ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በተስፋ እና በፈተና መካከል ትገኛለች፡፡ በአንድ በኩል የነገውን ብሩህ ጊዜ ማጣጣም የሚያስችል ጥርጊያ መንገዷን እያበጃጀች ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የእርስ በእርስ ግጭቱና አለመግባባቱ እየጎነታተላት ነው፡፡ በእርግጥ አገሪቱ በዚሁ ሁሉ ውስጥ ታላቅ ተስፋ የሰነቀችበትን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን አራተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በድል ማጠናቀቅ ችላለች፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ወደስራ የገባው አገራዊ የምክክር ኮሚሽንም ፈተና የሆነባትን ጉዳይ እልባት ይሰጣታል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ ከእነዚህ ሁለት አንኳር ጉዳዮች ጋር አያይዘን ከታሪክ ምሁሩ ከዶክተር አየለ በክሪ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ አራተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ጋር ተያይዞ በግብጽ በኩል የሚታየው ተግዳሮት እንደ አንድ የታሪክ ምሑር እንዴት ያዩታል?
ዶክተር አየለ፡- በግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አማካይነት ከሰሞኑ የወጣውን መግለጫ አንብቤዋለሁ:: ነገር ግን በኢትዮጵያ በኩል እየተከናወነ ያለው ተግባር እኤአ በ2015 የተፈረመውን የመርህ ስምምነት የጣሰ አይደለም:: ሊጣስም አይችልም:: በዛ መርህ ውስጥ ኢትዮጵያ የገነባችውን ግድብ ውሃ እንዳትሞላ የሚከለክል አንቀጽ የለም:: ይህ ሆኖ እያለ የግብጽ አቋም እያመላከተ ያለው እሷ ተበዳይ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ በዳይ ተደርጋ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲታይ ለማድረግ ነው::
ግብጾች በ1959 እኤአ 55 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ለራሳቸው ሲያደርጉ እና ለሱዳን ደግሞ 18 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ሲሰጡ ኢትዮጵያን ይመለከትሻል ብለው አላማከሩም:: ከዚህ አኳያ እንዲያውም በታሪክ የተናጠል እርምጃ የወሰደች አገር ብትኖር ግብጽ ናት ማለት ይቻላል:: ከዚህ ሌላ ግብጽ የአስዋንን ግድብ ስትገነባ ኢትዮጵያን አላማከረቻትም:: በወቅቱ ያሉት እነዚህና መሰል ሁኔታዎች ሲጤኑ ግብጽ እያደረገች የነበረው ውሃውን የምትጠቀመው ሙሉ ለሙሉ ማለት በሚያስደፍር መልኩ በሞኖፖሊ ነው:: ወይም ደግሞ አንድ አገር ሌላውን በሚቆጣጠርበት አይነት መንገድ (Hegemonic) ነው::
በዚህ አይነት ግብጽ የለመደችው ውሃውን በባለቤትነት እና የራሷ ብቻ አድርጋ በምታስብበት መንገድ መጠቀምን ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ኢትዮጵያ ሚዛናዊ እና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ልጠቀም ማለቷ ሊዋጥላት አልቻለም:: ምክንያቱም ይህ ሁኔታዋ የሚያሳየው እርሷ በዚያ በቅኝ አገዛዝ ዘመን የነበራት ብርታት አሁንም አለኝ በሚል ሙጭጭ ማለቷን ነው::
