በመመካከር ሰላማችንን በጽኑ መሰረት ላይ እናኑር!

እኛ ኢትዮጵያውያን በአንደበታችን የሰላምን ከፍ ያለ ዋጋ እንተርካለን፤ ስለ ሰላም የሁሉ ነገር መሰረትነት እንናገራለን፤ ስለ ሰላም የፈጣሪ መገለጫነት እንመሰክራለን። በተለይም እንደ ሀገርና ሕዝብ በግጭትና ጦርነት ምክንያት ብዙ ዋጋ እንደከፈለ ሕዝብ የሰላምን ዋጋ በመገንዘብ ረገድ የምንሰጠው ዋጋ እጅግ ከፍ ያለ ነው።

“ሰላምን እሻት፣ ተከተላትም” እንዲል ቃሉ፤ ታዲያ ይህችን በብዙ የምናወራላትን ሰላም፣ በምናወራላት ልክ ምን ያህል ተገንዝበናት በመካከላችን ልናመላልሳት፤ በፀና መሰረት ላይ ልናኖራት፤ እንዳትናወጥ አድርገን ከእኛ ጋር ልናዘልቃት እየሠራን ነው? የሚለው ላይ ሁሉም ራሱን ሊጠይቅ የሚገባው ጉዳይ ነው።

ምክንያቱም ሰላም ከመሰረቷ የራስን፣ የቤተሰብን፣ የጎረቤትን፣ የአካባቢን፣ የማሕበረሰብን፣ የሀገርና አሕጉርን፣ ብሎም የዓለምን ጸጥታ የምትወስን ናትና። ለሰው ልጆች ዕረፍት የምትሰጥ፣ ርጋታን የምታላብስ፣ ርካታን የምታጎናጽፍ፤ በዚህ ሁሉ መካከል ደግሞ የሰው ልጆችን በፍቅርና በአንድነት ተቻችሎ አብሮ የመኖርን ከፍ ያለ ስሜትና ልዕልና የምታስገኝ ሰገነት ናት።

ለምሳሌ፣ ሰላምን ‘የጦርነት አለመኖር፣ ወይም ያለመረበሽ ወይም ነፃነት ነው” በማለት የሚገልጹ መዛግብትና ምሁራን አሉ። ይሄ ነጻነት ባለበት ቦታ ደግሞ፣ ‘እርቅ፣ ፀጥታ፣ እርጋታ፣…’ በእጅጉ ጎልተው የሚስተዋሉ የሰላም መገለጫዎች ስለመሆናቸውም አያይዘው ይዘረዝራሉ።

በሌላ በኩል፣ “ሰላም ማለት የግጭት አለመኖር ማለት አይደለም“ ሲሉ የሚሞግቱ የዘርፉ ምሁራንም አሉ። እነዚህ ደግሞ ሰላምን ከሕሊና እረፍት እና ፀጥታ ማግኘት፣ ከሁከት ከሽብርና ከሰቀቀን መራቅ፣ ከአንድነትና ስምምነት መኖር ጋር አዛምደው ይገልጹታል። የግጭት አለመኖር የሠላም መኖር ምልክት እንጂ በራሱ ሰላም አይደለም የሚል ጭብጥም ያቀርባሉ።

እነዚህ በሁለቱም መንገድ የሚነሱ ሀሳቦች የተለያዩ ይምሰሉ እንጂ ማጠንጠኛቸውም፤ መዳረሻቸውም አንድ ነው፤ ሰላም። የሰው ልጆች ደህንነት፤ የሕብረተሰብ አብሮነትና እረፍት፣ ሙሉነት፣ ስኬት፣ ሁለንተናዊ ደህንነት፣… የሚሉትን የሰውና የማሕበረሰብ ሰላም ጉዳዮችን ይመለከታሉ።

ታዲያ ይህችን የዕረፍት ሰገነት የሆነችውን ሰላም በጽኑ መሰረት ላይ ማኖር፤ ዘላቂ በሆነ ውቅር ላይ ማጽናት ደግሞ ከሁሉም ዜጋ ይጠበቃል። በተለይ እንደ እኛ በሰላም እጦት ዋጋ ለከፈለ፤ በጦርነት አረር ለተመታ፤ በመፈናቀልና በርስ በርስ ግጭት ለታመሰ፤ ወንድማማቾችን በተቃርኖ ጎራ አሰልፎ ሰይፍ ለተማዘዘ፤ ዛሬም ድረስ በዚሁ ጠባሳ ምክንያት እየተናቆረ ላለ ሕዝብ ይሄን ማድረግ ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም።

