ሀገራዊ ችግሮችን በምክክር ለመፍታት የምሁራን ድርሻ

ምሁራን በማስተማር፣ጥናትና ምርምር በማፍለቅ ለሀገር ግንባታ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው፡፡በተለይ ሀገራዊ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት መፍትሄ እንዲያገኙ መስራት ከእነሱ የሚጠበቅ ትልቅ ኃላፊነት ነው፡፡ ለሰላምና ለልማት እንቅፋት የሆኑ ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠርና የሚፈለገውን ዕድገት ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ግንባር ቀደም ሚና እንዳላቸውም ይገለጻል።

በኢትዮጵያ ለግጭት የሚዳርጓትንና ያለ መግባባታችን መንስኤ የሆኑትን ልዩነቶችን በምክክር ለመፍታት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በርካታ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡ ኮሚሽኑ ችግሮችን በምክክር ለመፍታት በዘጠኝ ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ባደረገው የአጀንዳ ማሰባሰብና የምክክር መድረክ ከ105 ሺህ በላይ ማህበረሰቦች መሳተፍ መቻላቸውን የኮሚሽኑ መረጃ ያመለክታል፡፡

ከማህበረሰቡ የሚሰበሰቡ አጀንዳዎችም ትልቅ ትምህርት የሚሰጡ፤ ለሀገራዊ መግባባትና ዘላቂ ሰላም ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ ናቸው ብሏል፡፡ በእነዚህ የምክክር መድረኮችም የምሁራን ተሳትፎ ጉልህ መሆኑን ይገልጻል፡፡

ዘላቂ ሰላም ለማስፈን፣ ሀገራዊ መግባባትን ለማምጣትና አንድነትን ለማጠናከር የማህበረሰቡ ሚና እንዳለ ሆኖ የምሁራን ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ምሁራን በምርምራቸው፣ በመፍትሔ አፍላቂነታቸው፣ በእውቀታቸው፣ ሀገርን የሚጎዱ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት ሁነኛ መፍትሄ ለማምጣት ትልቅ አቅም

አላቸው፡፡ ሰሞኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የምሁራን ሀሳብ በአጀንዳ ማሰባሰቡና በምክክር መድረኩ ለማካተትና የሚጨበጥ ውጤት ለማምጣት ህዳር 6 ቀን 2017 ዓ.ም ከ56 ዩኒቨርሲቲዎች ከተውጣጡ ሊሂቃንና የተማሪ ተወካዮች ጋር ምክክር አድርጓል፡፡

ሀገራዊ መግባባትን ለማምጣት ሰላማዊ፣ ሀገር ወዳድ፣ ምክንያታዊ ትውልድ ማፍራት፣ የተሳሳተ ትርክትን ማረም አስፈራጊ ነው፡፡ ሰላማዊ፣ ሀገር ወዳድ፣ምክንያታዊ ትውልድ ለማፍራትም ሆነ የተሳሳተ ትርክትን ለማረም ደግሞ ምሁራን ያላቸው ሚና ትልቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የሚስተዋለውን አለመግባባትና ግጭት ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኘ ለማድረግ የምክክር ኮሚሽኑ እየሰራ ባለው ስራ ምሁራን ምን ዕይታ አላቸው? ሀገሪቱ እየገጠማት ያለውን ችግር ለመፍታትስ የምሁራን ሚና ምንድ ነው? በሚሏቸው ጉዳዮች ምሁራን አስተያየታቸውን ሰጥተውናል፡፡

የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የጽህፈት ቤት ኃላፊ መለሰ ጥፉ፤ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተቋቋሙ ጀምሮ ሀገራዊ መግባባትን ለማምጣት በርካታ ስራዎችን ሰርቷል፤ አሁንም እየሰራም ነው፤ ግጭትና አለመግባባት እያመጡ ያሉ ጉዳዮችን ነቅሶ ለማውጣት ታች ወርዶ ከማህበረሰቡ ጋር እያደረገ ያለው ውይይት የሚበረታታ ነው ይላሉ፡፡

ከሚሽኑ ለሀገር ሰላምና እንቅፋት ፀር የሆኑ ችግሮችን ነቅሶ ለማውጣትና ሰላምን ለማምጣት ከዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ ከመምህራን፣ ከሰራተኞች፣ ከተማሪዎችና ከማህበረሰቡ ጋር በርካታ ውይይቶችን አድርጓል፤ ውይይቱም ቀድመው የነበሩ አሉታዊ ትርክቶችን በማረምና የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ የሚያስችል መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

በሀገር ደረጃ የሚደረግ ምክክር በርካታ ችግሮችን ወደ አንድ አምጥቶ፤ የጋራ አጀንዳን ለመቅረፅ፣ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ያስችላል፤ መልካም ውጤትም ያመጣል ነው ያሉት፡፡

ምክክር የጋራ ችግርን ወደ ጋራ ሃሳብ ለማምጣትና ለተግዳሮቶች የጋራ መፍትሔ በመስጠት በሰላምና በአንድነትን ለመኖር ትልቅ ጥቅም አለው የሚሉት ምሁሩ፤ የጋራ መፍትሔ ለማምጣትም በኢትዮጵያ ምክክር እየተደረገ ነው ሲሉ ይናገራሉ፡፡

