ሁላችንም በሀገራችን ባህልና ወግ ተምጠን የተወለድን ነን

 ሀገራችን ኢትዮጵያ የብዙ ባህልና ስርዓቶች መነሻ ሀገር ናት:: የተለያዩ ሀይማኖቶች ተከባብረውና ተቻችለው የዘለቁባት የሕብረ ብሔራዊነት እናት ናት:: በህዝቦቿ የአንድነትና የአብሮነት መንፈስ የሶስት ሺ ዘመን ታሪክና እሴቶቿን ጠብቃ ከትውልድ ትውልድ ተራምዳለች:: እኚህ የሀገር ካዝማ እሴቶች በባህል፣ በሀይማኖት፣ በታሪክና በስርዓት የሚገለጡ የብዝሀነት ማሳያዎች ናቸው::

በዓለም ደረጃ ከምንታወቅባቸው እውነቶች የመጀመሪያው ሕብረብሔራዊነታችን ነው:: ሕብረብሔራዊነት ከብዙሀነት የሚነሳ የብዙ ማንነቶች እሴቶችና አስተሳሰቦች ነጸብራቅ ነው:: ይሄ ማንነት፣ እሴትና እሳቤ ነው ሀገራችንን ሰፊና ብዙሀን፣ ልዩና ውበታም ያደረጋት::

ይህንን እውነት በሀይማኖት በኩል ካየነው ተመሳሳይ የምናገኘው ነገር ነው:: ለብዙዎች መማሪያ በሚሆን መልኩ ተቻችለው በፍቅር የሚኖሩ የተለያዩ አማኞችን እናገኛለን:: በዚህ ረገድ የተሳካልን ህዝቦች ነን:: ክርስቲያን ሆኖ ሙስሊም ጎረቤት የሌለው፣ ሙስሊም ሆኖ ክርስቲያን ዘመድ የሌለው፣ ያልተዋለደና ያልተሳሰረ አይገኝም::

ትልቁ ውበታችን እንዲህ ያለው የአብሮነት መስተጋብራችን ነው:: ይሄ የቅርብ ጊዜ ወይም ደግሞ ሰሞነኛ ሳይሆን ከታሪካችን ጋር የተሳሰረ ራሳችንን ለዓለም ያስተዋወቅንበት ጥንተ መሰረታችን ነው:: ተቻችሎ፣ በደስታና በሀዘን ያለውን እየተካፈለ የመጣ ህዝብ አንድነት ይጠፋዋል ማለት ዘበት ነው:: ስናሸንፍና ስንበረታ የነበረው ጥንት ባልተበገሩ ዛሬም ባልሰለሉ ሕብር እጆቻችን ነው::

ያለፉ የታሪክ ዳናዎቻችን በፍቅር የተሰመሩ ናቸው:: የትዝታዎቻችን አጥቢያ እንኳን በነዚህ እሴቶች ላይ የሚንጸባረቅ ነው:: እኔ ከሙስሊም ወዳጆቼ ጋር ብዙ ትዝታ አለኝ በተመሳሳይም እነሱ ከኔ ዘንድ የተቋደሱት እልፍ የወዳጅነት ትውስታ አላቸው:: ይሄ የአንድ እና የሁለት ሰዎች ታሪክ ሳይሆን የሀይማት መቻቻልን በተመለከተ የሁላችንም የጋራ ስሜት ነው::

አዛን ሲል እና ተንስኦ ሲል እንደሆነ ኃይል ነፍሳችንን የሚጸሙን የአንድነት ትውስታ አለን:: በአረፋና በመውሊድ በገናና በፋሲካ ከአፍጥር ጀምሮ እስከ ስግደት ድረስ ይሄ ነው የማንለው የተወራረስነው ናፍቆት አለን:: ዛሬም ድረስ በዛ መንፈስ ውስጥ ወጥተን የምንገባ ነን:: ለብቻችን ኖረን ያለፍነው ትዝታ የለንም:: ሙስሊም ከክርስቲያኑ ጋር፣ ክርስቲያን ከሙስሊም ወዳጁ ጋር የኢትዮጵያዊነትን የጋራ አሻራ ያኖረ ነው::

