲመራ የሙያ ነፃነት መኖሩ ለተከታታይ ዓመታት የኢትዮጵያ አየር መንገድ “የአፍሪካ ምርጡ አየር መንገድ” (Best African Airline) የሚል ዘውድ እንዲደፋ ማድረጉ አያጠራጥርም።

ይህ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ፈተናዎች (የኮቪድ ወረርሽኝ የመሰሉ) በሚመጡበት ወቅት ኪሳራን ማወጅ ሳይሆን ትርፍን ማግኘት እንዲያስችለው አድርጎታል። በርካቶች የአየር መንገዱ ስኬት “በዓለም ላይ ያለው የምጣኔ ሀብት ቀውስ መባባስ፣ የነዳጅ ዋጋ መናር እንዲሁም ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ” ባለበት ወቅት መሆኑ ጥንካሬውን እንደሚያሳይ እንዲመሰክሩለት አስገድዷቸዋል።

ሌላው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የስኬት ምንጭ መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ። ይህንን እድል ለመጠቀም የአቪዬሽን የአመራር ጥበብ የሚጠይቅ ቢሆንም እድሉ በራሱ የሚያመጣው ስኬት በቀላሉ የሚታይ አይሆንም። የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ላይ ትኩረታቸውን አድርገው የሚፅፉ ተንታኞች ኢትዮጵያ መካከለኛው ምስራቅን ከአፍሪካ፣ ከእስያና ከአውሮፓ ጋር የምታገናኝ ማእከል እንድትሆን መልከዓ ምድራዊ አቀማመጧ ምቹ አጋጣሚን የሚፈጥር እንደሆነ ይናገራሉ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዲስ አበባ በርካታ የአቪዬሽን ትራፊክን መሳብ እና ማስተላለፍ የምትችልበት ማዕከል ሆናለች። የአየር መንገዱ ኤክስፐርቶች አመራሮች ይህንን እድል በአግባቡ ለመጠቀም ምክንያት እንደሚሆኑ አያጠራጥርም። በተለይም ከእስያ ወደ አሜሪካ አህጉራት የሚደረጉ በርካታ በረራዎች በዚሁ ትራፊክ ክልል ውስጥ እንደሚደረጉ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ሌላው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስኬት የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ እንደሆነ ይነገራል። ባለፉት ሁለትና ሶስት አስርት ዓመታት ውስጥ በመሰረተ ልማት ረገድ በርካታ ለውጦች አስመዝግቧል። የአንድ አየር መንገድ ስኬት በሚያገኘው ትርፍ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን በመልሶ ማልማትና ኢንቨስትመንት አማራጭ እንደሆነ ይታወቃል። በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስኬት ተጠቃሽ ነው።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአገር ውስጥ በመሰረተ ልማት ማስፋፊያ ከሚያከናውናቸው ተግባራት ባሻገር በሌሎች አገራት የሚመሩ አየር መንገዶችን ድርሻ በመግዛት የሄደበት ርቀት ዓለም አቀፍ ተፅእኖ ፈጣሪነቱን ከሚያሳዩ ማስረጃዎች መካከል በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱት ውስጥ ነው።

አዲስ አበባ በአፍሪካ ትልቁን አየር ማረፊያ ለማልማት እቅድ እንዳላት የቀድሞው የአየር መንገዱ ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም ይፋ ማድረጋቸውን እናስታውሳለን። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይህንን መሰረተ ልማት ለማልማት 5 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ወጪ ለማውጣት ማቀዱን ስንሰማ በመሰረተ ልማት ረገድ ለማምጣት የታሰበውን ለውጥ እና ቁርጠኝነት ያሳየናል። ይህ ፕሮጀክት እውን ሆኖ ቢጠናቀቅ የተጨናነቀ አውሮፕላን ማረፊያ ከማስቀረት ባሻገር ኢትዮጵያ ተመራጭ መዳረሻ እንድትሆን እንደሚያስችላት አያጠራጥርም።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጥልቅ ስኬት መንግስት ከጣልቃ ገብነት የፀዳ ጥበቃ በማድረጉ ላይ የተመሰረተ እንደሆነ መታመን ይኖርበታል። ይህ አካሄድ ተገቢና ቀጣይነት ሊኖረውም ይገባል። በተለይ ሙያዊ ነፃነት እንዲኖረው፣ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱ እንዲጨምር እንዲሁም በማንኛውም ሁኔታ ድጋፍ ሲያስፈልገው እንዲያገኝ በመንግስት በኩል የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

መንግስት ከስራቸው መራቅ ባለመቻሉ የሞቱት አየር መንገዶች በርካታ ናቸው። በምሳሌነት ናይጄሪያ ኤርዌይስ ሊሚትድ፣ ኤር አፍሪካን፣ ጋና ኤርዌይስ፣ ጋምቢያ አየር መንገድ፣ ኤር አንጎላ፣ ቦትስዋና አየር መንገድ፣ ኮንጎ አየር መንገድ፣ ኤር ጅቡቲ እና ሌሎችም መጥቀስ ይቻላል። ይህ የሚያመላክተን የፖለቲካና የመንግስት አላግባብ እጅ መርዘም የአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ስኬት ጋሬጣ እንደሚሆን ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ይህንን መገንዘቡ የምስራቅ አፍሪካ ፈርጥ፣ የአፍሪካ ኩራት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲፈጠር እድል ሆኗል።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር በታህሳስ 21 ቀን 1945 የተመሰረተ ሲሆን ሚያዝያ 8 ቀን 1946 ስራ ጀምሯል። ከጅምሩ ጀምሮ ስኬታማ ለመሆን እና በአፍሪካ አውራ አየር መንገድ ለመሆን ያስቻሉት በርካታ ስራዎች አከናውኗል። ከላይ ካነሳናቸው ምስጢሮች ባሻገር የጥገና መሰረተ ልማቱን ማዳበር፣ የአብራሪዎች፣ የመሀንዲሶች እና የካቢን ሰራተኞች አጠቃላይ ስልጠና መስጠት መቻሉ የስኬቶቹ ምንጭ ነው። በዚህ ምክንያት በአህጉሪቱ ከመጀመሪያዎቹ አየር መንገዶች እና አንጋፋና ስኬታማ ያደርገዋል። ለዚህ ነው ይህንን አየር መንገድ ማንኛውንም ዋጋ ከፍለን ልንጠብቀው፣ ልናሳድገውና የኢትዮጵያውያን የኩራት ምንጭ ልናደርገው የሚገባው። ሰላም !

ሰው መሆን

አዲስ ዘመን መስከረም 23/2016

Recommended For You