ከትላንት ያደሩ ወረቶቻችን የዛሬ ስንቆቻችን ናቸው

ሀገር በአንድ ጀንበር ተገንብታ አታድርም። ትላንት ለዛሬ አሻግሮ በሚሰጠውና ዛሬም በተራው በሚያቀብለው ወረት ነው ሀገር እየተገነባች የምትጓዘው። በአጭር አማርኛ ዛሬ ያለትላንት የለም፤ ነገም ያለ ዛሬ ህልውና የለውም።

አዲስ የገባው 2016 ዓ.ም ያለ 2015 ዓ.ም እውን ሊሆን አይችልም። በ2015 በበጎም ሆነ በክፉ የተከሰቱ ጉዳዮች በ2016 ዓ.ም በበጎም ሆነ በክፉ አሻራ ማሳረፋቸው አይቀሬ ነው። ስለዚህም በ2015 ዓ.ም እንደ ሀገር ያገኘናቸው ድሎችና ያጋጠሙን ተግዳሮቶች አዲስ በያዝነው ዓመት ላይ የራሳቸውን አሻራ ማሳደራቸው አይቀሬ ነው።

እንደ ሀገር የነበሩን ጥንካሬዎች ለመጪው ጊዜ እርሾ ሆነው ያበረቱናል። ድክመቶቻችንም እንዲሁ ታርመው ለነገ ጥንካሬያችን ምንጭ ይሆኑናል። በአጠቃላይ ጥንካሬዎቻንን አጎልብተን፤ ድክመቶቻችን ቀርፈን የተሻለች ሀገር እንደትኖረን እንደ መልካም እድል ሆነው ያገለግሉናል።

የሸኘነው 2105 ዓ.ም እንደ ሀገር በርካታ ውጤቶች ያገኘንበትና በዚያው መጠንም የተፈተንበት ዓመት ነው። በ2105 ዓ.ም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ጎልታ የወጣችበት፤ በግብርና ምርት ውጤት ያመጣችበት፤ የድሆችን እንባ ያበሰችበትና ሰላምንም ለማጽናት ብዙ ርቀት የተጓዘችበት ነው።

ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ለሁለት ዓመታት ሲካሄድ የነበረው ደም አፋሳሽ ጦርነት የቆመበትና የፕሪቶርያው ስምምነት የተፈረመበት ታሪካዊ ቀን ነው። የፕሪቶሪያ ስምምነት ኢትዮጵያውያን ያለማንም ጣልቃ ገብነት የሀገራችውን ሰላም ማስጠበቅ እንደሚችሉ ያሳየና በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድም ግርማ ሞገስን ያላበሰ ታሪካዊ ክንውን ነው።

ይህም ስምምነት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ሲካሄድ የነበረውን ጦርነት አስተማማኝ በሆነ መልኩ የቋጨና ሞት፤ የአካል መጉደል፤ ስደትነና መፈናቀልን በማስቀረት ኢትዮጵያ ፊቷን ወደ ልማት እንድትመልስ ያስቻለ ነው። ይህ ስምምነት ኢትዮጵያውያን የጦርነት ብቻ ሳይሆን የሰላም ጀግኖች እንደሆኑ ያሳየና በሀገሪቱ ታሪክም አዲስ ታሪክ እንዲጻፍ ያስቻለ ነው።

2015 ዓ.ም ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ ጎልታ የወጣችበት ዓመት ነበር ማለትም ይቻላል። በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ፣ ከተደረገው የሰላም ስምምነት በመከተል ከዓለም አቀፍ ተቋማትና ከአውሮፓ አገራት ጋር ተቀዛቅዞ የነበረው ግንኙነት በመልካም ሁኔታ መቀጠል መጀመሩ በዓመቱ ከተከናወኑ ዓበይት የዲፕሎማሲ ድሎች መካከል የሚዘከር ነው።

