ሌላኛው የኢትዮጵያ አረንጓዴ ወርቅ-እንሰት

የእንሰት ተክል ከ1939 ዓ.ም ጀምሮ የተካሔዱ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ ጠቃሚነቱ ታውቆ በሺ ለሚቆጠሩ ዓመታት ለምግብነት ሲውል ቆይቷል። ይህ ተክል በብዛት ለሰው ልጆች ለምግብነት እና ለከብቶች መኖ፣ ለመድሃኒትነት እና ምንጣፍን ለመሳሰሉ የተለያዩ አገልግሎቶች መዋል ይችላል። ለአፈር እና ውሃ ጥበቃ የሚያበረክተው አስተዋፅኦም በጣም ከፍተኛ መሆኑ የተነገረለት ይኸው ተክል፤ ደጋ እና ወይናደጋ ብቻ ሳይሆን ቆላም ማደግ የሚችል መሆኑ በጥናት ተረጋግጧል።

የእንሰት ተክል ድርቅን በመቋቋም በኩልም ሰፊ አስተዋፅኦ አለው። እንሰት ለምግብነት እና ለቤት ውስጥ ለተለያዩ መገልገያዎች መጠቀሚያነት ለመዋል የሚደርስበት ጊዜ እንደሚተከልበት አካባቢ መለያየት እና እንደእንሰት ዝርያው ዓይነት ከሁለት ዓመት ተኩል እስከ ስምንት ዓመት ሊቆይ እንደሚችል የዘርፉ ተመራማሪዎች ይናገራሉ። በባህላዊ መንገድ ከመሬት ከተነሳ በኋላ ለምግብ ዝግጁ ለመሆን እስከ ሁለት ወር የሚፈጅ ሲሆን፤ አሁን ግን በምርምር የእንሰት ማብላያ በመዘጋጀቱ ከሰባት እስከ አስር ቀን ባለ ጊዜ ውስጥ ዝግጁ መሆን እንደሚችል በሳይንስ አረጋግጠናል የሚሉት አዲሱ ፍቃዱ (ዶ/ር) ናቸው።

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ እና የእንሰት ፕሮጀክቶች አስተባባሪው አዲሱ (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ እንሰት አንዴ ከተብላላ በኋላ ተሸፍኖ ከዓመት በላይ መቆየት ይችላል። ምርቱ በማንኛውም ወቅት ከመሬት መነሳት የሚችል እና በየትኛውም ወር በሚፈለግበት ጊዜ በቀላሉ ለምግብነት የሚውል ነው።

እንሰት ለምግብነት ሲውል ለሰውነት ከሚያስፈልጉ ንጥረ ነገሮች መካከል ተጠቃሽ የሆኑትን፤ ፋይበር እና ካርቦ ሃይድሬት የመሳሰሉትን እንደያዘ የሚያስረዱት ደግሞ በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር ዮሐንስ ገብሩ (ዶ/ር) ናቸው።

እንሰት በኢትዮጵያ ብቻ በቀድሞ አጠራሩ በደቡብ ክልል በስፋት ለምግብነት የሚውል ሲሆን፤ በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎችም የሚገኝ ተክል ነው። ለረዥም ጊዜ ውሃ ሳያገኝ መቆየት የሚችለው ይኸው ተክል፤ በ1977 ዓ.ም በኢትዮጵያ ተከስቶ በነበረው ድርቅ እንሰት አብቃይ አካባቢዎች ያለመጠቃታቸው ምክንያት ይኸው መሆኑን ዮሐንስ (ዶ/ር) አስረድተዋል።

አዲሱ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደገለፁት፤ ድርቅን በመቋቋም እና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ሰፊ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት በጥናት ማመላከት ተችሏል። እስከ አሁን በተካሔደው ጥናት በአንድ ቦታ ላይ ለሶስት ዓመት ሳይቋረጥ ስንዴ ሲተከል ከእንሰቱ የሚገኘው ምርት የስንዴውን እጥፍ መሆኑን ማወቅ ተችሏል።