የኢትዮጵያ ውሃውን መጠቀም ማንንም የሚጎዳ አይደለም:: ይልቁኑ ግብጽንም ጨምሮ ሌላውን የሚጠቅም ነው:: ለአብነት ያህል አንደኛ ጥቅም ውሃው መደበኛ የሆነ ፍሰቱን ይዞ እንዲጓዝ ያስችለዋል:: ሁለተኛው ደግሞ የደለል ችግር እንዳይፈጠር መልካም ሁኔታን ይፈጥራል:: በዚህ አግባብ የተሻለ እና የበለጠው ውሃ እንዲደርሳቸው የራሱን ሚና ይጫወታል ማለት ነው:: ይህ በመሆኑ ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለው እንቅስቃሴ በምንም አይነት መመዘኛ እነርሱን የሚጎዳ ግንባታ እና ውሃ ሙሌት አይደለም::
ነገር ግን አንድ ነገር ልብ ሊባል ይገባል፤ ይኸውም እኛ ሁሌ የእነርሱን ሙግት በማስተባበል እና ስለእነርሱ በመከራከር ጊዜ ማጥፋት የለብንም:: የዓባይን ውሃ ለልማታችን ምቹ ነው በሚያስብለን መንገድ ሁሉ መጠቀም መቻል አለብን:: እንደሚታወቀው ግድቡ የመሰረት ድንጋይ ሲቀመጥለት በደመነፍስ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መንገድ እቅድ ተነድፎለት ነው:: ጠቅላላ የአባይ ግድብ የሚይዘው የውሃ መጠን 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ሲሆን የግብጹን የአስዋን ግድብ የያዘው የውሃ መጠን ግን 162 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ነው:: ስለሆነም በእኛ በኩል እየተገነባ ያለው ግድብ ጥቅም እንጂ ጉዳት የሚያስከትልባቸው አይሆንም::
እንደሚታወቀው ደግሞ ግብጾች በአሁኑ ወቅት ለሕዝባቸው የኤሌክትሪክ ኃይል መቶ በመቶ አዳርሰዋል ማለት ይቻላል:: ወደ እኛ ሲመጣ ግን በመቶኛ ሲሰላ በጣም አነስተኛ እንዲያውም የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያገኘው ሕዝብ ከግማሽ በታች ነው:: በሌላ በኩል ደግሞ የእኛ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በሕዝብ መዋጮ የተሰራ የሕዝብ ግድብ ነው:: ስለሆነም ብዥታ የሚያመጣ ቃላትን ከመጠቀም መቆጠብ የግድ ይላል ባይ ነኝ:: ከሁላችንም የሚጠበቅብን ይህን በማድረግ እና ቶሎ ግድቡን በማጠናቀቅ ላይ መረባረብ ነው::
find for sale has the mind with bravery and courage.we supply the high quality yosemitehwyherald with cheap price.አዲስ ዘመን፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ ከተጣለ ጀምሮ ሲቃወሙ ይሰማል:: በሂደትም ለውጥ አልመጣም:: ለምንድን ነው?
ዶክተር አየለ፡- …እነርሱ እኮ ታሪካዊም ተፈጥሯዊም የመጠቀም መብት አለን እኛ ነን የሚሉት ነገር አላቸው:: ነገር ግን ይህ መብት የላቸውም:: እሱ የቅኝ ገዢዎች አቋም ነው:: ለምሳሌ በእነርሱ በኩል ድርቅ እንዳጋጣሚ ቢከሰት እንኳ የያዙት ውሃ ለአስር ዓመት ያህል ዋስትና የሚሰጣቸው ነው::