ከዲፕሎማሲያዊ ድሎቹ መካከል ተጠቃሽ የሆነው አንዱ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊነትን ከያዙ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት ያደረጉት አንቶኒ ብሊንከን፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርን ጨምሮ ከተለያዩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ስለሀገራቱ ቀጣይ ግንኙነት መወያየታቸው ነው።

ሌላው ተጠቃሽ የሚሆነው ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በጣሊያን ሮም በተካሄዱ የተባበሩት መንግሥታት የልማትና ፍልሰት ጉባዔ እንዲሁም የዓለም ምግብ ድርጅት የምግብ ሥርዓት ስብሰባ ላይ ተሳትፈው ኢትዮጵያ በምግብ ራስን በመቻልና ሕገ ወጥ ስደትን በመከላከል በኩል ያላትን ልምድ ማካፈላቸው ነው። ከጉባዔው ጎን ለጎን ከተለያዩ አገራት ጋር የሁለትዮሽ ውይይትም አድርገዋል።

የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት አጃይ ባንጋ ባሳለፍነው ዓመት ኢትዮጵያ በመምጣት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተነጋግረዋል። የፕሬዚዳንቱ ጉብኝትም የዓለም ባንክ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን የትብብር አድማስ በማስፋት ለኢኮኖሚ እድገታችን በኮንሴሽናል ፋይናንስ፣ በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን በኩል ጠንካራ የኢንቨስትመንት ፋይናንስ አቅርቦት በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይታመናል። የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ፕሬዚዳንት ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ መጥተው 17 ስምምነቶችን የተፈራረሙትም በዚሁ ዓመት ነው።

በሐምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም በአንድ ጀንበር 569 ሚሊዮን ችግኝ በመትከል ዓለምን በሌላ አዲስ ታሪክ ጉድ ያሰኙት በዚሁ ዓመት ነው። እንደ ሀገገርም ባለፉት አራት ዓመታት ከ31 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል በበረሃማነትና በአየር ጸባይ ለምትሰቃየው ዓለማችን መድህን መሆን ችለናል።

ስንዴ ከራስ ፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያም የቀረበው በዚሁ በሸኘነው 2015 ዓ.ም ነው። በዚህ ዓመት ብቻ 32 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለውጭ ገበያ መቅረቡ የዚሁ ስኬት አንዱ ማሳያ ነው። በሩዝ ዘርፍም እየተከናወነ ያለው ተግባርም ኢትዮጵያን ከሩዝ ተቀባይነት ወደ አስመጪነት የሚያሸጋግራት ነው።

ኢትዮጵያ እንደ ስንዴው ሁሉ ለሩዝ ምርት ትኩረት በመስጠት ከሀገራዊ ፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያ ለመላክ በትኩረት በመስራት ላይ ትገኛለች። በተለይም ሀገሪቱ ለሩዝ ምርት ተስማሚ የሆነ የአየር ጸባይና ምቹ መሬት ያላት መሆኑ ያቀደችውን ወደ ተግባር ለመለወጥ እንደማያዳግታት የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ።

ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለከትውም፤ በኢትዮጵያ 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር በሩዝ መልማት የሚችል መሬት ቢኖርም በየዓመቱ ከ200 ሺህ ቶን በላይ ሩዝ ወደ ሃገር ውስጥ በማስገባት በየዓመቱ 200 ሚሊዮን ዶላር ወጭ ታደርጋለች።

በኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ስርዓት መተግበር ከጀመረ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ መንግስት ፊቱን ወደ ሩዝ ምርት በማዞር በአጭር ጊዜ ውስጥ አበረታች ውጤቶች መመዝገብ ጀምረዋል።

አሁን ላይ ሩዝ በስፋት የሚመረተው በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝ እና ትግራይ ክልሎች ሲሆን በዘንድሮው 2015/2016 የምርት ዘመን በአማራ 150 ሺህ ሄክታር መሬት በሩዝ በመሸፈን 8 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ነው።

