አዲስ አበባ፡– በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወነ ያለው የከተማ ግብር ሥራ ለሌሎችም ከተሞች ተምሳሌት የሚሆን መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ የእንስሳት ልማትና ልህቀት ማዕከል ኃላፊ ፀጋ ለማ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የማዕከሉ ኃላፊ ፀጋ ለማ(ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ቀደም ባሉት ዓመታት ለከተማ ግብርና ይሰጥ የነበረው ግምት ዝቅተኛ መሆን የሚፈለገው ውጤት እንዳይገኝ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል፡፡ አሁን ላይ ይህ አመለካከት እየተቀረፈ በመምጣቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማ ግብርና ስራ በሌሎችም ከተሞች ተምሳሌት የሚሆን ሥራ እየተሠራ ይገኛል፡፡
ያለንን አቅም በአግባቡ ጥቅም ላይ ባለማዋላችን በእንስሳት ተዋጽኦ ዋጋ መናር ማህበረሰቡ ሲፈተን መቆየቱን አስታውሰው፤ እንደ ሀገር ለከተማ ግብርና በተሰጠው ትኩረት እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ጥሩ ውጤት እያስገኙ ነው፡፡ ይህም ገበያው እንዲረጋጋ በማድረግ የነዋሪውን የኑሮ ጫና ከማቅለል አንጻር ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል ብለዋል፡፡
በማህበረሰቡ ዘንድ ከእንስሳት እርባታ ጋር በተያያዘ የተዛባ አስተሳሰብ እንደነበር አስታውሰው፤ በተሠራው የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ከዚህ በፊት የነበሩ አመለካከቶች ተቀይረው አሁን ላይ በርካታ ዜጎች ሥራው ላይ ተሠማርተው እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በከተማ ግብርና ለሌሎችም ከተሞች ምሳሌ የሚሆን ሥራ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ የራስን የምግብ ፍላጎት ከማሟላት አልፎ ወደ ገበያ በማቅረብ ለገበያ መረጋጋት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የከተማ ግብርና በአነስተኛ ቦታ መከናወን የሚችል መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር ፀጋ፤በልማት የሚነሱ አርሶ አደሮች፣ ወጣቶች እና የቤት እመቤቶች እየተደራጁ በአነስተኛ ቦታዎች ላይ ከተማ ግብርናን እየሠሩ ውጤታማ መሆን ችለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የሥራ እድል ፈጠራ ሥራዎች በአምራች ዘርፉ ላይ ትኩረት ያደርጉ እንደነበሩ አስታውሰው፤ አሁን ላይ የከተማ ግብርና የብዙዎች የሥራ እድል እና የሀብት ምንጭ መሆን መቻሉንም ገልጸዋል፡፡
የዘርፉን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በመንግሥት በኩል ሥራውን በቴክኖሎጂ የመደገፍና የምርጥ ዘር አቅርቦት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይነትም ከግብዓት አቅርቦትና በተለይም ከእንስሳት መኖ ዋጋ መናር ጋር ተያያዞ የሚነሱ ችግሮችን ለመቅረፍ በትኩረት እንደሚሠራ ኃላፊው ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ኅዳር 10 ቀን 2017 ዓ.ም