ልጆቻችን ባወረስናቸው ችግርና መከራ ሳይሆን በበጎ ነገሮች እየኮሩ እንዲኖሩ

በርካታ የዓለም አገራት በትርምስና በግጭት ውስጥ አልፈዋል፤ እያለፉም ይገኛሉ። ይሁንና ጉዳዩ የአፍሪካ አገራት ላይ አይሎና ገዝፎ ይስተዋላል። በእርግጥ በአህጉርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለትርምስም ሆነ ለግጭት የሚቀመጥ ምክንያት ይኖራሉ። እርስ በእርስ የሚጋጨውም አካል ቢሆን ለመጋጨቱ በምክንያትነት የሚያስቀምጠው የራሱ የሆነ ሰበብ አለ ው።

ለግጭቱና ሰላም መታጣቱ ዋናው ምክንያት የሚባለው ጉዳይ እንደየአገራቱ ነባራዊ ሁኔታ ይለያይ እንጂ አብዛኞቹ ከሚደረድሯቸው ምክንያቶች መካከል ግንባር ቀደሞቹ የፖለቲካ፣ የብሔር፣ የጎሳ፣ የኃይማኖት ልዩነቶችና መሰል ጉዳዮች ናቸው። ይሁንና እነዚህ ችግሮች በአብዛኛው ሽፋን እንጂ እውነተኛ የግጭት መንስዔ ሊሆኑ የሚችሉ እንዳልሆኑ ይታመናል ።

በአህጉሪቱ የሚገኙ ለራሳቸው የተለያዩ ስያሜ የሚሰጡ ግለሰቦችና ቡድኖች የራሳቸውን ፍላጎት ለማሳካት ሲሉ ለሚያነሷቸው ግጭቶች ብሔራቸውን፣ ቋንቋቸውን እንዲሁም ኃይማኖታቸውን በምክንያትነት መጥቀስ የተለመደ ነው። በተለይ በአፍሪካ አገራት፤ መሰል ሰበብ የተለመደና የአህጉሪቱን ህዝቦች እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ ብዙ ዋጋ እያስከፈለ የሚገኝ እርግማን ነው።

የሚያሳዝነው ችግሮቹ ብዙዎችን ለህልፈት ከዳረጉ፤ ከፍተኛ የሆነ የሀብት ውድመት ካስከተሉ በኋላ ችግሩን ለመፍታት በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት ወደ ውይይት ብሎም በድርድር መግባታቸው ነው። ይህም ቢሆን በተሰጠ የሰላም ፈላጊነት መንፈስ ስለማይገራ ብዙም ስኬታማ ሲሆን አይታም።

ይህ ማለት ግን ችግሮቻቸውን በድርድር መፍታት የቻሉ ሀገራት የሉም ማለት አይደለም ። ለዚህ ደቡብ አፍሪካ መጥቀስ ይቻላል። እንደሀገር ደቡብ አፍሪካውያን የገቡበትን የከፋ ሀገራ ዊ ስጋት በእርቅ መንገድ መፍታት በመቻል ከዓለም ተጨባጭ ምሳሌ መሆን ችለዋል። ላገኙት ስኬት ጥረዋል፣ በብዙ ደክመዋል ።

ደቡብ አፍሪካውያን ከብዙ የመስዋዕትነት ትግል በኋላ የአፓርታይድ ስርዓት በመገርሰስ፤ ቀጣዩን ዘመን ከቂምና በቀል ነጻ አድርገው ሀገራቸውን እንደሀገር በሰላም ለማስቀጠል፤ የቀድሞ እስከፊ ታሪካቸውን በእርቅ ዘግተዋል። “የሐቅና የእርቀ ሰላም ኮሚሽን” የተባለ ተቋም መስርተው ስለ እርቅ በጽናት ተንቀሳቅሰዋል ። በዚህም ደቡብ አፍሪካውያን እውነትን በመናገር እርቅን ማውረድ ችለዋል።

በዚህ አካሄድ የነበረውን ቂምና ቁርሾ እንዲሁም ጥላቻና አለመተማመን በእርቀ ሰላም በመቋጨቱ ዛሬ ደቡብ አፍሪካ ሰላሟ ሰፍኖ በኢኮኖሚዋም ጠንካራና ከአህጉራችንም ፊተኛው መስመር ላይ የተሰለፈች ሀገር ለመሆን በቅታለች። ይህ ዝም ብሎ ሳይሆን ስለ ሰላም እርቅ በተከፈለ ከፍ ያለ ዋጋ የመጣ ስኬት ስለመሆኑ መላው ዓለም የሚያውቀው አደባባይ የሞቀ እውነታ ነው።

በኛም ሀገር ወደ ግጭት የሚወስዱ ሀገራዊ አለመግባባቶችን በእርቅና በድርድር ለመፍታት የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል፤ ለዚህም “የእርቀ ሰላም ኮሚሽን” በሚል በአዋጅ ቁጥር 1102/2011 ዓ.ም ተቋቁሞ ሲንቀሳቀስ ነበር። ከዚህ ባለፈም አሁን ላይ፤/በ2014 ዓ.ም”የኢትየጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጁ ወጥቶ ፣ ኮሚሽኑ ተቋቁሞ ወደ ስራ የገባበት ሁኔታ አለ ።