እኛን ኢትዮጵያውያንንም የሚመለከተን ይሄው ነው፤ በፀጥታ እና በሕሊና እረፍት ውስጥ መኖር። በአብሮነትና በሕብረት መድመቅ፤ በሰላም በስኬት ጎዳና ላይ መመላለስ፤ በፍቅር ወደ ይቅርታ እና እርቅ ማምራት፤ በወንድማማችነት ስሜት በጋራ ቁጭ ብሎ መነጋገርና ችግሮችን መሻገር።

ዛሬ የሚያስፈልገን ይሄን መሰሉ የሰላም መንገድ ነው። ይሄን ዓይነቱ የሰላም ማምጫ ሥርዓት ነው። መደማመጥ፣ መከባበርና በሃሳብ ብዝኃነት አምኖ ለአብሮነታችን ጋሻ የሚሆን ጡብ ከሁላችንም አንደበት እንዲወጣ፤ በሁላችንም እጅ እንዲሰራ ማድረግ ነው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽንም በአዋጅ ተቋቁሞ ወደ ስራ ሲገባ ይሄንኑ ማድረግን ታሳቢ በማድረግ ነው። የሚሠራውም የትናትን ጠባሳዎችን ማከም፤ ስብራቶችን መጠገን፤ ቂምና ቁርሾን መሻር፤ ፍቅርና አብሮነትን ማጽናት፤ በይቅርታና እርቅ ጠብንና የመጠላላት ግድግዳን መናድ፤ ስለ ሰላም እውን መሆን ሁሉን አቀፍ ሥራ ማከናወንን ታላሚ አድርጎ ነው።

ኮሚሽኑ ታዲያ ኢትዮጵያውያን ስለ ሰላማቸው ቁጭ ብለው እንዲመክሩ መድረክ ይፈጥርላቸዋል እንጂ፣ አንደበት ሆኖ አይናገርላቸውም። የአብሮነትን ልዕልና ተረድተው ስለ ሕብረብሔራዊ አንድነታቸው ሲሉ ይቅርታና እርቅን ሀብታቸው እንዲያደርጉ በትር አያነሳባቸውም።

ነገር ግን ይሄን እንዲያደርጉ መድረክ ይፈጥርላቸዋል፤ የሰላምን መንገድና ልዕልና ያመላክታቸዋል፤ ስለ እርቅና ይቅርታ፣ ስለ ፍቅርና አብሮነት፣ በቀና ልብና ሕሊና ቁጭ ብሎ መምከር ስላለው ከፍ ያለ ፋይዳ፤… በማስገንዘብ ወደ ንግግርና ሰላም እንዲያመሩ ሁኔታዎችን ያመቻችላቸዋል።

ይሄ ማለት በተፈጠረው ዕድል ተጠቅሞ ለመመካከር በጋራ የመቀመጥ፤ ወደ አንድነት የሚያመጡ መልካም ሃሳቦችን የማዋጣት፤ የሚያለያዩ እና በታሪክ ሂደት የተፈጠሩ ችግሮችን በግልጽ ተነጋግሮ በሰላም የመፍታት፤ በእርቅም ለመሻገር ቁርጠኛ የመሆን ትልቁ የቤት ሥራ ያለው እኛው ሕዝቦቹ ላይ ነው።

በመሆኑም በሰከነ አዕምሮ ተነጋግሮ፤ በንጹሕ ኅሊና ተወያይቶ፤ በቅን ልቡና አቀራራቢ ሃሳቦችን ገዝቶ፤ ከትናንት እስከ ዛሬ ዋጋ ያስከፈሉንን ጉዳዮች በማስወገድ፤ ከትናንት እስከዛሬ ለአብሮነታችን መሰረት የሆኑ እሴቶችን የበለጠ በማላቅ፣ የራቀንን ሰላም ለማቅረብ፤ የጠፋብን የሕሊና እረፍት ለመመለስ መትጋት ይኖርብናል።

ስለሆነም በተዘጋጀልን የምክክር መድረክ ላይ ስንሰየም፣ ዘመናትን ዋጋ ያስከፈለንን የሰላም እጦት በሰላም ለመተካት፤ በመምከርም ሰላማችንን በጽኑ መሰረት ላይ ለማኖርና ለማዝለቅ፤ እኛም ከሰላሙ ሰገነት ስንገኝ በብዙ እንደምናተርፍ አምነን ሊሆን ይገባል!

አዲስ ዘመን መስከረም 22/2016

Recommended For You