አንዋር መስኪድና ራጉኤል ቤተክርስቲያን አዛንና ቅዳሴ እኩል የሚሰማባቸው የኢትዮጵያዊነት ፊተኛ መልኮች ናቸው:: ጥምቀትና መስቀል ሲደርስ ቤተክርስቲያንን ከሚያጸዱት ውስጥ አብዛኞቹ ሙስሊም ወንድሞቻችን ናቸው:: ልክ እንደዚህ አረፋና መውሊድ ሲመጣም መስኪድ የሚጠርጉት ክርስቲያን ወንድሞች ናቸው:: ገንዘብ ለምነው መስኪድና ቤተክርስቲያን የሚያሰሩ ፍቅረ ፈጣሪ ያደረባቸው አማኞች እንዳሉ በተለያየ ጊዜ ሰምተናል::

ሀይማኖታዊ ክብራችን ምን ያክል እንደሆነ ከዚህም የላቁ አንዳንድ ታሪኮችን ሰምተን እናውቃለን:: ነብዩ መሀመድ ተከታዮቻቸውን ወደሀበሻ ምድር ሲልኩ..‹በዛ ፍቅር እና ነጻነት አለ፣ ማንም የማይበደልበት ምድር ነው ወደዛ ሂዱ› ብለው ነው:: ኢትዮጵያዊነት የእኔ የአንተ የሌለበት ፍቅርና አብሮነት የነገሰበት የነጻነት መሬት ነው::

የሰሞኑ ደግሞ ለየት ይላል:: እኚህ ወንድማማች ሀይማኖቶች በይበልጥ ሊያደምቁን በአንድ ላይ ከተፍ ብለዋል:: የአዲስ ዓመት መጀመሪያው መስከረም በሀይማኖት አፋቅሮ፣ በባህልና ወግ በስርዓትም አጋምዶ ጅማሬአችንን አሳምሮልናል:: አዲስ ዓመትን በጋራ አክብረን አሁን ደግሞ መስቀልና መውለድን በጋራ ልናከብር ሽር ጉድ ላይ ነን:: ከዚህ አለፍ ባልን ማግስት ደግሞ በጋራ የምንደምቅበት እሬቻ ይጠብቀናል::

እኚህ ሀይማኖታዊና ህዝባዊ በዓላት የማንነታችን መልኮች ናቸው:: አንድነት ሲጨምርባቸው ደግሞ ይበልጥ እንዲያምሩ እድል ይሰጣቸዋል:: በኢትዮጵያ ውስጥ የብቻ ታሪክ፣ የብቻ እሴት የለም:: እንዲህ ከመሰለው ሀይማኖታዊና ህዝባዊ በዓላት ውስጥ ደምቀው ወጥተው ያደመቁን ናቸው:: ስናከብራቸውም በጋራ ነው::

 ባረፋና መውሊድ፣ በገናና ፋሲካ የፍቅር ሁሉ ዳርቻ በሆነው ቤተሰባዊነት ተጠራርተንና ተመራርቀን ኖረናል:: አሁንም ዳግም ልንመራረቅ ቅዳሴና አዛኑን በአንድ ባጣመረ ክብረበዐል ፊት እንገኛለን:: ሁለቱ ታላላቅ ሀይማኖቶች ክርስትናና እስልምና በስርዓት፣ በጨዋነትና በግብረገብነት ትውልዱን ከማረቅ አኳያ ሚናቸው የላቀ ነው:: አሁን ላለችው ኢትዮጵያ በጎ ትውልድ ከማፍራት አኳያ የላቀ ሚና ተጫውተዋል::

ጨዋነት ከእምነት ነው የሚነሳው:: በፈጣሪ እና በአማኝ መካከል በተገነባ የስርዓት አውድ በኩል ነው ትውልድ እውነትን ህዝብ ፍቅርን የሚማረው:: እንደሕዝብ ብርታቶቻችን ከምንም ሳይሆን በእምነታችን በኩል የተንጸባረቁ ናቸው:: እነዚህ ነጸብራቆች ናቸው ዛሬ ላይ በአንድነቱ የበረታና በፍቅር የሰለጠነ ሕዝብ ብለን ስለራሳችን አፋችንን ሞልተን እንድንናገር ሆነ እንድንጽፍ እድል የሰጡን::

