በተያዘው የኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመት የቀናት ልዩነት ሶስተኛው የዓለም ክብረወሰን በሴቶች የአንድ ማይል ውድድር ተመዝግቧል። በቡዳፔስቱ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በ1ቨሺ500 ሜትር የብር ሜዳሊያ በማጥለቅ በርቀቱ ያላትን ተስፋ ያሳየችው ወጣቷ አትሌት ድርቤ ወልተጂ ደግሞ የድሉ ባለቤት ናት። በላቲቪያ ሪጋ ትናንት ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው የዓለም የጎዳና ላይ ቻምፒዮና ኢትዮጵያ በሁለቱም ጾታ ሁለት የወርቅ፣ አራት የብርና አንድ የነሃስ በጥቅሉ ሰባት ሜዳሊያዎችን እንዲሁም አምስት ዲፕሎማዎችን ማስመዝገብ ችላለች።
ከዚህ ቀደም ሲካሄድ ቆይቶ የተቋረጠውን የዓለም የግማሽ ማራቶን ቻምፒዮና ጨምሮ ሌሎች ርቀቶችን በማካተት የተካሄደው ይህ ቻምፒዮና የዓለም አትሌቲክስ ከሚመራቸው ውድድሮች መካከል አንዱ ነው። ከቡዳፔስቱ የዓለም ቻምፒዮና ማግስት እንዲሁም ከፓሪሱ ኦሊምፒክ ዋዜማ በተደረገው በዚህ ውድድር ላይም በርካታ አትሌቶች ከመም ባለፈ በጎዳና ላይ ውድድሮች ያላቸው ብቃትም የተፈተነበት ሆኗል። በጥቅሉ በ 13 አትሌቶች የተወከለው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድንም ከኬንያ ቀጥሎ ስኬታማ በመሆን አጠናቋል።
በቻምፒዮናው ከተገኙት አስደሳች ውጤቶች መካከል አንዱ የአንድ ማይል የሴቶች ውድድር ሲሆን፤ በጠንካራዋ አትሌት ድርቤ ወልተጂ አሸናፊነት ተደምድሟል። በዓለም ቻምፒዮናው ቀድሞ ከምትታወቅበት የ800 ሜትር ርቀት ውጪ በ1 ሺ500 ሜትር የተካፈለችው ድርቤ ባልተጠበቀ ሁኔታ የዓለም ክብረወሰን ባለቤቷን አትሌት በመፎካከር እንዲሁም በርቀቱ ልምድ ያላቸውን በመርታት የብር ሜዳሊያ ማጥለቋ የሚታወስ ነው። የ21 ዓመቷ አትሌት በቅርቡ በተካሄደው የዳይመንድ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር ላይም በተመሳሳይ ከኬንያዊቷ አትሌት ጋር በመፎካከር ሁለተኛ ብትሆንም፤ በጎዳና ላይ ውድድር ግን ልትረታ አልቻለችም።
በዚህም 4:20.98 በሆነ ሰዓት ርቀቱን በመሸፈን ካጠለቀችው የወርቅ ሜዳሊያ ባሻገር የዓለም ክብረወሰንንም ሰብራለች። አትሌቷ ከውድድሩ በኋላም ‹‹እዚህ የመጣሁት አሸናፊ ለመሆን፣ ታሪክ ለማጻፍ እንዲሁም ተተኪውን የአትሌቲክስ ትውልድ ለማነሳሳት ነው። የርቀቱ መጨረሻ ላይ ያለውን መስመር ስመለከት ኪፕዬጎንን መፋለም እንዳለብኝ ወሰንኩ፤ ነገር ግን አትሌቷ እንደተዳከመች ተረዳሁ። ስለዚህም በቀላሉ ማሸነፍ ቻልኩ›› ማለቷን ሮይተርስ ዘግቧል። ድርቤን ተከትላም ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ 4:23.06 በሆነ ሰዓት በመግባት ለሀገሯ የብር ሜዳሊያ እንዲሁም የግሏን ፈጣን ሰዓት አስመዝግባለች።