ሀገራዊ መግባባትን ለማምጣት ምሁራንና መምህራን ልዩነትን ያመጡ ነገሮች ምንድናቸው ብለው ሰፊ ጥናት የማድረግ፣ ልዩነቶች ሰፍተው ችግሮች እንዳይባባሱ መፍትሔ የመስጠት ኃላፊነት አለባቸው ያሉት አቶ መለሰ፤ ምሁራን ትውልድን በስነ- ምግባር በማነፅ፤ ማህበረሰብን በመልካምነት በማገልገልና ምርምር በመስራት ምክክሩን እውን የማድረግ ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የዋና ዳሬክተር ጽህፈት ቤት ኃላፊ መለሰ አምሽጎ በበኩላቸው፤ ኮሚሽኑ እየሰራ ያለው ስራ የኢትዮጵያን አንድነት ለማምጣት ተስፋ የሚሰጥ ነው፡፡ ሀገራዊ ምክክሩ ተጠናክሮ ከቀጠለ የቀድሞው የህዝብ አንድነት ተመልሶ ይመጣል፤ ባህልንና ሃይማኖትን አክብረን ከሄድን ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን ማምጣት እንችላለን፤ አንድነትን ለማምጣት እየተደረገ ያለው ምክክር የሚበረታታና መልካም ውጤት ለማግኘት ተስፋ የሚጭር ነው ይላሉ፡፡

ምክክር ኮሚሽኑ እየሰራ ያለው ስራ ባህልን ከባህል፤ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር አስታርቆ ዘላቂ ሰላምን ማምጣት የሚያስችል መሆኑን ገልጸው፤ይህን ከማሳካት አኳያ ምሁራን ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው፤ ሀገሪቱ እየገጠማት ያሉ ችግሮችን ፈትቶ አንድነትን ለማምጣት ተማሪዎች ሀገራዊ ፍቅር እንዲኖራቸው አድርጎ የማስተማር፤ ሕዝብን በአንድነትና በእኩልነት የሚመራ ትውልድ የማፍራት፣ ችግሮችን በምርምር የመለየት፣ ለተለዩ ችግሮች ሁነኛ መፍትሔ የመስጠት ግዴታ አለባቸው ሲሉ ይጠቅሳሉ፡፡

ሀገርን የሚመራ ምሁር ነው፡፡ ሀገርን የሚመራ ምሁር የሚወጣው ከዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ከዚህ መነሻነት የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተማሪዎች ሀገር የሚወዱ ጥሩ ዜጋ ሆነው እንዲወጡ የማድረግ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት፡፡

በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን መወያየት፣ መመካከር፣ ሀሳብ መለዋወጥና የጋራ መግባባት ላይ መድረስ አስፈላጊ ነው፡፡ የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስም የምክክር ኮሚሽኑ እየሰራ ያለው ስራ የሚበረታታ ነው ሲሉ የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ መምህር ፈሪያ ሀሰን (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡

ዜጎች በፍቅርና በአንድነት እንዲኖሩ ለማድረግ የምሁራን ሚና ከፍተኛ ነው፤ እኛ ምሁራን ለግጭት የዳረጉንን አለመግባባቶች በመለየት ለችግሮቹ መፍትሔ የመስጠት ኃላፊነት አለብን፤ ይህን ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል ሲሉ ነው የገለጹት፡፡

ሀገራዊ አንድነትን ለማምጣት ግጭት ያለባቸውን ክልሎች በምክክሩ የማካተትና የማሳተፍ ስራ ሊሰራ ይገባል፤ ሁሉን ያሳተፈ ምክክር በማድረግ ሀገርን ወደ አንድነት የማምጣት ስራ መስራት አስፈላጊ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡

ሀገራዊ መግባባትን ለማምጣት ምሁራን ተማሪዎችን የማስተማር፣ የሀሳብና የልምድ ለውውጥ ማድረግ ሚናቸውን የመጫወት፣ የሃይማኖት አባቶች ምዕመናንን የማስተማር እንዲሁም ከብሔር ብሔር ብሔረሰቦች የተወጣጡ ማህበረሰቦችን ስለሰላም በማሰልጠን በአካባቢያቸው የሚገኙትን ሰዎች እንዲያስተምሩ የማድረግ ስራ ልንሰራ ይገባል ሲሉ ነው ያመለከቱት፡፡

ሀገራዊ ምክክሮችን በማድረግ አዲስ ያደገና የተለወጠ ሥርዓት ባለቤት ለመሆንና በዜጎች መካከል የተሻለ ማህበራዊ ግንኙነት እንዲኖር ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር፤ እንዲሁም ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታትና ውይይትን ባህል ያደረገ ችግር አፈታት እንዲዳብር ምሁራን ጉልህ ድርሻ አላቸው፡፡ ይህን ሚናቸውን ከተወጡም የሚፈለገውን ዘላቂ ሰላምና ልማት ማምጣት ቀላል እንደሚሆን ብዙዎች ይስማማሉ፡፡

ታደሠ ብናልፈው

አዲስ ዘመን ኅዳር 10 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You