ሀይማኖታዊ ክብራችን ልንወልዳት በምናምጣት ኢትዮጵያ ላይ የራሱ አስተዋጽኦ አለው:: በፍቅር የምንሰራው ቤት ነው አቻችሎና አከባብሮ የሚያኖረን:: በፍቅር ስም ይዘናቸው የመጣነው እነዛ የአንድነት እሴቶቻችን አሁን ላለው ሀገራዊ መንገጫገጭ ዋስትናቸው የት የሌለ ነውና በሀገራዊ ምክክሩም ሆነ እየተናቆርንበት ባለው የብሔር ቡዳኔ ብንጠቀማቸው ለውጥ ያመጡልናል::

ሀይማኖት መጀመሪያው ፍቅር ነው..መጨረሻውም ፍቅር ነው:: እምነት መነሻው ሕብረት ነው መድረሻውም እንደዛ:: የምንኖረው ከምናመልከው በኩል የሰማነውንና ያየነውን ነው:: እውነቱ ይሄ ከሆነ ከፍቅር ውጪ በማንም ላይ እዳ እንዳይኖርብን ያስገድደናል ማለት ነው::

እኛ ኢትዮጵያውያን ከአንድ ወንዝ የተቀዳን፣ ከአንድ ምንጭ መንጭተን በአንድ ቦይ የምንፈስ የስልጣኔና የነጻነት ፋናወጊዎች ነን:: እኚህ ቀደምት ስልጣኔዎቻችን እንዴት መጡ ብለን ስንጠይቅ ፍቅር የዋጀው የወንድማማችነት መንፈስን እናገኛለን:: እንዳንለያይ ሆነን የተቀየጥን፣ እንዳንፈታ ሆነን የተቋጠርን መሰረቶች ነን:: ኢትዮጵያዊነትን በተመለከተ ልክና ተስማሚ የሚሆነው በጀመርነው እና በምንታወቅበት ታሪክ ባበጀንበትም አብሮነት መቀጠል የሚለው ነው::

የመለያየት እውቀቶች ሀገር እንደማያጸኑ አይተናል፣ እያየንም ነው:: ”ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ ነው” እንደሚባለው ምን እንደሆነ የምናውቅ ህዝቦች ነን:: የሚያምርብን ልዩነቶቻችንን ፈትተን ባልተቀየመና ባልጠላ ልብ ስንተቃቀፍ ነው:: የሚያምርብን ዘረኝነትን ትተን በኢትዮጵያዊነት ስንጠራና ለሁላችን የሚበቃ የጋራ ታሪክ ስንጽፍ ነው:: የሚያምርብን አብረሀም ሎጥን ወንድሜ እንዳለው..እኛም ወንድሜ..እህቴ ስንባባል ነው::

ቀዳዳዎቻችን እየሰፉ አለመግባባትን የፈጠሩት ከለመድነው ኢትዮጵያዊነት አውድ ስለወጣን ነው:: የከፍታዎቻችን ማማ አሁንም እኛን እየጠበቁ ናቸው:: ፍቅር ዝቅታ የለውም:: ከመቃብር የከፉ የዝቅታ አዘቅቶች በጥላቻ መንፈስ የሚፈጠሩ ናቸው:: ጥላቻ የራስ ሞት የሚጀምርበት፣ የትውልድ ሞት የሚቀጥልበት፣ በስተመጨረሻም ሀገርን የሚያጠፋበት መርዝ ነው:: ሀይማኖቶቻችን ፍቅርን የሚያስተምሩ፣ አንድነትን የሚሰብኩ ናቸው:: ለምናምነው ፈጣሪ የእውነት የምንገዛ ከሆነ የጥላቻ መንፈስ አይጎበኘንም::