እኛ ማድረግ የሚጠበቅብን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በቂያችን ነው ብለን መቀመጥ እንደሌለብን ነው:: ቀጥሎ መምጣት ያለበትን ልማት ማሰብ የግድ ይለናል:: ልክ እንደ አስዋን ግድብ ሁሉ የሕዳሴው ግድብ ውሃ ዋስትና እስኪኖረው ድረስ የበኩላችንን መስራት ይጠበቅብናል:: ኤሌክትሪክ ማመንጨት የሚያስችሉን ተርባይኖች በቂ ውሃ ሊያገኙ ያስፈልጋል:: አሁን በተያዘው ውሃ ብቻ የትም መድረስ አያስችለንም:: ከዚህ ግድብ በተጨማሪም ገና ሶስት እና አራት ግድቦችን መስራት ይጠበቅብናል:: ይህን የምናደርገው ደግሞ የራሳችንን የመልማት ፍላጎት አስልተን መሆን አለበት::
እነርሱ በእያንዳንዱ እርምጃቸው እና ንግግራቸው ታሪካዊ የሚሉት ፈሊጥ አላቸው፤ ይህንን ሲሉ ግን ልክ እኛ ታሪክ እንደሌለን ለመቁጠር አስበው ከሆነ በእጅጉ ተሳስተዋል:: ልክ እነርሱ በውሃው የመጠቀም መብት እንዳላቸው ሁሉ እኛ ደግሞ ውሃ አመንጪ አገር እንደመሆናችን የበለጠው መብት ያለን አገር መሆናችን ሊዘነጋ አይገባም::
የሚያስገርመው እስካሁን ድረስ የግብጾች አቋም አለመቀየሩ ነው:: እንዲያውም በይበልጥ የመስኖ መሬታቸውን እያስፋፉ ነው:: በረሃውንም ጭምር እያለሙ ነው:: በነገራችን ላይ ግብጽ ሁልጊዜ ውሃ የሚመጣው ከናይል ነው የሚል ሙግት ታበዛለች:: ነገር ግን ዋናው ቁምነገር ምንድነው ቢባል ግብጽ በአፈር ውስጥ ያለ ውሃ (Aquifer) አላቸው:: ይህ ሁሉ እያለ የኢትዮጵያ እድገት እና ልማት ወደፊት እንዳይቀጥል በተለያየ መንገድ ሲሰሩ ይስተዋላል::
እኛ በተለያዩ ግጭቶች ተጠምደን የሚፈለገውን ስራ እንዳንሰራ ለማድረግ እየሞከሩ ነው:: ከዚህ አካሄድ መውጣት የግድ ነው:: ዓላማችንን ማሳካት የምንችለው ከግጭት እና መሰል ከሆኑ ችግር ውስጥ በመውጣት ነው::
ከዚህ ውጭ የግድቡ ውሃ እንዳለፉት አራት ዙር የውሃ ሙሌት ከላይ መፍሰሱን ማሳየት ያቆም እንደሆን እንጂ በቀጣይም ወቅቱን ጠብቆ የሚሞላ እንደሆነ እሙን ነው:: በዚህም መንገድ የታቀደለትን 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ እስከሚይዝ ድረስ የሚቀጥል እንደሆነ ይታወቃል::
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ እና ግብጽ ታሪካዊ ቁርኝታቸው ምን ይመስላል?
ዶክተር አየለ፡– እርግጥ ነው ግብጽ የዓለም ስልጣኔ ሲነሳ ተጠቃሽ አገር መሆኗ ይታወቃል:: ብዙዎቹ የስልጣኔ እሴቶች የሚባሉት ከእዛ የመነጩ መሆናቸውም ግልጽ ነው:: ጥንታዊቷን ኢትዮጵያ እና ጥንታዊቷን ግብጽ የተመለከትን እንደሆነ በጣም አዎንታዊ የሆነ ግንኙነት የነበራቸው አገራት ናቸው:: ግብጾች ሁልጊዜ ኢትዮጵያን የሚሉት ነገር ቢኖር በተራራ የተከበበች፣ የተቀደሰች አገር ናት ነው:: ኢትዮጵያ የውሃ ምንጫችን እንደመሆኗ የሕይወታችን ምንጭ ናት ይሏትም ነበር:: ከዚህ የተነሳ ኢትዮጵያን የሚያነሳሷት በማመስገን እንጂ በጥላቻ እንዳልነበር የሚታወቅ ነው::
የጥላቻ መንፈስ የመጣው በተለይ በተለይ ዘመናዊ ግብጽ ከተፈጠረች በኋላ ነው:: እንደሚታወቀው እንግሊዝ በቅኝ ገዝታት በነበረ ጊዜ ከኢትዮጵያ ጋር በዚህ በውሃ ምክንያት ንትርክ ውስጥ የምትገባው የናይልን ውሃ ሙሉ በሙሉ ልቆጣጠር በሚል ነው:: ከዚህ ውጭ በኢትዮጵያ እና በግብጽ መካከል በጥንት ታሪካቸው ያለው ወዳጅነት መልካም የሚባል ነው::