በተመሳሳይም በኦሮሚያ ከ1 ሚሊዮን ሄክታር በላይ በሩዝ ለመሸፈን ታቅዶ እስካሁን 700ሺ ሄክታሩን ማሳካት ተችሏል። የሁለቱ ክልሎች እንቅስቃሴ ብቻ በሀገር ውስጥ ለምግብ ፍጆታነት የሚጠበቀውን ከ6ሚሊዮን ያልበለጠ ፍላጎት በመሸፈን ቀሪውን ምርት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል ነው።

የ2015 ዓ.ም ትሩፋቶች ከሆኑት ውስጥ የአባይ ግድብ አራተኛ የውሀ ሙሌት ተጠቃሽ ነው። በዚህ ትውልድ ጠንሳሽነት ግንባታው በመገባደድ ላይ የደረሰው የአባይ ግድብ በርካታ ፈተናዎችና አሜካላዎች ቢገጥሙትም በዚህ ትውልድ አይበገሬነት ዛሬ ከራስ አልፎ ለጎረቤት ሀገራት ብርሃን መሆን ችሏል። በ2105 ዓ.ም በተሰሩ ስራዎችም በያዝነው ዓመት ተጨማሪ አምስት ተርባይኖችን ወደ ስራ የማስገባት ስራዎች ይከናወናሉ። በአጠቃላይም በዚህ ዓመት ብቻ ሰባት ተርባይኖች አገልግሎት ይሰጣሉ።

በ2015 ዓ.ም እንደ ሀገር ከተገኙ የዲፕሎማሲ ስኬቶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ደግሞ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆን መቻሏ ነው። በተሰሩት እልህ አስጨራሽ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ብዙዎች የተመኙትን የብሪክስ አባልነት ኢትዮጵያውያን ማሳካት ችለዋል። ይህም ለሀገሪቱ በርካታ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥቅሞች ይዞ የሚመጣ ነው።

የለውጡ መንግስት ሀገሪቱን መምራት ከጀመረ ወዲህ እየጎለበቱ ከመጡ መልካም ተግባራት መካከል መረዳዳትና መደጋገፍ አንዱ ነው። በተለይም ጧሪ እና ደጋፊ የሌላቸውን ወገኖች አንዱ ባህል እየሖነ የመጣ መልካም ተግባር ነው። ይህም የበጎ ፈቃድ ስራ በ2015 ዓ.ም ተጠናክሮ የቀጠለበት ዓመት ነበር።

የ20ሺ አቅመ ደካማ ቤቶች ታድሰው በአዲሱ ዓመትም ቤት ለእንቦሳ ተብለዋል። ብዙዎችም በማዕድ ማጋራትም አዲሱን ዓመት ተደስተው ውለዋል። በአዲሱ ዓመት ዋዜማ የአዲስ አበባ አስተዳደር ብቻውን ከ450ሺ በላይ ለሚሆኑ አቅመ ደካሞች ማዕድ አጋርቷል።

በ2105 ዓ.ም የአላላ ኬላ የቱሪስት ማዕከል ተገባዶ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል። የኮይሻ፤ የጎርጎራ፤ የወንጪ፤ የቱሪስት መስህቦች እየተገባደዱ ነው። በአዲስ አበባም እየተከናወኑ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች መጪው ጊዜ ብሩህ መሆኑን ያመላክታሉ።

በነሐሴ ወር 2015 ዓ.ም. በሀንጋሪ ዋና ከተማ ቡዳፔስት በተዘጋጀው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በዘጠኝ ሜዳሊያ ከዓለም ስድስተኛ ሆና አጠናቃለች። በሴቶች 10ሺህ ሜትር ውድድር አትሌቶቻችን ከአንድ እስከ ሶስት ተከታትለው በመግባት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች “አረንጓዴ ጎርፍ” በሚል የሚታወቁበትን የአጨራረስ ስልት ዳግም በማሳየት አኩርተውናል።