እኛ ኢትዮጵያውያን አማኝ ህዝቦች ነን:: ከመቶ ሲሰላ አብዛኛው ህዝብ የእኔ ከሚለው ፈጣሪው ጋር የተቆራኘ ነው:: ቁርኝቱ ደግሞ በህግና በስርዓት፣ በእምነትና በተግባር የተቃኘ ነው:: ይሄ ማለት ለፍቅር የሚሆን፣ ለአብሮነት የሚሆን፣ ለወንድማማችነት የሚሆን ብዙ እውቀትና ማስተዋል አለን ማለት ነው:: እናም ጥላቻን የሚገል፣ አለመግባባትን የሚሽር መንፈሳዊ መረዳት ውስጥ ነን ብለን መናገር እንችላለን::

እዚም እዛም ለኢትዮጵያዊነት አስተዋጽኦ ያደረጉ ብዙ የጨዋነት እሴቶች አሉን:: ከነዚህ ውስጥ ሀይማኖታዊ እና ህዝባዊ ስርዓቶቻችን ቀዳሚዎቹ ናቸው:: ትውልድ የገነቡ፣ ታሪክ ያስቀመጡ የሕብረ ብሔራዊነት ወዞች አሁንም ባልነጠፈው በኢትዮጵያዊነት ውስጥ አሉ:: መልካም እሴት ከአንድ ብርቱ ስርዓት እኩል የሕገ መንግስት ያክል ነው:: ያደፉብንን ለማጥራት፣ የወየቡብንን ለማድመቅ እኚህ መልካም እሴቶች አስፈላጊዎቻችን ናቸው::

 በአብሮነት ሀገር ካልሰራን በምንም ብንሰራ ልክ አንሆንም:: አንዳንድ እውነቶች ፊትና ኋላ ናቸው:: ፍቅር ቀድሞ አንድነት የሚለጥቅባቸው:: በፍቅር ቀድመን በአብሮነት ስንለጥቅ ነው ከድብዛዜአችን ወጥተን ወደሚደነቅ ብርሀን የምንሄደው:: ትውልዱ በስርዓትና በጨዋነት በመከባበርም እንዲቆም ፍቅር አስተማሪ አባቶች ያስፈልጉታል:: ኢትዮጵያዊነትን ሳይስቱ ከትላንት ወደዛሬ ያመጡን ሀይማኖታዊና ህዝባዊ በአላቶቻችን ይበልጥ የምንደምቅባቸው፣ ይበልጥ የምንዋሃድባቸው ስለሆኑ መጪውን በዓል እንደመልካም እድል መቁጠር ይቻላል::

በዓሎቻችን በጋራ የምንደምቅባቸው የጋራ እሴቶቻችን ናቸው:: የእኔ የአንተ በሌለው ሕብር ማንነት ውስጥ የብቻ ስም እየሰጡ ራስን መነጠል ሀገር በማዋለድ ሂደት ውስጥ ወደ ኋላ መቅረት ነው የሚሆነው:: ኢትዮጵያውያን የሚደምቁበት መስቀልና አረፋ እሬቻና ሌሎች ሕዝባዊ በዓላትም ሙስሊምና ክርስቲያኑን በፍቅር የሚደምቁበት ሌላም የሚዋሃድበት በዓላት ናቸው:: እንዲህ አይነቱ በዓል ይበልጥ አብሮነታችን የሚጠነክርበት ከመሆኑ በተጨማሪ ወንድማማችነትንም የሚፈጥር ነው::

ብዙሀነት ፈትሎ ባደራት ሀገር ውስጥ፣ ሕብራዊነት ሸምኖ በቋጨው ሕዝብ ውስጥ ብቻነት የማይታሰብ ነው:: በሁላችን ዋጋ ለሁላችን በምትበቃ ሀገር ውስጥ ነን:: ከተግባባን በቅቶን የሚተርፍ ብዙ ነገር አለን:: ከተዋደድን እልፍ የበረከት ጸጋዎች አሉን:: ያጠበበን ጥላቻ ነው:: ያሳነሰን እኔነት ነው:: እንድንሰፋ..የፍቅርን በርኖስ እንልበስ::