ሌላው ቀርቶ የኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር ከግብጽ ጋር አንድ አይነት ነበር:: እነርሱም ዘንድ 12 ባለ 30 ቀን ወራት አሉ:: የመጨረሻዋ አምስት አሊያም በአራት ዓመት አንዴ ስድስት የምትሆነው ጳጉሜን ያለችው የጥንታዊቷ ግብጽ ላይ ብቻ ነው፤ ሌላ ቦታ የለም:: ስለዚህ እሱ አይነት ቀን አቆጣጠር ቀርቶ በአሁኑ ወቅት ግብጻውያኑ በአውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በመጠቀም ላይ ናቸው:: እኛ ግን ከጥንት ጀምሮ ሳንቀይረው እዚህ ደርሰናል::
በዚህ አጋጣሚ መጥቀስ የምፈልገው የግብጽን 25ኛው ስርወ መንግስት የሚባለውን ትቆጣጠር የነበረችው ኢትዮጵያ ናት:: በወቅቱ ደግሞ የኢትዮጵያ ግዛት አሁን ያለውን ብቻ ሳይሆን ሱዳንንም (ኑቢያ) ጭምር የሚያካትት ነበር:: 25ኛ ስርወ መንግስት ቢያንስ ቢያንስ ለ80 እና ለ90 ዓመታት ያህል ኢትዮጵያ ጨምሮ ኑቢያን እና ግብጽን ይገዛ የነበረ ነው:: በወቅቱ ይህ ስርወ መንግስት በጣም ኃያል የነበረ ነው::
ስለዚህም ጥንታውያን ግብጾች እኛ ኢትዮጵያውያንን እንደ ሕይወት አፍላቂ አድርገው ይቆጥሩን የነበሩ ናቸው:: ለዚህ ምክንያታቸው ደግሞ ለጥማቸው እርካታ የሚሆነውን ውሃ አፍላቂዎች ናቸው ብለው ያምኑ ስለነበርም ነው:: ይህን ሲጠቅሱም በተቀደሰና ክብር ባለው መንገድ እንደነበር ታሪክ ምስክር ነው::
አሁን አሁን በግብጽ በኩል እየታየ ያለው ስግብግብነት ነው:: በአሁኑ ወቅት አገሪቱ የሌላትን ኃይል አለኝ ብላ ሕዝብ ለሕዝብ እያጋጨች እና መሳሪያ እየሰጠች እየረበሸችም ጭምር ትገኛለች::
አዲስ ዘመን፡- በዚህ ዓመት እንደ አገር ከተያዘው ትልቅ እቅድ አንዱ በሀገራዊ ምክክር ነው:: የፖለቲካ ስብራት የፈጠረውን አለመግባባት በምክክር መድረኩ መጠገን ይቻላል?
ዶክተር አየለ፡- እኔ የምለው ይቻላል ነው፤ እንደ አለመታደል ሆኖ በአሁኑ ወቅት ግጭቶች በዝተዋል:: በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ያሉ ግጭቶች መቆም አለባቸው:: ከዚህ ቀደም ትግራይ ላይም አድርገነዋል:: በእርስ በእርስ ጦርነት የምንጎዳው እንደ አገር ነው:: ከዚህ ደግሞ ማንም ተጠቃሚ አይሆንም:: በአገራችን የሚከሰቱ ግጭቶች የውጭ ጠላትን ለመጋበዝ በጣም ምቹ ናቸው:: ስለዚህ ከዚህ አይነት አካሄድ መላቀቅ ተጠቃሚ ያደርገናል እንጂ አይጎዳንም::
እንደሚታወቀው አገራዊ የምክክር ኮሚሽን እንደ አገር ከመቋቋም አልፎ በርካታ ስራዎችን በማከናወን ወደ ዋና ስራ በመግባት ላይ ይገኛል:: ይሁን እንጂ የተሰጠው ኃላፊነት በእኔ እምነት አነስተኛ ነው:: ምክንያቱም ውሳኔ ሊያሳልፍ አይችልም:: መደረግ ያለበት ለዚህ ለምክክር ኮሚሽን የበለጠ ስልጣን መስጠት ነው:: ጉዳዮች በውይይት እንዲፈቱ ኮሚሽኑ አወያይ ቢሆን ደግሞ የበለጠ መስራት ያስችለዋል የሚል አስተያየት አለኝ::
ምክክር ኮሚሽኑ ያሉንን የሽምግልና ስርዓቶችን በመጠቀም የሚጋጩ ወገኖች ወደስምምነት መምጣት አለባቸው ባይ ነኝ:: ይህን ማድረጉ ለምክክር ኮሚሽኑ በእጅጉ ይጠቀማል::
አዲስ ዘመን፡- በእርስዎ በኩል እንደ አገር መግባባት ላይ ያልተደረሰባቸው የትርክት መንስኤዎች ምንድን ናቸው ይላሉ? ደግሞም እንዴትስ ቢፈቱ መልካም ነው ይላሉ?