በደቡብ በተለይም በጉራጌ አካባቢ ሴቶች ሞያቸው የሚለካው እንሰትን ለብዙ ጊዜ በጉድጓድ ውስጥ በማስቀመጥ ነው። ነገር ግን ከመሬት ተነስቶ ከተዘጋጀ በኋላ ለምግብነት ከመዋሉ በፊት ለዓመታት ጉድጓድ ውስጥ ተከማችቶ እና ተሸፍኖ መቆየቱ የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ ለቆጮ ተመጋቢ ሰዎች ጠዓሙ ቢጨምርም፤ የምግብ ይዘቱ ይቀንሳል ብለዋል። በሌላ በኩል ሲቆይ የተለየ ሽታ የሚያመጣ ሲሆን፤ የምግብ ይዘቱን እንዳይቀንስ እና ሽታውን ለማሻሻል ጥናቶች በመካሔድ ላይ መሆናቸውን ዮሐንስ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

እንሰት በፊት በነበረው የቤት ቆጠራ ዋነኛ የምግብነት ተጠቃሚ ቁጥር 20 ሚሊየን ይደርሳል ተባለ እንጂ፤ ከምርታማነቱ አንፃር አሁን ላይ የእንሰት ተመጋቢው ቁጥር ከ30 ሚሊየን የሚያንስ አለመሆኑን አዲሱ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

እንደ አዲሱ (ዶ/ር) ገለፃ፤ እንሰት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ያስችላል የተባለባቸው የተለያዩ ምክንያቶች አሉ። ድርቅን የመቋቋም ዝንባሌ አለው ያሰኘውም እንሰት በቀላሉ ውሃን የሚይዝ በመሆኑ፤ ለአንድ ብቻ ሳይሆን ለሁለት ዓመት ዝናብ ባይኖርም ሌሎች የምግብ ሰብሎች ስንዴ፣ ጤፍና በቆሎን የመሳሰሉ የሰብል እህሎች ማምረት ባይቻልም እንሰት ሳይጠወልግ ቆይቶ በቀላሉ በማንኛውም ጊዜ ለምግብነት መዋል ስለሚችል ነው።

በሌላ በኩል ከምርታማነት አንፃርም እስከ አሁን በተካሔደው ጥናት በአንድ ቦታ ላይ ለሶስት ዓመት ሳይቋረጥ ስንዴ ሲተከል ከእንሰቱ የሚገኘው ምርት የስንዴውን እጥፍ መሆኑን ማወቅ ተችሏል። በተጨማሪ እንሰት በተተከለበት በትንሽ ቦታ ብዙ ምርት ማግኘት ከመቻሉም ባሻገር፤ እንደሌሎች ሰብሎች ምርቱ የሚሰበሰብበት ወቅት የተወሰነ አይደለም። መስከረምም ሆነ ነሐሴ ጥቅምትም ሆነ ሕዳር በማንኛውም ጊዜ እንሰትን ለምግብነት ማዋል ይቻላል ሲሉ አዲሱ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

እንሰት ላይ ያለው ችግር አጠውልግ የሚባል በሽታ ነው። ከአጠውልግ በተጨማሪ እንሰትን የሚቦረቡሩ ጥቃቅን ነፍሳቶችም አሉ። እነዚህ እንሰት ላይ የተጋረጡ ፈተናዎችን ለመከላከል ብዙ ምርምሮች የተካሔዱ ሲሆን፤ በተለይ የበሽታው መንስኤ እና የመከላከያው መንገድ ምንድን ነው በሚል ጥናቶች በመካሔድ ላይ ናቸው ብለዋል።

በጥናት ንፁህ፣ ከበሽታ እና ከተባይ የፀዳ የእንሰት ችግኝ ለአርሶ አደር የሚያቀርብ የችግኝ ምንጭ አለመኖሩ፤ በተለመደው መንገድ አርሶ አደሮች ችግኙን የሚሻሻጡበት ሁኔታ መኖሩ ለበሽታው መስፋፋት በመንስኤነት የተቀመጠ ሲሆን፤ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በከፍተኛ መጠን ችግኞችን በማባዛት ለማሰራጨት ጥረት እያደረግን መሆኑን አዲሱ (ዶ/ር) አመላክተዋል።