ሀገር የምትፈጠረው ከፍቅር ጀምሮ በፍቅር ካበቃ የአብሮነት እሴት ነው:: አብዛኞቹ እሴቶቻችን ደግሞ መነሻቸውን ፍቅር ያደረጉ መድረሻቸው ደግሞ በሀገርና ህዝብ የተቋጨ ነው:: ንትርክ እና ሽኩቻ ማንንም ፊተኛ አድርገው አያውቁም:: ያለፈን በመርሳት ወደነገ የሚሄድ ተራማጅ አስተሳሰብን በመፍጠር ሁነኛ መሆን ይቻላል:: ልማዶቻችንን ለዳግም ብስራት ትላልቅ ድሎችን እንዲፈጥሩልን በፍቅር አሀዱ እንበል::

ኢትዮጵያ የብዙሀነት መናኸሪያ ናት:: የተለያዩ ብሔሮች ከባህልና ወጋቸው፣ ከስርዓትና እምነታቸው ጋር ተከባብረውና ተቻለው የሚኖሩባት:: በዓለም አደባባይ ደምቀንና አምረን የታየነው እንዲህ ባለው ዘመን ባስቆጠረ የጋራ ስርዓታችን እንደሆነ የሚታመን ነው:: ከጥንት ይዘናቸው የመጣነው ወደ ነገም የምናሻግራቸው መልካም እሴቶቻችን አብሮነትን በመፍጠር ረገድ የጎላ ሚና ስላላቸው ብንጠቀምባቸው አትራፊዎች ነን::

የብዙዎቻችን ታሪክ የተወራረሰ ታሪክ ነው:: በባህል ረገድ አንዱ በአንዱ ባል ደምቆ፣ በሀይማኖት በኩል አንዱ የአንዱን እያከበረ የመጣን ነን:: ብዙዎቻችን ያደግነው በእንዲህ ባለው ተለያይቶ በተስማማ፣ ተራርቆ በቀረበ ማንነት ውስጥ ነው:: በያገባኛል መንፈስ ጎረቤቶቻችን እየቀጡንና እየተቆጡን፣ እያስተማሩና እየመከሩን ያደግን ጥቂቶች አይደለንም:: ዛሬም ያን መሳይ የመዋደድና የመፈላለግ ጽኑ መሻት ያስፈልገናል::

ከስም ሁሉ ገናና በሆነው በኢትዮጵያዊነት ብዙ ኩራቶችን ኮርተን ብዙ ድሎችን ተቀዳጅተናል:: ፍቅር የገባበት ልብ ሁሌም አሸናፊ ነው:: ድላችን ያለው በአንድነታችን ውስጥ ነው:: ተከባብረን ስንኖር መጪውን ትውልድ መከባበር እያስተማርነው ነው:: ስንቻቻል እንደዚሁ የመቻቻል ባህልን እያዳበርን ነው::

ኢትዮጵያ የተማገረችው የተለያየ ሀሳብና እሴት ባላቸው ብሔር ብሔረሰቦች ነው:: የነዚህ እልፍ ማንነት ባህልና ስርዓት፣ ወግና ልማድ ሌላ ድምቀት ሆኖ ሀገሬን የሶስት ሺ ዘመን ባለታሪክ አድርጓታል:: ዛሬም የፍቅር ታሪክ እንሻለን:: የአብሮነትና የወንድማማችነት ታሪክ እንፈልጋለን:: ሁሉም ነገር ከሆነ ውበት ጋር የተፈጠረ ነው:: እንደመታደል ሆኖ የእኛ ውበት ደግሞ አብሮነት ነው:: አብሮነት ጥንት ያማረብን ዘንድሮም ያማረብን ከርሞም የሚያምርብን ውበታችን ነው::

ልክ እንደ እናት ጉያ ሀገር የትውልድ ቤት ናት:: ተከባብረንና ተቻችለን የምንኖርባት:: የመስቀልም ሆነ የአረፋ በዓል ከጥንት ጀምረን አብረን ያከበርናቸው ከሀይማኖታዊ እኩል የበጎ እሴት መገለጫዎቻችን ናቸው:: ሁላችንም በሀገራችን ባህልና ወግ ውስጥ ተምጠን የተወለድን ነን:: እናም ሁሉም የጋራችን ነው::

 ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው።በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 21 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You