ዶክተር አየለ፡- በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው፤ ይህን ጥያቄ ብዙ ጊዜ ተጠይቄ ምላሽ ሰጥቼበታለሁ:: አንድ መገንዘብ ያለብን ነገር አለ፤ ማንኛውም የታሪክ ድርጊት የራሱ የሆነ ትርክት ይኖረዋል:: ስለሆነም የተለያየ ትርክት መኖሩን ልንገታውና ልናቆመው አንችልም::
ዋናው ቁም ነገር የሚሆነው ያን ትርክት እንዴት አድርጎ ነው ወደ ፖለቲካዊ ጥቅም ማዋል የሚቻለው የሚለው ነው:: ዋናው የፖለቲካ ሽኩቻ እንጂ በአገራችን ሕዝብ መካከል እምብዛም ቁርሾ አለ ብዬ አላምንም:: እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ታሪክ ያላት አገር ናት፤ በዚህ ረጅም ታሪክ ውስጥ ሕዝቡ አንዱ ከሌላው ጋር ተደበላልቆ ኖሯል:: በደስታውም ሆነ በመከራው አብሮ ያሳለፈ ነው:: በዚህ እንቅስቃሴው ውስጥ ያፈራቸው ብዙ ትውፊቶች አሉ:: በርካታ እሴቶችም አሉት:: እነዚህ እሴቶቹ ሊመጡ የቻሉት ደግሞ ሕዝብ አብሮ በመኖሩ ነው:: ምንም እንኳ በቋንቋ፣ በሐይማኖትም ሆነ በብሔሩ ቢለያይም፤ አብሮ መኖርን የሚያውቅ ሕዝብ ነው:: በታሪክ የሚታወቀው ሕዝብ አብሮ የመኖርና አብሮ ተባብሮ የመስራት መንፈስ እንዳለው ሁሉ ጠላትም ቢመጣ እንዲሁ ተባብሮ ያንን ጠላት የሚያሸንፍ ሕዝብ እንደሆነ ነው::
ይህ ሁሉ መልካም እሴት ወደኋላ የመገፋቱ ምስጢር በአሁኑ ጊዜ ያለው ሁኔታ ስልጣን ፈላጊ በመብዛቱ የመጣ ፈተና ነው የሚል አተያይ አለኝ:: ያ እንዳይሆን ሕዝብ የመረጠው በግልፀኝነት ስራውን ቢሰራና በአገሪቱም ዴሞክራሲ የበለጠ እንዲሰፍን ማድረግ ቢችል መልካም ነው:: በምንም መልኩ በጠብመንጃ ወደስልጣን ለመምጣት መሞከርም ሆነ በጠብመንጃ ከስልጣን ለማውረድ ማሰብ ፈጽሞ ኋላቀር የሆነ አካሄድ መሆኑ በግልጽ ግንዛቤ ሊያዝበት ይገባል::
ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ስልጣንን ከአንዱ ወደሌላው መቀየር መሻትን ብናዳብር ጥሩ ነው:: ይሁንና እሱ እየሆነ አይደለም:: ምክንያቱም ዛሬም ጠብመንጃችንን ለማንሳት እንሯሯጣለን:: በዚህ መሃል ደግሞ ቀላል ቁጥር ነው የማይባል ሕዝብ ያልቃል:: በአሁኑ ወቅት እያስተዋልን ያለነው እሱን ነው::
እንደ እኔ አመለካከት መንግስት ጉዳዩ ሕዝብን እና አገርን እንደሚጎዳ አስተውሎ አስፈላጊውን እርምጃ ቢወስድ የተሻለ ነው:: ለምሳሌ ስልጣን በጠብመንጃ ከተቀየረ አገሪቷ ያላትን መልካም የሆኑ ነገሮችን አጥታ እንደገና ‹‹ሀ›› ብላ እንድትጀምር የሚያደርጋት ነው:: ይህ ከሆነ ደግሞ እንደ አገር የምንኮራበት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብም ሆነ ሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶች ሊቆሙ ይገደዳሉ::
ነገር ግን ይህ ሁሉ እንዳይከሰት አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ አሁን ያለበት ሁኔታ በጣም ወሳኝ ስለሆነ ለኮሚሽኑ አቅም እንዲኖረው አድርጎ ምክክሩን በማስጀመር የሚያስፈልጉትን ቅድመ ሁኔታዎች በማመቻቸት እንዲሰራ ቢደረግ ሸጋ ነው ብዬ አስባለሁ::
አዲስ ዘመን፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እንዲሁም አረንጓዴ አሻራና የመሳሰሉት ሀገራዊ ትርክትን የሚፈጥሩ ናቸው:: ከዚሁ በተጻራሪ ልዩነትን የሚፈጥሩ ትርክቶች አሉ:: ህዝቡ በከፋፋይ ትርክቶች ስር እንዳይወድቅ ምን መደረግ አለበት ?
