ዛሬ ከትናንት እንዲሻል

የአይሁድ ዝርያና የደች ዜግነት ያለው ታዋቂው የፍልስፍልና ጠቢብ ባሩች ስፒኖዛ Baruch Spinoza ‹‹ If you want the present to be different from the past, study the past/ዛሬ ከትላንቱ የተሻለ እንዲሆን ከፈለግክ የትላንቱን በሚገባ አጢነው/››የሚል አባባል አለው፡፡ ይሕን አባባል በተለይ አዲስ ዓመትን ስንጀምር ይበልጥ ትርጉም ይሰጣል፡፡ ወደ አዲስ ዓመት ስንሸጋገር ካለፈው ልምድና ተግባራችን ትምህርት መቅሰም እንደሚገባን ያስገነዝባል፡፡

ይሁንና አንዳንዶች በአሮጌ ዓመት የሰሩትን ስህተት በአዲሱ ዓመትም ደግመው ሲሰሩ ራሳቸውን ያገኙታል። ይሕም ያለፈውን ልምዳቸውን የመለየትና ለመፍትሄ የመራመድ ፍላጎትም ሆነ ልምድ ስለሌላቸው የሚከሰት ስለመሆኑ እርግጥ ነው፡፡

ዛሬ ላይ ሆኖ የትላንት ተግባር ምን ጠቀመን? ስህተቱስት ምን አስተማረን? የሚሉ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ትክከለኛውን መልስ ፈልጎ ማግኘት የቻለ ግን ከዚህ ቀደም የጨበጠው እሳት ዳግም እንደማይጨብጠው የሚያጠራጥር አይደለም፡፡፡

የዘመን በዘመን የጊዜ በጊዜ መተካት የማያቋርጥ ሂደት ቢሆንም አዲስ ዓመት ሰው ከራሱ ጋር ይታረቅ ዘንድ እቅዱ ከግቡ እንዲስማማ ውጫዊና ውስጣዊ ሕይወቱ እንዲጣጣም ወሳኝ ድርሻ አለው፡፡ አዲስ ዓመት የሰው ልጅ ራሱን የሚያሻሽልበት ያለፈውን ሕይወቱን ገምግሞ ደካማውን ሽሮ ጠንካራውን ይዞ እንዲቀጥልበት ለራሱ የፈጠረው የቀን ቀጠሮ ነው፡፡ አዲስ ዓመትም ራስን ለመለወጥ፣ አስተሳሰብን ለማደስ፣ አኗኗርን ለማስተካከል፣ ለማሰብና ለማሰላሰል እድል ይሰጣል፡፡ ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ ሰው ባሰመረው የጊዜ ድንበር ለአዲስ ዓመት ሁሌም አዲስ ያስባል፡፡

ኢትዮጵያውያንም 2015 ዓ.ም አሮጌ ብለው ሸኝተው አዲሱን 2016 ዓ.ም ተቀብለዋል፡፡ አዲስ ዓመትም በአብዛኛው ኢትዮጵያውያን ዘንድ አዲስ ቃል የሚገቡበት ዕለት ነው፡፡ ሁሉም በየፊናው መጪው ጊዜ መልካም እንዲሆን፤ ኑሮው እንዲሳካ ጎጆው እንዲሞላ፣ መንፈሱ እንዲረካ፣ አዕምሮው እንዲሰላ፣ ነፍስያው እንዲጠግብ፣ የውስጡም የውጪውም ሕይወቱ እንዲያምር ያቅዳል፡፡

ለአብዛኞቻችን ኢትዮጵያውያንም እውነተኛው የአዲስ ዓመት ትርጉሙም አዲስ ሰውነት፣ አዲስ አስተሳሰብ፣ አዲስ ለውጥ፣ አዲስ የሕይወት መንገድ የሚበጅበት፣ ለራሳችን ቀና አስተሳሰብ የምንቀይስበት በአጠቃላይ አዲስ የምንሆንበት የአዲስነት የጅማሮ ቀን ነው፡፡

አዲስነት የትላንቱን ድካም፤ ያለፈውን አጉል ልማድ መድገም ሳይሆን አዲሱን ኑሮ በአዲስ ሰውነት፣ በሰለጠነ አስተሳሰብና በቀናነት መጀመር ነው፡፡ አዲስነት በግንዛቤ መበልጸግ፣ በጥበብ መጎልመስ፣ ራስን በመቆጣጠር መርቀቅ ጭምር ነው፡፡

ዓመቱ አዲስ እንዲሆን ደግሞ አዲስ ሰው መሆንን የግድ ይላል፡፡ አዲስን ወይን ጠጅ በአሮጌ አቁማዳ ውስጥ እንደማይጨምሩት እና አዲሱና አሮጌው እንደማይስማሙ ሁሉ ሰው በአዲስነት ካልተቀበለው አዲስ ዓመትም የቁጥር ለውጥ ብቻ ይሆናል፡፡

