አዲስ አበባ፡– የሆቴልና መሰል ተቋማት የባለሙያዎች አለባበስ ደንብ በአግባቡ ተፈጻሚ እንዲሆን የጋራ ኃላፊነት ያስፈልጋል ሲሉ የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ (ዶ/ር) ሂሩት ካሳው ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነ ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ በሆቴልና መሰል ተቋማት ባለሙያዎች አለባበስ እና የመዋቢያ ጌጣጌጥ አጠቃቀም ደንብ አፈፃፀም ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትናንትናው እለት ተወያይቷል፡፡
የቢሮው ኃላፊ ሂሩት ካሳው (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፤ በሆቴልና መሰል ተቋማት የባለሙያዎች አለባበስ ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ የማህበረሰቡ እንዲሁም የውጭ ጎብኚዎች አጀንዳና ጥያቄ ሆኖ ቆይቷል። በዚህም ከተማ አስተዳደሩ ከፍትህ ቢሮ ጋር እንዲሁም ከተለያዩ የሆቴል ማህበራት ጋር በመሆን ደንቡ እንዲፀድቅ ተደርጓል።
በሆቴልና መሰል ተቋማት ባለሙያዎች አለባበስ እና የመዋቢያ ጌጣጌጥ አጠቃቀም ደንብ ወደ ትግበራ ሲገባ በቂ የሆነ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እንደሚሰራ ገልጸው፤ ደንቡ በአግባቡ ተፈጻሚ እንዲሆን የጋራ ኃላፊነት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ደንቡ ዓለም አቀፍ መስፈርት (ስታንዳርድ) ላይ መሰረት ያደረገና ሙሉ በሙሉ ባህላችንን የሚጠብቅ መሆኑንም ገልጸዋል።
ደንቡን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት የሆቴልና ቱሪዝም አገልግሎት ሰጪዎች አገልግሎት ምደባ ቡድን መሪ አቶ አምደ ማርያም ማሞ በበኩላቸው፤ በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ ለሚሰሩ ባለሙያዎች ወጥ የሆነ የአለባበስ፣ የጌጣጌጥ እና የመዋቢያ አጠቃቀም ሥርዓት በመዘርጋት የሀገር ባልህና እሴት እንዲጠበቅ ለማድረግ ደንቡ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል በዘርፉ ተሰማርተው የሚሰሩ ሙያተኞች ሊደርስባቸው ከሚችለው አካላዊ፣ ሥነልቦናዊ ጫና እና አላስፈላጊ ጥቃቶችን ለመከላከል የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ሆቴል ማኔጅመንት አሶሴሽን ጸሐፊ አቶ በሱፍቃድ ደባይ እንደገለጹት፤ በአዲስ አበባ በአሁኑ ጊዜ ዓለም አቀፍ መድረኮችን የምታዘጋጅ ከተማ ሆናለች፡፡ በዚህም ሆቴሎች እንዲሁም መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሀገርን ገጽታ በሚገነባ መልኩ እንግዶችን ማስተናገድ ይኖርባቸዋል፡፡
ለዚህም የወጣው ደንብ የትኛውም አገልግሎት የሚሰጥ አካል ሥርዓትን የጠበቀና ኢትዮጵያዊነትን የሚያንጸባርቅ አለባበስና አጋጌጥ እንዲኖር የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡
ደንቡ የሀገር ባህልና እሴት እንዲጠበቅ ከማድረግ አንጻር ተስፋ ሰጪ ነው ያሉት አቶ በሱፍቃድ፤ ሆኖም ተፈጻሚነቱ ላይ ሁሉም አካል ጠንክሮ መስራት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
ዳግማዊት አበበ
አዲስ ዘመን ኅዳር 10 ቀን 2017 ዓ.ም