ኮሚሽኑ የተቋቋመው በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካና የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል መሰረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚታየውን የሐሳብ ልዩነቶችና አለመግባባቶች እንዲሁም የታሪክ ትርክቶች ዙሪያ በውይይት እና ምክክር ወደ አንድ መግባባት ለመድረስ ነው ።

ኮሚሽኑ ከፖለቲካ ወገንተኝነት፣ ከማንኛውም የመንግስት ወይም ሌላ አካል ተጽዕኖ ነጻ ወደ ስራ ከገባ ውሎ አድሯል፣ በአሁኑ ወቅትም የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቶ የውይይት ተሳታፊዎች ልየታና ሌሎች ጉዳዮችን በማከናወን ላይ ይገኛል።

ኮሚሽኑ ወደ ግጭት ሊወስዱ የሚችሉ አለመግባባቶችንና ታሪክ ትርክቶችን በውይይት ለመፍታት ለሚያደርገው ጥረት ሁሉም ዜጋ ኃላፊነት እንዳለበት ይታመናል ። የተቋሙ ስራ ስኬታማ እንዲሆን ተባባሪ በመሆን ከሁሉም በላይ ተጠቃሚ የሚሆነው ትውልዱ ነው ። ለዚህም ያሉንን መልካም የእርቅና መሰል አገራዊ እሴቶቻችን በአግባቡ መጠቀምም አስፈላጊነቱ ለጥያቄ የሚቀርብ አይሆንም።

በእርግጥም መመካከር መልካም ነው። ምክክር ሲባል የጋራ መፍትሔ ፍለጋ ላይ ያተኮረ የሐሳብ ልውውጡ ነው። በዚህ መልኩ የሚደረግ መመካከር ያማረ ውጤት ይኖረዋል። ውጤታማነቱ ደግሞ ዘላቂ ሰላም እንዲኖር የሚያስችል ሀገራዊ አውድ ተፈጠረ ማለት ነው ፤ ይህ ደግሞ ለምንፈልገው ልማታችን አልፋና ኦሜጋ ነው ። ከዚህም ባለፈ ቅቡልነት ያለው አገረ መንግስት ለመገንባትም ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።

ስለሀገራዊ ዘላቂ ሰላም ፤ ብሄራዊ ምክክሩን በቀና መንፈስ ማካሄድ ወሳኝ ነው ፤ ለዚህ ደግሞ ከእኛ ከዋንኛዎቹ ባለጉዳዮች /ከዜጎች የሚጠበቀው ብዙ ነው። ከሁሉም በላይ የእኛን ቅንነት ለእውነትና ለሃቅ መቆምን የሚጠይቅ ነው።

ሰላም ለአንድ ሀገርና ህዝብ ካለው ሁለንተናዊ አስተዋጽኦ አንጻር፤ ሀገራዊ ሰላማችንን ለማጽናት ባለን አቅም ሁሉ ልንተጋ ይገባል። እልህ ከመጋባት ወጥተን አንዳችን ለሌላችን ምርኩዝ መሆን ይጠበቅብናል። በደል ቆጣሪ ከመሆን ወጥተን ይቅር ባይ ልንሆን ይገባል። ቂም ገዝግዞ የሚጥል ነቀርሳ ነው። የቂም ነቀርሳ ሊታከም የሚችለው ይቅር በመባባል ብቻ ነው ለዚህ ደግሞ ሁሌም ዝግጁ እንሁን።

ለሰላም ዝቅ እንበል። ለሰላም ዝቅ ባልን ልክ ለልጆቻችን ለልጅ ልጆቻችን የምናስቀምጣት አገር ከቂም በቀል የጸዳች የለማችና የበለጸገች ትሆናለች። በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ብንሆን ለሰላም ዝቅ ማለት ነገ ከፍ የማለታችን ምስጢር እንደሚሆን ተረድተን እራሳችን ልናዘጋጅ ይገባል።

እንደ አንድ አገር ህዝቦች ተሳስበን ተዋደን፤ አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ ተባብለው እንድንኖር ከሁሉም በላይ ለሰላምና እርቅ ዝቅ ብለን ነጋችንን ብሩህ ማድረግ አለብን። ልጆቻችን ባወረስናቸው ችግርና መከራ ሲታመሱ የሚኖሩ ሳይሆኑ፣ ባስቀመጥንላቸው በጎ ነገር እየኮሩ እሱን እያስቀጠሉ ሰላማዊ አገር የሚመሩ እንዲሆኑ ሁላችንም ስለ ሰላም በኃላፊነት መንፈስ እንቀሳቀስ ።

 ወጋሶ

 አዲስ ዘመን መስከረም 22/2016

Recommended For You