ሌላኛው በአዲሱ (ዶ/ር) የተገለፀው ችግር እንሰት የሚዘጋጅበት መንገድ አድካሚነትን የተመለከተው ጉዳይ ነው። ሲዳማ፣ ጌዶዮም ሆነ ጉራጌ በየትኛውም አካባቢ ያሉ ሰዎች እንሰትን የሚፍቁት አድካሚ በሆነ መልኩ በባህላዊ መንገድ በእንጨት፣ በአጥንት እና በቀርከሃ ነው። በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አዳዲስ መፋቂያዎችን በማዘጋጀት እና አርሶ አደር ጋር ደርሶ በመሞከር በመጨረሻም አርሶ አደሩ ምቹ ነው የሚለውን በማባዛት እየተጠቀሙበት ነው። ነገር ግን እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ከባድ ችግር ቢያቃልሉም፤ አባዝቶ ለአብዛኞቹ ተጠቃሚዎች የማድረስ ችግር አለ።

አዲሱ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ ለእንሰት አንድ ዶላር አይወጣም። እንሰት አምራች አርሶ አደር የግብርና ባለሞያም ሆነ ማዳበሪያ አይጠቀምም። ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ እንሰት ሌላኛው አረንጓዴ ወርቅ መሆኑን የመገንዘብ ችግር አለ። እያዳንዳቸው ከ30 እና 40 በላይ እስከ 200 እንሰት ያላቸው አርሶ አደሮች አሉ። ይህ እንሰት የአገር ሃብት ነው። ለዓመታት ከሚቆይ ተፍቆ ለምግብነት ቢውል እና በእርሱ ቦታ ሌላ ቢተከል እጅግ ብዙ ጥቅም ማግኘት ይቻላል። በዘመናዊ መንገድ ተመርቶ ለአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ለውጪ ገበያ ቢቀርብ፤ የውጭ ምንዛሪን ያስገኛል። ነገር ግን በእንሰት አብቃይ አካባቢዎች እንሰት ቦታ ይዞ ወደ ምግብነት ሳይቀየር እና ገበያ ላይ ሳይውል ከመቆየቱም በተጨማሪ፤ ከተፋቀ በኋላ ጉድጓድ ውስጥ ለረዥም ዓመት የመቅበር ባህል አለ። ይህ አንዳንዴ ጎርፍ ገብቶ ምርቱ የሚጠቁርበት እና ሙሉ ለሙሉ የሚበላሽበት ሁኔታ መኖሩንም አዲሱ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

ጉድጓድ ውስጥ ማስቀመጥ ብቻ ሳይሆን፤ በሌላ በኩል አንድ አርሶ አደር ከ100 እንሰት ውስጥ 5ቱን ለምግብነት አውሎ 95ቱን የደረሰ እንሰትን አራት እና አምስት ዓመት ማስቀመጡ በተመሳሳይ አርሶ አደሩንም ሆነ አገርን ማክሰር ነው። ተፍቆ ጉድጓድ ውስጥ ገብቶ ለብዙ ዓመታት ቢቀመጥም ኪሳራ ነው። ነገር ግን ምግቡ ለሰው ልጅ ውሎ ሌላ ቢዘጋጅ የተሻለ ነው። አንደኛ አርሶ አደሩ ለራሱ ተጨማሪ ገቢ ያገኛል፤ ሌሎችም በተመጣጣኝ ዋጋ ይመገባሉ ብለዋል።

ከኢኮኖሚ እና የምግብ ይዘትን ከመቀነስ አንፃርም ጉድጓድ ውስጥ ባይቀመጥ ይሻላል ያሉት አዲሱ (ዶ/ር)፤ ቀድሞ ከውጪ የሚገባውን ስንዴ በአገር ውስጥ ተተክቷል። አሁን ደግሞ በስፋት ማዳበሪያ እየገባ ነው። የማዳበሪያ ወጪንም ለመቀነስ እንሰት ላይ ቢሠራ ትልቅ ጥቅም ማግኘት ይቻላል ብለዋል።