ይሑንና በዘመን ሂደት በትውልድ ቅብብል የማይጠቅምን አስተሳሰብን ማራመድ እንደ አገርም ሆነ እንደ ህዝብ ጉዳቱ ግልፅ ነው። አንድ ከማድረግ ይልቅ የሚነጣጥል፤ መሰብሰብን ትቶ የሚበትን፣ ከማዋሃድ ይልቅ የሚለያይ አስተሳሰብን ማራመድ ኪሳራ እንጂ ትርፍም የለውም።

አንድ መታወቅ ያለበት ወሳኝ ጉዳይ ቢኖር ማሰብ መቻል ልዩ ፀጋ ነው። መልካምን ሃሳብን መርጦ መተግበር ደግሞ ሰው በራሱ ላይ የሚያመጣው በረከት ነው። ማንም ለሆዱ የሚስማማውን ምግብ እንደሚመርጠው ሁሉ ለአዕምሮውም የሚመጥን ሃሳብን መመገብ ራስን መጥቀም ነው።

ንፁህ ምግብ ሰውን ከበሽታ እንደሚከላከለው ሁሉ ንጹህና መልካም ሃሳብም ሰውን አፍራሽ ተልዕኮ ካለው ተግባር ያቅበዋል። ሰው ሃሳቡን እያበጠረ ገለባ ሃሳቡን የሚያስወጣበትና ጠቃሚውንና ፍሬ ሃሳቡን የሚያስቀርበት የሕሊና ወንፊት መስራት ይገባዋል። ሃሳብ እንደ ስንዴ አንክርዳዳድ ካልተጣራ ንጹሁንም ሃሳብ ያበላሻል።

እኛ ኢትዮጵያውያን ትላንት በሃሳብ ቀድመው ከፍ ከፍ እንዳላልን ዛሬ አዲስ ሃሳብ መስራት፣ ሃሳቡን ማርቀቅ፣ ሃሳቡን ማጎልመስ፣ ሃሳቡን በተሻለ ሃሳብ መጣል፣ ሃሳቡን በሃሳብ ማድመቅ የሚያስችል ባህል ጠፍቶብናል። ትላንትም ሆነ ዛሬ እየተመላለሰ የሚደቁሰንና አዙሪት ሆኖብን ወደፊት አላንቀሳቅስ ያለን ችግራችንን በአስተሳሰብ ልእልና ተነጋግረንና ተወያይተን ፍቱን የሆነ መፍትሄ ማስቀመጥ አለመቻላችን ሆኖም ይታያል፡፡

በኢትዮጵያ ምድር ያለፈው ዓመት ደስታና ሀዘን ተስፋና ፍርሀት ድልና ትግል የተፈራረቁበት እንደነበር ይታወሳል፡፡ የምንሰማውና የምንናገረው የምንፈልገውን ብቻ ሆኖ በጥቂቱ አውቆ በብዛት መድምደም፣ በከፊል ሰምቶ በሙሉ መፍረድ፣ መርጦ በመመልከትና በመስማት ሳይመርጡ ማውገዝ የሁላችንም መገለጫ ሆኖም ታይቷል።

ይሕን ታሪክ በአዲስ ዓመት መለወጥ ይኖርብናል። ኢትዮጵያውያን በአዲሱ ዓመት ካለፈው ተምረን መጪውን ለማሳመር በተለይም አገር ሰላም እንድትሆን ካሳለፍናቸውም መልካም ሆነ እኩይ ታሪኮች ተምረን መጪውን ለማሳመር ማድረግ ያለብን ብዙ ነው፡፡

ኢትዮጵያችን በአዲስ ዓመት አዲስ አስተሳሰብ ያለው ዜጋን ትፈልጋለች፡፡ የሚክሳት አንጂ የሚከሳት አያስፈልጋትም፡፡ ዘመን የሚዋጅ፣ ትውልድን እንደ አዲስ የሚቀርፅ ትውልድ ትባጃለች፡፡ ትንሳኤዋን የሚሻ፣ ወደ ኋላ የሚጎትትና የማይጠቅም አስተሳሰብ በአዲስና በተሻለ አስተሳሰብ መለወጥ የሚችል ዜጋን ትናፍቃለች፡፡ ሊገነባ፣ ትውልድ ከፍ ከፍ ሊያደርግ የሚችል አስተሳሰብ ትሻለች፡፡