ሌላኛው ኢትዮጵያ የወርቅና የብር ሜዳሊያዎችን ያስመዘገበችበት ውድድር የወንዶች 5 ኪሎ ሜትር ሲሆን፤ አትሌት ሃጎስ ገብረህይወት እና ዮሚፍ ቀጄልቻ ተከታትለው ገብተዋል። በቡዳፔስቱ የዓለም ቻምፒዮና ሀገራቸውን በ5ሺ ሜትር ወክለው ውጤታማ መሆን ያልቻሉት ሁለቱ አትሌቶች በሌላኛው ቻምፒዮና ለኢትዮጵያ ሜዳሊያ አስመዝግበዋል። ከ10 ዓመታት በፊት ከ20 ዓመት በታች ቻምፒዮና የነበረው አትሌት ሃጎስ ከረጅም ጊዜ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው የዓለም የጎዳና ላይ ቻምፒዮና ኢትዮጵያን በድጋሚ አስጠርቷል። የ29 ዓመቱ አትሌት ርቀቱን ለመሸፈን 12:59 የሆነ ሰዓትም ፈጅቶበታል።
አትሌቱ ከሩጫው በኋላ ከዓለም አትሌቲክስ ጋር በነበረው ቆይታም ‹‹እዚህ የመጣሁት ቡዳፔስትን እያሰብኩ ነው። በወቅቱ ታምሜ ስለነበር ጥሩ መሮጥ አልቻልኩም ነበር፤ ስለዚህም አሸናፊ በመሆኔ እጅግ ኮርቻለሁ። በመጀመሪያው ቻምፒዮና በመሆኑም ለራሴና ለሀገሬ ታሪካዊ ውድድር ነው›› ብሏል። በቡዳፔስት የነበረው የአየር ሁኔታ እጅግ ሞቃታማ ሲሆን፤ ሪጋ ደግሞ በመጠኑ ከኢትዮጵያ ጋር ተቀራራቢ መሆኑ እንደረዳውም አትሌቱ አክሏል። በኦሪጎኑ ዳይመንድ ሊግ በ3ሺ ሜትር የብር ሜዳሊያ ባለቤት የነበረው አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ ደግሞ የቡድን አጋሩን ተከትሎ 13:02 በሆነ ሰዓት ውድድሩን ፈጽሟል።
በ5 ኪሎ ሜትር የሴቶች ውድድርም ከፍተኛ ፉክክር ያደረጉት ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች በኬንያውያኑ ሊቀደሙ ችለዋል። በዚህም በቡዳፔስት የ 10 ሺ ሜትር የነሃስ ሜዳሊያ ባለቤቷ አትሌት እጅጋየሁ ታዬ በ 14፡40 ሶስተኛ በመሆን የነሃስ ሜዳሊያውን ወስዳለች። አትሌት መዲና ኢሳ ደግሞ 4ኛ ደረጃን ይዛለች።
በግማሽ ማራቶን ውድድር በሁለቱም ፆታ ኬንያውያን ከአንድ እስከ ሶስት በማጠናቀቅ የበላይነቱን ይዘዋል። በወንዶች ጀማል ይመር በ59:22 ሰዓት 4ኛ፣ ንብረት መላክ በ 1:00:11 ሰዓት 7ኛ፣ ፀጋዬ ኪዳኑ በ 1:00:21 ሰዓት 10ኛ ሆነው ያጠናቀቁ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው። በተመሳሳይ በሴቶች ጽጌ ገ/ሰላማ በ1:07:50 4ኛ፣ፍታው ዘርዬ በ1:08:31 6ኛ፣ ያለምጌጥ ያረጋል በ1:11:34 28ኛ ደረጃ በመያዝ ጨርሰዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 21 ቀን 2016 ዓ.ም