“ ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግና ኢኖቬሽንን ማስፋፋት ወሳኝ ነው ” – ሙፈሪሃት ካሚል የሥራና ክህሎት ሚኒስትር

አዲስ አበባ:- የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ ኢንተርፕሪነሽፕና ኢኖቬሽንን ማስፋፋት ወሳኝ ነው ሲሉ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።

16ኛው የዓለም ኢንተርፕረነርሺፕ ሳምንት በኢትዮጵያ “ኢንተርፕረነርሺፕ ለሁሉም” በሚል መሪ ሃሳብ ትናንት መካሄድ ጀምሯል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ ኢንተርፕሪነሽፕና ኢኖቬሽንን ማስፋ ፋት ወሳኝ ነው።

ኢንተርፕረነርሺፕ የዜጎችን፣ የተቋማትን፣ የሀገርንና የዓለምን ታሪክ የሚቀይር በመሆኑ ለሁሉም ተደራሽ የምናደርገው እና ዓመቱን ሙሉ የምንሰራበት ተግባር ነው ብለዋል።

ኢንተርፕሪነርሽፕና ኢኖቬሽን የዘመናችን ሁነኛ የልማት መሳሪያዎች ናቸው ያሉት ሚኒስትሯ፤ ለኢትዮጵያ የሚሆን የኢንተርፕረነርሺፕና የኢኖ ቬሽን ስነ ምህዳር ለመፍጠር በትብብር መስራት እንደሚገባም አስታውቀዋል።

ኢንተርፕረነርሺፕ ለሀገር ኢኮኖሚ ከሚያ በረክተው አስተዋጽኦ ባለፈ ከዓለም ሀገራት ጋር የሚያስተሳስረን ቁልፍ ዘርፍ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

እውቀትና ፈጠራ መር የሆነ ኢኮኖሚ ለመገንባት ኢንተርፕረነርሽፕ ተቋማዊ መልክ ይዞ እንዲሄድ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አቅጣጫ መሰጠቱን አስታውሰው፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዘርፉ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተሰሩት ስራዎች ትልቅ መነቃቃት መፈጠሩን ገልጸው፤ በአንድ ጊዜ ሶስት ሺህ የሚደርሱ ዜጎች የፈጠራ ሀሳብ ውድድር እያደረጉ መሆኑን አስረድተዋል።

በሌላ በኩል ዓለም አቀፉ የአንተርፕሪነርሺፕ ሳምንት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴርና የኢንተርፕ ሪነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት ከሌሎች አጋር ተቋማት ጋር በመተባበር በግንዛቤ ማስጨበጫና መረጃ ሰጪ በሆኑ የተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚያከብሩት አመላክተዋል።

የአንተርፕሪነርሺፕ ሳምንቱ ስራ ፈጣሪዎችን፣ ባለሀብቶችን፣ የፖሊሲ አውጪዎችን፣ ተመራማ ሪዎችን፣ ደጋፊ ድርጅቶችን እና ሌሎች የምጣኔ ሀብትና ፈጠራ ስራን ለማሻሻል ድጋፍ የሚያደርጉ ተባባሪ አካላትን የሚያሳትፍ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የኢንተርፕረነርሺፕ ሳምንት በፖለቲካና ኢኮኖሚ ያደገች እና የተለወጠች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ያግዛል።

ኢንተርፕረነርሺፕ ለሀገር እድገት ወሳኝ መሆኑን ካደጉት ሀገራት መማር ይቻላል ያሉት ሚኒስትሩ፤ መንግሥትም ለዘርፉ ምቹ ምህዳርን ለመፍጠር እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

ስራ ፈጣሪዎችን የሚያበረታታ እና የፈጠራ ሃሳባቸውን ወደ ተግባር መቀየር የሚያስችል የፖሊሲ ማሕቀፍ መዘርጋት እንደሚገባም አስታውቀዋል።

ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን ኅዳር 10 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You