እንደ አዲሱ (ዶ/ር) ገለፃ፤ እንሰት በአገር ውስጥ የማዳበሪያ ወጪንም ሆነ ከውጪ የሚገቡ ለምግብነት የሚውሉ ምግቦችን፣ የውጭ ምንዛሪ ወጪን እና የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ የሚኖረው ጠቀሜታ እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው። ነገር ግን እንሰትን በዚህ መልኩ በመረዳት በኩል ሰፊ ክፍተት መኖሩን አብራርተዋል።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እንሰት ከጉድጓድ ይውጣ የሚል ዘመቻ በማካሔድ እና እንሰትን ለማብላያነት የሚያገለግል እና ማስቀመጫ የሚሆን ዕቃ በማዘጋጀት የማስተዋወቅ ሥራ እየሠራ መሆኑንም ተናግረዋል። ይህንን ዩኒቨርሲቲው ቢሠራም፤ በተለይ ወደ ደቡብ ምዕራብ ወደ ሃድያ ዕቃውን የማስተዋወቅ እና የማስፋፋት ሥራ አለመሰራቱ እና የተጠቃሚውን ቁጥር በሰፊው መጨመር አለመቻሉ ሌላኛው ችግር ነው ብለዋል።

በተመሳሳይ ዮሐንስ (ዶ/ር) የተገለፀው ችግር አጠውልግ የሚባል የእንሰት በሽታ ሲሆን፤ ሌላኛው ምግቡን ለማዘጋጀት አድካሚ መሆኑን ነው። በተለምዶ አጠውልግ የሚባለው በሽታ ባክቴሪያ ሲሆን፤ ለመድሃኒትነት የሚውሉትን የተመረጡ የእንሰት ዝርያዎችን እያጠፋ መሆኑን አብራርተዋል። እንሰትን ለምግብነት ለማዋል ሴቶች እግራቸውን ሰቅለው ለረዥም ሰዓት ሲፍቁ መዋላቸው በጣም እየጎዳቸው መሆኑንም ተናግረዋል። ይህን ተከትሎ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ሁለቱ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ እየሠራ መሆኑንም አስረድተዋል።

እንደ ዮሐንስ (ዶ/ር) ገለፃ፤ ወደፊት ሁለቱን ነገሮች መከላከል ካልተቻለ እንሰት ሊታጣ የሚችልበት አደጋ ያጋጥማል። ይህንን ለመከላከል ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የእንሰት ዘሮች ማባዣ እና ማቆያ ጣቢያ አዘጋጅቷል። በጣቢያቸው ሊጠፉ የደረሱትን ጠብቀው ይዘዋል። ከመያዝ ባሻገር እስከ 2014 ዓ.ም ዝርያዎቹን መልሰው ለሕብረተሰቡ ሲያሰራጩ ቆይተዋል።

በተጨማሪ ጥናት በማካሔድ ችግኝ በሚጓጓዝበት ጊዜ ባክቴሪያዎቹ ካሉበት አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ የማስፋፋት ሁኔታዎች መኖራቸውን አውቀዋል። ይህን ተከትሎ ባክቴሪያዎቹ የሚስፋፉባቸውን የተለያዩ መንገዶችን ለሕብረተሰቡ ስልጠና እየሠጡ መሆኑንም ተናግረዋል።

አዲሱ (ዶ/ር) ሲናገሩ፤ እንሰት ቢያንስ አንድ አራተኛው የአገሪቱን ሕዝብ የያዘ ነው። የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ያለው ሚና በጣም ከፍተኛ ነው። በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ውስጥ ካለው የእንሰት ምርት ውስጥ ሩብ የሚሆነው እንኳ ጥቅም ላይ አልዋለም። ውስን ሥራዎች በትኩረት ቢሠሩም፤ በተመጣጣኝ ዋጋ የእንሰት ምግብን በቀላሉ ለገበያ የሚውልበት እና ብዙዎች የሥራ ዕድል የሚያገኙበት ዕድልን መፍጠር ይቻላል ሲሉ ወደፊት መሆን ያለበትን አመላክተዋል።

እንሰት ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ለምግብነት የሚውል በመሆኑ፤ ለምግብ ቱሪዝም ማዋልም ይቻላል። ያሉት ዶክተር አዲሱ፤ ምንም ዓይነት ኬሚካል የማይነካው፤ ያልተዳቀለ ጤናማ ምግብ ሲሆን፤ የማስተዋወቅ ሥራ ቢሠራ በዓለም ደረጃ ገበያ ላይ በመሳተፍ ከምግብ ቱሪዝም በተጨማሪ በውጪ የእንሰት ምርት ሽያጭ ብዙ ማግኘት ይቻላል ብለዋል።