ዶክተር አየለ፡– አስቀድሜ እንደጠቀስኩልሽ የምክክር ኮሚሽኑ ተግባሩን አስፍቶ በአገራችን ከትውልድ ትውልድ እየተላለፈ የመጣውን የሽምግልና ስርዓት (የጃርሱማ) ስርዓት አለ፤ እሱን ማካተት ለሒደቱ አጋዥ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ::
ከዚህ በላይ ግልጽ በሆነ መንገድ ተዋህደን ችግራችንን እንፍታው በሚል ታላቅ ዘመቻ ከተጀመረ እሱን አሻፈረኝ ብሎ ወደኋላ የሚቀር አካል አይኖርም፤ ካለም የሕዝብ ጠላት ይሆናል ማለት ነው:: ምክንያቱም በአሁኑ ወቅት ሕዝቡ የሰለቸው ነገር ቢኖር ጦርነት ነው:: በተለይ ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ አይነት ሁኔታ ሲመጣ በጣም ተጎጂ የሚሆነው ምንም የማያውቀውና በጉዳዩ የሌለበት ሕዝብ ነው:: በተለይም አርሶ አደሩ፣ አርብቶ አደሩና ሰርቶ ለመኖር የሚጣጣረው አካል የሚጎዳ ይሆናል:: ለጦርነቱም ቢሆን የሚማገዱት ከእነዚህ አብራክ የወጡ ታዳጊ ልጆች ናቸውና ለኮሚሽኑ ተግባር ራስን ምቹ ማድረግ ተገቢ ነው እላለሁ:: ኮሚሽኑም ቢሆን የሚሰራው ስራ ስኬታማ እንዲሆን ሕዝብ መያዝ የግድ ይለዋል::
በአሁኑ ወቅት ትልቁ ችግር የሚባለው የተለያዩ ትርክቶች የሚመጡት አንደኛ ታሪክን በሚገባ ካለማወቅ የተነሳ ነው:: ታሪክን በአግባቡ ሳይረዱ መቅረት ራስን ለከንቱ ስሜታዊነት አሳልፎ እንደመስጠት ይቆጠራል፤ ስሜት ደግሞ ብቻውን መቼም እውነት መሆን የማይችል ነው:: ስሜታዊ የሆኑ አካላት ጥላቻን ይዘሩና የሕዝቡን ስሜት ወዳልተፈለገ ሒደት የሚቀሰቅሱ ይሆናሉ::
ይህን የሚያደርጉ ደግሞ የራሳቸውን ጊዜያዊ ጥቅም የሚያሳድዱ እንጂ የሕዝብን ጥቅም ከግምት የሚያስገቡ አይደለም:: እንዲህ አይነቱ አካሄዳቸው ኢትዮጵያንም እነርሱን በተናጠልም የሚጠቅማቸው ጉዳይ አይደለም:: አንዳንድ በአገራችን ከተካሄዱ ሁነቶች መካከል ታሪክ የፈጠራቸው ነገሮችን መዘንጋት አሊያም መረሳት አሊያም ደግሞ መተው ማለት አይደለም:: ምክንያቱም ሕዝብ ለሕዝብ ሲከባበር፣ ሲቻቻል አብሮ ለመስራት ያለው ፍላጎት እየጨመረ ይሄዳል::
አብዛኛውን ጊዜ ያለው ችግር አንድን የማያግባባን ነገር ከታሪክ ውስጥ ቁንጽል አድርገው ያውጡና እሷን ብቻ በማጮህ ሕዝቡ እንዲረበሽ እና እንዲያምጽ ብሎም እርስ በእርሱ እንዲጣላና መተማመን እንዳይኖር የሚያደርጉ ኃይሎች አሉ:: በአሁኑ ወቅት በአገራችን ውስጥ በጣም አስቸጋሪ የሆኑት እነርሱ ናቸው::
ነገር ግን በሌላ አነጋገር ደግሞ የህዝብ ብሶት ካለ እና አይሎ ከወጣ ለዚያ ብሶት ምላሽ እና መፍትሔ መስጠት ያሻል:: ከሕዝብ ጋር በመሆን የሕዝብን የልብ ትርታ ማዳመጥ መቻል መልካም ነው:: የሕዝብን የልብ ትርታ እያዳመጥን መስራት ከቻልን ደግሞ ነገሮችን በቶሎ ወደሰላም ማምጣት የሚቻልበት ሁኔታ ይፈጠራል እላለሁ::
አዲስ ዘመን፡- የምክክሩ ሁኔታ ከአገር ውጭ ባለው ጣልቃ ገብ የሆነ ኃይል እንከን ይገጥመዋል የሚል ስጋት ይኖርዎ ይሆን?