በአዲስ ዓመት ለመናቆር ሳይሆን ለመፋቀር ቦታ እንስጥ፡፡ ፀጉር ከመንጨት፣ ሃሳብ ማመንጨት እናስቀድም። ከመቆላለፍ መተላለፍን፣ ከመተናነቅ፣ መደናነቅን እንምረጥ። የአምናውን ዕዳ አንውረስ፡፡ የአምናውን ክፋት አንጨርስ፡፡ አዲስ ጎዳና ይተለም። አዳዲስ ፈትል ይቀለም፡፡ ተከፋፍሎ መፍረስ ይብቃ፡፡ ለቆጡ ተንጠራርተን የብብቱ አያምልጠን፡፡

የእብደቱ መንገድ ቁልቁለቱ፣ በዘር ሀረግ መለቃቀም፣ በእምነት ጥላ መጠቃቀም ይብቃን፡፡ በሰውነት እንከባበበር። ማድላት ማግለል እንቅበር። ቅን እናስብ። ቅን እንናገር፡፡ አፍና ልባችን አንድ ይሁን፡፡

በአዲሱ ዓመት በአስተሳሰብ ለውጥ ‹‹እኛ እነሱ››፣ ‹‹የእኛና የእነርሱ››የሚል ዘረኛ ቀይ የጎጥ መስመር ከማጋደም እንቆጠብ፡፡ በብሄር መነፅር ተሸፍነን ‹‹እንዲህ ነን››ስላልን ‹‹እንዲያ››እንደማንሆን እንገዘብ፡፡ የባንዲራ ክብር ይታየን። በጎጥና መንደር የጠበበ ሰው አስፍቶ ማሰብ ይሳነዋልና ከጎጥ አስተሳሰብ እንገንጠል፡፡

ምግባርና ተግባር የጎደለን፣ የሚጨበጥና የሚያዝ የሌለን አንሁን፡፡ ህሊና ያድሰን፡፡ ሰውነት ይመልሰን። ሃይማኖት ይፈውሰን፡፡ የሀገር ፍቅር ድምጽ ይሠማን። ሁሉም ወቃሽ ከመሆን አንቆጠብ፡፡ ‹‹ተበድያለሁ›› ከሚል በደል ቆጣሪነት እንፋታ፡፡ ከተገፊነት ተረክ እንላቀቅ። ከሚያነቃቅፈን ይልቅ የሚያስተቃቅፈንን እንምረጥ፡፡ ቃልና ተግባራችን ይመጣጠን፡፡

በአዲስ ዓመት ባለፈውና ባሳለፍነው አጉል ጊዜ መቆጨትን ማቆም እና ለወደፊቱ መሻልን ማሰብ ልንጀምር ይገባል፡፡ ከማፍረስ ይልቅ መካብ ሊቀለን፣ ሃሳብ ልዩነት ሁሌም ሊገለን ይገባል። ኋላቀርነት ሊማርከን፣ መጥፎ ታሪክ ሊጎትተን፣ ዘመን ሊያድሰን፣ ክፉ ትናንት ሊቀይረን አይገባም፡፡ ከመጥበብ መስፋትን እንምረጥ፡፡ ለሕዝብ የማይበጅ የሴራ ፖለቲካ መጎንጎን ማቆም አለብን፡፡

በአዲስ ዓመት በዚህ አስተሳሰብ ለመቃኘትና አስተሳሰቡን ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ ለዚህ የሚመጥን ጭንቅላት መፍጠር ግድ ይለናል። አስተዋይ ጭንቅላት አንድም ከመጽሐፍ ማሕፀን በንባብ ምጥ የሚወለድ፤ አንድም ትላንትን በማስተዋልና የኋላ ታሪክን ተጠቅሞ በበጎ እሳቤ በመለወጥ እውን እንደሚሆን ልንረዳም ይገባል፡ ፡ ይህ ማድረግ ከቻልን የተሻለችና በሁሉም መስኮች የተሳካላት ኢትዮጵያን ማየት ህልም አይሆንብንም፡፡

አዲሱ ዓመት ምንም ልንለውጠው ከማንችለው ትናንት ይልቅ የምንፈልገውን ነገር ሁሉ ልናደርግበት በምንችልበት ነገ ላይ እንረባረብ፡፡ ስለትናንትና አበክረን ስንናገር ዛሬና ነገ እንዳያመልጡን እንንቃ፡፡ መጪው ዓመት ያለፈውን እያስታወሰንና እያወሳን የምንጋጭበት ሳይሆን መጪውን እያለምንና እየተለምን በአንድነት በፍቅር ተደምረን የምንፈስበት ጨርሶ የመጀመር ዓመት ይሁንልን፡፡

ታምራት ተስፋዬ

አዲስ ዘመን መስከረም 23/2016

Recommended For You