በዚህ ውጤት ጉዳፍ ፀጋይ ወርቅ፣ ለተሰንበት ግደይ ብር እንዲሁም እጅጋየሁ ታየ ነሐስ አምጥተዋል። በሴቶች ማራቶን ደግሞ አማኔ በሪሶ እና ጎተይቶም ገብረስላሴ ተከታትለው በመግባት የወርቅ እና ብር ሜዳሊያ አግኝተዋል። በወንዶች 10 ሺህ ሜትር ውድድር ሰለሞን ባረጋ ሶስተኛ በመውጣት ለሀገሩ የነሐስ ሜዳሊያ ሲያስገኝ፤ በሴቶች 1500 ሜትር ድርቤ ወልተጂ ሁለተኛ ሆና የብር ሜዳሊያ አስገኝታለች።

በወንዶች 3 ሺህ ሜትር መሰናክል የዓለም ክብረ-ወሰን ባለቤቱ ለሜቻ ግርማ ሁለተኛ ሆኖ በማጠናቀቅ ብር ማግኘት ችሏል። በመጨረሻው ቀን በተካሄደ የወንዶች ማራቶን ልዑል ገብረስላሴ ሶስተኛ ሆኖ በማጠናቀቅ ነሐስ አግኝቷል። ኢትዮጵያ በጠቅላላው ዘጠኝ ሜዳሊያዎችን ሰብስባ ከአፍሪካ ሁለተኛ ከዓለም ስድስተኛ ሆና አጠናቃለች።

ከእነዚሁ ስኬቶች ጎን ለጎን ጦርነት፤ ግጭት፤ መፈናቀል፤ ስደት፤ ድርቅ፤ የመሳሰሉት ችግሮች ኢትዮጵያን ፈትነዋታል። አለመተማመን፤ መወነጃጀል፤ ጥላቻና ቂምም የፖለቲካችን አንዱ መለያ ሆኖ አብሮን ቆይቷል። ይህም ሁኔታ በተወሰኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች ጦርነት እንዲቀሰቀስ፤ ግጭት እንዲበራከት፤ ሞትና የንብረት ውድመት እንዲከሰት አድርጓል። በዚህም በርካቶች ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፤ ተሰደዋል።

ይህ ታሪክ ግን አንድ ቦታ ማብቃት አለበት። የሕዳሴ ግድብን የገነቡ ክንዶች፤ በአንድ ጀንበር ከ569 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን የተከሉ እጆች፤ የተራቡና የታረዙ ወገኖችን የታደጉ ስብናዎች ለግጭትና ለጦርነት ቦታ ሊኖራቸው አይገባም።

ስለዚህም የመገጫጨት፤ የመጠፋፋት እና የመገዳዳል ታሪካችን ሊዘጋ ይገባል። አሁን ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ግጭት፤ ጦርነትና መወነጃጀል ሳይሆን ውይይትና ምክክር ብቻ ነው። ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህልም እንደሀገር ሊጎለብት ይገባል። የስልጣኔም አንዱ መለኪያም ይኸው ነውና። በኢትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካ ሥራ ውስጥም ሆነ በሌሎች መስኮች የተሰማሩ ወገኖች፣ ለውይይት ቅድሚያ መስጠት አለባቸው።

ኢትዮጵያ ከፊቷ የተጋረጡ በርካታ ችግሮች ያሉባት አገር ናት። የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ ለመነጋገርና ለመደማመጥ ጊዜ መስጠት አለባቸው። ጽንፍ ለጽንፍ ሆኖ ቃላት መወራወርና ይዋጣላን ማለት እንደሀገር ዋጋ አስከፍሎናል። በዚህም መንገድ ለዘመናት ተጉዘን ያተረፍነው ድህነትን፤ ኋላቀርነትና ዕልቂትን ብቻ ነው።

የታሪካችን አንዱ ክፋይ ሆኖ ዘመናትን የተሻገረውን ጦርነትና ግጭትን ለማስወገድና የተረጋጋች፤ ሰላሟ የተጠበቀ እና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመጭው ትውልድ ለማውረስ ሀገራዊ ምክክሩ ይዞ የመጣውን ዕድል ልንጠቀምበት ይገባል።

 አዲስ ዘመን መስከረም 22/2016

Recommended For You