ዶክተር አየለ፡- እኔ ይህንን ጉዳይ በሁለት አይነት መልክ አየዋለሁ:: በአንድ በኩል ይህ የምክክር መድረክ ስኬታማ ይሆን ዘንድ ዳያስፖራው አዎንታዊ ሚና ሊጫወት ይችላል:: ከዚህም የተነሳ በምክክር መድረኩ መሳተፉ ይበጃል እላለሁ:: በሌላ በኩል ደግሞ በእርግጥ ጣልቃ ገቦች ይኖራሉ:: ለእነሱም ክፍተት መስጠት አይገባም::
አዲሰ ዘመን፡- ሊኖሩ የሚችሉ ጣልቃ ገብነቶችን ሊጠቅሱልን ይችላሉ ?
ዶክተር አየለ፡- እንደሚታወቀው ግጭቶች በሚኖሩበት ጊዜ የውጭ ኃይሎች በአገራችን ጣልቃ የመግባት ፍላጎታቸው እየጨመረ ነው የሚመጣው:: ያንን ደግሞ ልታስቆሚው አትችይም:: እንደ ግብጽ አይነቶቹ ሰላማዊ የምክክር መድረኩም ሆነ ልማታችን በተቻላቸው መጠን እንዲስተጓጎልና ጊዜው እንዲረዝም ይፈልጋሉ:: እንዳንድ ምዕራባውያን ሀገሮች ደግሞ የሕዝቡን የአንድነት መንፈስ በተለያዩ ጠቃሚ በሚመስሉ ርዕሰ ጉዳዮች በማስመሰል መሸራረፍ ይፈልጋሉ:: በተለይ ደግሞ እንደወልቃይት አይነቱን ጉዳይ በማንሳት አዲስ አገር ወይም በዛ በኩል ሌላ ነገር እንዲፈጠር ይፈልጋሉ::
እኛ አንድ ማድረግ ያለብን ነገር ቢኖር ጸጋችንን ይኸውም ብዝሃነታችንን ማክበር ነው እንጂ ለጥላቻችን መንስዔ ማድረግ የለብንም:: አንድ ታላቅ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፤ አድዋ ላይ ድል እንድንጎናጸፍ ያደረገን ብዝሃነታችን ነው፤ ሁሉም ከየአቅጣጫው መጥቶ በግንባር ውሎ ላይ ባያሳትፍ ኖሮ ይህኔ ምን ሊፈጠር እንደሚችል አናውቅም:: ሌላው የቅርብ ጊዜ ማሳያ ደግሞ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠቃሽ ነው፤ ይህን ግድብ መገንባት የተቻለው ሁሉም አለኝ ያለውን በማዋጣቱ ነው:: እናም እሱ አይነት ትብብር የብዝሃነታችን ውጤት ነው:: ያንን በማስከበር አሁንም ማስቀጠል የግድ ይለናል::
ይሁንና ፖለቲካ እና ብሔር መለየት አለባቸው የሚል አተያይ አለኝ:: ምክንያቱም የፖለቲካ ዓላማ የተለያዩ ሰዎችን አንድ ላይ ሊያስመጣ ይችላል:: ምንም እንኳ በኃይማኖትም ሆነ በሌላ ጉዳይ ቢለያዩም ዓላማቸው ግን አንድ ሊሆኑ ይችላሉ፤ እናም ያንን አይነት ስርዓት መፍጠር መቻል አለብን፤ ኬንያውያን አድርገውታል፤ ናጄሪያውያንም አድርገውታል:: እናም አንድ ስልጣን የሚፈልግ ሰው ከራሱ ብሔር ውጭ ከሌላውም ብሔር ድምጽ ማግኘት መቻል አለበት የሚል ሕግ ከወጣ ያን ጊዜ ለሌሎችም ማሰብ ይጀመራሉ ማለት ነው:: ያኔ ሕብረት እና ትስስር የበለጠ ይመጣል::
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ::
ዶክተር አየለ፡– እኔም አመሰግናለሁ::
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 21 ቀን 2016 ዓ.ም