ባዛሩ ለዕደ ጥበብ ውጤቶች የገበያ ትስስር የሚፈጥር ነው

አዲስ አበባ፡የንግድ ትርዒቱና ባዛሩ የሀገር ውስጥ ምርታማነትን የሚያሳድግ፣ ለዕደ ጥበብ ውጤቶች የገበያ ትስስር የሚፈጥር መሆኑ ተገለጸ።

በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ‹‹ሀገራዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት›› በሚል መሪ ቃል የ19ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን የተመለከተ የንግድ ትርዒትና ባዛር እየተካሄደ ነው።

የንግድ ትርዒትና ባዛሩን በንግግር የከፈቱት የአዲስ አበባ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ቡዜና አልከድር፤ የ19ኛውን የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን አስመልክቶ የተዘጋጀው የንግድ ትርዒትና ባዛር የሀገር ውስጥ ምርትና ምርታማነት የሚያሳድግ፤ ለዕደ ጥበብ ውጤቶችም የገበያ ትስስር የሚፈጥር ነው።

የንግድ ትርዒቱና ባዛሩ በመንግሥት አነሳሽነትና አስተባባሪነት የተደረገ እንደሆነ የገለጹት አፈጉባኤ ቡዜና፤ ወጣቶች የፈጠራ እውቀትና ክህሎታቸውን ተጠቅመው ያመረቷቸው ልዩ ልዩ ምርቶችንና የዕደጥበብ ውጤቶችን ለተጠቃሚ ማህበረሰብ በማስተዋወቅ የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው እድል የሚሰጥ ነው ብለዋል።

19ኛውን የብሔር፣ ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን ቀን አስመልክቶ የተዘጋጀው የንግድ ትርዒትና ባዛር ኢትዮጵያ ያላትን ብዝሀ ፀጋ እንድታለማ፤ የሀገር ውስጥ ምርትና ምርታማነትን እንድታሳድግ እንዲሁም ለዕደ ጥበብ ውጤቶች የገበያ ትስስር እንዲፈጠር የሚያበረታታ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የንግድ ትርዒቱና ባዛሩ ባህልን ከማስተዋወቅ ባለፈ የተለያዩ እሴቶችን በመጨመር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማሳለጥ ከፍተኛ የሆነ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን አመልክተው፤ የባህል፣ የቁስና የመንፈሳዊ ፀጋዎችን በማልማት፣ ቱሪዝሙን በማስፋፋትና ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር ሀገራዊ ኢኮኖሚን ለማሳደግ እየተሰራ ነው ሲሉ አብራርተዋል።

ባዛሩ ስራ ፈላጊዎችና ፈጣሪዎች ልምድ እንዲለዋወጡ፤ አዳዲስ ሃሳቦች እንዲያመነጩ የሚያነሳሳና ኢንቨስትመንት ለመሳብ ትልቅ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።

የኢንዱስትሪው ዘርፍ በማልማት ከመስኩ የሚገኘውን ገቢ ማግኘት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው፤ ከዘርፉ መገኘት የሚገባውን ጥቅም ለማግኘትም የለውጡ መንግሥት እየሰራበት ይገኛል ሲሉ ጠቁመዋል።

ቋንቋዎች፣ ሃይማኖቶች፣ ባህሎች የሀገር ምንዳዎች ናቸው፤ የሀገር ምንዳ የሆኑ የብዝሃ ፀጋዎችን አልምቶ ሁለተናዊ እድገትን በማረጋገጥ ሁሉንም ማንነቶች ያቀፈ እውነተኛ ህብረ ብሔራዊ ሥርዓት መገንባት አስፈላጊ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ቱሪዝም ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶሚ አበበ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን ለማክበር ከሚከወኑ ክንዋኔዎች ውስጥ የንግድ ትርዒትና ባዛር አንዱ ነው፤ በክንዋኔውም ኢንዱስትሪያኒስቶች፤ ኢንተርፕራይዞች፣ የሀገር ውስጥ ምርቶችንና የዕደጥበብ ምርቶችን ከተጠቃሚ ማህበረሰቡ ጋር ይተዋወቃሉ።

19ኛውን የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ምክንያት በማድረግ እየተካሄደ ያለው የንግድ ትርዒትና ባዛር የሀገር ውስጥ ምርቶችን በሚፈለገው ልክ እንዲያድጉ የሚያበረታቱበት፣ የዕደጥበብ ውጤቶች ለገበያ የሚተዋወቁበት ነው ብለዋል።

19ኛውን የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል እየተካሄደ ባለው የንግድ ትርዒትና ባዛር 150 ተሳታፊዎች እየተሳተፉ እንደሚገኝ ታውቋል።

ታደሠ ብናልፈው

አዲስ ዘመን ኅዳር 10 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You