ዮሐንስ (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ በዩኒቨርስቲያቸው በኩል ባህላዊ የእንሰት ምግብ አመራረት ዘዴን ለማዘመን በመስራት ላይ ይገኛሉ። ማህበረሰቡ እንዲጠቀምበት ማድረግ እና ከእንሰት የተለያዩ ምግቦችን የማስተዋወቅ ሥራን በማከናወን ላይ ናቸው። አርሶ አደሮቹም ቴክኖሎጂን ተጠቅመው ጥሩ ምርት በማምረት ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ ለወጣቶች የሥራ ዕድል እየተፈጠረበት ነው ማለት ይቻላል።

ዮሐንስ (ዶ/ር) የእንሰት አጠውልግ በሽታ በጣም ረዥም ጊዜ የቆየ መሆኑን አስታውሰው፤ በእነርሱ ዩኒቨርሲቲም ወደፊት በሽታውን የሚቋቋሙ ዝርያዎችን መፈለግ አንደኛው ሥራቸው አድርገው በመስራት ላይ የሚገኙ መሆኑን ተናግረዋል። በሽታውን የሚያጠፋ መድሃኒት በመፈለግ ላይ መሆናቸውን ጠቁመው፤ የመድሃኒት ፍለጋው በዘመናዊ መልኩ ብቻ ሳይሆን፤ ህብረተሰቡ በባህላዊ ዕውቀቱ ለረዥም ጊዜ በሽታውን ሲከላከል የቆየበትን መንገድም እያዩ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህን በሽታ ለማጥፋት ያልተቻለው ህብረተሰቡ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ባህላዊ መድሃኒቱን ተጠቅሞ፤ ሌሎች ቦታዎች ላይ ሳይጠቀም ሲቀር የተስፋፋ ነው የሚል መላምት ተይዞ ጥናት እየተካሔደ ነው ብለዋል።

እንሰት እየፋቁ የሚደክሙ ሴቶች ድካማቸውን ለመቀነስ ዘመናዊውን ማሽን ወደ ገበያው ማስገባት እና በማሽን እንዲያመርቱ ማድረግ ላይ ወደፊት በስፋት መሰራት እንዳለበት አመልክተው፤ በዚህ ላይ ዩኒቨርሲቲው ብቻ ሳይሆን ሌሎች ተቋሞችም አተኩረው መሥራት አለባቸው ብለዋል። ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ሁለት የናሙና ማሽኖችን ፕሮቶታይፕ ለመስራት ጨርሷል። አንደኛው ረዥም ጊዜ የቆየ ሲሆን፤ ሁለተኛው ግን ከአንድ ዓለም አቀፍ ኢንሼቲቭ ጋር በመተባበር፤ ማሽኖቹን አምርተው ለማስፋፋት ዝግጅታቸውን እንደጨረሱ ተናግረዋል።

በመጨረሻም ወደ ፊት ሥራውን በመሥራት ማሳ ላይ በስፋት ያሉትን እንሰቶች ለምግብነት ለማዋል ማሽኑን በፍጥነት ወደ ሥራ የማስገባት ዕቅድ ይዘው በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸውን አመልክተው፤ በሽታው ላይም ጥልቅ ምርምር ለመሥራት ማቀዳቸውን ተናግረዋል።

እንደ ምሁራኑ ገለፃ፤ በአጠቃላይ እንሰት እጅግ ጠቃሚ ነገር ግን ተገቢውን ትኩረት ያልተሰጠው ተክል ነው። ይህንን ተክል የተደቀነበትን የአጠውልግ በሽታ መከላከል እና የአዘገጃጀት ሁኔታውን ቀለል ማድረግ ካልተቻለ በተመጋቢው ላይ የሚፈጥረው ችግር ከፍተኛ ሲሆን፤ በተክሉ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ከተሠራ ግን ድርቅ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ፤ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፤ ከምግብ ቱሪዝም ተጠቃሚ ለመሆን እና የተክሉን ምርት ለውጪ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪን ለማግኘት ያስችላል።

 ምሕረት ሞገስ

 አዲስ ዘመን መስከረም 22/2016

Recommended For You